>

የእድሜ ልክ አርበኛው- ታማኝ በየነ (አቻምየለህ ታምሩ)

በኢትዮጵያውያን ላይ የሚደርሰው በደል በእያንዳንዳችን ኢትዮጵያውያን ላይ ቢጋባብን ኖሮ፡ ዛሬ የምናየውና የተንሰራፋው ደንታቢስነት ቤታችንን ሞልቶት ወያኔ እስኪያንገሸግሸን አይመትረንም ነበር። በኢትዮጵያውያን ላይ የሚደርሰው ግፍና ሰቆቃ የተራዘመው፡ በእኔ እምነት፡ የሀብትና የእውቀት ባለቤቶች ደንታ ቢስ ሆነው ከወያኔ ጋር በመሰረቱት ከንቱ የእከከኝ ልከክህ ወዳጅነት ምክንያት ነው። ኢትዮጵያውያን የሀብታቸውና የእውቀት ባለቤቶች ባላቸው መጠን የህዝባቸውን የአለኝታነትና አደራ በሀላፊነት መንፈስ መሸከም ቢችሉ ኖሮ፡ ዛሬ የምናየውና አለምን ያስመረገመው የኢትዮጵያውያን ግፍና ሰቆቃ እንደራሳቸው በደል ተጋብቶባቸው፤ የአለኝታነት ስሜትና የተቆርቋሪነት ወኔ ተፈጥሮባቸው፤ አንድ እግራቸውን አገር ቤት ሌላኛውን ደግሞ አውሮፓና አሜሪካ አንፈራጥጠው በድሎት በደንታቢስነት አይኖሩም ነበር።
ከነዚህ የደስታቢስነት መንፈስ ከተጠናወታቸው ኢትዮጵያውያን በጣም ባፈነገጠ አኳኋን፣ አገሩ የጣለችበትን ታላቅ ታሪካዊ አደራ በመረከብ ረገድ ታማኝ በየነ ግን ከሁላችንም ልዩ ነው። ታመኝ በየነ ብሔርተኝነት የሚበል ዘመን አመጣሽ በሽታ ሳያጠቃው፤ የሀይማኖት ድንበር ሳይገድበው፤ የተገፉት፣ በጭካኔ የተገደሉት፣ የተሰደዱት፣ የታረዙት፣ በግፍ የታሰሩት፣ ጧሪ ቀባሪ ያጡት፣ በረሀ ለበረሀ ሲንከራረቱ የወደቁት፣ አውሬ የበላቸው፣ የውስጥ እቃቸው የተሸጠው፣ ባጠቃላይ የምስኪን ኢትዮጵያውያን ሁሉ የበደል ስሜት ተጋብቶበት፣ ተፈጥሮ በቸረችም ልዩ ችሎታው የተጋባበትን የወገኖቹን በደል በቋንቋ ጭምር ለማስረዳት ሳይቸገር ፤ የእድሜ ልክ አርበኛ ሆኖ እስከ ዛሬ፣ አገሬ፣ ኢትዮጵያ እንዳለ አለ።
እንደ ታማኝ አገር ወዳድ፣ ቤት ትዳሩን ትቶ በእሳት የሚማገድ፣ ህይወቱንና ጊዜውን ከአገሩ በላይ የማይወድ፣ የዚህ ዘመን አንድ የቁርጥ ቀን ሰው ጥራ ብባል የማውቀውና ብቸኛው ሰው ታማኝ በየነን ነው። እኔ አርበኛ ሲባል የማውቀው አገሩን እየተከላከለ ለአምስትና ለስድስት አመታት ያህል ጠላትን የወጋን ነው። ታማኝ ግን እድሜውን በሙሉ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይልና ሳይሸነፍ በአርበኝነት የኖረ የእድሜ ልክ ጀግና ነው። በእድሜ ልክ አርበኝነቱም እውነትን አዚሞ ለህዝብ በመቆም፤ ስንቶች መቶ ሰማኒያ ዲግሪ ታጥፈው በደም ከቦካ እጅ ቀለብ ሲሰፈርላቸው፣ እሱ ግን ትናንትናም ዛሬም ንቅንቅ ሳይል ሲጀምር በቆመበት ቦታ ላይ ጽንቶ ላገሩ እየኖረ ይገኛል።
ታማኝን የእድሜ ልክ አይበገሬ ታጋይ እንዲሆን ያደረገው፣ ሁላችን የሌለን የእሱ ግን ያለው፣ በሰው ላይ የሚደርስው በደል የሚፈጥረውን ስሜት ከማንም በላይ በመረዳቱና በደሉም ስለሚጋባበት፤ መረዳቱና የተጋባበትን በደል ዝም እንዳይል ደግሞ የሚጣላ ህሊያ በመያዙ ይመስኛል። በእውነት ይህንን ሀውልት ቢቆምለት የሚያንሰውን ድንቅ ሰው በቃላት መግለጽ ይቸግረኛል። ወንድሙ ተወልደ በየነ « ድጋሚ የምፈጠር ቢሆን ደግሜ የታማኝ ወንድም ሆኜ መፈጠር ነው የምፈልገው» ሲል የታማኝን ታላቅነት ገልጾታል።
እኔም ከቃላት በላይ የሆነውንና መግለጽ የማይቻለውን ታማኝን ለማሳወቅ በሆሄ ድርደራ የአንባቢን ጊዜ እንዳልሻማ፣ አባ ወልደ ተንሳይ ታማኝን ባጭሩ የገለጹበትን ሀረግ ልጠቀምና ሀተታየን ላብቃ። አባ ታማኝን ሲገልጹት እንዲህ ብለው ነበር፤
«ስሙ መጥቶ ያለቀለት!» አሉ። እውነትም «ስሙ መጥቶ ያለቀለት!»
ውድ ታማኝ፤ ላንተ ያለኝን ክብር በቃላት ልግለጽ ብየ ብሞክር፤ ቃላት የውስጥ ስሜትን ሁሉ ለመግለጽ የሚያስችል ጉልበት ስለሌላቸው ንፉግ የሆንሁ ያህል ይሰማኛል። ብቻ በጣም አከብርሀለሁ። እያደረግኸው ለኖርከውና ላለኸው ታላቅ ስራ ሁሉ የድሆች አምላክ ረጅም እድሜና ጤና ይስጥህ!
Filed in: Amharic