>

ስደተኛዉ የአዲስ ጉዳይ መፅሔት ጋዜጠኛና አዘጋጅ ኢብራሒም ሻፊ አረፈ

በካሳሁን

ካስዬ እባክህ ጥሩ ስሜት ላይ አይደለሁም…አዝኛለሁ…ደብሮኛል…ጉልበቴን አሞኛል…” ሲለኝ  “ኢብሮ ታዲያ መታከሚያ ገንዘብ…” ንግግሬን አላስጨረሰኝም ካስሽ እኔ ምንም አልፈልግም” አለኝ። በቂ ነገር ኑሮት እንዳልሆነ ከባህሪው እረዳለሁ::
ከ20 በላይ ጋዜጠኞች በተሰደዱ ወቅት ገንዘብ አሰባስበን በግሎባል አሊያንስ በኩል ወገናዊ እገዛ ስናደርግ ኢብሮ “ካስሽ እባካችሁ ሌሎቹን እርዷቸው እኛ ከነሱ እንሻላለን” የሚል  ነበር የኢብሮ የመጨረሻ ቃል።

ኢብሮ ሕልሙን ሳይኖር ያለፈ የህወሓት ሰለባ ወንድማችን ነው። በምርጫ 97 በፖለቲካ አመላከከቱ ምክንያት ታስሮ ሰቆቃ torture ተፈጽሞበታል።በሸዋሮቢት ታስሮ በደረሰበት ድብደባ የጉልበት በሽተኛ ሆኖ ያነክስ ነበር::
የዚያ ስቃይ እስከ ዕለተ ሞቱ አብሮት ኖሯል። በስቃይ ተሰዶ፣ በስቃይ ሞቷል። እኛም እንደዋዛ አጥተነዋል። በስደት ሕይወት ካጣናቸው ጋዜጠኞ መካከል ሁለተኛው ነው። በኬንያ መዲና ናይሮቢ የሚሊዮን ሽሩቤን አሟሟት እናስታውሳለን።
በስደት አብረውት ሆነው እስከመጨረሻው ህልፈቱ ድረስ ለረዱት ጋዜጠኞች ምስጋና ይድረሳቸው:: ፈጣሪ እናንተን ከክፉ ይሰውር::
እኔ ግን ለምን እንደተፈጠርኩና ለምን እንደምኖር ትርጉም አጣሁ::
…………………………………………………………………………
ማሳሰቢያ
ቢያንስ ለእናቱ መጽናኛ፣ ልጃቸውን በሕይወት መልሰው ባያገኙትም እኛ ወገኖቹ ዋጋ እንደምንሰጠው ላማሳየት የገንዘብ እርዳታ እናደረጋለን።
እስከዚያው ስለርሱ የወገን ተቆርቋሪነት እና እስር የሚያውቅ  Tewdros Belay  የተባለ ወንድም ኢብሮ ከ2 ዓመት በፊት በተሰደደ ወቅት የጻፈውን አንደወረደ ላካፍላችሁ

ጋዜጠኛ ኢብራሂም ሻፊ የ1997 ዓ.ም ብሔራዊ ምርጫን ተከትሎ በተነሱ ግጭቶች በአገዛዙ በደል ከደረሰባቸው መካከል ነው፡፡ ኢብራሂም በጊዜው ፈረንሳይ ለጋሲዮን አከባቢ ከፍተኛ 12 ተብሎ በሚጠራው ትምህርት ቤት ውስጥ የሲቪክስ መምህር ነበር፡፡ በወቅቱ ተቃውሞው በተጀመረ ሰዓት ኢብራሂም ከሚያስተምርበት ት/ቤት ወጥቶ ወደ መኖሪያ ሰፈሩ በመሄድ ላይ ነበር፡፡ በመንገድ ላይ ሳለም ፌደራል ፖሊሶች የተወሰኑ የእርሱን ተማሪዎች አንበርክከው ሲገርፏቸው ይመለከታል፡፡

በአደባባይ በፌደራል ፖሊስ ከሚገረፉ ተማሪዎች መካከል እርሱ የሚያስተምራቸው ተማሪዎች ነበሩበት፡፡ ከሚደበደቡት ተማሪዎች መካከል የመምህሩን በዚያ ማለፍ የተመለከተው ተማሪ ድምፁን ከፍ አድርጎ «ቲቸር እርሶ ፖሊስ የህዝብ ነው ብለው አስተምረውናል፡፡ እርሶ ፖሊስ ህዝብን የመማታት ስልጣን የለውም ብለው አስተምረውናል፡፡ እንደምታዩት ግን ፖሊስ በአደባባይ እየቀጠቀጠን ነው» በማለት እያለቀሰ ይነግረዋል፡፡

ይህንን የተመለከተው የጊዜው መምህር፣ የትላንት ጋዜጠኛ እና የዛሬ ስደተኛ ኢብራሂም ሻፊ ፖሊሶቹን ሊያነጋግራቸው ይቀርባል፡፡ «ተማሪዎቼ ናቸው፤ እንደሰማችሁት ስለ ፖሊስ እና ስለ መሰል ጉዳዮች ትምህርት ሰጥቻቸዋለሁ፡፡ ፖሊስ ህዝብን የመደብደብ መብት እንደሌለውም ጭምር … » ከማለቱ ተማሪዎቹ ላይ የደረሰው ዱላ በእጥፉ እርሱ ላይ ይሰነዘርበት ጀምር፡፡ እዛው መንገድ ላይም ደበደቡት፡፡

በኋላም ወደ ሸዋሮቢት ይላክና ለረጅም ጊዜያት ታሰረ፡፡ በእስር ጊዜው ከባድ የሚባሉ ህመሞች ገጥመውታል፡፡ ካገጠሙት ህመሞች መካከል እስከ አሁን ድረስ ሲራመድ እንዲያነክስ የሆነው በፌደራል ፖሊስ በደረሰበት ከባድ ድብደባ ነው፡፡

Filed in: Amharic