>

ድምጻዊ ቴድሮስ ካሳሁን በኤርትራ መዲና አስመራ የሙዚቃ ስራዎቹን ማቅረብ እንደሚፈልግ ገለጸ

ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል ኤ ኤፍ ፒ ቃለመጠይቅ የሰጠው ቴዲ አፍሮ በአስመራ የሙዚቃ ኮንሰርት በማቅረብ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል እንደሚፈልግ አስታውቋል። በሌላ በኩል ለመጪው የኢትዮጵያ የገና በዓል በአዲስ አበባ የሙዚቃ ዝግጅት ለማቅረብ የአገዛዙን ፈቃድ በመጠበቅ ላይ መሆኑንም ኤ ኤፍ ፒ በዘገባው አመልክቷል።

አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ሰሞኑን በድምጻዊ ቴስሮስ ካሳሁን ቤት ጎራ ብሎ ነበር። ድምጻዊውን በሙዚቃዎቹና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ያነጋገረበትን ቃለ መጠይቅም ለንባብ አብቅቷል። የ41 አመቱ ድምጻዊ ቴድሮስ ካሳሁን በቅርቡ ያወጣው ኢትዮጵያ የተሰኘው አልበሙ በአለም አቀፉ የሙዚቃ ሰንጠረዥ ውስጥ በአንደኛ ደረጃ ተቀምጦ እንደነበር ኤ ኤፍ ፒ በዘገባው አስፍሯል። ምንም እንኳን በቢልቦርድ ሰንጠረዥ ቀዳሚ ቦታን ይዞ የነበረ ቢሆንም ሙዚቃዎቹ ግን በሀገር ቤት በሚገኙ መንግስታዊ የመገናኛ ብዙሃን እንዳይተላለፉ መታገዳቸውን ኤኤፍ ፒ በዘገባው ላይ አመልክቷል።

ድምጻዊው በኢትዮጵያውያን ዘንድ እጅግ ተወዳጅ እንደሆነም አትቷል። ቴዲ አፍሮ በሙዚቃዎቹ በኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት እንዲሰፍን የሚሰብክ መሆኑን የገለጸ ሲሆን ይህንንም እስከመጨረሻው እንደሚገፋበት በቃለምልልሱ ላይ ገልጿል። ሙዚቃዎቹ አነጋግሪም ናቸው ።በብዙዎች ዘንድ የሚታወሱት የቴዲ አፍሮ ሙዚቃዎች በስልጣን ላይ ያለውን አገዛዝ የሚተቹ ተደርገው ነው የሚወሰዱት ያለው ኤኤፍ ፒ በዚህም ምክንያት በአገዛዙ ባለስልጣናት ዘንድ በበጎ እንዲታይ አላደረገውም ሲል ያክላል። በተለይም በአውሮፓውያኑ 2005 ላይ ያወጣው ጃ ያስተሰርያል የተሰኘው አልበሙ የተቃውሞ መዝሙር ተደርጎ ይወሰዳልም ይላል ዘገባው። ደም ያፋሰሰው ምርጫ ከመካሄዱ ከቀናት በፊት አልበሙ መለቀቁንም ያስታውሳል። ይህን ያልወደዱት የአገዛዙ ባለስልጣናት ድምጻዊውን በጥርጣሬ እንደሚያዩትም አንስቷል።

በፈረንጆቹ 2008 በመኪና ሰው ገጭቶ በመግደል ወንጀል ክስ ተመስርቶበት ለእስር የተዳረገ ቢሆንም የጥበብ አፍቃሪዎቹ ግን ጉዳዩ ፖለቲካዊ ምክንያት አለው ብለው እንደሚያምኑ ጠቁሟል። በተደጋጋሚ ሊያቀርባቸው የነበሩት የሙዚቃ ዝግጅቶች እንደተሰረዙበት በቅርቡም የአዲስ የሙዚቃ አልበሙ የምርቃት ፕሮግራም በፖሊስ መታገዱንም አስታውሷል። ለመጪው የገና በአልም የሙዚቃ ዝግጅቱን ለማቅረብ የአገዛዙን ባለስልጣናት ፈቃድ በመጠባበቅ ላይ መሆኑን ገልጿል። የገና ዋዜማ አንድ ሳምንት የቀረው ቢሆንም እስካሁን ከአገዛዙ በኩል ምላሽ ስለመሰጠቱ የታወቀ ነገር የለም ብሏል ዘገባው። በሌላ በኩልም ድምጻዊ ቴድሮስ ካሳሁን በኤርትራ አስመራ የሙዚቃ ዝግጅቱን ለማቅረብ ፍላጎት እንዳለው ከአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ጋር በነበረው ቆይታ ገልጿል።

በአስመራ የሙዚቃ ዝግጅቱን ማቅረብ ቢችል በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ማሻሻል ይቻላል ብሎ እንደሚያምንም ድምጻዊው ተናግሯል። የሚያስፈልገን የፍቅር፣ሰላምና ይቅር ባይነት ነው ያለው ድምጻዊ ቴድሮስ ካሳሁን በሙዚቃ ስራዎቹ ይህን ማስተጋባት እንደሚችል ጠቅሷል። ድምጻዊ ቴድሮስ እንዳለው ልጆች ሆነን የማስታውሰው ሁላችንም እንደ አንድ ህዝብ ነበር የምንኖረው፣ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ነበር የምናውቀው አሁን ግን በብሔር ማንነታችን ነው የምንለየው ይሄ ደግሞ በጣም አደገኛ እየሆነ መቷል። ቴዲ አፍሮ መጪው ጊዜ በጣም እንደሚያሰጋውም ሳይገልጽ አላለፈም።

ያሬድ ይልማ

Filed in: Amharic