>

አገር በአንድ ትውልድ አልተገነባም፣ በአንድ ትውልድ እብደትም አይፈርስም (ካሌብ ቢንያም)

ኢትዮጵያዊነት በደም፣ በነፍስና በመንፈስ ውስጥ ያለና የሚኖር ማንነት ነው። ይህን የህይወት ውህድ ከእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ማንነት ለመነጠል የሚታትር ደግሞ የማንነት ቀውስ የገጠመውና በስነ ልቦና በሽታ የተጠቃ ሰው ብቻ ነው። አገር በአንድ ትውልድ አልተገነባም፣ በአንድ ትውልድ እብደትም አይፈርስም። እኛ ከሌለን ኢትዮጵያ ትበታተናለች፣ ትፈርሳለች የሚለው የጨቋኞች የሃያ ሰባት ዓመት ነጠላ ዜማ “የሞኝ ለቅሶ መልሶ መላልሶ” የሚለውን የአበው ብሂል ያስታውሰኛል። በመሰረቱ ህወኃት ኢትዮጵያን አልመሰረታትም፣ ኢትዮጵያንም አያፈርሳትም። ነገር ግን እዚህ ላይ የማይካድ ሃቅ አለ፣ ህወኃት ባለፉት አርባ ሁለት ዓመታት የፀረ ኢትዮጵያ ትግሉ ኢትዮጵያዊ አንድነትን አልጎዳውም ማለት አይደለም፣ እጅጉን አቁስሎታል እንጂ። ሆኖም ግን ቆስለንም፣ ታመንም፣ አልጋ ላይ ተኝተንም፣ እስር ቤት ተጥለንም ሁሌም የነፍሳችን ጩኸት የከበረው ኢትዮጵያዊነት ነው። ይህን የጥቁር ህዝብ የክብር ካባ ሳይደርቡ አገር መምራት ይቻላል፣ ሆኖም ግን ህዝባዊ ተቀባይነትና የመሪነት ሞገስ ፈፅሞ ማግኘት አይቻልም። ለዚህም እውነተኛ ማሳያው የአቶ ለማ መገርሳ የኢትዮጵያዊነት መዝሙር ምን ያህል ይህን ሰው በልባችን እንዳነገስነው ለሁላችንም የተሰወረ አጀንዳ አይደለም።

አገር ለመምራት ፍቅር ያስፈልጋል፣ ታማኝነት ያስፈልጋል፣ እውነተኛ መሆን ያስፈልጋል፣ አገር መውደድ ያስፈልጋል፣ ቅን መሆን ያስፈልጋል። እነዚህ መሰረታዊ ነገሮች በሌሉበት ማንነት ፀጉርን አሳድጎ እኔ አርበኛ ነኝ ተከተለኝ ማለት የህዝቡን ምላሽ “አንተ ክፉ ሰይጣን ከምድራችን ጥፋ” የሚለውን በተስፋ መጠበቅ ያስፈልጋል። ህወኃት/ኢህአዴግ ባለፉት 27 ዓመታት የህዝቡን ልብ አሸንፈው የመሪነት ሞገስ/ Charisma/ ተላብሰው መምራት የተሳናቸው ዋናው ነገር እነዚህ የአንድ መሪ ባህሪያቶች በግለሰብም ይሁን በቡድን ደረጃ ስለታጡባቸው ነው። አገር መምራት ከግለሰብ ጥቅምና ስልጣን በላይ የሆነ ከባድ ኃላፊነት ነው፣ የዘጠና ሚሊዮን ህዝብ አደራና ኃላፊነት መሸከም ነው። ዛሬ ስርዓቱን የሚያንገዳግደው ይህን አገራዊና ህዝባዊ አደራ ለመሸከም የሚያስችል የመሪነትና የኢትዮጵያዊነት ቁመና ስለሌላቸው ነው። የትኛውም ስርዓት በራሱ ፍፁም አይደለም፣ ነገር ግን ለአገርና ለህዝብ ጥቅም የቆመ ስርዓት ከችግሮቹ እየተማረ፣ ከትናንት ይልቅ ዛሬ የተሻለ ቁመና እየያዘ ህዝብን በአንድነት፣ በፍቅርና በአገራዊ ስሜት አስተባብሮ መምራት መቻለል ነው ዋናው ቁም ነገሩ።
አገር ያለ ህዝብ፣ ህዝብም ያለ አገር መሪ አያስፈልጋቸውም። በመሆኑም መሪዎች የአገርንና የህዝብን ዋጋ የሚለኩበት ሚዛን አባያ መሆን የለበትም። አገርን ወክሎ፣ ህዝብን ወክሎ፣ በእውነት፣ በቅንነት፣ በማስተዋል፣ በጥበብና በሞገስ የሚገለጥ መሪ ያስፈልጋል። ነገር ግን በአገራችን ለዘመናት የምናየው እውነት የዚህ ተገላቢጦሽ ነው። በንጉሱ ዘመን ” የምትወደንና የምንወድህ ህዝባችን” ተብሎ ይቀለድ ነበር። ሆኖም ግን ህዝቡ ሲወዳቸው እንጂ ህዝቡን ሲወዱት አልታየም። በደርግ ዘመንም “ጭቁን ህዝቦች” ተብሎ ይዘመር ነበር፣ ነገር ግን ደርግም ያው ዋና ጨቋኝ ኃይል ሆኖ መገለጡ ነው አሳፋሪው። በዘመነ ህወኃት/ኢህአዴግ “ነፃ አውጪ” ነን እያሉ ነበር ወደ ምንሊክ ወንበር የወጡት። ሆኖም ግን ወደ ኋላ ዘወር ብለን ስናየው ያለፉት 27 ዓመታት ለአገራችን ህዝቦች የነፃነት ዓመታት ሳይሆኑ የባርነት ዓመታት ሆነው አልፈዋል።
ዋናው ጉዳይና መነሳት ያለበት አጀንዳም ዛሬ ምን እናደርግ? የሚለው ነጥብ ነው። ህዝባችን ውሸት ከርፍቶታል፣ ማስመሰል ሰልችቶታል፣ በላዩ ላይ በኃይል የረጫነበትን የጭቆና ቀንበር ለመሰባበርም ቆርጦ ተነስቷል። በመሆኑም በመሪነት ላይ ያሉ ኃይሎች ዛሬ ቆም ብለው አገራዊ ችግሮችን ለመፍታት በፍቅር፣ በቅንነት፣ በእውነትና በታማኝነት እስካልተንቀሳቀሱ ድረስ በእርግጥም መጪው ዘመን ብሩህ ሳይሆን ጨለማ ነው፣ ሰላም ሳይሆን ጦርነት ነው፣ መረጋጋት ሳይሆን ብጥብጥ ነው የሚነግሰው። የመሪዎች ማስተዋል ማጣት፣ ቅንነት ማጣት፣ ተቀባይነት ማጣት፣ ተደማጭነት ማጣት አሁን ለደረስንበት አገራዊ ቀውስ ዋና ምክንያቶች ናቸው። በመሆኑም መጪው ዘመን ያለ ፍቅርና መከባበር፣ ያለ ቅንነትና እውነተኛነት ጨለማ ስለሆነ ዛሬ ቆም ብሎ መፈተሽ ያስፈልጋል። “የሞኝ ለቅሶ መልሶ መላልሶ” የሆነው የህወኃት ኢትዮጵያ ትፈርሳለች የሚለው የማስፈራሪያ የዘመናት ቋንቋ መቀየር አለበት። ምክንያቱም አገር በአንድ ትውልድ ጤናማነት አልተገነባም፣ በአንድ ትውልድ እብደትም አይፈርስም።

Filed in: Amharic