>
5:30 pm - Saturday November 1, 8302

'ፓርቲው ባሉበት ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች የተነሳ ሀገር ማስተዳደር አቅቶታል'' (ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ)

 በኢትዮጵያ ያለው አገዛዝ በሕገ መንግስቱ መሰረት የአስቸኳይ ጊዜ ምርጫ ለማካሄድ የሚገደድበት ሁኔታ መፈጠሩ እንደማይቀር የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ተናገሩ። ዶክተር ነጋሶ እንዳሉት ኢሕአዴግ እንደ ፓርቲ መቀጠልና ሀገር የማስተዳደር ሕልሙ በማክተም ላይ ነው። የኢትዮጵያ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ወቅታዊውን የሀገሪቱን የፖለቲካ ሁኔታ በተመለከተ አስተያየታቸውን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ገልጸዋል። እናም ዶክተር ነጋሶ እንደሚሉት ሕዝብ ላነሳቸው ጥያቄዎች ተገቢው ምላሽ ባለመስጠቱ ሀገሪቱ አደጋ ላይ ወድቃለች ። ገዥው ፓርቲም ባሉበት ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች የተነሳ ሀገር ማስተዳደር አቅቶታል ነው ያሉት። ኢህአዴግ ጥልቅ ተሃድሶ በማድረግ የፖለቲካ ምህዳሩን አሰፋለሁ ቢልም ያለውን በተግባር መተርጎም እንዳቃተውም ዶክተር ነጋሶ ገልጸዋል። የሕዝብ ጥያቄዎችን በአግባቡ አለመመለሳቸውም አሁን በሀገሪቱ ያለውን ችግር ለማባባስ ምክንያት ሆኗል ብለዋል። እንደ ዶክተር ነጋሶ ገለጻ የሕዝብን ጥያቄ መፍታት ባለመቻሉም ኢሕአዴግ በሕገመንግስቱ መሰረት የአስቸኳይ ጊዜ ምርጫ ማካሄድ የሚገደድበት ሁኔታ መፈጠሩ አይቀሬ ይሆናል። እርሳቸው እንደሚሉት ኢሕአዴግ በአሁኑ ጊዜ በሀገሪቱ ያለውን ችግር ብቻውን ሊፈታው አይችልም። እናም በሰላማዊ መንገድ እየታገሉ ከሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመምከር ምላሽ መስጠጥ ይጠበቅበታል ነው ያሉት። ይህን ማድረግ ካልቻለ ግን ይላሉ ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ይህን ማድረግ ካልቻለ ኢሕአዴግ እንደ አንድ ፓርቲ የመቀጠልና ሀገር የማስተዳደር ሕልሙ ጨርሶ ያከትማል።
Filed in: Amharic