>

ሁለቱ እጆች . . . ! (አሰፋ ሃይሉ)

 

 

 

‹‹በቀኙ እጄ የምታዩትን ለምለም የዘንባባ ዝንጣፊ ይዣለሁ፤

በግራው እጄ ደግሞ የምታዩትን ታጣፊ ክላሽ ይዤያለሁ፤
እባካችሁ ግራ እጄን እንድመርጥ አታስገድዱኝ፤ 
እኔና ሕዝቤ ሠላምን ከምንም ነገር በላይ እንፈልገዋለንና!!!››

— የፍልስጥኤማውያን ነፃ አውጭ መሪ፣ ያሲር አራፋት፣ በአንድ የመንግሥታት ጉባዔ መድረክ ላይ፣ ጠብመንጃና ቅጠል ይዞ ለዓለም መሪዎች ያሰማው ንግግር፡፡

አሁን የምናገረው ስለሁለት ቀኝ እጆች ነው፡፡ ያኛው እጅ የደቡብ ኮርያ እጅ ነው፡፡ ይሄኛው እጅ ደግሞ የኢትዮጵያ እጅ፡፡ የእነሱ እጅ በፖሃንግ ግዛት፣ ሃሚጎት በተባለች ቀዝቃዛ የባህር ዳርቻ ላይ የቆመ ነው፡፡ የኛ እጅ ደግሞ በአርሲ ዞን፣ አኖሌ በተባለች ቀዝቃዛ ለምለም መስክ ላይ የቆመ፡፡ የሃሚጎቱ ቀኝ እጅ የቆመበት ዋነኛ ምክንያት ኮርያኖች በእርስ በርስ የግዛት ጦርነት የረገፉ ወገኖቻቸውን ለመርሣት ነው፡፡ የአኖሌው ቀኝ እጅ የቆመበት ዋነኛ ምክንያት ደግሞ ኢትዮጵያኖች በእርስ በርስ የግዛት ጦርነት የረገፉ ብሔሮቻቸውን ላለመርሣት ነው፡፡

የፖሃንጉ መዳፍ የተዘረጋበት ዋነኛ ዓላማ … የዛሬ 60 ዓመት ገደማ … 1 ሚሊየን፣ 730 ሺህ ሠላማዊና 793 ሺህ ዩኒፎርም ለባሽ ተዋጊ ጎበዛዝቶቻቸውን የበላባቸውን የኮርያኖች የወገን እልቂት አስረስቶ … በሁለቱ የኮርያ ሕዝቦች መካከል … እርቅና ይቅር ባይነት ያልተለየውን… የወደፊት የአብሮ መኖር ተስፋን ለማጫር ነው፡፡ የአርሲው ቀኝ እጅ የቆመበት ዋነኛ ዓላማ ደግሞ … የዛሬ 120 ዓመት ገደማ … በሃገር ውስጥ የግዛት ማስፋፋት የተነሣ በተደረገ ውጊያ … ያለቁትን 12,000 የሚሆኑ የአካባቢውን ጎበዛዝት ተዋጊዎች እልቂት እዳይረሳ ነጥሎ በማስታወስ … በሁለት ታሳቢ በአንዲት አገር ውስጥ ባሉ ብሔሮች መካከል … ቂምና ጥላቻ ያልተለየውን … የወደፊት አብሮ የመኖር ተስፋን ለማጫር ነው፡፡

የኮርያው ቀኝ እጅ ስም፡- ‹‹ዘ ሃንድ ኦፍ ሃርመኒ›› ነው፡፡ ‹‹ዘ ሃንድ ኦፍ ኮኤግዚስተንስ›› እየተባለም ይጠራል፡፡ ከፍ ብሎ በተዘረጋ የርህራሄ እጅ ለሥምምነት፣ አብሮ ለመኖር የተዘረጋን እጅ… ለቀጣዩ ትውልድ እንዲያሳይ የተሰጠው ስያሜ እንደማለት፡፡ የኢትዮጵያው ቀኝ እጅ ደግሞ፡- ‹‹የአኖሌ እልቂት መታሰቢያ›› ነው፡፡ ‹‹የአኖሌ ሰማዕታት ኃውልት›› እየተባለም ይጠራል፡፡ ከፍ አድርጎ በተዘረጋ የጭካኔ እጅ ያለፈውን ጠባሳ፣ የተቆረጠን ጡት… ቀጣዩ ትውልድ እንዳይረሳ አድርጎ እንዲያሳይ የተሰጠ ስያሜና ቅርፅ እንደማለት፡፡

ከ2 ሚሊዮን ኮርያውያን አሳዛኝ እልቂት በኋላ በደቡብ ኮርያ ፖለቲከኞች አማካይነት የተተከለው ኮርያዊ ቀኝ እጅ… — ‹‹ሃንድ ኦፍ ሃርመኒ›› — አሁንም በሁለቱ ኮርያኖች መካከል የኒውክሊየር ፍጥጫ እንኳ ባለበት… በሁለቱ ወንድማማች ሕዝቦች መካከል… ፖሃንግን ያለፈ… ሃሚጎትን የተሻገረ… ፅድቅንና ሠላምን ይሰብካል፡፡ ከ10ሺህዎች ኢትዮጵያውያን አሳዛኝ እልቂት በኋላ… በኢትዮጵያ ፖለቲከኞች አማካይነት የተተከለው ኢትዮጵያዊ ቀኝ እጅ… — ‹‹ዘ ሃንድ ኦፍ ስሎተርድ ብሬስት›› (የአኖሌ ሠማዕታት ኃውልት) ደግሞ — አሁንም በሁለቱ ሕዝቦችና ብሔረሰቦች መካከል ምንም የኒውክሊየር ፍጥጫ እንኳ በሌለበት… በሁለቱ ወንድማማች ሕዝቦች መካከል… አሩሲን ያለፈ… አኖሌን የተሻገረ… ክፋትንና ጥላቻን ይሰብካል፡፡

ከሚሊዮኖች ነፍሶች በላይ የተላለቁት ፅኑ የኮርያ ሕዝቦች — ወዳጅነታቸውን ላለመርሳት — የእርቀ-ሰላም ኃውልት፣ የአብሮ መኖር ኃውልት፣ የወዳጅነት ኃውልት ይገነባሉ፡፡ በመቶ ሺህዎች ነፍሶች የተላለቁት እንግሊዞችና አይሪሾች — ወዳጅነታቸውን ላለመርሳት — ‹‹ከግንቡ ባሻገር የሚሻገሩ እጆች›› የሚል ትልቅ የወዳጅነት ኃውልት ለቀጣይ ትውልድ ያቆማሉ፡፡ በመቶ ሺህዎች ነፍሶች የተላለቁት ፈረንሳዮችና ጀርመኖች — ወዳጅነታቸውን ላለመርሳት — የጋራ የወዳጅነትና የመተሳሰብ ፓርክ አንፀው፣ የዘወትር መታሰቢያ ያኖራሉ፡፡ እኛስ??

እኛም ለኩባውያን ሲሆን የኢትዮ-ኩባ ወዳጅነት ኃውልትና አደባባይ በመሃል ጥቁር አንበሣ ሆስፒታል ጋር እናቆማለን፡፡ እኛም ለቻይናውያን ሲሆን የኢትዮ-ቻይና ወዳጅነት ኃውልትም አደባባይም በመሃል ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ጋር እናቆማለን፡፡ እኛም ለጃፓናውያን ሲሆን የኢትዮ-ጃፓን ወዳጅነት መታሰቢያ ኃውልት ጎሃ-ፅዮን መንገድ ዳር እናቆማለን፡፡ እኛ ለእኛስ? እኛ ለእኛማ ሲሆን… በቃ ክፉ አታናግሩን አቦ… !!!!!!!!!! በስንቱ ተቃጥለ፣ አርረን፣ መርረን እንዘልቀው ይሆን…??

ድንገት ዛሬ ደግሞ… ያ ማዕከላዊ የተባለ ለዘመናት በመጡ ጉልበተኞች ሁሉ… ምንም ኃይል የሌላቸውን ንፁሃን ለማሰቃያነት ሲውል የነበረ… ራሱን የቻለ… ትልቅ ኦና… የኦሽዊትዝ ብጣቂ ማጎሪያ… ያ የዳሳዉ የልጅ ልጅ… ያ የእነሶቢቦር ማጎሪያዎች የአበልጅ… ያ… አስቀያሚ የወፌላላ መሸክሸኪያ አባቶር… ያ ሰውን ያህል ታላቅ ሰብዓዊ ፍጡር በቁም ሲያቃዥ የኖረ… ሰው-በላ ወና ማስፈራሪያ…. ዛሬ ዛሬ ደግሞ… ፈጽሞ ካገነገነበት የጉልበተኞች ጋኔን ነፃ ሊወጣ፣ ፈጽሞ ከሰፈረበት የስንት ሺህ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ነፍስ ጣዕር ሊገላገል፣ ከሰፈረበት የሌጌዎን አዙሪት… ነፃ ሊወጣ ነው….፣ ከማጎሪያነት ወደ ሙዝየምነት ሊቀየር ነው የሚል ዜና እየተሰማ ነው፡፡ ያ ታላቅ ብሥራት ነው በእውነቱ፡፡

ያ የማዕከላዊ ጣዖት…. ያ የማዕከላዊ የሥልጣናት መቅደስ…. በቁሙ፣ በግምቡ፣ በጥርቡ በሁለ-ነገሩ… ከነአካለ-አምሳሉ… እስከዛሬ መኖሩ ራሱ . . . ታላቅ ከ60ዎቹ አንስቶ የሚቀፈደድ የወገንን እጅ ከፍ አድርጎ እየዘረጋ . . . ፍቅርን በተዘረጋ እጅ ከሚሰብከው የኮርያ የእርቀ-ሰላም እጅ በተቃራኒው…. እንደ አኖሌው መዳፍ ውስጥ የመሰለን… የተቆረጠ ጡት… የተተለተለ የወጣቶች አካል… የተገረፈን የጉልበትአልባዎች ጀርባ… የባከነን የወገንን ታላቅ አዕምሮ… ለአላፊው፣ ለአግዳሚው፣ ለዓለሙ ሁሉ ከፍ አድርጎ… ከፍ ባሉ የግምብ አጥሮቹ የሚያውጅ… የጥላቻ፣ የጉልበት፣ የጅብነት ባህርያ ተምሳሌት ነበረ እንግዲህ፡፡ እና አሁን.. እና ዛሬ.. ያ የወፌላላዎች ደብር፣ ያ የመከረኞች ቅፅር… ባዶውን ሊቀር ነው ሲባል… እሰየሁ አልን፡፡

ለምን??? ጥላቻን የሚያጠፋው የጥላቻ ኃውልት፣ የጥላቻ ደብር፣ የእልቂት መቃብር አይደለማ!!! ጥላቻን የሚያጠፋው ፍቅር ብቻ ነው፡፡ ቂምን የሚያሽረው በሰፊው ለእርቅ የተዘረጋ እጅ ብቻ ነው፡፡ ሠላምን የሚያመጣው የወደፊቱን አብሮነት፣ የወደፊቱን ወንድማማችነት በመተለም ነው፡፡ እንጂ በጥላቻ የተዘረጋን እጅ ከፍ አድርጎ በማሳየት አይደለም፡፡ ልክ በጥላቻ የተገነባ ማጎሪያ እንዳልሆነው ሁሉ፡፡

እናማ… እናማ . . . በነካ እጃችን…. ምናለ… የዘረጋነውን የጥላቻና የቂም እጅ አጥፈን… የእርቅና የፍቅር እጅን እንደኮርያኖች ብንዘረጋስ?? ለእነ ኩባ፣ ለነቻይና፣ ለነጃፓን፣.. ለነኮርያ ራሱ.. ስንት የወዳጅነት ኃውልት ስናቆም… እንዲያው ለኛ ለራሳችን .. ለእርስ በርሳችን … የዘረጋናቸውን የክፋትና የጥላቻ እጆች በልበ-ሰፊነትና በአርቆ-አስተዋይነት አውርደን…. እንዲያው ለገዛ ራሳችን መዳኛ… ለተከፋፈለና ለከፋ ነፍሳችን ማርከሻ… ላለፈው ሁሉ ምድራዊ ኃጢያታችን ማስተሠረያ የሚሆን… እንዲያው ለኛ ለራሳችን… ለእርስ በርሳችን የሚበጀን… እንዲያው አንድ የወዳጅነት፣ አንድ የሐርመኒ፣ አንድ የአብሮነት፣ አንድ የኮኤግዚስተንስ፣ አንዲት የሰላም፣ አንዲት የወገናዊ ወንድማማችነት፣ አንድ እንኳ የመተሳሰር፣ አንድ እንኳ የመግባባት፣ የመተቃቀፍ፣ የመዋደድ፣ የመወራረስ… ኧረ የስንቱን የስንቱን በልባችን ያለ.. ያልከሰመ የመልካም ወዳጅነትና የበጎነታችን ማሳያ የሚሆን… የሁላችንንም ልጆች… የህዝባችንን ቀጣይ ትውልድ በቂም-እንዲረገዝ ከተለፈፈ የጥፋት ጉግማንጉግ የሚታደግ…. የማይበገር ወዳጅነታችንን ማሳያ የሚሆን… ኃውልት ብናቆም ምናለበት ??

ኮርያውያን እኮ አልነበሩም እጃቸውን ይዘረጋሉ የተባለላቸው… !!! ‹‹እጆቿን ወደ አምላኳ ትዘረጋለች›› በተባለች አገር ሠማይ ላይ የጥላቻና የክፋትን እጆች ዘርግተን… አምላክ እንዴት ነው ኢትዮጵያን የሚባርካት??? እውነት ግን ከጥላቻ ይልቅ ፍቅር ምናለበት ?? የምር ግን ከቂም ይልቅ እርቅ ምናለበት???እንዲያው ግን ከግፍ ይልቅ ፅድቅ ምናለበት?? እውነት ግን ከክፋት ይልቅ በጎነት ምናለበት????እውነት ግን ከክፋት ይልቅ በጎነት ምናለበት? የምር ግን ከቅዠት ይልቅ በጎ ህልም ማንን ገደለ?? !!!!!

‹‹ጭለማን ሌላ ጨለማ አያፈካውም፡፡ ጨለማን በጨለማ ማፍካት አይቻልም፡፡ ጨለማን ማፍካት የሚቻለው በላዩ ላይ ብርሃንን በመፈንጠቅ ብቻ ነው፡፡ ጥላቻንም ሌላ ጥላቻ አያጠፋውም፡፡ ጥላቻን በጥላቻ መፋቅ አይቻልም፡፡ ጥላቻን ማጥፋት የሚቻለው በላዩ ላይ ፍቅርን በመፈንጠቅ ብቻ ነው፡፡››

— ታላቁ የሰብዓዊነት አቀንቃኝ፣ ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁንየር፡፡

አምላክ ቸር ቸሩን ሁሉ ያሰማን፡፡ መልካሙን ሁሉ በልቦናችን ያሳድር፡፡ አንድዬ ፈጣሪ አምላካችን… ባለማድያቲቱን እናት ኢትዮጵያችንን…. ከናስጠለለቻቸው መላ ምስኪን ሕዝቦቿ ሁሉ ጭምር… አብዝቶ አብዝቶ ይባርክ፡፡ ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር፡፡ በፍቅር፡፡ በወዳጅነት፡፡ በድል፡፡ አበቃሁ፡፡

Filed in: Amharic