>

በአማኙ የተረሱት መነኮሳት በደል በርትቶባቸዋል (ጌታቸው ሽፈራዉ)

በእስር ላይ ከሚገኙት የዋልድባ መነኮሳት መካከል  አባ ገ/ስላሴ ወ/ሀይማኖት  ፀሎት ያደርጋሉ፣ ለእስረኞች ምግብ  ያካፍላሉ፣ ፀበል ይሰጣሉ ተብለው ጨለማ ቤት ከገቡ ሰነባብተዋል። የምንኩስና ልብሳቸውን እንዲያወልቁ ሲጠየቁ አላወልቅም በማለታቸው ተደብድበዋል።

ትናንት ታህሳሰ 19/2010 ዓም ደግሞ ዞን ሁለት የነበሩት  አባ ገ/እየሱሰ ኪ/ማርያምም ፀሎት  ያደርጋሉ፣ የምንኩስና ልብሳቸውን እንዲያወልቁ ሲጠየቁ እምብይ ብለዋል በሚል ጨለማ ቤት ገብተዋል።

ያው በእኛ ሀገር በሁሉም መስክ ባለ ጊዜን እንጅ መከረኛን ብዙ ሰው አያስታውሰውም። እነዚህ ለእምነታቸው የቆሙ መነኮሳት በሲኖዶሱ ሰፈር ቢሆኑ ዘመናዊ መኪና ልግዛላችሁ የሚለው ብዙ ነበር። ደጅ የሚጠናው ደጁን ይሞላው ነበር። አሸርጋጁ ብዙ ነበር።  እነዚህ መነኮሳት መከታ ያደረጉት እውነትን እንጅ ስልጣን ላይ ያሉትን ስላልሆነ  ብዙ አማኝ “የራሳቸው ጉዳይ” ብሎ ትኩረት የነፈጋቸው ይመስላል።

መምህር ግርማ የታሰሩ ሰሞን የጠያቂያቸው መዓት፣ ፍርድ ቤታቸውን የሚከታተለው ሰው ብዛት ታይቷል።  እነዚህ መነኮሳት ህዝብ አለኝ የሚለው ገዳም  በመነካቱ  አቤት ሲሉ ጥርስ ተነከሰባቸው። ታሰሩ። እየተሰቃዩ ነው።  በግል ጉዳይ  ጮሌ “ሰባኪ” ታሰረ ሲባል የሚጎርፈው ገዳማት መፍረሰ የለባቸውም ብለው ሲታገሉ ለኖሩት ትኩረት የለውም! ረስቷቸዋል። አሳሪዎቹም የሚጮህላቸው የለም  ብለው የስቃይ በተራቸውን አጠንክረውባቸዋል!

Filed in: Amharic