>

ህዝብና የዘመኑ ዘረኝነት ከእራሴ ቤተሰብ እይታ (ዶ/ር አበበ) 

ብዙዎች የአማራን ህዝብ በተለይ የሸዋ አማራን ጨቋኝና ዘረኛ እንዲሁም በሃይማኖትም መድልዎ የሚያሳይ እያስመሰሉ የኦሮሞ ህዝብና የትግራይ ህዝብ በአማራ ላይ ጥላቻ እንዲያሳድር ብዙ ጥረዋል በመጠኑም ተሳክቶላቸዋል። እውነታው ግን እጅግ በጣም የተለየ ነው። የኢትዮጵያ ታሪክ የሚያሳየው የተለየ ሃቅን ነው። በዚህ ክህደት በተሞላው ታሪክን የማሳደፍ እንቅስቃሴ ውስጥ ሁለት ነገስታት ስማቸው ሁሌም በጥላቻ በፀረ ኢትዮጵያ ድምፆች ይነሳል። አፄ ምኒልክና አፄ ሃይለሥላሴ። ገራሚው ነገር አማራን ከትግራይ ጋር ለማጣላት የውሸት ታሪክን ለመፍጠር አልተቻለም ምክንያቱም ወራሪውም የሚገባው በሰሜን ነው። የመሃል ሃገር ሰውም ከሰሜን ወገኖቹ ጋር እዛው ድረስ በመሄድ ሃገርን ድንበርን ስለሚጠብቅና ስለታሪኩም ብዙ ስለተፃፈ ምንም ማድረግ አልተቻለም ስለዚህ ከሰሞኑ የተጀመረው ጨዋታ የደርግ መንግስት የአማራ መንግስት እንደሆነና የትግራይን ህዝብ እንደጨፈጨፈ ነው የሚያዉሩት። ሃቁ ግን ደርግ ሃይማኖትና ዘር ያልነበረው በደም የሰከረ የነፍሰ ገዳይ ጥርቅምና የአማራን ህዝብና ባላባቶቹን ከፋሽት ጣልያን በላይ የጨፈጨፈ ነበር።
ወደ ኦሮሞ ህዝብ ስንመጣ ግን ብዙ የማጣላት ስራ የተሰራው አፄ ምኒልክ የኢትዮጵያን ግዛት ወደቀደመ ድንበሩ ለማስፋት በወሰዱት እርምጃ ላይ የሃሰት ወሬዎችን በማዛመት ነው። እውነታው ግን አፄ ምኒልክ የኢትዮጵያን ድንበር ያሰፉት በአማራ ጦር ብቻ አይደለም ግን የኦሮሞን ህዝብ ይዘው ነው። የአድዋን ድል የተጎናጸፉት የትግራይን ህዝብ ይዘው እንደሆነ ሁሉ። በዛም ምክንያት የአፄ ምኒልክ መንግስት ታላላቅ የኦሮሞ መኳንንቶችን ያቀፈ ነበር። አንዱም ታላቅ ሰው ፊትአውራሪ ሃብተ ጊዮርጊስ ነበሩ። ስልጣናቸውም የጠቅላይ ምንስትርም የመከላከያም ምንስትርነትም ጭምር ከመሆኑም በላይ አፄ ሃይለሥላሴንም ወደስልጣን ያመጡ ሰው ነበሩ። ግን ያን ሲያደርጉ የአፄ ሃይለሥላሴ ወዳጅ ሆነው አልነበረም። ሃቁ የሚያሳየው በተቃራኒው እንደማይወዷቸው ነበር ግን እራሳቸው እንዳሉት “ተፈሪ ተንኮለኛ ነው ግን ለኢትዮጵያ የሚበጃት እሱ ነው” ብለው ወደ ዘውዱ ማምጣት ብቻ ሳይሆን በጦርነት ላይም የልጅ እያሱን አባት ንጉስ ሚካኤል ገጥመው አሸንፈው የጃንሆይን ዙፋን ያረጋጉ ታላቅ የጦር መኮንን ነበሩ። ግን የቀደመ ማንነታቸውን ስናይ ምንም አይነት የመሳፍንትም የመኳንንትም ዘር ያልነበራቸው የኦሮሞ ገበሬ ልጅ ነበሩ። ታላቁ የጦር መሪ ባልቻ አባነፍሶም በተመሳሳይ ሁኔታ ከምንም ተነስተው በሺህ የሚቆጠር የግል ሰራዊት የነበራቸው ታላቅ መኮንን ለመሆን የበቁት በአፄ ምኒልክ መሪነት ነበር። እነዚህን ሁለት መኳንንት ለምሳሌነት ጠቀስኩ እንጂ እጅግ በጣም ብዙ የኦሮሞ መኳንንት ከአፄ ምንሊክ እና አፄ ሃይለሥላሴ ጋር ሆነው ኢትዮጵያን አቅንተዋል። ራስ ጎበና አንዱ ከመሆንም አልፈው የአፄ ምኒልክን ልጅ አግብተውም ነበር። በትግራይም ከሄድን የአፄ ምንሊክ ሌላኛዋ ሴት ልጅ ንግስት ዘውዲቱ የመጀመርያ ባላቸው ራስ አርአያሥላሴ የአፄ ዮሐንስ ልጅ ነበሩ። ቂም የማያውቁት አፄ ምኒልክ ይህንን ትዳር የተቃወሙትንና መልከመልካሙን አርአያሥላሴን ለማግባት ዘውዲቱ ቁንጅና የላቸውም ብለው የተቃወሙትን ራስ አሉላን በመንግስታቸው ሾመው ሸልመው የተቀበሉ ነበሩ።
በአፄ ሃይለሥላሴም ጊዜ ኢትዮጵያና መንግስቷ እነ ገረሱ ዱኪን እነ ጃጋማ ኬሎን እነ አብዲሳ አጋን የመሰሉ ብርቅዬ የኦሮሞ ልጆችን አብቅላለች። በተጨማሪም ለምሳሌ ያህል የጃንሆይ የመጨረሻ ወንድ ልጅ ልዑል ሳህለሥላሴ ያገቡት አሁን በህይወት ያሉትንና የልዑል ኤርምያስን እናት የወለጋ ኦሮሞ ተወላጇ ልዕልት ማህፀንተን ነበር።
ከእራሴ ቤተሰብ እይታ ወዳልኩት ስመለስ እናቴም አባቴም የሸዋ አማሮች ነን። የእናቴ አያቶችና የአባቴ እናትና አያቶች ከራስ መኮንን ጋር ሃረር ገብተው ከዛም በተለያዩ ቦታዎች ኑሮዋቸውን መስርተው ይኖሩ ነበር። በተለይ የአባቴ እናት ቤተሰቦች በተለያዩ የኦሮሞ ቦታዎች ሰፍረው ይኖሩ ነበር አሁንም የሚኖሩ አሉ። በተለይ በአሰቦት ሥላሴ ገዳም አካባቢ ብዙ ነበሩ። ላነሳ የፈለኩት ታሪክ የዛ አካባቢን ነው። ጣልያን ሲገባ ከወሰዳቸው እርምጃዎች አንዱ የኦሮሞን እና አማራን ህዝብ ማጋጨትና ማጋደል ነበር። በዚህም ምክንያት የተወሰኑ የኦሮሞ ተከታዮችን አስታጥቆ በሃረር ትንንሽ ከተሞችና መንደሮች ውስጥ በሚኖሩ አማሮች ላይ አዝምቶ ነበር። የአሰቦት ሥላሴ ገዳም አካባቢ የሚኖሩ አማሮችን ለመጨፍጨፍ ሲያሰማራ የዛ አካባቢ ኦሮሞዎች ተሳታፊ መስለው መረጃ አጠናቅረው ወደገዳሙ በመምጣት አማራው እንዲዘጋጅ አድረገው በአቡነ ሳሙኤል የሴቶች ገዳም ህፃናቱ እናቶችና አረጋውያን እንዲደበቁ ተደርጎ ፲፯ የአማራ አልሞ ተኳሽ ወጣቶችና የአካባቢው የታጠቁ ኦሮሞ ወጣቶች ሆነው አድፍጠው ጠበቁ። ወራሪዎቹ ሲደርሱም ጣልያኖቹን አንድም ሳያስተርፉ ሲገድሉ ከልባቸው ከጣልያን ጋር የተሰለፉትን የሌላ አካባቢ ኦሮሞዎችን እዛው እራሳቸው የኦሮሞ ገበሬዎች ጨረሷቸው። የዛ አካባቢ የኦሮሞ ገበሬዎች መረጃ ከማምጣትም ባለፈ ተዋግተው ገዳሙንና አማራውን አዳኑት። በዛን ዘመን እነዛ ገዳሞች አካባቢ የነበሩ አንበሶችን ነብሮችንና አጋዘኖችን የአካባቢው ህዝብ አይነካም ነበር የገዳሙ ቅዱሳን እንስሶች ናቸው እያለ። ከእነዛ አማሮች ውስጥ ብዝዎቹ ዘመዶቼ ሲሆኑ ከነዛ ውስጥ አንዱ አጎናፍር የሚባል የአባቴ አጎትና በእርጅና ዘመኑ በጃንሆይ ጊዜ ሶማሌ ኢትዮጵያን ስትወር ብቻውን ሄዶ ብዙ የሱማሌ ወራሪዎችን ፈጅቶ የሞተ ጀግና ነበር።
በልጅነቴ የማስታውሰው የዛ አካባቢ ዘመዶች ቤት ሲመጡ ኦሮምኛ ስለሚቀናቸው ከአባቴ ጋር በኦሮምኛ ነበር የሚያወሩት። አሁን ድረስ አባቴ ኦሮምኛን ማውራት ያስደስተዋል። ሁልጊዜም የኦሮምኛ ቃላቶችን ይወረውራል። በእርጅናው ጊዜ ብዙ ቋንቋዎችን እየረሳ መጣ እንጂ ከእንግሊዘኛ ውጭ ጀርመንኛ የማይረሳው ጣልያንኛን እና ፈረንሳይኛ ይናገር ነበር። አሁን ግን የማይረሳውና እጅግ የሚወደው የልጅነት ጊዜውን የሚያስታውስበት ከነምሳሌዎቹ የሚያውቀውን ኦሮምኛን ነው። ዘራችንን ለማያውቅ አባቴን ብዙ ላወራው ሰው አማርኛ አቀላጥፈው የሚያወሩ ኦሮሞ ግለሰብ ብሎ ለማሰብ ቀላል ነው።
በትግራይ በኩል ከሄድን ደግሞ ምንም ቅልቅል የሌለባቸው የሸዋ አማራ የሆኑት አያቴ የአባቴ አባት ልጅ ሰይፉ ሚካኤል በመጨረሻ ዘመናቸው ያገቡትና የአባቴን ታናናሽ ፫ ወንድሞች የወለዱት ከባለቤታቸው ከትግራዩ መስፍን ከደጃዝማች ሃይሉ ልጅ ከወይዘሮ አስቴር ሃይሉ ነበር። ወደው ፈቅደው አገቡ እንጂ ዘር አልገደባቸው ስም አላስገደዳቸው። ይህ የአማራ ቤተሰብ ታሪክ ከሌላው የአማራ ቤተሰብ ታሪክ ጋር በጣም ይማሰላል ስለዚህ ውድ ዘረኞች ዘረኝነትን ኢትዮጵያን ለማያውቃት እና በራሱ ውሳኔ ለደነቆረ መሃይም ስበኩ። ኢትዮጵያ ለዘለአለም በሥላሴ ቸርነት ትነሳ ትኑር ይመርባት።
በዚህ አጋጣሚ ላመሰግነው የምፈልገው በአማራ ህዝብ ላይ በሚደርሰው በደል ምክንያት እኔም ዘረኝነት ሊጠናወተኝ ሲል በጠንካራ አባታዊ ወንድማዊ ተግሳፅ አርመው በኢትዮጵያዊነት ላይ ተስፋ እንዳልቆርጥ እና ወደአስቀያሚው ዘረኝነት በሽታ እንዳልሄድ ያረሙኝን ከወላጆቼ ስርአት እንዳልወጣ የመከሩኝን ታላቁን ኢትዮጵያዊ የአርበኞቹን ልጅ ዶክተር አበበ ሃረገወይንን ነው።
ኢትዮጵያ ማንም ወደደ ጠላም የአማራ የኦሮሞ የትግሬም የደቡቡም የምስራቁም የምእራቡም የሰሜኑም የክርስትያኑም የሙስሊሙም ናት። ይህቺን ኢትዮጵያ ነበር እምዬ ምኒልክ መልሰው ያነጿት አፄ ሃይለሥላሴ በአለም ፊት አቆንጅተው እሳቸው ኮርተው አኩርተው ያቀረቧት።
Dr Abebe
አሞራው ምንአለ ባሻ

Filed in: Amharic