ትላንት አቶ አባዱላ የጣሉትን መዶሻ ዳግም ሊጨብጡት እንደሆነ ሲሰማ ‘ድሮውንም ብለን ነበር…’ የሚሉ ወዳጆቻችን በብዛት ፈሰዋል!
እዚህ ጋ ልብ ማለት ያለብን ነገር በአባዱላ ስልጣን መልቀቅ የተደነቀው ህዝብ ሰውየው ከዚህ በኋላ ጫካ ይገባሉ በሚል ተስፋ ሳይሆን በዛ ደረጃም ቢሆን አስደንጋጩን ድርጅታቸውን በማስደንገጣቸው ነው። አሁንም ቢሆን በምን አይነት ድርድር ዳግም ወደ መዶሻ ተራ እንደተመለሱ የምናውቀው ነገር የለም። ምናልባትም የኢህአዴግ ባለስልጣናት እርሳቸውንም ሆነ በረከትን ሽማግሌ ሰብስበው ይቅር በሉን ብለዋቸው ይሆናል…? ወይ ደግሞ አንዱ ወዳጄ እንዳለው ሲያስቡት በፌደራል ውስጥ ስልጣን መያዛቸው የተሻለ የትግል አቅም ይሰጠኛል ብለው ይሆናል፣ ወይ ደግሞ ከዝች ስልጣን ከለቀክ የሙስና መዝገብህ ይገላበጣል ብለው አስቦክተዋቸው ይሆናል! ምንም ሆነ ምን ግን የሰው ልጅ ሲጀግን አስይ የኔ አንበሳ ማለት ሲደክምም አይዞህ ብሎ ማበርታት ተፈጥሯዊ ነው እና ትላንት አባ ዱላ ኢህአዴግን ሲያስታጥቁልን እሰይ ማለታችን እንዲፀፅተን አይገባም።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ‘ኦህዴድ ተለወጠ የምትሉ ተመልከቱ አባዱላን…’ የሚሉ ወዳጆችም ተመልክቻለሁ… ኦህዴድ ተለውጧል ወይም እየተለወጠ ነው የሚለው ሃሳብ የመጣው ከአባዱላ መዶሻ ጋር ተያይዞ አይደለም። እርሱ ተጨማሪ ማጣቀሻ ነበር እንጂ ዋናው… የነ አቶ ለማ እና ዶክተር አብይ ባጠቃላይ አዲሱ አመራር ለውጥ የሚመስል አካሄድ ነው። በተለይም አቶ ለማ እና ዶክተር አብይ የክልላቸው ህዝብ ዘንድ ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት ከማግኘታቸውም በተጨማሪ ኢትዮጵያዊነት ላይ የሚያሳዩት አቋም እስካሁን ከኢህአዴግ ሰፈር ያልታየ ብርቅ ስለሆነ ይመስለኛል። ኦህዴዶች ይሄንን ስላሉ በቃ ዘላልም የማይሻሩ ዘላለም በልባችን ታትመው የሚቀረ ናቸው ማለት አይደለም የማይሻር የማይለወጥ እና የማይሳሳተው ፈጣሪ ብቻ ነው (አሜን በል እዚህ ድረስ ዘልቀህ ያነበብክ አንበሳ ሃሃ) ነገር ግን አሁን የኦህዴድ አመራሮች ለሰጡን ነገር እናመሰግናለን። ይህ ነገርም እንዲቀጥልላቸው እና እንፀልይላቸውለን… ከዛ በተረፈ ግን ሲመጡም ሲሄዱም ረግመን አንችለውም። ሰውነታችንም አመስጋኝነትን ይፈልጋል… ሁል ግዜ ነገሮችን ሁሉ በአሉታዊ መልኩ ባየን ቁጥር ከፊታችን ላይ ፈገግታ እየጠፋ እየጠፋ ጨለምተኛ ሆነን እንቀራለን። ለማሸነፍ ሃይል የሚሆነው ደግሞ ጨለምተኝነት ሳይሆን ተስፈኝነት ነው… ካላመናችሁኝ… መቼስ ምን አደርጋለሁ ሃሃ.