>

ጎንደር እንዴት ነሽ...? (አፈንዲ ሙተቂ)

በዚሁ የፌስቡክ ሜዳ ላይ ስለ ሀረር ጽፈናል፡፡ ስለገለምሶ በብዛት ጽፈናል፡፡ ስለድሬ ዳዋም ጽፈናል፡፡ ስለ ሸገርም ጽፈናል፡፡ ስለ ሰላሌም ጽፈናል፡፡ ስለ ወለጋም ጽፈናል፡፡ ስለወሎም ጽፈናል፡፡ ስለትግራይ ጽፈናል፡፡ ስለኤርትራም ጽፈናል፡፡ ዛሬ ደግሞ ተራው የጎንደር ሆኖ ተገኘ፡፡ ይህም መነሻ አለው፡፡
—-
አንድ መሳፍንት የሚባል ነገረኛ ጎንደሬ እዚህ ፌስቡክ ላይ ይገኛል፡፡ ነገሮችን እየነካካ ሰውን ያስለፈልፋል፡፡ በፌስቡክ እየጫጫረ ብዕር ያስመዝዛል፡፡ ምን እንደነካው እንጃ በኔዋ ሀረርጌ ጉያ ውስጥ በሰነበተበት ጊዜ ያየውን ሲተረተረልን ነው የከረመው፡፡ በዚያ አካሄዱ እኛ ጎንደሬዎች ሀረርጌን በብዕራችን ተቆጣጥረናታል የሚል ነበር የሚመስለው፡፡ ይሁንና እኛም ዋዛ አይደለንም! እርሱ ሀረርጌን በብዕሩ ጠቅልሎ የሚወርስ ከሆነ እኛም ጎንደርን መውረስ እንደምንችል ለማሳየት ይቻለን ዘንድ እነሆ የኢትኖግራፊ ፈረሳችንን ኮርኩረን ተነስተናል፡፡ ቼ ፈረሴ! ሽቅብ ብረር ወደ ጎንደር!!

አዎን! ይህ ልጅ ጎንደሬ መሆኑን የነቃንበት “መሳፍንት ነኝ” ብሎ ሲተዋወቀን ነው፡፡ “መስፍን ነኝ” ቢል ኖሮ መገኛውን ለማወቅ በጣም ይቸግረን ነበር፡፡ መሳፍንት ግን ምንጊዜም ጎንደሬ ነው-እኛ እንደምናውቀው፡፡ “መሳፍንት ሽፍራው”ን ታስታውሱት የለ?… በምርጫ 97 በግል ተወዳዳሪነት ቀርቦ በነበረበት ወቅት ሲያካሄደው በነበረው የምረጡኝ ዘመቻ ማንኛውም የአዲስ አበባ ነዋሪ የሚያስታውሰው ይመስለኛል፡፡ በሀገር ባህል ተጀቡኖ የተነሳቸውን ትልልቅ ፎቶግራፎች በመኪናው ላይ ለጥፎ፤ በፎርቶ መጋላው ላይ በተሰቀሉት ማይክራፎኖች “ሰፊው የወረዳ 12 ህዝብ፣ እንደምን ሰነበትክ;..እኔ ወኪልህ አለሁልህ” እያለ የምረጡኝ ጥሪውን ሲያጧጡፈው ትውስ ይለናል፡፡ መሳፍንት ሙጬንስ ታስታውሱታላችሁ? አይ መሳፍንት! እንዲህ ዓይነት ስም መኖሩን ለመጀመሪያ ጊዜ ያወቅኩት የርሱን ስም በፖስተሮች ላይ በማየቴ ነው፡፡

“መሳፍንት ሙጬ” ተቀማጭነቱ በአስመራ ነበረ፡፡ ከ1983 በፊት በአስመራው “ኮከብ ሙዚቃ ቤት” አሳታሚነት ይወጡ በነበሩት የነ አክሊሉ ስዩም፣ ስዩም ጥላሁን እና ዳውድ አማን የሙዚቃ ስራዎች ላይ ዋነኛው የግጥም ደራሲ ሆኖ ይሳተፍ የነበረው እርሱ ነው፡፡ እናም በነዚያ ፖስተሮች ላይ ከአፍሮ ጸጉሩ ጋር በተነሳው ፎቶ ስር “የግጥም ደራሲ፡ መሳፍንት ሙጬ” ተብሎ ዘወትር ይጻፍ ነበር፡፡

በነገራችን ላይ “ሙጬ”ም የጎንደር ስም መሆኑን ልብ አድርጉልኝ፡፡ ስያሜው ኦሮምኛ ነው፡፡ በአማርኛ ሌላ ትርጉም እንዳለው ግን እንጃ! የበርካታ የጎንደር ሰዎች የአባት ስም ሆኖ አጋጥሞኛል፡፡ ለምሳሌ ታደሰ ሙጬ የሚባል የስራ ጓደኛ ነበረኝ፡፡ ታዋቂ የሳይኮሎጂ ምሁር የሆኑት ፕሮፌሰር ማሞ ሙጬም አሉላችሁ፡፡ የቴዲ አፍሮ ባለቤት የአባት ስምም ሙጬ ነው (አባቷ የጎንደር ሰው እንደሚሆኑ አልጠራጠርም)፡፡

አቦ ኤጭ! ጎንደሬው መሳፍንት “በዘበዛ” አደረገን እኮ! ይሄ ቀሽቲ የሆነ ልጅ! ስለሌላ ጉዳይ አወራለሁ ብዬ ስለርሱ ስም እፈላሰፋለሁ እንዴ?…. ከስሙ ምን አለኝ እስቲ?! ቢፈልግ ካሳ ይሁን! ቢፈልግ ገብርዬ ይሁን! ቢፈልግ ውቤ ይሁን! ቢፈልግ መኳንንት ይሁን! ቢፈልግ “አፈንዲ” ይሁን! ከእንግዲህ እርሱን ሳናስፈቅድ ከርሱ ስም ጋ ድርሽ አንልም! እርሱን ያስገኘችውን ጎንደርን ግን አትንኳት ሊለን አይችልም፡፡፡

የጎንደሪቱን ወሬ ከምን እንጀምር? ከየትም መጀመር እንችላለን፡፡ እንደኔ ግን ከጎንደር ጋር የተዋወቅኩበትን አጋጣሚ ባስቀድም የተሻለ ይመስለኛል፡፡

የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤታችን ካፈራቸው አስደናቂ ተማሪዎች አንዱ አያሌው አብነት መሆኑን ነግሬአችሁ ነበር አይደል?… አዎን! የሁለተኛ ክፍል አለቃችን የነበረው አያሌው እንግሊዝኛ እዘፍናለሁ ይልና እንዲህ ይዘባነንብን ነበር (አያሌው ይህንን ዘፈን ሲዘፍን እኛ ውሪዎች በዙሪያው ተኮልኩለን “ፐረስ ፐረስ” እያልን እንቀበለው ነበር)፡፡

አይ ጌቾ ጌቾ
አይ ጌቾ ቤቢ
ማዘር ከፋዘር
ወለዱ ሲስተር
ሄዱ በአየር
ገቡ ጎንደር፡፡

አያሌው “ገቡ ሀረር” ወይንም “ገቡ ጨርጨር” ቢል እንኳ ግጥሙ ቤት ይመታለት ነበር፡፡ ነገር ግን የሚያውቃትን ሀረርን ትቶ የማያውቃትን “ጎንደር”ን የጠራበትን ምክንያት በፍጹም አላውቀውም፡፡ እርሱ የጠቀሳት “ጎንደር” የት እንደምትገኝም እውቀቱ አልነበረንም፡፡ እናም አንድ ቀን “ጎንደር ምን ማለት ነው?” ብዬ ስጠይቀው ከትምህርት ቤታችን ግድግዳ ላይ ወደነበረው ትልቅ የኢትዮጵያ ካርታ መራኝና “ጎንደር ማለት ይህቺ ናት” ብሎ አሳየኝ (አያሌው በእድሜው ከኛ ትልቅ ነው፤ ትምህርቱንም አቋርጦ እንደገና የጀመረ በመሆኑ እኛ የማናውቀውን ብዙ ነገር ያውቃል)፡፡

ስለ ጎንደር ሰፋ ያለ መረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰጠኝ ደግሞ ወላጅ አባቴ ነበር፡፡ አባቴ ጎንደርን ያነሳልኝ “ድሮ ሐኪሞች የት ነበር የሚሰለጥኑት?” የሚል ጥያቄ ባቀረብኩለት ወቅት ነበር፡፡ የርሱ ምላሽም “ጎንደር ነው” የሚል ነበር፡፡ በሌሎች ከተሞች እንደዚያ ዓይነት ኮሌጅ ሳይኖር በጎንደር የሐኪም ማሰልጠኛ የተከፈተበትን ምክንያት ስጠይቀው “ይህንን ያደረገው የንጉሡ መንግሥት ነው፡፡ በዚያ ዘመን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሲከፈት በሀረርም የመምህራን ኮሌጅ ተከፍቶ ነበር፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላም የአሁኑ የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ የሀረር እርሻ ኮሌጅ ተብሎ ተቋቋመ፤ ለብዙ ዘመናት በሀገሪቱ የነበሩት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እነርሱ ነበሩ፤ ከዚያም በ1960ዎቹ መጀመሪያ ላይ የጎንደር ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ተከፈተ፤ አዲስ አበባ ዋና ከተማ ስለነበረች ነው ዩኒቨርሲቲ የተከፈተላት፤ ሀረር እና ጎንደር ግን የዘመኑ ትልልቆች በመሆናቸውና በጣም ጥንታዊ በመሆናቸው ኮሌጅ የተከፈተላቸው ይመስለኛል” አለኝ፡፡ በዚህም መነሻነት ጎንደርን አከበርኳት!
———
አዎን! ዛሬ የኢትኖግራፊ ፈረሳችን ጎንደር ገብቷል፡፡ ሽቅብ እየሰገረ ታሪክ ሲሰራባት ወደ ከረመባት የሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያዋ ጥንታዊት ከተማ ደርሷል፡፡

ጎንደር! የሰርፀ ድንግል ሀገር! የሱስንዮስ ሀገር! የፋሲለደስ ሀገር! የባካፋ ሀገር! የአድያም ሰገድ እያሱ ሀገር! የቴዎድሮስ ሀገር! የሱልጣን ሙክታር ሀገር! ነገሥታት ታሪክ ሲሰሩባት የነበሩባት ምድር!

ጎንደር የራስ ዓሊ ሀገር! የእቴጌ ምንትዋብ ሀገር! የራስ ማርዬ ሀገር! የደጃች ውቤ ሀገር! የደጃች ክንፉ ሀገር! የደጃች አሞራው ውብነህ ሀገር! መሳፍንትና መኳንንት ፖለቲካን እንደ እንዝርት ያሽከረከሩባት መንደር!

ጎንደር! የቅኔ ሀገር! የተረት ሀገር! የግጥም ሀገር! የዘፈን ሀገር! የወረብ ሀገር! የመዝሙር ሀገር! የዜማ ሀገር! የመዲና ሀገር! የዘለሰኛ ሀገር! የምትሀታዊ ቅላጼና የተውህቦ ማህሌት ደብር!

ጎንደር! የስሜን ተራሮች ሀገር! የጣና ሀገር! የጎርጎራ ምንጮች ሀገር! የዋሊያ ሀገር! የቀይ ቀበሮ ሀገር! የጭላዳዎች ሀገር! ውብ የተፈጥሮ ጸጋዎች ከርስ!

ጎንደር! የአለቃ ገብረሃና ሀገር! የብርሃኑ ዘርይሁን ሀገር! የአስማማው ሀይሉ (አያ ሻረው) ሀገር! የታማኝ በየነ ሀገር! የደርባባው አቡኑ ሀገር! የይርጋ ዱባለ ሀገር! የሻምበል በላይነህ ሀገር! የየሺ እመቤት ዱባለ ሀገር! የአሰፉ ደባልቄ ሀገር! የማዲንጎ አፈወርቅ ሀገር! የማን አልሞሽ ዲቦ ሀገር! የምድር ጨው የሆኑ ደራሲያንና የጥበብ አዝመራዎች የተገኙበት መሬት!
——-
ጎንደር የቆንጆዎች ምድር ነው፡፡ ውበታቸው ማንንም ያስንቃል ይባላል፡፡ እነ ጣይቱ ብጡል እና እነ እቴጌ ምንትዋብ ደማቸው ከወሎ ኦሮሞ ቢሆንም የተወለዱት በጎንደር ነው፡፡ ሌሎች ብዙ ቆንጃጅትም ከጎንደር ተነስተዋል፡፡ ጎንደሬ የወንድ ሸበላዎችም በሽበሽ ናቸው፡፡ ሺህ ምንተሺህ ይሆናሉ፡፡ በጥቅሉ ለጎንደሬዎች እንዲህ ተብሎ ተገጥሞላቸዋል ይባላል፡፡

የጎንደር ልጅማ የጣት ቀለበት ነው
ሹልክ ያለ እንደሁ ፈላጊው ብዙ ነው፡፡

——-
“አፈንዲ” የሚለው ስም መሰረቱ ቱርክ ነው፡፡ በ19ኛው ክፍለ ዘመን በቱርክ ኢምፓየር የበላይነት ስር የነበሩት ግብጾች ስሙን ከቱርክ ቋንቋ ወርውሰት ነበር፡፡ ይህንን ስም ወደ ኢትዮጵያ ያስገቡትም እነኛ ግብጻዊያን ናቸው፡፡ ዘመኑም ሀረርን ከ1875-1885 በያዙበት ጊዜ ነው፡፡ ታዲያ እኔ የማውቃቸው አፈንዲዎች በሙሉ የሀረር ሰዎች በመሆናቸው “አፈንዲ” በምስራቅ ኢትዮጵያ ብቻ የሚገኝ ይመስለኝ ነበር፡፡ ይሁንና በጎንደርም የሚታወቅ ስም መሆኑን ስረዳ በጣም ነበር የተገረምኩት፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡

በ1989 የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያለሁ ጉንፋን ቢጤ ጠልዞኝ ወደ ክሊኒክ ሄድኩ፡፡ ያጋጠመችኝ ነርስ ሰሚራ ትባላለች፡፡ ህክምናውን አድርጋልኝ ካበቃች በኋላ ትውልዴንና እድገቴን ጠየቀችኝ፡፡ ከሀረር መሆኔን ነገርኳት፡፡ “አፈንዲ ምን ማለት ነው” አለችኝ፡፡ በአቅሜ አብራራሁላት፡፡ “ይገርማል.. የአባቴ ስም አፈንዲ ነው፤ ሰዎች በአባቴ ስም በጣም ይደነቃሉ” አለችኝ፡፡ “ያንቺ ትውልድ የት ነው” ስላት ጎንደር መሆኑን ነገረችኝ፡፡ በነገሩ ተገረምኩ፡፡ “ምናልባት ጎንደር በታሪካዊነቷ የሀረር እህት በመሆኗ በሀረር የሚበዛው አፈንዲ እዚያም መገኘቱ ግዴታ ሆኖ ይሆን?” እያልኩ ተደመምኩ፡፡
——-
የጎንደር ክፍለ ሀገር በጥንት ዘመናት “ቤጌምድር” ነበር የሚባለው፡፡ “ጎንደር” የአንድ አውራጃ ስም እንጂ የክፍለ ሀገሩ ስም አልነበረም፡፡ በተለይም “ጎንደር” በሚለው ስም የምትታወቀው የአርባ አራት አድባራት መዲና የሆነችው ጥንታዊቷ ከተማ ናት፡፡ “ቤጌምድር” የሚለው ስም እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሤ ዘመን ድረስ በኦፊሴል ያገለግል ነበር፡፡ ደርግ ሲመጣ ግን ክፍለ ሀገሩም ሆነ አውራጃው በአንድ ስም እንዲጠሩ ተደረገ፡፡

በገዥዎች የሚፈጸመው እንዲህ ዓይነቱ የስም ለውጥ ብዙ ነገሮችን ያቃውሳል፡፡ በተለይ የታሪክ መረጃንና ማስረጃን ከመጠበቅ አንጻር ጉዳቱ ከፍተኛ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ወጣት አንባቢ በጥንት ሰነዶች ውስጥ የተመዘገበው ቤጌምድር የአሁኑ የጎንደር ክፍለ ሀገር እንደሆነ ለማወቅ በጣም ይቸገራል፡፡ “ቤጌምድር” እና “ጎንደር” የአንድ አካባቢ ስያሜዎች መሆናቸውን ለማወቅ የሚችለው ስለሁለቱም ያነበበ ሰው ብቻ ነው፡፡ በሌላ በኩል የጥንት ስያሜዎች ከተለወጡ አንዳንድ የታሪክ ሽሚያ ናፋቂዎች “በዚህ ስም የተጠቀሰው የኛ አካባቢ ነው” በማለት ውዝግብ ሊፈጥሩ ይችላሉ፡፡ የታሪክ ምሁራንም በጥንት ስያሜ የተጠቀሰውን አካባቢ ለመጠቆም በመላምት ብዙ ይባዝናሉ፡፡ (ለምሳሌ አንዳንድ ተመራማሪዎች “ደዋሮ” የሚባለውን ጥንታዊ ሱልጣኔት ከአሁኑ የዳውሮ ዞን ጋር በማመሳሰል የታሪክ ስህተት እንደሚፈጽሙት ማለት ነው)፡፡
ስለዚህ ክፍለ ሀገሩ እንደ ጥንቱ ቤጌምድር ተብሎ ቢጠራና ጎንደር የታሪካዊቷ ከተማ ስም ሆኖ ቢቀጥል ጥሩ ነበር የሚል ሃሳብ አለኝ፡፡
——
ጎንደርን የቆረቆራት አጼ ፋሲል ነው፡፡ ፋሲል የአጼ ሱስንዮስ ልጅ ነው፡፡ ይህ ሱስንዮስ አጼ ያዕቆብ በሚባለው ወንድሙ ላይ ሸፍቶ ለረጅም ዐመታት ሸዋ ከትቶ ነበር፡፡ ወንድሙን ድል አድርጎ አልጋውን ከያዘ በኋላ ግን ከህዝብ ጋር ያጋጨውን ትልቅ ስህተት ፈጸመ፡፡ ይኸውም “እየሱሳዊያን” በሚባሉት ሚስዮኖች አማካኝነት የካቶሊክ ክርስትናን መቀበሉ እና ህዝቡም በዚህ እምነት እንዲገባ አዋጅ ማወጁ ነው፡፡ ነገር ግን ለሺህ ዓመታት በእስክንድርያው የተዋህዶ እምነት ውስጥ የኖረው ህዝብ የሱስንዮስን እርምጃ በግልጽ ተቃወመ፡፡ ከአባቶቹ የወረሰውን እምነት እንደማይቀይር በግልጽ አስታወቀ፡፡ አጼ ሱስንዮስ አዋጁን በግዴታ ለማስፈጸም ተነሳ፡፡ ሀገሪቱ በጦርነት አዙሪት ውስጥ ተዘፈቀች፡፡ ብዙዎች አለቁ፡፡ ብዙዎች ተጋዙ፡፡ ብዙዎች ተሰደዱ፡፡ ይህ ምስቅልቅል ጋብ ያለው አጼ ሱስንዮስ ስልጣን በቃኝ ብሎ ወደ በረሃ ከኮበለለ በኋላ ነው፡፡ በርሱ ምትክ የነገሠው ፋሲለደስ መጀመሪያ የወሰደው እርምጃ አባቱ ያበላሸውን ማቃናት ነው፡፡ በመሆኑም የካቶሊክ እየሱሳዊያንን “በጥበብና በሙያችሁ ልታግዙኝ ትችላላችሁ፤ እምነታችሁን በህዝቤ ላይ እንድትጭኑ ግን አልፈቅድላችሁም” በማለት በሱስንዮስ ጊዜ የተሰጣቸውን የፈላጭ ቆራጭነት ስልጣን ነፈጋቸው፡፡

ፋሲል ሀገሩን ካደላደለ በኋላ ዝም ብሎ አላረፈም፡፡ ለዘመናት ቋሚ መዲና ሳይኖረው ከቦታ ቦታ ሲዘዋወር ለነበረው የኢትዮጵያ ሰለሞናዊ ነገሥታት መንግሥት ዋና ከተማ የመቆርቆሩን ሃሳብ ወዲያውኑ ነው የተገበረው፡፡ በመሆኑም ዛሬ የዓለም ቅርስ ሆነው የተመዘገቡትን አብያተ መንግሥታት በመገንባት ቋሚ መዲና ወጠነ፡፡ ቤተ ክርስቲያናት በስፍራው ተገነቡ፡፡ ህዝብ በከተማዋ ሰፈረባት፡፡ ጎንደር ለሁለት መቶ ሀምሳ ዓመታት የኢትዮጵያ መዲና ሆና ታሪክን የዘወረችበትን ጉዞዋን አሀዱ ብላ ጀመረች፡፡

Filed in: Amharic