>
5:09 pm - Thursday March 3, 8129

አቶ ለማ የግምገማውን ቪዲዬ OBN ላይ የመልቀቅ መብቱ ሊጠበቅለት ይገባል (ኤርሚያስ ለገሠ ዋቅጅራ)

አቶ ለማ መገርሳ ከተናገረው ነገር በሙሉ ቁልፍ አድርጌ የማየው ” በቤተመንግስት ለ17 ቀናት የተካሄደው ግምገማ ምንም ሳይቆራረጥ ለኢትዬጲያ ህዝብ ይፋ እንዲሆን እፈልጋለሁ!” ያለው ይመስለኛል።ምክንያቶቼ የሚከተሉት ናቸው።

ምክንያት አንድ:-
በግምገማው ወቅት ማን ኢትዬጲያን ለማዳን እንደተንቀሳቀሰ በግልፅ ማየት ይቻላል።

ምክንያት ሁለት:-
በግምገማው ወቅት ማን የራሱን ድርጅት ለማዳን አሊያም የበላይነት ለማረጋገጥ እንደሞከረ ለማየት ይቻላል።

ምክንያት ሶስት:-
የግምገማው ውጤት ሲገለፅ ” ህዝበኝነት” የአንዳንድ ስራ አስፈፃሚዎች(ሰአኮ) ቁልፍ ችግር እንደሆነ ይፋ ሆኗል። አቶ ለማ መገርሳ በህዝብ ፊት እንደጠየቀው የቤተመንግስቱ ስብሰባ ሳይቆራረጥ ይፋ ቢሆን እነማን ” ሕዝበኝነት!”  የሚል ታፔላ እንደተለጠፈባቸው ማወቅ ይቻላል።

ምክንያት አራት:-
“የህውሃት/ የትግራይ የበላይነት የለም” ብለው የተከራከሩ የሰአኮ እና የህውሓት/ኢህአዴግ የጡት አባቶች እነማን እንደሆኑ ማወቅ ይቻላል። አቶ ለማ ቪዲዬው ይፋ ይሁንልኝ ብሎ እንደተማፀነው ይፋ ቢደረግ የበላይነት አለ/ የለም ለሚለው መከራከሪያ ሆነው የቀረቡትን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት፣ የመከላከያ፣ ደህንነት እና ፌደራል ፓሊስ የበላይነት፣ የእውነተኛ ስልጣን ባለቤትነት… ወዘተ” ላይ ተሰብሳቢዎቹ ያራመዱትን አቋም መመልከት ይቻላል። ግንባርና ደረት እየመታ የገደለው የፀጥታ ሀይል ምስጋና ይገባዋል ያለው ማን እንደሆነ ይታወቃል።

ምክንያት አምስት:-
ከሰአኮ አባላትም ውስጥ ሆነ ከብሔር ድርጅቶች ውስጥ መርህ አልባ ግንኙነት የፈጠሩት እነማን እንደሆኑ የኢትዬጲያ ህዝብ የሰሚ ሰሚ ሳይነግረው በቀጥታ መመልከት ይቻላል። የተፈጠረው ኔትወርክ መነሻ እና መድረሻው ምን እንደነበረ ማወቅ ይቻላል።

ምክንያት ስድስት:-
አቶ አባዱላ ” ህዝቤና ድርጅቴ እየተዋረዱ በስልጣን አልቀጥልም!” በማለት በይፋ ያቀረበውን ቁምነገር እንዴት በመግለጫ አስደግፎ እንዳብራራው ማየት ይቻላል። የአባዱላን ህዝብና ክብር ያዋረደው ማን እንደሆነ የኢትዬጲያ ህዝብ ማወቅ እና የህሊና ፍርድ መስጠት ይችላል።

  ምክንያት ሰባት:-
የፓለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ ጥያቄ ያቀረበው፣ ጥያቄው ተገቢ ሆኖ የደገፋት፣ መፈታት የለባቸውም ብለው የተቃወሙት እነማን እንደሆኑ ለማወቅ ይቻላል። ይሄ አጀንዳ በቤተመንግስቱ ስብሰባ የተነሳ አይመስለንም በማለት ለሚከራከሩ ሰዎች ምላሽ ይሰጣል።

ምክንያት ስምንት:-
በግለሰብ ደረጃ የሰአኮ አባላት እዛው ሳለ የመንግስት ባለስልጣናት በመሆናቸው ሂስ ግለሂሳቸውን መስማት ይቻላል። ህዝቡ ግምገማቸውን በማየት ብቃታቸውን በቀላሉ መመዘን ይችላል። ለምሳሌ አቶ ሐይለማርያም ደሳለኝ/ አቶ ደብረጲዬን/ አቶ ገዱ / አቶ ለማ ራሳቸውን እንዴት ተመለከቱ? ሌሎች እንዴት ተመለከቷቸው የሚለው መታወቅ ይኖርበታል።

ምክንያት ዘጠኝ:-
” ግምገማው ከሰማይ በታች ያልዳሰሰው ነገር የለም!” በማለት HD የነገረን ምን ያህል እውነት እንደሆነ ህዝብ ተመልክቶ ይወስናል። ህውሃት ድብቅ አላማውን ምን ያህል ይፋ እንዳደረገ ህዝብ ፍርዱን ይሰጣል።

  እናም አቶ ለማ መገርሳ በኢትዬጲያ ህዝብ ፊት ” ግምገማችን ይፋ ይደረግ!” ብሎ የጠየቀው ሳይውል ሳያድር እንዲፈፀም ድጋፌን እሰጣለሁ። አቶ ለማ ኦህዴድን ወክሎ ጥያቄ ያቀረበ በመሆኑ በሚሊዬን የሚጠጉ የኦህዴድ አባላት ጥያቄ እንደሆነም እገነዘባለሁ። ህውሃት ፈቅዶ ይሄን ከፈፀመ ማእከላዊነትን ለመተው ፍላጐት እያሳየ መሆኑን የሚጠቁም ይሆናል። አለበለዚያ ግን አቶ ለማ የግምገማውን ቪዲዬ OBN ላይ የመልቀቅ መብቱ ሊጠበቅለት ይገባል።

Filed in: Amharic