>

የትግራይ የበላይነት ጉዳይ (ቀለል ባሉ ምሳሌዎች!) [ጌታቸው ሺፈራው]

 

ለሀገር ሲባል ተሸፋፍኖ ሲታለፍ የኖረ ሀቅ ሞልቷል። እንዳላየህ ስታልፈው ሀፍረት የሚሰማው ሲጠፋ ግን አፍርጦ መነጋገር አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው። ለወደፊት ግንኙነት የሚጠቅመው ይሄ ነው። የትግራይ የበላይነት የለም የሚሉ ሰዎች አብዛኛዎቹን በደሎች፣ ለዚህ የበላይነት ምክንያት የሆኑ ሀቆች መስማት የማይፈልጉ ከበላይነትም በላይ የቅኝ ግዛት ዘመን አስተሳሰብ የተጠናወታቸው ናቸው። በእየ አካባቢያችን ያሉትን ሀቆች በግልፅ ብናወራ ትህነግ/ህወሓት የቀደዳቸውን ቦዮች ያለ ገደብ የሚጠቀመውን፣ የሚዘርፈውን፣ የሚዘልፈውን መጥቀስ እንችላለን። እኔ የተወሰኑትን ቀላል ምሳሌዎቹን ብቻ ልጥቀስ።

~ እኔ ለመጀመርያ ጊዜ ስራ የጀመርኩበት፣ በኋላም መለስ ላይ ፃፍክ ተብዬ በትህነግ/ህወሓት ካድሬዎች የተባረርኩበት ኢመድኤ /INSA ከነበሩት 8 ዳይሬክቶሬቶች 6 በትግራይ ልጆች የተያዙ ነበሩ። ዋና ኃላፊው ደግሞ ሜ/ጀ ተክለ ብርሃን ወልደ አረጋይ ነው። ተክለብርሃን ወ/አረጋይ በቅርቡ የትግራይን የበላይነት ለማስቀጠል ምን መደረግ እንዳለበት በይፋ የተናገረው ጀኔራል ነው። ኢመድኤ/INSA ቢያንስ ከ80 በመቶ በላይ የሆኑ የትግራይ ልጆችን ይዞ ስራ የጀመረ ተቋም ነው። የአሁኑ ኦህዴድ ሰው አብይ አህመድ እና መሰል ሰዎች ግፊት ከየ ዩኒቨርሲቲው መቀበል ሳይጀመር አብዛኛዎቹ ሰራተኞች ከመቀሌው የቴክኖሎጅ ተቋም የመጡ ነበሩ።

~ ኢመድኤ እያለሁ ከጓደኛዬ ሚሊዮን ጋር ለህክምና ወደ ጦር ኃይሎች ሆስፒታል ሄድን። ኢመድኤ/INSA ሰራተኞቹን ጦር ኃይሎች ስለሚያሳክም ነው። ከበር ጀምሮ፣ እስከ ዶክተሩ አብዛኛዎቹ ሰራተኞች የሚያወሩት ትግርኛ ነው። ይህን ሄዶ ማረጋገጥ ብቻ ነው።

~ አንድ የቀድሞ የፖሊስ አባል ጋር ካፌ ቁጭ ብለን እያወራን ነው። ከመልቀቁ በፊት ይሰራ የነበረው ሜክሲኮ ከሚገኘው ዋና መስርያ ቤት ነው። ለምን ለቀቅክ ስል ለጠየኩት ጥያቄ “ትግርኛ ስለማልችል” ብሎ ነበር የመለሰልኝ። ቢያጋንነውም ምን ለማለት እንደፈለገ ግን ግልፅ ነው።

~ እኔ እስር ቤት በነበርኩበት ወቅት የቂሊንጦው ኃላፊ ተክላይ፣ የሸዋሮቢት እስር ቤት ኃላፊ የማነ፣ የዝዋይ አሰፋ ኪዳነ፣ የቃሊቲው ገብረየሱስ ነበሩ። የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ዋናም የትህነግ/ህወሓት ታጋይ ነው። የየዞኑ ኃላፊዎች የትህነግ ታጋዮች ናቸው። ለምሳሌ የቂሊንጦ ዞን ኃላፊዎች ልዕላይ፣ ካህሱ፣ ኃይላይ… … ናቸው። የጥበቃና ደህንነቱ ገ/ማርያም ወልዳይ ነው። ሌላው ቀርቶ እስር ቤት ውስጥ ለእነዚህ ኃላፊዎች መረጃ የሚያቀብሉት፣ አሁን በቃጠሎው በተከሰሱት ላይ የሚመሰክሩት አብዛኛዎቹ የትግራይ ልጆች ናቸው። ማዕከላዊ በነበርኩበት ወቅት የአማራና የኦሮሞ ልጆችን አምነው የሌሊት ተረኛ አያደርጓቸውም። ደግነቱ የማዕከላዊ ጠባቂ ፖሊሶች እንደሚታሰበው ክፉዎች አይደሉም።

~ በአንድ ወቅት ሰብሰብ ብለን ወደ ቂሊንጦ አቀናን። ሳሙኤል አበበ አይኑ ጥግ ምልክቶች አሉበት። የትግራይ ሰው ነው ያለው የቂሊንጦ ፈታሽ በትግርኛ አዋራው። ሳሙኤል ትግርኛ እንደማይችል ሲገልፅለት “በቋንቋህ ለመናገር ታፍራለህና አላስገባህም” አለው። ሳሙኤል መግባት ነበረበትና አንዱ ጓደኛችን ዘቡን በትግርኛ አዋራው። ሳሙኤል አዲስ አበባ ስላደገ ትግርኛ እንደማይችል ገለፀለት። ደስ እያለው አስገባን። በዚሁ እስር ቤት የኦሮሞ ልጆች ጠዋት ወደ ፍርድ ቤት ሲጠሩ “ጅራ” ሲሉ ታጋዩ ሁላ ደሙ ይፈላል። ኦሮምኛ የማንችለውም የእነዚህን ሰዎች ደም ለማሞቅ “ጅራ” እንል ነበር። ታጋዮቹ “አንተ ደግሞ ምን አውቀህ ነው?” ይሉናል።

~ ብርሃነ ፀጋዬ የትህዴን ታጋይ ነበር። ሞላ አስግዶም ከተመለሰ በኋላ እሱም ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስ ከሰሱት። አንድ ቀን ያመውና ትርሃስ ጋር ይሄዳል። ትርሃስ የቂሊንጦ እስር ቤት ነርስ ነች። ትርሃስ ብርሃነን እየመዘገበች ነው። የተወለደው አድዋ ነው። ፆታው ፣ እድሜው፣ “ብሔሩ”………ተመዘገበ። በመጨረሻ የተከሰሰበት “የወንጀል አይነት” ይጠየቃል። ብርሃነ “ሽብር” ብሎ መለሰ። የትግል ልምዷ ተቆጥሮላት ቂሊንጦ የተመደበችው ትህራስ ደሟ ፈላ፣ እስክርቢቶዋን ጠረጴዛ ላይ ጣለች፣ ብርሃነ ላይ አፈጠጠች። “ትግሬ ሆነህ እንዴት ታሸብራለህ?” ብላ አንባረቀችበት። ፖሊስ ሆስፒታል ሄዶም ተመሳሳይ ደፍ አፈላ። ህክምና ተከለከለ። እነዚህ “የህክምና ባለሙያዎች” ትግሬ ምን አንሶት” ያሸብራል? ” ምን ብሎ ያምፃል? ሀገሩ፣ ስርዓቱ ሁለመናው የእሱ አይደለምን? ማለታቸው ነውኮ! ማረጋገጥ የሚፈልግ ቂሊንጦ ዞን 3 ብሎ ይግባ፣ ብርሃነ ፀጋዬ ብሎ ያስጠራ፣ ጠይቆም ያረጋግጥ።

~ አንድ ቀን እኔም ትህራስ ጋር ሄድኩ። የተከሰስኩበትን ጠየቀችኝ። ነገርኳት። “ሽብር” ብዬ። ወዲያውኑ የጠየቀችኝ “አማራ ነህ ኦሮሞ” ብላ ነው።

~ከትህራስ የተለየች አንዲት ታጋይ ነርስ አለች። ከመታሰሬ በፊት የሸዋስ አሰፋ ነግሮኝ ነበር። ማዕከላዊ ነው የምትሰራው። የአማራና የኦሮሞ ልጆች እንደሚቀጠቀጡ ታውቃለች። ቀጥቅጠው እሷ ጋ ነው የሚልኳቸው። ደረጀ አለሙን የማዕከላዊ ሰዎች ግንባሩን ፈለጡት። ልክ እንደደረጀ የአማራና የኦሮሞ ልጆች ሲፈለጡ፣ ሲቀጠቀጡ የምታውቀው የትህነግ ታጋይ የገባትን ሌሎች ቢገባቸው መልካም ነበር። “እዚህ ሀገር ግን እንደ ደቡብ አፍሪካ ዘር እየተለየ ማጥቃት ተለመደ?” አለችው ደረጀን። ደረጀ ተጠቂ ነው አይመልስላትም። ሀቁ ግን ዘር ይለያል። ግልፅና ቁልጭ ያለ ሀቅ ነው! እንደዚች ሀኪም ብልጭ የሚልለት ጥቂት በመሆኑ የተፈጠረውን የአስተሳሰብ ችግር መቅረፍ አልተቻለም።

~ ይህ ደግሞ ቴሌ ውስጥ የሚሰራ ጓደኛዬ ያጫወተኝ ነው። አብራቸው የምትሰራ የትግራይ ሰው ነበረች። ሰው የትግራይ ሰውነች ብሎ በቀላሉ የሚለያት ሰው ነች። በሄደችበት አገልግሎት መስጫ ሁሉ መንገድ ይለቀቅላታል። እሷ ይህን አልፈለገችው። “አዲስ አበባ ዘረኛ ከተማ ነው” ብላ ወደመቀሌ ተመለሰች። ይህን ዘረኝነት፣ ፍርሃት፣ ስጋት፣ የትግራይ ሰዎችን አለማመን ማን ፈጠረው የሚለው ግልፅ ነው። ማረጋገጥ ከፈለክ ካፌ ውስጥ፣ ታክሲ ውስጥ ትግርኛ ጮህ ብለህ አውራ! ብዙ ሰው ዞሮ ያይሃል፣ ይጠራጠርሃል፣ ይፈራሃል። የዛሬው መፈራት፣ መጠላት ከየት መጣ ብሎ የሚጠይቅ የትግራይ ህዝብ ተቆርቋሪ ነኝ ባይ የለም። መሸፋፈን ነው! ተጨማሪ ጥቅም፣ ተጨማሪ ስልጣን ፍለጋ ነው!

~ አንድ በወልቃይት ጉዳይ የታሰረ ሰው ቤተሰብ ሰነድ ይፈልግና ወደ አንድ ትልቅ መስርያ ቤት ይገባል። መጨረሻ ግን ሰነዱ ታየ። የአማራ ማንነት አስመላሽ ግለሰብ ሰነድ ነው። በትግርኛ ተጠቅሞ ገባ፣ ሰነዱ የማን እንደሆነ ሲታወቅ ግን “ውጣ” ተባለ። “አሁንም ወደ ቂሊንጦ የምገባው ይችን ቋንቋ ተጠቅሜ ነው” ብሎኛል! “ጠቃሚ” ቋንቋ አለ!

~ ተስፋዬ ዋቴ ነው። የወጣለት አጭበርባሪ ነው። ቂሊንጦ ዞን 2 እያለሁ እኔ የነበርኩበት 5ኛ ቤት አስተዳደር ነበር። ሀኪሞቹን በትግርኛ አዋርቶ ከሌላው ቀድሞ መድሃኒት ተቀብሎ ይመለሳል። ዝዋይ ስቃይ ቤት ሆነን ሳሙና የነበረው ብቸኛ ሰው እሱ ነበር። ያመጡለት ታጋዮቹ ናቸው። ትግርኛ ይናገራልና! እሱም በትግርኛው የባለስልጣን ዘመድ ነኝ ብሎ ያጭበረብራል፣ በትግርኛው ታጋዮችን የፈለገውን ይቀበላቸዋል።

~ስለ ደህንነቱ፣ ስለ መከላከያው፣ ስለ መሰረተ ልማት፣ ስለ ጦር ኃይሉ ስብጥር፣ ስለ መርማሪዎች፣ ስለ ኢፈርት ሀብት፣…… የሚታወቅ ነው። እንዲያው ቀላል ምሳሌዎች ይሻላሉ ብየ ነው። ግልፅ ያደርጉታል ሁኔታውን። ሀቁን እናውራ ከተባለ የትህነግ ሰዎች ከላይ እስታች የራሳቸውን ሰዎች ነው የሚቀጥሩት።በአካባቢ ይመርጣሉ፣ በቋንቋ ይመርጣሉ። በሌሎች አካባቢዎች ካሉ መሰረታዊ የህዝብ ጥያቄዎች በላይ የ”ቐ” ትስተካከል ጥያቄ መፍትሄ ያገኛል። ኃላፊ ከተባለ አማራ እና ኦሮሞ በላይ የትግራይ ሰው በምክትልነት ይሰማል! ቋንቋው ያግዛል!

~ትህነግ/ህወሓት ሲተች “የልጆቻችን ደም ላይ” የሚል ትግርኛ ተናጋሪ ብዙ ነው። ትህነግ/ህወሓት በሌላ ህዝብ ላይ በደል ሲፈፅም ተው የሚለው በጣም በጣም ጥቂት ነው። አትንኩት እያለ፣ ሲረግጥ ዝም እያለ “ህዝብና ፓርቲን ለይ” ለማለት ከባድ ሆኗል።

~ትህነግ/ህወሓት የአማራና ኦሮሞ ወጣቶችን ሲያኮላሽ፣ ህዝብ ሲሰድብ፣ ሲዘርፍ ያልወቀሰ፣ ሲተች “ህወሓት የልጆቻችን ደም ውጤት ነው” እያለ ሲከላከል የቆየ፣ የህወሓትን የበላይነት፣ የህወሓት አድሎ፣… አብሮ መጋራት የግድ ሊለው ነው። የአማራ ህዝብ ግንቦት 7፣ የኦሮሞ ህዝብ ኦነግ ነው እያለ ሲከስ ከርሞ፣ “ወያነን አትንኩብኝ” ሲል ከርሞ አሁን የትህነግ የበላይነት፣ የትግራይ የበላይነት ነው ሲባል ማመን ይከብደዋል። ጆሮ ዳባ ልበስ ነው ነገሩ። አሁንም የሚፈልገው ሌላ ጥቅም፣ ሌላ ስልጣን……ሌላ!

እንግዲህ ትህነግ የትግራይን ህዝብ በሙሉ ወርቅ ሊያነጥፍለት የሀገር ሀብትም አይችልም። ቢችል እንኳ እወክለዋለሁ በሚለውም ህዝብ መካከል ልዩነት ያደርጋል። አድዋ እና ተንቤን እንኳ እኩል አይታይም። በትግራይና በሌሎች ክልሎች መካከል ግን ግልፅ የሆነ ልዩነት ተፈጥሯል። ትግርኛ መናገር ጥቅም ሲያስጠብቅ አልኖረም ማለት አይቻልም።

~ሀቅ የሚፈልግ የትም መሄድ አይጠበቅበትም። ደፋር ካለ ሰብሰብ ብለን ጥናት እንስራ። አማርኛ፣ ኦሮምኛ እና ትግርኛ እያወራን ጥናት እንስራ! ወደ ትልልቅ ተቋማት እንግባ እና አገልግሎት እንጠይቅ! ተክላይም፣ ተክለብርሃንም፣ አበበም፣ ገመዳም ላይ ገብተን እንጠይቅ፣ ታክሲ ሰልፍ ላይ፣ ካፌ ውስጥ በእነዚህ ቋንቋዎች ጥናት እንስራ። ማን ነህ ደፋር! ና እውነቱን እንጋፈጥ እስኪ!

መፍትሄ:_ እነ ደብረፅዮን ድሮ ድሮ “በትግራይ ህዝብ ስም የሚጠቀም” ብለው አላመኑም ነበር። አሁን ዳር ዳር እያሉ ነው። ሌላ ችግር ፈልጎ ማመን በሽታ ነው። እውነታውን አሁኑኑ አምኖ፣ ጥላቻም፣ ፍርሃቱንም ከማስወገድ ውጭ ሌላ አማራጭ የለም። እውነታውን መጋት ነው። ግን አያምኑም! ይከብዳቸዋል!

Filed in: Amharic