>
5:13 pm - Sunday April 18, 2715

'የትግራይ የበላይነት አለ' ተባለ" ብሎ በንዴት ከመጦፍ ይልቅ...! (ጋዜጠኛ ካሳሁን ይልማ)

“አለ፣ የለም” ከሰሞኑ ያየሁት ክርክር ነው። የማያከራክር ጉዳይ ቢሆንም ሰዎች የህወሓትን የመከላከያ፣ የደኅንነት፣ የመንግሥት ተቋማት ስልጣንና የኢኮኖሚ የበላይነትን እየዘረዘሩ የትግራይ የበላይነት መኖሩን ለማስረዳት ሞክረዋል።

እስኪ ቀላል ጥያቄዎችን በመጠየቅ ልጀምር:: ህወሓቶች እንደ ፓርቲ፣ እንደ ቡድን እና እንደ ግለሰብ ከሚፈጽሙት ተግባር ተጠቃሚውና ተጎጂው ማን ነው?
በጠመንጃቸውና በስልጣናቸው ከሚያስሩት፣ ከሚያሰዱድትና ከሚገደሉት አበዛኛው ቁጥር ወይም የጥቃቱ ሰለባ ማን ነው?

እነርሱ ከሚገነቡት ኢኮኖሚ ተጠቃሚው ማን ነው? ለምሳሌ በትግራይ መልሶ ማቋቋም ድርጅት ከሚሰሩ ልማቶች ማን ይጠቀማል?
ህወሓትም ሆነ ድርጅቱ የተቋቋመው ለትግራይ አለያም ትግራይን መልሶ ለማቋቋም እንጂ ኢትዮጲያን እንደሀገር ለማቋቋም እንዳይደለ በግልጽ ተቀምጧል።

ከ6 ወር በፊት የትራክተር ፋብሪካ መቀሌ ላይ ስራውን ሲጀምር የትግራይ መልሶ ማቋቋም ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆኑት ወይዘሮ አዜብ መስፍን “በትግራይ መልሶ ማቋቋም ስር የሚገኙ ተቋማት ሀገሪቱ ወደ ኢንዱስትሪ ለመሸጋገር የምታደርገውን ጥረት እየደገፉ ናቸው” ብለዋል። ድርጅታቸው ሀገሪቱ ወደ ኢንዱስትሪ እንድትሸጋገር አስቦ ከሆነ ፋብሪካዎቹን ለምን ትግራይ ላይ ብቻ መገንባትን መረጠ?
“ሀገሪቱ” የሚሉት ፋብሪካዎቹ ጥሬ እቃዎችን ከሌሎች ክልሎች ስለሚጭኑ ይሆን? አሰታውሳለሁ አቶ መለስ ዜናዊ በሞቱ ማግስት ወይዘሮ አዜብ ጥቁር ለብሰው “መለስ ትግራይን የኢንዱስትሪ ማእከል አደርጋለሁ ብሎ የጀመረውን እቅድ ከግብ ሳያደርስ መሞቱ ይቆጨኛል” በማለት የመለስን ራዕይ እውን እንደሚያደርጉ ቃል ገብተው ነበር። ቃላቸውንም እያከበሩ እንደሆነ በተግባር እያየን ነው።
ባለፉት እንድ ዓመት ከግማሽ ብቻ የትምህርት፣ ወርቅ ማምረቻ ፋብሪካ፣ ኬሚካል ፋብሪካ በኢትዮጲያ የመጀመርያው ሲሚንቶ፣ መኪና መገጣጠሚያ፣ ትራክተር መገጣጠሚያ፣ ሌዘር ፋብሪካ፣ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካና ሌሎች ልማቶች በትግራይ ተከናውነዋል። ጥቂቶቹ ደገሞ በቅርብ ይጠናቀቃሉ ተብሏል። መረጃዎቹን ከነ ቀናቸው አስቀምቻለሁ፣ ምስላቸውም ከታች ተያይዟል።

ከነዚህ ፋብሪካዎች የሚጠቀመው ማን ነው? ሠራተኞች የሚቀጠሩት ከየት ነው ገቢውን የሚያገኘው ማን ነው ?
በደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ ግዙፍ ኩባንያዎችና እርሻዎች በአጠቃላይ ስልጣናን ኢኮኖሚው የነጮች ነበር። በዚምባብዌም እንደዛው። በዚያ የግፍ አገዛዝ ሁሉም ነጮች ተጠ ቃሚ ባይሆኑም የነጭ የበላይነት መኖሩ እሙን ነበር። በአሜሪካ የጥቁሮች የነፃነት ትግል ወቅት ከነ ማርቲን ሉተር ኪንግና ማልከም ኤክስ ጎን የተሰለፉ ጭቆናን የተጠየፉ ነጮች ነበሩ። ዛሬም ከጥቁሮችና ስደተኞች ጎን የሆኑ ነጮች ሚሊየን ናቸው። ያ ማለት ግን የነጭ የበላይነት የለም ብሎ ለመከራከር የሚያስደፍር አይደለም። ነጮች ሁሉ ተጠቅመዋል ማለትም አይደለም።

ስለዚህ ህወሓት ስንል የምናወራው ስለ ትግራይ ነፃ አውጪ ነው። ህወሓት ደግሞ ትግሬ ነው። ለፖለቲካ ትክክለኝነት ሲባል “NO የህወሓት የበላይነት እንጂ የትግራይ የበላይነት የለም” ተብሎ ቢነገር እንኳ በሌላ ቋንቋ የትግሬ የበላይነት አለ ማለት ነው። የበላይነቱ በስልጣንና ኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን በሥነልቡናም ጭምር ነው። ባለፉት 27 ዓመታት “ቧይ” የሚለው ቃል ምን ያህል አስፈሪ እንደሆነ ወይም ትግርኛ አነጋገር ዘዬ እንዲኖረው ያልተመኘ፣ ግንባሩ ላይ ምልክት እንዲኖረው ያልተመኘ ማን አለ? ያለስጋት ለመኖር ሲባል። እውነቱን ለመናገር ባዶ የስልጣን ስም ከተሰጣቸው በርካታ የሌላ ብሔር ተወላጆች ይልቅ ይህ ቃል (ቧይ) ኃይል ነበረው::

ትግሬዎች “ለምን ‘የትግራይ የበላይነት አለ’ ተባለ” ብሎ በንዴት ከመጦፍ ይልቅ በርግጥ ህወሓት የማይወከላቸው ከሆነ “በትግራይሕዝብ ስም የሚነግደው” ድርጅት ላለፉት 27 ዓመታት ሌላውን ኢትዮጲያዊ በጠላትነት ፈርጆ በዘሩ፣ በኀይማኖቱ እና በፖለቲካ አመለካከቱ ሲያሳድድ፣ሲያስርና ሲገድል ስለምን ዝምታን መረጡ? 27 ዓመታት በሙሉ!
ህወሓት ለ17 ዓመት” ደርግ…” እያለ አነሳስቶ ለስልጣን በቃ:: ታዲያ ለምን ለ27 ዓመታት እስካሁን “ደርጊ” እያለ ጭራቅ ይስልብኛል ብሎ የጠየቀ ስንት ነው? ካድሬዎች የትግራይ ሕዝብ ከሌላው እንዲነጠል ድልድዩን ለዓመታት ሲያፈርሱ “ጀጋኑ” ከማለት በስተቀር “በቃችሁ” ያላቸው አለ ወይ? ከዚያ ይልቅ ሠላም ባስ ሲቃጠልና “ከመተማና መቱ ትግሬዎች ተፈናቀሉ” ብለው ዘመቻ ማድረግና እርምጃ እንዲወሰድ መጠየቅን መርጠዋል።
አሁንም የኢትዮጲያ ሕዝብ “እያንዳንዱ ትግሬ ተጠቃሚ ነው” ብሎ አያምንም። ሁሉንም ላበልጽግ ቢባል ኢኮኖሚውም አይፈቅድም:: ምስኪን የትግራይ አረሶ አደሮች፣ ምስኪን ትግሬ ወገኖች በየቦታው እንዳሉ ያውቃል። ነገር ግን ከሌላው የተሻለ ነገን ያለመ ሥራ በህወሓት ወይም ትግራይ መልሶ ማቋቋም ድርጅት እየተሰራ እንደሆነ ጠንቅቆ ይረዳል:: ምን እየተከናወን እንደሆነ ያገናዝባል:: በፍርሀት ዝም ቢልም ቂል ነው ተብሎ እንዳይታሰብ::
ረጅም የኢንዱስትሪ እቅድ አስቀድሞ የታቀደው ለዘለቄታዊና አስተማማኝ የኢኮኖሚ መሠረት ተብሎ ነው::ይህ የአደባባይ ምስጢር እንጂ ድብቅ እውነት አይደለም። በዚህ ዓመት (2010ዓም) ብቻ የተሰሩት 5 ፕሮጀክቶችን ከታች ማየት በቂ ነው። የ27 ዓመታቱን ለማቅረብ ጊዜ እንጂ የተለየ ምርምር አይሻም።
የህወሓት የበላይነት አለ:: ህወሓት ደግሞ የትግራይ ክልል ተወካይ ድርጅት ነው። የክልሉ ሕዝብ ደግሞ ትግሬ ነው። ስለዚህ የትግሬ የበላይነት አለ!
“አይ ድርጅቱ የትግራይን ሕዝብ አይወክልም” ብሎ የሚያምን ካለ ከቄሮና ፋኖ ጋር ሆኖ ይህን ከፋፋይ አረመኔ ስርዓት “በቃህ!” ለማለት የፍትሕና ዴሞክራሲ ትግሉን መቀላቀል እንጂ የአንድ ሰውን የእድሜ ዘመን እኩሌታ ያህል አግጥጦ የሰነበተን ሀቅ መካድ አያዋጣም። ከዚያ ሁላችንም እኩል ኢትዮጲያዊ እንሆናለን!

መቀሌ

——–
1.የእንግሊዙ ኢንትሬድ ኩባንያ በመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ ሊሰማራ ነው (ታህሳስ 30፣2010 ፋና)
2.መሰቦ ሲሚንቶ የ70 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ስምምነት ተፈራረመ (ታኅሳስ 29-2010 ሪፖርተር)

3. በ75 ሚሊየን ብር በአዲስ መልክ የተገነባው የአፄ ዮሃንስ አራተኛ መሰናዶ ትምህርት ቤት ተመረቀ (ታህሳስ 20፣ 2009 ፋና)

አስገደ ፅምብላ ወረዳ

———————-
4.የመሊ የወርቅ ማምረቻ ፋብሪካ ወደ መደበኛ ምርት ገባ (ታህሳስ 24፣ 2010)

ውቅሮ ከተማ

————-
5.ሼባ ሌዘር በ10 ሚሊየን ብር ያስገነባውን የእጅ ቦርሳ ማምረቻ ፋብሪካ አስመረቀ መስከረም 23፣ 2010 ፋና
6.መስፍን ኢንዱስትሪያል በውቅሮ ያቋቋመውን የትራክተር መገጣጠሚያ አስመረቀ (ሃምሌ 16፣ 2009 ፋና)

ዓራቶ (ከመቀሌ በስተምስራቅ 25 ኪሎሜትር)

——————————————
7.በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የኬሚካል ማምረቻ ፋብሪካ በ5 ቢሊየን ብር ሊገነባ ነው (መጋቢት 16፣ 2008 ፋና)
8. የትግራይ መልሶ መቋቋም አስር ዘመናዊ አንቡላንሶችን ለወረዳዎች አስረከበ (ጥር 20/2009 ኢዜአ)

Filed in: Amharic