>

የኢትዮጵያ ሕዝብ የግድ በወያኔ/ኢሕአዴግ ላይ ሊይዘው የሚገባው የጸና አቋም! (ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)

ስንት ሲባልለት ከሰነበተው የወያኔ/ኢሕአዴግ የሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ በኋላ የወጣው የወያኔ መግለጫ በርካቶችን አበሳጭቷል፡፡ ሰው የጠበቀው ወያኔ አስቀድሞ ከስብሰባው ሾልኮ የወጣ መረጃ እያስመሰለ እንዲነዛ እንዲራገብ ባደረገው ወሬ መሠረት ብቻውን ጠቅልሎ የያዘውን ሥልጣንና የበላይነት ለኦሕዴድና ለብአዴን የሚያጋራ መሆኑን የሚገልጽ መግለጫ ነበር የጠበቀው፡፡

የኔ ጥያቄ “እንዲህ ተደርጎስ ቢሆን የኢትዮጵያን ሕዝብ ምን ይጠቅም ነበረ?” የሚለው ነው፡፡ ለይስሙላ ሥልጣን ለመያዙማ አቶ ኃይለማርያምስ የሀገሪቱ መሪ ነው ተብሎ ተቀምጦ አልነበረም ወይ? ግን ምን ፈየደ? የብአዴንና የኦሕዴድ ባለሥልጣናትስ “ማንም ጣልቃ የማይገባባቹህ የየክልላቹህ መሪዎች፣ ባለሥልጣናት ናቹህ!” ተብለው አልነበረም ወይ? ነገር ግን የወያኔ ጉዳይ ፈጻሚዎች፣ ተቀጣሪዎች፣ ባሮች ሆነው ለወያኔ ጥቅም የገዛ ሕዝባቸውን የሚያሰቃዩ የሚፈጁ ሆኑ እንጅ የየሕዝባቸው አገልጋይ፣ ጠባቂ፣ ተሟጋች፣ አሥተዳዳሪ፣ ሠራተኛ፣ መፍትሔ ሰጭ፣ አለኝታ ሆኑ ወይ??? በኢሕአዴግ ውስጥ የሚደረግ ማንኛውም ለውጥ “ጉልቻ ቢለዋወጥ…!” ከመሆን አልፎ ምን ሊፈይድ ይችላልና ነው የተወራው ወሬ እንዲፈጸም ተፈልጎ የነበረው???

ይመስለኛል ሰው ለኦሕዴድና ብአዴን ሥልጣን መተላለፉን በበጎና በጉጉት ጠብቆ የነበረው ሕዝባዊው ዐመፅ እያየለ ከመምጣቱ ጋር በተያያዘ ወያኔ ኦሕዴድንና ብአዴንን የሱ አሽከሮች፣ ተቀጣሪዎች፣ ባሮች መሆናቸውን የሚገልጥባቸውን ተግባራት አስትቶ ወክሎናል ወይም እንወክለዋለን ለሚሉት ሕዝባቸው ተቆርቋሪ መስለው እንዲታዩ፣ እንዲተውኑ በማድረግ ሕዝብ ተስፋ እንዲጥልባቸው በዚህም ምክንያት ዐመፁ እንዲበርድ ብሎም እንዲወገድ ለማድረግ ለዘመናት ከወያኔ በላይ ወያኔ ሆነው የገዛ ሕዝባቸውን ለትግሬ ሕዝብ ጥቅም ሲፈጁ፣ ሲያሰቃዩ፣ ሲበድሉ የነበሩትን ኦሕዴድንና ብአዴንን ከኢሕአዴግ ያፈነገጡ እያስመሰለ ያሠራቸው ድራማዎች (ትውንተ ኩነቶች) እና ሴራዎች ለሰው እውነት መስሎ ስለታየው ነው ሥልጣን መውሰዳቸውን በበጎና በተስፋ እንዲመለከተው አድርጎት የነበረው፡፡

ነገር ግን ቀደም ባሉ ጽሑፎቸ እንደገለጽኩት “የሚወራው ወሬ ሁሉ ሕዝብን ለማዘናጋት፣ ለመደለል፣ ለማታለል፣ ፖለቲካዊ ጥቅም ለማግኘት የተተወኑ ትዎናዎች፣ የተሴሩ ሴራዎች ለመሆናቸው በቀጣይ ጊዜያት ከወሬ በዘለለ እዚህ ግባ የሚባል ምንም ዓይነት ለውጥ ካለመምጣቱ የምታረጋግጡት ይሆናል!” እንደማለቴ ወያኔ ድራማዎቹ (ትውንተ ኩነቶቹ) ያልተፈለገ ውጤት እያመጣበት ስለተቸገረ ያንን ሁሉ የውሸት የለውጥ ማዕበል እንቅስቃሴን አክስሞ ማለትም “ኦሕዴድና ብአዴን የሕወሓት የበላይነት ማክተም አለበት የሚል የጸና አቋም ይዘው ቀረቡ፣ አቶ አባዱላ የሕወሓት የበላይነት መኖሩን እየኮነነ ተናገረ፣ ወያኔ እጅ ሰጠ እያለቀሰም ይቅርታ ጠየቀ፣ ሕወሓት ተሸነፈ የበላይነቱ አከተመ፣ አላግባብ ይዞት የነበረውን ሥልጣን አብላጫ የሕዝብ ቁጥር ላላቸው ኦሕዴድና ብአዴን ለማስተላለፍ ቃል ገባ!” ወዘተረፈ. እየተባለ እንዲነዛ እንዲራገብ ያደረገውን ወሬ እንደጉም አብንኖ ሁኔታውን ቀድሞ ወደነበረበት ቦታው ሊመልሰው ችሏል፡፡ ወያኔን በወያኔነቱ ለማወቅና ለማስተናገድ አለመፈለጋችን ገና ብዙ ብዙ ዋጋ ያስከፍለናል!

ሕዝባችን በተለይም የልኂቃኑ ክፍል የወያኔን መቸም ቢሆን በምንም ሁኔታም ሊለወጥ የማይችለውን የፀረ ሕዝብነት፣ የፀረ ኢትዮጵያነት፣ የጠባብነት፣ የጎጠኝነት፣ የጠላትነት፣ የዘረኝነት፣ የባንዳነት፣ የከሀዲነት፣ የቅጥረኝነት፣ የርካሽነት፣ የሥርዓት አልበኝነት፣ የወንበዴነት፣ የዋልጌነት፣ የጭንጋፍነት፣ የወራዳነት፣ የምናምንቴነት፣ የቆሻሻነት፣ የነውረኛነት፣ የሸፍጠኝነት፣ የሴረኝነት፣ የዕኩይነት…. ማንነቱን ተረድተን ከዚህ ነውረኛና ፈጽሞ ኃላፊነት ከማይሰማው የወሮበላ ቡድን እራሳችንን ነጻ ለማውጣት የሚያስችሉንን ቆራጥ እርምጃዎች በግልና በቡድን ከመፈጸምና ከመንቀሳቀስ ይልቅ እጅ እግራችንን አጣምረን ይሄንን ነቀርሳ ሊከላ፣ ሊያስወግድ የሚችል አንዳች ተአምር በመጠበቅ ብቻ መወሰናችን ወይም ይሄ ሁሉ ዕኩይ ሰብእና ያለበት እርኩስ የጥፋት ኃይል ድንገት ወደ ቅዱስነት ተለውጦ ችግራችን እንዲቀረፍልን መጠበቃችን እያያየነው እንዳለውና ስናየው እንደኖርነው ምን ያህል ለውርደት ዳርጎ የእነዚህ ደናቁርትና አህዮች መጫወቻ መቀለጃ እንዳደረገን የምናየውና የምናውቀው ነው፡፡

ሊገባኝ ያልቻለው ነገር ሕዝባችን በተለይም ልኂቃኑ በዓለማችን ላይ መቸና የት ሀገር እንደ ወያኔ ያለ የተመረዘ ጽንፈኛ የጥፋት ኃይል ወደ ቅዱስነት ተለውጦ መልካም ሥራ ሲሠራ ዓይቶና ሰምቶ ወያኔም አንድ ቀን ይለወጣል ብሎ እንደሚጠብቅና ተስፋ እንደሚያደርግ ነው ባስበው ባስበው ጨርሶ ሊገባኝ ያልቻለው ነገር፡፡

ሕዝባችን ከሃይማኖነኝነቱ የሚመነጭ ሥነ ልቡናዊ አስተሳሰብ ነው ብየ እንዳልወስደው ቅዱስ ቃሉ የሚለው “ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳል!” ነው የሚለው፡፡ ባሕላዊ አስተሳሰባችንም “በቆፈሩት ጉድጓድ ይገቡበታል! ፣ ሥራ ለሠሪው እሾህ ለአጣሪው!….” የሚሉ ናቸው፡፡ ሁለቱም ሃይማኖቱና ባሕሉ የሚያረጋግጡት ነገር የክፉ መጨረሻ የማያምር መሆኑን፣ የፈለገ ነገር ቢሆን ክፉ የሥራውን ማግኘቱ የማይቀርለት መሆኑን ነው፡፡

ታዲያ ሕዝባችን ባሕሉና እምነቱ ቢለያይም እንኳ የወል አስተሳሰቡ ግን ይሄ ከላይ የገለጽነው ከሆነ እንዴት ሆኖ ነው ታዲያ የክፋት ሁሉ ቋት የሆነው፣ በግፍ ቁንጣን የተጨነቀው፣ እርኩስ ዕኩይና አረመኔ የሆነው ወያኔ ጭልጥ ብሎ ከሔደበት፣ ጥልቅ ብሎ ከሰመጠበት፣ ክፍት ብሎ ከረከሰበት፣ ክርፍት ብሎ ከገማበት፣ ጭክን ብሎ ከሰየጠነበት የህልውናው መሠረት አድርጎ ከያዘውና ከተላበሰው ዕኩይ አረመኔያዊ ማንነቱ ተለውጦ ቅዱስ በመሆን ችግራችንን ይፈታልናል፣ ሰላም ያወርድልናል ብሎ ተስፋ በማድረግ የወያኔን መለወጥ ሊጠብቅ የቻለው??? እንዴት ሰይጣን ወደ መልአክነት ይለወጣል ተብሎ ይጠበቃል? እንዴት ከእባብ እንቁላል እርግብ ይፈለፈላል ተብሎ ተስፋ ይደረጋል? ይሄንን ተስፋ አድርጌ እልፍ ዓመታት ብኖርና ብጠብቅ አፌን እንደከፈትኩ ከንቱ ሆኘ እቀራለሁ እንጅ ተስፋዬ እውን ሊሆን ይችላል ወይ??? ፈጽሞ ሊሆን የማይችል ከሆነስ በራሴ ላይ እየቀለድኩ፣ በሕይዎቴም እየተጫወትኩ አይደለም ወይ?

በመሆኑም በዚህ ጅልነት በተሞላ ከንቱ የደነቆረ አስተሳሰባችን ምክንያት ለወያኔ ተጨማሪና ማለቂያ የሌለው ጊዜ በሰጠነው ቁጥር ወያኔ የባሰ ፈርጣማና አረመኔ ሆኖ በፍጹም ሊገረሰስ የማይችል የጥፋት ኃይል ሆኖ እንዲወጣ ዕድል እየሰጠነው፣ ምቹ ሁኔታ እየፈጠርንለት መሆኑን ጠንቅቀን ልናውቅ ይገባናል፡፡ ሰሞኑን የወያኔ የመረጃ መረብ ደኅንነት ድርጅት (ENSA) ኃላፊ ሜ/ር ጄኔራል ተክለብርሃን ወልደ አረጋይ ወራይና ከተባለ መጽሔት ጋር ባደረገው ቃለምልልስ በግልፅ የተናገረውን አልሰማቹህም እንዴ? የትግሬ ሕዝብ ካለውና ከሚታወቅበት ሰብእናው፣ ማንነቱ ፍጹም ተቃራኒ የሆነ ባሕርይ ከቀባጠረና ትግሬ የሌለውን ታሪክና ቅርስ እንዳለው አድርጎ ካወራ በኋላ ሕወሓት ወደፊት በኢትዮጵያ የትግሬን ፍጹማዊ የበላይነትን እውን ለማድረግ በወጣቱ የትግሬ ትውልድ ላይ በርትቶ እየሠራ እንደሆነ ማንንም ሳይፈራና ሳያፍር በይፋ ተናገረ እኮ! አልሰማህም እንዴ??? መስማትስ ትሰማለህ፣ ማየትም ታያለህ ሰምተህና ዓይተህ ግን የምታየውንና የምትሰማውን እውነት ማመን አትፈልግም እንጅ፡፡

ልኂቃን ተብየው ሆይ! እንግዲህ ማመን ፈለክም አልፈለክ እነሱ ግን ከመጀመሪያው ጀምሮ የሚያስቡትና በርትተውም እየሠሩበት የኖሩት ያሉትም ጉዳይ ይሄንን ነው፡፡ እውነቱና በግልጽ የሚታየው ይሄ ከሆነ ታዲያ 27 ዓመታት ሙሉ እያወከው ያንተ የወያኔ “ወደ ቅዱስነት ይለወጣል!” የሚለው ቅዠትህ ከየት መጣ??? አዎ ምድረ ከብት አንተ ብቻ ተኝተህ ቅዠትህን ቃዥ! እነሱም እራሳቸውን ለዘለቄታው ፍጹም የበላይ አድርገው ለማኖር ጥርሳቸውን ነክሰው ይሥሩ! ከዚያ ዘለዓለምህን እየማቀክ ስታልቅ ሒሳብህን ታገኛታለህ!!! ሰው እንዴት በገዛ ዓይኑ የሚያየውን፣ በገዛ ጆሮው የሚሰማውን ተጨባጭ እውነታ ትቶ በዓይኑ ያላየውን፣ በጆሮው ያልሰማውን፣ ሊሆንም የማይችለውን ቅዠቱን አምኖ ተስፋ ያደርጋል? ይሄ ጤነኝነት ነው???

የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ! ትሰማኝ እንደሆነ እስከ አሁን ስታደርገው የነበረውን የሕዝባዊው ዐመፅና እንቢተኝነት ዓላማ “በወያኔ ላይ ጫና አሳድሮ ወያኔ ለሁላችንም የሚጠቅም ለውጥ በሀገራችን እንዲያመጣ ለማድረግ!” ከሚለው “ይሄንን ነቀርሳ ጨርሶ ማጥፋት ማስወገድ!” ወደሚል መለወጥ ካልቻልክ አልቆልሀል!!!

በመሆኑም “ጫና ለማሳደር!” በሚል በመለስቀለስ ስናደርግ ከቆየነው ሕዝባዊ ዐመፅና እምቢተኝነት ወያኔ መጥፋቱን፣ መውደቁን፣ መገርሰሱን ካላረጋገጥን በስተቀር ከወጣን ወደማንመለስበት፣ ሁሉም ዜጋ የግድ ወደሚሳተፍበት የጨከነ፣ የቆረጠ፣ የለየለት ሕዝባዊ ዐመፅ መለወጥ ይኖርበታል!!! ከዚህ ሕዝባዊ ዐመፅ መሳ ለመሳም ሀገር አቀፍ የሆኑ የሥራ ማቆም አድማዎችን መመታት ይኖርባቸዋል፡፡

እዚህ ላይ ወያኔ የኢትዮጵያ ሕዝብ የቆረጠ፣ የጨከነ፣ የለየለት ሕዝባዊ ዐመፅ እንዳያደርግ ለማድረግ ስለሚነዛው ሸፍጠኛ ስብከቱ ግልጽ ማድረግ የምፈልገው ነገር አለ፡፡ ወያኔ እሱ በሕዝባዊ ዐመፅ ቢወድቅ፣ ቢገረሰስ፣ ቢወገድ “ሥልጣን የሚረከብ የተዘጋጀ፣ የተደራጀ፣ የሚተካ ኃይል ስለሌለ አስከፊ የእርስበእርስ እልቂት ይከሰታል፣ ሀገሪቱም ትፈራርሳለች!” እያለ ሕዝቡን በፍርሐት ጠፍንጎ ይዞታል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ! ወያኔ በግዛት ዘመኑ ጠንካራ የተቃዋሚ ኃይል እንዳይፈጠር እንዳይወጣ አድርጎ ሲያደናቅፍ ሲያሰናክል የቆየበት ምክንያትም በዚህ ማስፈራሪያ እያስፈራራ የግዛት ዘመኑን ለማራዘም ካለው ጠባብ፣ እራስ ወዳድ ምኞቱና ፍላጎቱ የተነሣ ነው፡፡ ነገር ግን እመነኝ የፈለገ ነገር ቢሆን ወያኔን ስታስወግድ ተከትሎ የሚመጣው መጠነኛ ችግር በወያኔ አስከፊ አገዛዝ ስር ሆነህ ብትቆይ ሊደርስብህ፣ ሊመጣብህ፣ ሊከሰትብህ ከሚችለው አደጋ፣ ጉዳት፣ ችግር፣ ቀውስ፣ ውድቀት፣ ውርደት፣ እልቂት…. ፈጽሞ አይብስብህምና በወያኔ ማስፈራሪያ ተሸብበህ፣ ተጠርንፈህ ወያኔን ነቅለህ ከመቅበር አትቆጠብ፣ ወደ ኋላ አትበል!!!

እርግጥ ነው እዚህም እዚያም በወያኔና ቢጤዎቹ ጭፍሮች ሊቀሰቀስ የሚችል ችግር መፈጠሩ አይቀር ይሆናል፡፡ ወያኔን ያህል ነቀርሳ ሲነቀል ምንም ዓይነት ችግር እንዳይከሰት ከጠበቅን የዋሀን መሆናችን ነው፡፡ ካልደፈረሰ አይጠራምና “ይለይለት!” ማለት ይኖርብናል፡፡ በምንም ተአምር ቢሆን ወያኔ የሚለውን ያህል ቀውስና አደጋ ግን ሊከሰት እንደማይችል እርግጠኛ ሆኘ ልነግርህ እወዳለሁ፡፡

ምክንያቱም አንተ (የኢትዮጵያ ሕዝብ) የላቀ ማንነት፣ የሠለጠነ ባሕል፣ ቀደምት ሥልጣኔ፣ ከፍያለ የቅስም (የሞራል) ደረጃ፣ ስር የሰደደ ሃይማኖት፣ የሚያኮራ ታሪክ፣ የበለጸገ ማኅበራዊ ሕይዎት፣ የጠበቀ የጠለቀ ትስስር፣ የዳበረ ግለኝነትን ተፃራሪ አስተሳሰብ ወዘተረፈ. ያለህ የከበርክ የላቅክ ታላቅ ሕዝብ ነህ!!! እንዲህ ዓይነት ሕዝብ የፈለገ ቢሆን፣ በምንም ዓይነት ሁኔታ እንደ አረማዊ ሕዝብ ወያኔ የሚለውን ዓይነት ቀውስ ሊያስተናግድ አይችልም፡፡

እርግጥ ነው በታሪክህ ከላይ የጠቀስኩትን እሴቶችህን የሚጻረሩ ቀውሶች አስተናግደህ ታውቃለህ፡፡ ሁሉም ቀውሶችህ ግን በባዕዳን ሸፍጠኛ ጣልቃ ገብነት የተፈጠሩ፣ የተከሰቱ እንጅ በራስህ የፈጠርካቸው፣ ያመጣሀቸው ቀውሶች አይደሉም፡፡ ባዕዳን ለየራሳቸው ጥቅም ሲሉ ያደረጉት ሸፍጠኛ ጣልቃገብነት ምን ያህል እንደጎዳህ፣ ለድህነት እንደዳረገህ፣ ሀገርህን እንዳመሰቃቀለብህ ጠንቅቀህ ታውቃለህ፡፡ ስለሆነም ከዚህ በኋላ የባዕዳንን ጣልቃገብነት የሚፈቅድ ብሔረሰብና የዚህ ወይም የዚያ ዕምነት ተከታዮች ይኖራሉ ተብሎ አይታሰብም፡፡ የገዛ ሀገሩ እንድትፈራርስ የገዛ ሕዝቡ ጨርሶ እንዲያልቅ የፈለገ ካልሆነ በስተቀር፡፡ ይሄ ደግሞ ሊታሰብ የሚችል አይመስለኝም፡፡ ካለፈው ታሪኩ ምንም ዓይነት ትምህርት ሳይወስድ እራሱን ለባዕዳን ባሪያ አድርጎ ቀጥሮ የገዛ ሀገሩንና የገዛ ወገኑን ጥቅም ለዓረብና ለምዕራባውያን አሳልፎ ለመስጠት የባዕዳንን እጅ የሚያስገባ፣ ጣልቃ ገብነታቸውን የሚፈቅድ የሚኖር ከሆነ ግን ዋጋ የሚከፍል ይሆናል፡፡ ተቃዋሚ ነኝ ሕዝብን እመራለሁ የሚል አካል ሁሉ ሕዝቡ በምንም ሁኔታ ቢሆን እራሱንና ሀገሩን ለችግር እንዳይዳርግ፣ በጠላት ሴራ እንዳይጠለፍ የማንቃቱን ሥራ ከወዲሁ በርትተው ይሥሩ፡፡

እነኝህ እነኝህ ጥንቃቄዎች በሚገባ ከተወሰዱ፣ ሕዝባችን “ከራስ በላይ ነፋስ!” ብሎ ለራሱ፣ ለሀገሩ ጥቅም ቅድሚያ በመስጠት የባዕዳንን ጣልቃገብነት መከላከል እስከቻልክ ጊዜ ድረስ፣ ጆሮህን ለባዕዳን እስከደፈንክና ለራስህ ለሀገርህ እስካሰብክ፣ እስካደላህ፣ እስከተቆረቆርክ ጊዜ ድረስ ፈጽሞ የወያኔ ማስፈራሪያ ሊያሠጋህ አይችልምና አትፍራ!!! አንዴ ብቻ ሕዝባችን ከወያኔ እጅ ወጥቶ ከእጃችን በገባልን እንጅ እንኳን ለኢትዮጵያ ለአፍሪካ የሚበቃ ጀግና፣ ቆራጥ ሕዝብ አለን! እንኳን ወንዱ ሴቷ፣ እንኳን ወጣቱ ሽማግሌው ዘምቶ ሀገሩንና ሕዝቧን አረጋግቶ ሁሉን አቀፍ የሆነ ሕዝባዊ መንግሥት እንዲመሠረት ማድረግ የሚችል ቆራጥ ሕዝብ አለን አትፍራ!!!

ሕዝቡ የሚፈልገውና የሚያስበው እሱ እራሱ ሕዝባዊ መንግሥት መሥርቶ መብቱ ተከብሮለት በሀገሩ በነጻነት ለመኖር እንጅ እርስ በእርስ ተፋጅቶ ለመተላለቅ ባለመሆኑ ሕዝቡ ወያኔን ካስወገደ በኋላ ሊያስብ የሚችለው እራሱን አረጋግቶ በሕዝብ ምርጫ ሕዝባዊ መንግሥት እስኪመሠረት ድረስ የሽግግር መንግሥት ማቋቋሙን ብቻ ነው፡፡ የሕዝባችን ሐሳብ፣ ፍላጎትና ምኞት ይሄ ከሆነና እርስ በእርሱ እንዲጨፋጨፍ፣ ሀገሩን እንዲያፈራርስ የሚያስገድደው አካል ሳይኖር እንዴት ነው ታዲያ ሌላ ጉዳይ ተፈጽሞ ሀገር ልትፈርስ ሕዝብስ ሊያልቅ የሚችለው? ይሄንን የሚያደርግ ከማርስ የሚመጣ ሌላ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይኖራል ወይ?

ስለሆነም የወያኔ ማስፈራሪያ ፍጹም ተጨባጭነት የሌለው ነውና አትፍሩ!!! ከላይ እንደጠቀስኩት ግን ወያኔ በሕዝባዊ ዐመፅ ተጠርጎ በሚወድቅበት ሰዓት እዚህም እዚያም የወያኔ ጭፍሮች የሚቀሰቅሷቸው ችግሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ መጠበቅ ይኖርብናል፡፡ ያ ጊዜ ለወያኔና ለጭፍሮቹም የቀውጢ ሰዓት ስለሚሆንና እራሳቸውን ከሕዝብ ሠይፍ ለማዳን እንዲሯሯጡ ሁኔታው ስለሚያስገድዳቸው ሊቀሰቅሱት የሚችሉት ችግር ምንም ሳይከሰት ወያኔን ልንገላገለውም እንችል ይሆናል፡፡ በዛም ሆነ በዚህ ወያኔና ጠንቁ የግድ ከስር ተነቅሎ ካልጠፋ በስተቀር ሀገርና ሕዝቧ ዘለዓለም በዚህ ነቀርሳ ሲማቅቁ መኖራቸው ስለሆነ የሚከፈለው መሥዋዕትነት ተከፍሎ ወያኔንና ጠንቁን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመገላገል መቁረጥ፣ መጨከን አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው፡፡

ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ እንደገለጽኩት ከወያኔ ጋር ተደራድረን በሰላም መለያየታችን ወይም ሰላማዊ ሽግግሽ እንዲከወን ማድረጉ ወይም ወያኔን ያካተተ ብሔራዊ እርቅ እንዲፈጸም ማድረጉ ለሕዝባችንና ለሀገራችን ጎጅ እንጅ ጠቃሚ አይደለምና ከወያኔ ጋር በሰላም ስለመለያየት ጨርሶ ፈጽሞ ልናስበው አይገባም፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ ሕዝብ ከወያኔ ጋር በሰላም ከተገላገለ እስከወዲያኛው እንዳጣቸው የሚቀሩ በርካታ ብሔራዊ ጥቅሞች አሉ፡፡ ወያኔ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል!” እያለ በክህደት በተለይ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ለተፈራረማቸው ስምምነቶች ሁሉ ተገዥ የመሆን ዕዳንም ጨምሮ ነው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚረከበው፡፡

በኃይል ቢወገድ ግን ቀድሞውንም ሥልጣን የያዘው በሕዝብ ይሁንታና ፈቃድ ሳይሆን በኃይል ስለሆነ የራሱን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲል የሀገር ክህደት በመፈጸም ከባዕዳን ጋር የተፈራረማቸውን ውሎች የኢትዮጵያ ሕዝብ “አናውቅም! ውክልና አልሰጠነውም ለአንድም ቀን አልተቀበልነውምና የሱ ስምምነቶች ሊገዙን አይችሉም! ይሄንን የማድረግ መብት አልነበረውም!” የማለት ዕድል ይኖረዋል፡፡ ይሄንን ዕድል አግኝተን ለሱዳን ለጅቡቲ የተሰጠውን መሬት ለሸአቢያ የተሰጠውን የአሰብ ወደብ ወዘተረፈ. መልሰን ለማግኘት እንዲቻል የተከፈለው መሥዋዕትነት ተከፍሎ ወያኔን በኃይል ማስወገድ ይኖርብናል! ለዚህም የኢትዮጵያ አምላክ ይርዳን! አሜን!!!

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
amsalugkidan@gmail.com

Filed in: Amharic