>

ያልተቋጨው የኢትዮጵያ ትንቢት…. (በያሬድ ይልማ)

ጣሊያን ኢትዮጵያን ደፈረ፣ እምዬ ምኒሊክ ኢትዮጵያዊያንን መርቶ ጣሊያንን ረታው፡፡ በወቅቱ ኢትዮጵያዊነትን የደፈረው የተረገመ አእምሮም ጭምር እንጂ ጣልያናዊነት ብቻ አልነበረም፡፡ ጣሊያን ላይመለስ ተረትቶ ከኢትዮጵያ ከወጣ ብዙ ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡ ሁለተኛው ኢትዮጵያዊነትን የደፈረ ሌላ መሪም አልፏል፣ የተመረዘ አእምሮውን የሚጋሩት አያሌዎቹ ግን አሉ፡፡

ውስጤ “መለስ” ብለህ እስኪ ከዚህች አጭር ጊዜ ታሪክ ጠይቅ ቢለኝ እና ብጠይቅ ያልተቋጨ ስለ አንድ ሟች መሪ የተነገረ ትንቢት አግኝቼ በመገረሜ ነው!
በአንድ ስብሰባ ላይ ሟቹ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ምን አሉ ብለን ብንጠይቅ ፣ መለስ እንዲህ አሉ፡፡ ከጨርቁ ችግር የለብንም አሉ፡፡ በባህላችን የሞተ ሰው እሱ ስለማይባል ፣ እሳቸው እያልኩ ነው የምጠራቸው፡፡

ሙት ወቃሽ አትበሉኝ…. ወይስ ትሉኝ….?….እንደውም በሉኝ ግዴለም፡ ቀጣፊ ናቸው ዋሽተዋል ፣

ከባንዲራችን ጋር ችግር ነበረባቸው፡፡ ያ ችግራቸው፣ ኢትዮጵያዊነት በሳቸው እድሜ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ፅፈው ሊከውኑ ካሰቡት ሾርት ፊልም አንፃር አይነፋም ነበር፡፡

አዲስ የትወና ታሪክ ለመፃፍ ረጅሙ እና ምንም ያልተቀላቀለበት ያ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያዊነት ታሪክ እና ባንዲራ ፣ የቀደሙት እድሜ ጠገብ ተዋናኞቹ ብዛት ፣ ከሾርት ፊልም አንፃር ሚካኤልን አይመችም፡፡

በተለይ አዲስ የታሪክ ትያትር ፅፎ እራሱ አዘጋጅ ፣ እራሱ አርታኢ ፣ እራሱ ዋና ተዋናኝ ሆኖ ፣ ታሪኩን መልሶ ለመፃፍ ለወጠነ ሰው፣ አእምሮው ባይመረዝ እንኳ፣ ታሪኩ ላጭር ፊልም አይመችም፡፡ ደግሞ እራሱ መሃንዲስ እራሱ ሰባጋዲስ ፡ ምናምን ፣ አላልኩም ከወዳጆቼ እንዳታጣሉኝ አደራ እንደፃፍኩት ብቻ አንብቡት፡፡

እና እኚህ ሟች፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የሚመዘግብላቸው ፈርቀዳጅ ሃሳባቸውና የውስጥ የልባቸውን ፈቃድ ግልፅ ያደረጉበት አጋጣሚ በቅርብ ጊዜ ታሪካችን መፅሃፍ ላይ በአንድ ገፅ ላይ እንደሰፈረው ላቅርበው፡፡ ህዝብ ሰብስበው ለቀረበላቸው አስገራሚ ጥያቄ የሰጡት መልስ፣ ዛሬ ላይ የሟች ከንፈር ያፈራው ፍሬ ሊባል ይችላል፡፡ በዚህ ንግግራቸው ኢትዮጵያዊነትን እና የሚወክላቸውን እሴቶች እና ሁለንተናዊ ግርማ፣ በአንድ ቃል በማርከስ ፈርቀደቀጅ ናቸው፡፡

አቤት ያኔ የተናገሩበት ልበሙሉነት፣ ያሰቡትን ሾርት ፊልም ስክሪፕት ፅፈው ጨርሰው፣ የፊልማቸው መግቢያ ላይ የነበረውን የመጀመሪያ ዳያሎግ እራሳቸውን ዳይሬክት እያደረጉ ሲናገሩ፣ የፊታቸውን ሁኔታ፣ የድምፃቸውን አወጣጥ ላየ ፣ በፍፁም ይህንን የጀመሩትን በአዲስ ታሪክ ላይ የተመሰረተ ሾርት ፊልም ሳይጨርሱ የሚሞቱ አይመስልም ነበር፡፡

ለሟች ከተሰብሳቢ የቀረበው ጥያቄ፡

እርስዎ የሚመሩት ሰራዊት በደረሰበት ስፍራ ሁሉ የኢትዮጵያን ባንዲራ አውርዶ አዋርዶ ፣ በራሴ ባላይም በውጭ ዜና እንደሰማሁት ህዝቡ ሰላማዊ ሰልፍም የወጣው በዚህ ምክንያት ነው፤ ማለትም ወታደሮቹ የኢትዮጵያን ባንዲራ አውርደው ኢሃዲግን አርማ ይሰቅላሉ ይባላል። እና በኢትዮጵያ ባንዲራ ላይ የእርስዎን ግልፅ ያለ አቊዋም ቢገልጡልን፤”

የሟች መልስ፡
“የባንዲራው ነገር ብለው የጀመሩት ሟች ፣ የጨርቁ ጥያቄ ለኛ ኢምንት ጥያቄ ነው፤ ከጨርቁ በስተጀርባ ያለው ጥያቄ ነው ለኛ መሰረታዊ ጥያቄ ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ በሚቀጥለው መድረክ ባንዲራችን ይቀየርልን ብሎ ቢጠይቅ የራሱ ጉዳይ ነው፤” ብለው ነበር የሾርት ፊልማቸውን ስክሪፕት ነገር ፣ ቁልጭ አርገው ያሳወቁት።

ሻለቃ አድማሴ
›››በተደጋጋሚ ጨርቅ እያለ የሚጠራ የኢሃዲግ ሰው የተመለከቱት ኢትዮጵያዊ፣ የተከበሩ ሻለቃ አድማሴ ፤ ንግግሩን ሰምተው ላስደነገጣቸው ሰው ፣ ማነህ የመጀመሪያው ተናጋሪ ብለው ለሟች መለስ፣ እንዲህ ብለው ትንቢት ተናገሩ፡፡

“የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያየው በጨርቅነቱ ሳይሆን ፤ በወርቅ በክብር ዘውድነቱ ነው የሚያየው፤ ስለዚህ በዚህ መንገድ ሰንደቅ አላማን መጥራት : በጎነት አይመስለኝም!!!፤
-ይህ የህዝቡ ስለሆነ እንደዚ አይነቱን የህዝብ እንቁ በጥንቃቄ ብናየው ፤ ምክንያቱም እኛ ህዝብ ውስጥ ነው ያለነው፣ ህዝብ ደግሞ ባህር ነውና መልሶ ቢተፋን ለሳግ የሚሆን ትንፋሽ አናገኝም!”

ብለው ነበር የቀድሞውን ሟች መሪ ሾርት ፊልም ተችተው፣ አማሟቱን እንቅጩን እዛው ስብሰባ አዳራሽ ውስጥ ከሃያ ምናምን አመት በፊት የተናገሩት።

….ሟቹ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር የሰጡት መልስ እንደቃላቸው ተፈፅሟል፡፡ ኢትዮጵያዊነት በማጣቀሻ ካልሆነ፣ ወይም በዘር ልኬት ጠቦ ተሰፍቶ ካልሆነ ትርጉሙ ግር የሚያሰኝበት ሁኔታ በሚገባ ተፈጥሯል፡፡ ምክንያቱም ጠያቂው እና ሻለቃ አድማሴ የሚወክሉት ማህበረሰብ፣ በጠያቂው ቃላት በባህር የተመሰለው የኢትዮጵያ ህዝብ ፣ ገና አሶቹን እንትፍ ብሎ አልተፋቸውም፡፡ የኢትዮጵያ ባንዲራን የሚበልጡ በክብር የላቁ ዘጠኝ ሰንደቅ አላማዎች ፣ የተከለሉ የኢትዮጵያን ክፍል ስስሚወክለሉ፡፡

ባንድወቅት እንደተባለው የኢትዮጵያዊነት “ሰንደቅአላማ!” ስሙ፣ ምንም እንኳን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትርን ሞት ቢቀጥፋቸውም ፣ ልክ እንዳሉት “ጨርቅ” ሆኗል፡፡ ታዲያ ሟቹ ሰው፣ ኢትዮጵያዊነትን ፣ እሪያ እግር ስር የጣሉበት የመጀመሪያቸው ንግግር ይህ ብቻ አይደለም፡፡

ለጊዜው ግን እሱን አንዴ ተወት ላድርገውና ፣ ከተሰብሳቢዎች አንዱ ነብይ ስለጠየቀው ጥያቄ እንነጋገር በሞቴ፡፡

ለምን እንደሆነ ባላውቅም፣ ሟች ከመለሱት መልስ ይልቅ የተጠየቁት ጥያቄ ፣ ዘመን እንደማይሽረው ቅኔያዊ ትንቢት የተለየ ፍላጎት ያጭርብኛል፡፡ እሰኪ በድጋሚ አትኩረን እንስማው፡፡

“እርስዎ የሚመሩት ሰራዊት በደረሰበት ስፍራ ሁሉ  የኢትዮጵያን ባንዲራ አውርዶ
(አዋርዶ ማለት ፈርቶ ነበር፣ አውርዶ ያለው፣ በግል ስለነገረኝ ነው)…የኢትዮጵያን ባንዲራ አውርዶ  በራሴ ባላይም በውጭ ዜና እንደሰማሁት ህዝቡ ሰላማዊ ሰልፍም የወጣው በዚህ ምክንያት ነው፤ (ማለትም ወታደሮቹ የኢትዮጵያን ባንዲራ አውርደው  – ኢሃዲግን ይሰቅላሉ ይባላል እና በኢትዮጵያ ባንዲራ ላይ የእርስዎን ግልፅ ያለ አቊዋም ቢገልጡልን፤”)

እኔ ያነበብኩትን ግልፅ ቅኔ ልንገራችሁ፣ ደግሞ ጠብ የማይል ትንቢትም ይዟል በውስጡ፡፡

“እርስዎ የሚመሩት ሰራዊት የኢትዮጵያን ባንዲራ በየደረሰበት አውርዶ ፣ በራሴ ባላይም በውጭ ዜና እንደሰማሁት ኢሃዲግን ይሰቅላሉ ይባላል። እና እርስዎስ ፣ በኢትዮጵያ ባንዲራ ስር ነው ወይስ በሌላ አገር ተሰቅለው የሚሞቱት፣ የእርስዎን ግልፅ ያለ አቊዋም ቢገልጡልን፤”

እሳቸው ከሃያ አመታት በፊት ያዩዋት ኢትዮጵያ፣ ታሪኳን ከዜሮ ለመጀመር እና የዚያ ታሪክ አብዛኛውን ምእራፍ በገዛ እራሳቸው አንታጎኒስትነት ሊተውኑ ተዘጋጅተው የነበረ በመሆኑ፣ አዲስ ድርሳን የጀመሩት ዘርፈብዙ ማፈራረስን በኢትዮጵያዊነት ላይ አዋጅ ብለው ነበር፣ ሞት ቀደመቀቸው እንጂ፡፡ የሳቸውን ሞት ደግሞ የከፋ የሚያደርገው፣ እስትንፋሳቸው እንኳ በቁስል ከተመታው ስጋቸው የተለየችው ልክ እኛን የሚወክለን ጠያቂ ቅኔ የሞላው ትንቢታዊ ንግግር፣ በኢትዮጵያ ምድር አለመሆኑ(በቤልጂየም)፣

እንደ አንድ የሶስት ሺህ አመትን በንቀት አሳንሶ መቶ እንዳደረገ ግለሰብ ዋና አክተር ሳይሆኑ ፣ እንዳዲስ የትእይንቱን መጀመሪያ ፣ የኢትዮጵያ ታሪክ የመቶ አመት ታሪክ ነው ብለው ተናግረው አሳጥረው ሽቅብ ሊወጡ አስበውት የነበረውን ባለሃፒ ኢንዲንግ ድርሳናቸውን ከጡዘቱ በፊት ፍፃሜ ያገኘ፣ አሳዛኝ የጭንገፋ ተረክ (Narrative of Tragic collapse) አድርጎታል፡፡ እውነት አይደለም ማለት መብታችሁ ነው፣ ግን አልፈርድባችሁም፣ ምክንያቱም ሁሉም ትንቢቶች ደስ አይሉምና፡፡ በተለይ የዚህ የሟች እውነት ደስ አይልም፡፡

እግር ጥሎኝ ይሄንን የስብሰባ ቪድዮ በድጋሚ ሳየው፣ ትንቢታዊው ቅኔ ሲያስገርመኝ ነው፣ የሟች መለስ ሙት አመት ሳይደርስ ብዙም ሳይታወቅ ስለኖረው የእርሳቸው ትንቢት ማውሳቴ፡፡ እኛ አገር በርግጥ ስለነገስታት የሚነገሩ ትንቢቶች፣ የነገስታቱን ልደት የሚቀድሙ ናቸው አብዛኞቹ፡፡

ሌላው ስለ ነገስታት የተነገሩ ትንቢቶች የሚታወቀው አስገራሚ መመሳሰል፣ አገዛዛቸው ብቻ ነው የተፃፈው፣ በዚህ እራሱ የኢትዮጵያ መሪዎች ታሪክ አንድ የኢንዲንግ ችግር እንዳለበት ይሰማኝ ነበር፣ ግን አሁን ታሪካችን ሶስት ሺህ አመት ሲሞላው ፍፃሜው ቀድሞ የተነገረለት መሪ አገኘን ማለት ነው፡፡ ልብ በል ልብ ያለህ የታሪክ ሰው፡፡ የሚገርመው ይህ የዚህ ፅሁፍ ትኩረት የሆነው ንግግር፣ አስተውላችሁ እንሆነ እንጃ እንጂ፣ ያልተፈጠመ ትንቢት አለው፣ ካላያችሁት እንካችሁ፡፡

“በራሴ ባላይም በውጭ ዜና እንደሰማሁት እርስዎ የሚመሩት ሰራዊት የኢትዮጵያን ባንዲራ በየደረሰበት አውርዶ ኢሃዲግን ይሰቅላሉ!!!”
ይህ ያልተፈፀመው የትንቢቱ ክፍል ነው፡፡

ኢትዮጵያዊነት ይለምልም!

Filed in: Amharic