>
5:13 pm - Sunday April 19, 6139

የአባዱላ ገመዳ መመለስ ህዝባዊ እምቢተኝነቱን ለማገዝ እንደሚሆን ተስፋዬ እጅግ ጠንካራ ነው (ያሬድ ጥበቡ)

አፈጉባኤ አባዱላ ገመዳ ሥራቸውን እንዳይለቁ በተደጋጋሚ ጥሪ አድርጌ ስለነበር በሥራ ገበታቸው ለመቆየት በመወሰናቸው ደስ ብሎኛል ። አፈጉባኤው ወደሥራቸው ለመመለስ ሲወስኑ የሃገራችን ኢትዮጵያ እጣም በእጃቸው ሥር መውደቁን ተረድተው ነው ብዬ ለማመን እወዳለሁ ።

ሃገራችን በምትገኝበት በዚህ ታላቅ ተስፋና አደጋ ተቆላልፈውና ተጋምደው በሚገኙበት ልዩ ታሪካዊ አጋጣሚ በተወካዮች ምክርቤት ጫንቃ ላይ ትልቅ ሃላፊነት መውደቁን አባዱላ ሊገነዘቡት ይገባል። እስከዛሬ እንደተለመደው ምክርቤቱ በአቶ አስመላሽ በኩል የሚቀርብለትን ወያኔያዊ አጀንዳ ማስፈፀሚያ የጎማ ማህተም ሳይሆን፣ ህዝቡ በየጎጆው የሚያነባውን እንባ እየተከታተለና በየአደባባዩ የሚያሰማውን ጩኸት እያዳመጠ ወቅታዊ ውሳኔዎችንና የህግ ድንጋጌዎችን እንዲያውጅ ከምክርቤቱ እንጠብቃለን ። የፀረ ሽብር አዋጁን በማሻሻል ጀምሮ የፖለቲካ እስረኞችን እስከመፍታት ፓርላማው ውሳኔዎች ማሳለፍ ይችላል።

የምክርቤቱ ውሳኔ ተፈፃሚ ይሆናል ወይስ አይሆንም የአፈጉባኤ አባዱላ ጥያቄና ጭንቀት ሊሆን አይገባውም። የርሳቸውና የሥራ ባልደረቦቻቸው ኃላፊነት ሃገሪቷን ትክክለኛ አቅጣጫ ማሳየት ነው ። ምክርቤቱ ያወጀውን አስተዳደሩ አልፈፅም ካለ፣ አገዛዙን የመቀየር ሃላፊነት የህዝቡ ይሆናል ። የህዝብ ተወካዮች ምክርቤትን ውሳኔዎች ወይም አዋጆች በተግባር አላውልም ያለ አስተዳደርን መተንፈሻ አሳጥቶ እንዲተገብር ማስገደድ የሰላማዊ ህዝባዊ እምቢተኝነት ተልእኮ ይሆናል ። የፓርላማውን ውሳኔዎች ተግባራዊ ማድረግ እምቢተኛ የሆነን ወያኔያዊ መንግስት ለማስጨነቅና መብቱን ለመፈልቀቅ ፈቃደኛ ያልሆነ ህዝብ ግን በባርነት ለመኖር በራሱ የፈረደ መንጋ ነውና ቢያለቅስ እንኳ ሊታዘንለት አይገባም ።

ለማጠቃለልም፣ የአባዱላ ገመዳ ወደሥራ ገበታቸው መመለስ ሰናይ ውሳኔ ሲሆን፣ መመለሳቸው ግን የአቶ አስመላሽን እዝ ለመቀበልና በሁለተኛ ደረጃ ዜግነት ለመቀጠል ሳይሆን ሰላማዊ ህዝባዊ እምቢተኝነቱን ለማገዝ እንደሚሆን ተስፋዬ እጅግ ጠንካራ ነው። አይዞን!

Filed in: Amharic