>
5:13 pm - Friday April 18, 3851

መንግስት ቄሮን ከሚመረምር ቄሯውያን ያነሷቸው ጥያቄዎች  ተገቢነታቸውን ቢመረምር...!

ዘውድአለም ታደሰ

በሃይለስላሴ ዘመነ መንግስት የአማራው የበላይነት አለ ተብሎ ይታሰብ ነበር። አምባሳደር ብርሃኑ ድንቄ ይሄ ከንክኗቸው «በርስዎ ዘመነ መንግስት አማራ ያለስሙ ስም ተሰጥቶት ፣ በናንተ የተንደላቀቀ ኑሮ የተነሳ ምስኪኑ የአማራ ህዝብ እየተወቀሰና እየተከሰሰ ነው» የሚል ደብዳቤ ለንጉሱ ፅፈው ሰድደው ነበር። በሚያስገርም ሁኔታ የአማራ የበላይነት አለ በተባለበት በዚያ ዘመን የአማራ ህዝብ በከፍተኛ ድህነት ውስጥ ይኖር ነበር። የወሎ ሽማግሌዎች ቤተመንግስት ደጅ መጥተው ልብሳቸውን እየቀደዱ ያለቀሱበት አሳዛኝ ዘመን ያ የአማራ የበላይነት አለ የተባለበት የንጉሱ ዘመን ነበር።

የፌደራሉ ፖሊስ ኮሚሽን «ቄሮ ላይ ጥልቅ ምርመራ ላደርግ ነው» ሲል ምን ትዝ አለኝ? በሚካኤል ሰርቫንቴዝ ተደርሶ ለዘመናት እንደተወደደ የዘለቀው «ዶን ኪሆቴ» የተሰኘ ልቦለድ ላይ ያለው «ዶን ኪሆቴ» የተባለው አዛውንት!

ዶን ኪሆቴ ብዙ የጦርና የጀብዱ ታሪኮችን ከማንበቡ የተነሳ የምናቡ አለም ከእውነተኛው አለም ጋር የተቀላቀለበት አስቂኝ ካራክተር ነው። የዶን ኪሆቴ ህመም ምናልባት የአእምሮ ሃኪሞች «ስኪዝኖፍሮኒያ» ብለው የሚጠሩት አይነት ህመም ሊሆን ይችላል።
የሆነ ግዜ ሰር ዶን ኪሆቴ በምናቡ የሳላት እመቤት ዱልሲኒያን ከጠላት ቁጥጥር ነፃ አውጥቼ ታላቅ ጀብዱ እፈፅማለሁ ብሎ አስቦ ሮዚናንቴ የተባለችውን ፈረስ ጭኖ ፣ ሳንቾ ፓንዛ የተባለውን ጋሻ ጃግሬውን አስከትሎ፣ አሮጌ ጋሻና ጦሩን ደግኖ ሲጓዝ መነኩሴዎች ይገጥሙታል። ዶን ኪሆቴ በምናቡ መነኩሴዎቹ እመቤት ዱልሲኒያን ያገቷት አስማተኞች ናቸው ብሎ በማሰብ መነኩሴዎቹን ካልገደልኩ ሲል የሚያሳይ አስቂኝ ታሪክ መፅሃፉ ላይ ሰፍሯል።

እውነታው ግን መነኩሴዎቹም መነኩሴዎች ናቸው። እመቤት ዱልሲኒያ የምትባል የታገተች እመቤትም ምድር ላይ የለችም።

ዛሬ መንግስት እንደዶን ኪሆቴ የሌለ ጠላት እየፈጠረ ይደነብር ይዟል። ምንም ምርምር በማያስፈልገው ጉዳይ ላይ ጥልቅ ምርምር ካላደረግሁ ይላል። ቄሮ ግን በቃ ቄሮ ነው። የአማርኛ ፍቺው ወጣት ማለት ነው። ቄሮ ማለት የስድስት ሚሊዮን ወጣት የወል ስም ነው። ኢፍትሃዊ አገዛዝን ተቃውሞ የወጣ ወጣት ስብስብ። ይሄን ለማወቅ ሻርሎክ ሆልምስን መሆን አይጠይቅም። ይሄን ለመረዳት ጥልቅ ምርመራ አያስፈልግም። የግድ አንድን እውነት ለማወቅ እንደጀምስቦንድ የሰለጠነ ሰላይ መሆን አይጠይቅም። መንግስት ቄሮን ከሚመረምር ቄሯውያን ያነሷቸው ጥያቄዎች ተገቢነታቸውን ቢመረምር ትርጉም ያለው ነገር ያገኛል ባይ ነኝ።

ኦሮማራ የሚለውን በአማራና በኦሮሞ መሃከል ያለውን የተለየ ህዝባዊ ግንኙነት መንግስት በመግለጫው «መርህ አልባ» ሲል አጣጣለው። አንዳን ሰዎችም ሙድ ሊይዙበት ሞከሩ። ይህ እጅግ አስቂኝ ነገር ነው።
ቆይ አንድ ህዝብ ከሌላው ህዝብ ጋር ወይም የአንድ ክልል ፓርቲ ከሌላ ክልል ፓርቲ ጋር መልካም ግንኙነቱን ለማጠንከር ምን አይነት መርህ ነው ሚያስፈልገው?

በኔ እምነት መርህ አልባው የህዝቡ ግንኙነት ሳይሆን ግንኙነቱን ያለምንም አመክኒዮ የሚያጣጥሉ ሰዎች ተግባር ነው። ጥያቄው መሆን ያለበትም ለምን የሁለቱ ህዝቦች ግንኙነት ጠነከረ ሳይሆን አንዳንድ ሰዎች በነዚህ ሁለት ታላላቅ ህዝቦች አንድነት ለምን ይናደዳሉ? የሚለው ነው!

ዛሬ በኦሮማራ ላይ ለመሳለቅ የሚሞክሩት ሰዎች ለዘመናት በሁለቱ ህዝቦች መሃከል መሰረተቢስ ጥላቻ ሲሰበክ አልተሳለቁም። አኖሌ የተባለው የጥላቻ ሃውልት ብዙ ሚሊየን ብሮች ፈስሰውበት ሲገነባ «ለምን?» ብለው አልጠየቁም። ታዲያ አሁን ለምንድነው የከፋቸው? ሰው ቢዋደድ ምን የሚያጡት ነገር አለ? የኦሮሚያ ወጣቶች ጣና ወርደው እንቦጭ ቢነቅሉ ምን ይቀርባቸዋል? ይሄ ነው ዋናው ጥያቄ!!

ጭንቅላቴ ውስጥ ያለው የብአዴኑ ገዱ ነው። ገዱ በስልጣን ዘመኑ ብዙ ስህተቶች ፈፅሞ ይሆናል። ግን ትናንተ የተሳሳተ ዛሬ ስህተቱን አያርምም ማለት በራሱ ስህተት ነው። ለማም ሆኑ ዶክተር አብይ ትናንት ላይ በተለያየ የስልጣን ስፍራዎች በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የሰሯቸው ስህተቶች ሊኖሩ ይችላሉ። አሉም። ዛሬ ግን በሚያስገርም ሁኔታ ከህዝብ ጎን ቆመዋል። የኦሮሞ ህዝብም በተለያየ መንገድ ድጋፉን እየገለፀ ከጀገኑት በላይ እያጀገናቸው ነው። ታዲያ ከነለማ ጋር ሆኖ ጥቂት ሰዋዊ ስሜት ያሳየው ገዱን የኦሮሚያን ፈለግ በመከተል ለምን አናጀግነውም? ለምን ከበረታው በላይ አናበረታውም? የትላንት ስህተቱን እያነሳን ከምንወቅሰው ዛሬ ላይ ያሳየውን ጠንካራ አቋም እያደነቅን ይበልጥ ከህዝቡ ጎን እንዲቆም ለምን ከጎኑ አንቆምም?

ገለቶማ!

Filed in: Amharic