የማነ ምትኩ

ህወሓት/ኢህአዴግ ስልጣኑን ለማስጠበቅ ሲባል ብቻ የማኪን ምክር አንድ በአንድ ከውኗል። ኢህአዴግ መሪዎቹን አንድ በአንድ በዚህ መፅሀፍ አጥምቆ ቃለመሀላ የፈፀመ ነው የሚመስለው። ቀውስ ባጋጠማቸው ቁጥር፥ የሚገልጡት መፅሀፍ ይህን መፅሀፍ እስኪመስል ድረስ፥ ትራሳቸው ስር ቀብረው የሚተኙ እስኪመስል ድረስ፥ መፅሀፉን አሟጠው ተጠቅመውበታል። ሆኖም አንዲት ምክሩን ልብ አላሏትም።
“ቅጣትህን ቶሎ አገባድድ” የምትለዋን። “ማስወገድ ያለብህን በአንድ ጊዜ አስወግደህ ጨርስ። ማወደም ያለብህን በአንድ ጊዜ አውድም። … ቶሎ ወደ መልሶ መቋቋም፥ ወደ ግንባታ፥ ወደ ልማት ግባ። …ካልሆነ እርምጃህ ቀጣይነት ካለው፥ ጠላት እያበዛህ፥ ህዝብን ለማይቀረው አመፅ እያነሳሳህ መሄድህ አይቀርም። ይህ ደግሞ በራስ ላይ ሞትን መደገስ ነው።” ማለፊያ ምክር ነበረች፥ ግን ሳቷት። ለ27 ዓመታት እንደጀመሩ እስኪጨርሱት ድረስ ጥፋቱን ተያይዘውታል።
ምክንያታቸው ደግሞ በጣም ግልፅ ነበር። ከመነሻው ጠላታቸውን ህዝብ አድርገዋል። ህዝብን ደግሞ በአንድ ጊዜ ማስወገድ አይችልም።