>

አቶ ለማ መገርሳ የሚተውኑት አስደናቂ ትወና ! (ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)

ከወያኔ/ኢሕአዴግ መግለጫ ከተነሡ ነጥቦች አንዱ ሕዝበኝነት ነው፡፡ ሕዝበኝነት (Populist) ማለት ለሕዝብ መቆርቆር፣ ለሕዝብ ማሰብ፣ ሕዝብን መደገፍ፣ ሕዝብን ማስቀደም፣ ሕዝብን ማድመጥ፣ የሕዝብ ጥያቄና ፍላጎት እንዲሟላ መጣር፣ እራስን ለሕዝብ አሳልፎ መስጠት…. ማለት ነው፡፡

በ17ቱ ቀናት የወያኔ/ኢሕአዴግ አስቸኳይ ስብሰባ ላይ ጥልቅ የተባለ ግምገማ መደረጉንና “ሕዝበኝነት!” እንደ እንከን ተቆጥሮ አንዱ የመገምገሚያ ነጥብ እንደነበረና በዚህም የመገምገሚያ ነጥብ ተከሰው የተወቀሱ የተተቹ መኖራቸውን ሰምተናል፡፡ ለምሳሌ እነ አቶ ለማ መገርሳ፡፡ አስቀድሜ በጻፍኳቸው ጽሑፎች ይሄንን ነገር እንዳታምኑ አመክንዮአዊ ነጥቦችን እየጠቀስኩ በተደጋጋሚ ማስጠንቀቄ ይታወሳል፡፡ ስለሆንም እነዚያን ነጥቦች ደግሜ ማንሣት አይጠበቅብኝም፡፡ አሁን ይሄንን ሕዝበኝነት የተባለውን የመገምገሚያ ነጥብ ያነሣሁት በሕዝበኝነት የተገመገሙት የወያኔ ባለሥልጣናት በትክክልም ሕዝበኝነትን ያንጸባርቁ ነበር ለማለት ሳይሆን ወያኔ ሕዝበኝነትን በአደባባይ መቃወሙ፣ መኮነኑ፣ ማውገዙ እጅግ ስለገረመኝና ፀረ ሕዝብ ማንነቱንም የሚያረጋግጥ ሆኖ ስላገኘሁት ነው፡፡

እንጅ እነ አቶ ለማ መገርሳ የሚተውኑት አስደናቂ ትወና ጉዳይማ በጣም ግልጽ ነው፡፡ እስኪ አስቡት እነ አቶ ለማ መገርሳ እንወክለዋለን የሚሉት የኦሮሞ ሕዝብ በቅርቡ በሶማሌ ልዩ ኃይል ኦሮሞ በመሆናቸው ብቻ ጥቃት ተፈጽሞባቸው ጉዳዩን እንዲያጠና የተወከለው “የሕዝብ ተወካዮች” አጥኚ ቡድን የጥናት ውጤት እንዳስታወቀው ከሆነ በ10 ሽህ የሚቆጠሩት ኦሮሞዎች ተጨፍጭፈው በተገደሉበት፣ በመቶ ሽዎች የሚቆጠሩት ከቀያቸው ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በተሰደዱበት ሁኔታ እነ አቶ ለማ መገርሳን ይሄ ነገር ቅንጣት ባይሰማቸውም ባያሳስባቸውም እንኳ እንዴት ሆነው ነው ይሄንን ጉድ እንዳላዩ፣ እንዳልሰሙ፣ እንዳልከፋቸው፣ መርፌ እንኳ እንዳልጠፋባቸው ሆነው ሊታዩ የሚችሉት ጃል???

የወያኔ ጠባቂ ቅጥረኞቹ እነ አቶ ለማ እንወክለዋለን የሚሉት ሕዝብ እንደጉድ እየተጨፈጨፈ ምናቸውም እንዳልተነካ ሆነው ቢታዩ የወያኔ ባሮች፣ አገልጋዮች፣ ዕቃዎች መሆናቸውን አያጋልጥባቸውም ወይ? ይሄስ ለወያኔ ፖለቲካ ጥሩ የሚሆን ይመስላቹሀል? ይሄንንስ ወያኔ ማወቅ የሚሳነው ይመስላቹሀል? ስለሆነም ነው እነ አቶ ለማ እየተወኑት እንዳሉት ሆነው እንዲተውኑ የተደረገው፡፡ ትወና ባይሆን ኖሮማ እነ አቶ ለማ መገርሳ የፈለገ ነገር ቢሆን ከ17ቱ ቀናት ስብሰባ በኋላ “ጭፍጨፋችንን አጠናክረን በመቀጠል፣ መውሰድ ያለብንን ሁሉ እርምጃ ወስደን የሕዝብ ተቃውሞንና የበቃቹህን ጥያቄን ፀጥ ረጭ እናደርገዋለን!” የሚል መግለጫን ተስማምተው ሊያወጡ ባልቻሉ ነበረ፡፡

እስከ አሁኗ ሰዓት ድረስ እነ አቶ ለማ ይሄ የወጣው መግለጫ የማይወክላቸው፣ የማይመለከታቸው ወይም ያልተስማሙበት መሆኑን ገለጹ ሲባል አልሰማንምና፡፡ እነ አቶ ለማ የሚባለውን ያክል ሕዝበኛ ቢሆኑ ኖሮ ምንም ይሁን ምን ሕዝብ የጠየቀው ጥያቄ መፈጸም መመለስ እንዳለበት የጸና አቋም ይዘው በዚህ መልኩ የሕዝብ ችግር እንዲፈታ ተቃውሞና ዐመፅ እንዲያደርግ የሚገደድበት ምክንያት እንዳይኖር ያደርጉ ነበር እንጅ “የሕዝብ ጥያቄንና ተቃውሞን በኃይል አዳፍነን እናጠፋዋለን!” የሚል መገለጫን ተስማምተው አያወጡም ነበረ፡፡

እነ አቶ ለማ እንደሚያወሩትና እንደሚወራላቸው “ሲፈልግ ገደል ይግባ!” ካሉት ከድርጅት፣ ከሥልጣን፣ ከምንም ነገር በላይ ለሀገርና ለሕዝብ የሚያስቡ፣ የሚቆረቆሩ፣ የሚገዳቸው ከሆነ እንዴትና ለምንስ ነው ታዲያ አሁን በዚህ ወቅት ኃላፊነትና ተጠያቂነት የሚባል ነገር ጨርሶ የሌለበት አገዛዝ አካል ሆነው እያገለገሉ የምናያቸውን ያህል መጠቀሚያ እየሆኑ ያሉት ታዲያ? ቢያንስ በዚህ ወቅት እንኳ ይሄ የሚጠበቅ ነገር ነው ወይ?

የ10 ሽህ ወገን ደም በከንቱ ፈሶ ኃላፊነት መውሰድና መጠየቅ ያለበት አካል ኃላፊነት እንዳይወስድና እንዳይጠየቅ ተደርጎ፣ ጭራሽ እንዲያውም ጨፍጫፊው አካል ተመስግኖና ተደንቆ የዚያ ሁሉ ሕዝብ ደም ደመ ከልብ ሆኖ የተፈጸመው ግፍ በይቅርታ እንዲታለፍ መስማማት ነው ወይ የሕዝብ ልጅነትና የሕዝብ አለኝታነት ማለት??? “ሥልጣኑ ምንትሱ ገደል ይግባ!” መባሉ ከልብ ከሆነ የሕዝብን መብት፣ ነጻነትና ጥቅም እንዳሻው የሚጥስ የሚፃረር፣ የወያኔን ጥቅም ብቻ ለማስጠበቅ የሚጥር፣ ገዳዮችንና የገዳዮችን እርምጃ የሚያወድስ የሚክብ መግለጫ እንዴት ተስማምተው ሊያወጡ ቻሉ??? ብላቹህ ራሳቹህን ጠይቃቹሀል?

ስለሆነም የእነ አቶ ለማ መገርሳን ሕዝበኝነት እርሱት፡፡ እነ አቶ ለማም ሆኑ እነ አቶ ገዱ የሚናገሩትና አሉ የሚባሉት ነገር ሁሉ አሉ ከመባላቸው ውጭ በተግባር በሚታይ ውጤት ተደግፎ የሕዝብን መብትና ጥቅም ሲያስጠብቅ ሲያስከብር ዓይተንና ሰምተን አናውቅም፡፡ ወያኔ ሕዝቡን በወሬ ብቻ መደለል እንደሚችል ስለሚያምንና ሲያደርገውም ስለኖረ ሰዉ እንዲሁ ነው በባዶ እየተደለለ ያለው፡፡

በፅንሰ ሐሳብ ደረጃ ግን ሕዝበኝነት ስለተባለው ነገር እንድናወራበት እፈልጋለሁ፡፡ ወያኔ የእነ አቶ ለማ መገርሳን የሕዝበኝነት ትወና እውነተኛ ለማስመሰል ብሎ ሕዝበኝነትን ሲኮንን ሳያውቀው ፀረ ሕዝብ ማንነቱን ሊገልጥ ችሏል፡፡ እውነትም ባይሆን ለማስመሰል ወያኔ የመሠረተው አገዛዝ ሕዝባዊ እንደሆነ፣ ሉዓላዊ ሥልጣ የሕዝብ እንደሆነ ይለፍፋልና ዲሞክራሲያዊ (መስፍነ ሕዝባዊ) ነኝ የሚል ሥርዓት ሕዝበኝነትን ያበረታታል ብቻ ሳይሆን መሠረታዊ መርሑና ግዴታውም ሆኖ እያለ ወያኔ ሕዝበኝነትን ማውገዙ መቃወሙና መኮነኑ ዲሞክራሲያዊ (መስፍነ ሕዝባዊ) ነኝ ከሚሉ በዓለማችን ካሉ አገዛዞች ወያኔ የመጀመሪያው ለመሆን ችሏል፡፡ በምዕራቡ የዓለም ክፍል አንድ የፖለቲካ ፓርቲ (የእምነተ አሥተዳደር ቡድን) የሕዝበኞች ነው (a party of populists) ከተባለ፣ መሪውም ሕዝበኛ መሪ ነው (a populist leader) ከተባለ የተለየ ዋጋና ክብር የሚያሰጠው ጉዳይ ነው፡፡

ወያኔ የቱንም ያህል አረመኔያዊ የሆነ ፀረ ሕዝብነቱን ሕገመንግሥት በሚለው የማጭበርበሪያ ሰነዱ ለመደበቅ ቢጥርም ሁሌም ቢሆን ግን ግፍ የተሞሉ ተግባሮቹ፣ የሕዝብን መብት ነጻነት የሚጻረሩ የተለያዩ አዋጆቹ የሚያሳዩት የሚያረጋግጡት ሀቅ ቢኖር አረመኔ ፀረ ሕዝብነቱን፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ውክልና የሌለውና ይሁንታውንም ያላገኘ የወንበዴ ቡድን መሆኑን ነው፡፡

አሁን ደግሞ ብሎ ብሎ ይሄው ወያኔ ሕዝበኝነትን በመኮነንና በማውገዝ “በሕዝብ የተመረጡ፣ በሕዝብ የተሾሙ የሕዝብ ተወካዮች፣ የሕዝብ አሥተዳዳሪዎች ናቸው!” የሚላቸውን ሎሌዎቹን በይፋ የራሱ ባሮች፣ የራሱ ተላላኪዎች፣ የራሱ ቅጥረኞች፣ የራሱ ዕቃዎች እንጅ የማጭበርበሪያ ሰነዱ እንደሚለው ተጠሪነታቸው፣ ተቆርቋሪነታቸው፣ ተጠያቂነታቸው፣ ኃላፊነታቸው፣ አገልጋይነታቸው ለሕዝብ አለመሆኑን በመግለጫው ላይ ሕዝበኝነትን በመኮነን በማውገዝ በግልጽ አስቀምጦታል፡፡

እናሳ ምን እናድርግ? ምን እናድርግማ እንቀጥል እንግፋ ነዋ! ጥርሳችንን ነክሰን ቆርጠንና ጨክነን እንደምንም ወያኔን ዘንድሮ መገላገል ካልቻልንና ከዚህ በኋላ በሚወስዳቸው የመደለያ፣ የማታለያ፣ የማጭበርበሪያ እርምጃዎቹ ተደልለን አፈር ልሶ እንዲነሣ ዕድል ከሰጠነው እያንዳንድሽ ያኔ ያልቅልሻል! እናም ይሄ እንዳይሆን እንጠንክር! እንበርታ! እንረባረብ!!!

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

Filed in: Amharic