>

ቴዎድሮስ ካሳሁንን ምን ነካህ? ተው ተው! ፈጥነህ ውጣ! (ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን)

አይ በጣም አዝናለሁ! ከቴዎድሮስ ካሳሁን ጋራ መጣላቴ ነው! ቴዎድሮስ ካሳሁን የያዘውን ሕልም፣ አቋምና ግብ አንድ ደረጃ ካላሳደገ በስተቀር ጠቃሚነቱ አገልግሎቱ አስፈላጊነቱ ያለፈበት ይመስለኛል፡፡ ቴዎድሮስ ካሳሁን “ኢትዮጵያ ወደ ፍቅር ጉዞ!” በሚል መሪ ቃል በተለያዩ የሀገራችን ከተሞች የሚያደርገውን የሙዚቃ ኮንሰርት (የዘፈን ትዕይንት) ጉዞ ወይም ዙር የመጀመሪያውን ጥር 12, 2010ዓ.ም. ባሕርዳር ከተማ ላይ ሊያቀርብ እንደሆነ ትናንት ጥር 3, 2010ዓ.ም. አስታውቋል፡፡

ይሄንንም ተከትሎ ከወያኔ ጭፍሮች ማለትም ከቤተ አማራ ነን ባዮች ከፍተኛ ተቃውሞ ቀርቦበታል፡፡ በዕለቱ አደጋ እንደሚያደርሱም በመዛት ለሚደርሰው ነገር ሁሉ ኃላፊነቱን ቴዎድሮስ ካሳሁን እንደሚወስድ እያስጠነቀቁ ይገኛሉ፡፡ አይገርሟቹህም? ምክንያት አድርገው የሚያቀርቡት ነገር ደግሞ “ሐዘን ላይ ነን!’ የሚል ነው፡፡ ባለፈው የቴዎድሮስ አልበም (የዘፈን ጥራዝ) እንደወጣ በተመሳሳይ ሁኔታ ተንጫጭተው ነበረ፡፡ ለምን ብየ ስጠይቃቸው የሰጡኝ ምክንያትም በተመሳሳይ “ሐዘን ላይ ነን!” የሚል ነበረ፡፡

ይታያቹህ አውሮፓና አሜሪካ ተቀምጠው እየተቀማጠሉ “ሐዘን ላይ ነን!” ይሉት ምክንያት እስኪ ማንን ያሳምንልናል ብለው ነው የሚጠቅሱት? እንዲያ ብለው ሲሉኝ ምን አልኳቸው “አማራ ከአምና ጀምሮ አይደለም ሐዘን ላይ ያለው መላ ዘመነ ወያኔን በሚሊዮኖች (በአእላፋት) የሚቆጠሩ ወገኖቹን አጥቶ ሐዘን ላይ ነው ያለው፡፡ ሐዘን ላይ ነን ብለን ግን አንበላም አንጠጣም አንደሰትም አላልንም፣ ጠጉራችንን ላጭተን፣ ጥቁር ልብስ ለብሰን፣ አንበላም አንጠጣም ብለን ሐዘናችንን እያዘንን አይደለም፡፡ ይሄንን ከባድ ሐዘን ይዘን፣ በየዕለቱ አማራ አማራ በመሆኑ ብቻ እየተገደለ እያንዳንዳችን በየግላችን ምን እያደረግን፣ ሐዘናችንን በምን መልኩ እያሳለፍን እንዳለን እያንዳንዳችን የምናውቀው ነገር ነው፡፡ በተግባር አድርጎ በማሳየት፣ ሆኖ በመገኘት እንጅ በማስመሰል የሚለወጥ፣ የሚገነባ ምንም ነገር የለም፡፡ ቴዎድሮስ ካሳሁን በዘፈኑ በአስረሽ ምችው አሸሸ ገዳሜ በማለት እየጨፈረና እያስጨፈረ ከመሰላቹህ በአላዋቂነታቹህ፣ በአላስተዋይነታቹህ ልታፍሩ ይገባል፡፡ እሱ በዘፈኖቹ ስለሀገርና ስለ ሕዝቧ አንድነትና ህልውና እያለቀሰ እየተማፀነ፣ ስለትንሣኤዋ እየሰበከ እየቃተተ፣ ወያኔና ግብረአበሮቹ እያጠፉት ያሉትን ታሪኳንና ጀግኖቿን በማሰብና በመዘከር ትውልዱ ታሪኩን ማንነቱን እንዲጠብቅ፣ ጀግናና ታሪክ ሠሪም እንዲሆን እያነሣሣ እየቀሰቀሰ ነው ያለው እንጅ እንደአብዛኞቹ ዘፋኞች ጨፍሮና አስጨፍሮ ትውልድ እያፈዘዘ እያደነዘዘ አይደለም ያለው፡፡ በዘፈን ደስታና ጭፈራ ብቻ አይደለም የሚገለጸው ላወቀበት ብዙ ቁምነገር ይሠራበታል፡፡ ለዚያም ነው እናት አባቶቻችን አርበኞች ለሀገራችን ነጻነት በዱር በገደል በሚዋደቁበት በሚሠውበት ወቅት እነ ፋኖ ፋኖን፣ ቀረርቶውን፣ ሽለላውን፣ ፉከራውን ያዜሙት፣ ያቅራሩት፣ ይሸልሉት፣ ይፎክሩት የነበረው፡፡ እናም እባካቹህ ማኅበራዊው የብዙኃን መገናኛ ተመቸን ብላቹህ ምንም በማታውቁት ነገር ያልበሰለና የደነቆረ አስተሳሰብ እየረጫቹህ ነገር አታበላሹ!” ብየ ለመገሰጽ ሞከርኩ፡፡

እነሱ ግን አያ አድሮ ጥሬ በመሆናቸው ይሄው አሁን ደግሞ ያንኑ የማይመስል፣ የማያሳምንና ለትዝብት የሚዳርግን ምክንያት ይዘው መልሰው ብቅ ብለዋል፡፡ ለነገሩ ሌላ ምን ብለው ያስመስሉ ታዲያ? “የወያኔ ቅጥረኛ ስለሆንንና ወያኔ ቴዲን ስለሚጠላው ነው እኛም የምንጠላው፣ ወያኔ ቴዲ ለሚሰብከው አንድነት፣ ፍቅር፣ መተሳሰብ፣ ታሪክ፣ ማንነት ልዕልና…፣ ለሚያቀነቅንላት ኢትዮጵያ ጠላት ስለሆነ ጌታችን ወያኔን መምሰል ስላለብን ነው ቴዲን የምንቃወመው!” አይሉ ነገር፡፡

አየ ምድረ የወያኔ ቅጥረኛ! በጣም እኮ ነው የሚገርሙት፡፡ ወገኖቸ ሆይ! ሲመስላቹህ የጀግናው፣ የአንድ ለእናቱ የዐፄ ቴዎድሮስ ተጋድሎ፣ ጀግንነት፣ ርእይ፣ ዓላማና ግብ፣ የሌሎች ጀግኖቻችንን ተጋድሎና ታሪክ የሚዘክርን አርዓያነታቸውን እንድንይዝ የሚሰብክን፣ የሚቀሰቅስን ይሄንን መድረክ የሚቃወሙ፣ የሚያወግዙ፣ ከዚያም አልፈው በሚታደመው ሕዝብ ላይ አደጋ ለመጣል የሚዝቱ የጥፋት ጭፍሮችና ጠላቶች እንዴት ሆነው ነው ከቶ አማራና ለአማራ ተቆርቋሪ ሊሆኑ የሚችሉት??? የገረመኝ ነገር ይህ የቴዲ የዘፈን ትዕይንት ከታች በምገልጽላቹህ ምክንያት በወያኔ ሙሉ ፈቃድና ችሮታ የተዘጋጀ ሆኖ እያለ ቤተ አማራ ነን ባይ የወያኔ ቅጥረኞች እንዴት ሊቃወሙት እንደቻሉ ነው፡፡

እኔ ከቴዲ ጋር የገጠመኝና የሚያጣላኝ ችግር ምንድን ነው መሰላቹህ፦ እንደምታዩት ወያኔ ኦሕዴድንና ብአዴንን ብቻ ሳይሆን የሃይማኖት መሪዎችንና የሀገር ሽማግሌዎችን ጭምር አሰማርቶ በፊት ሊያጠፋው ብዙ ሲጥርበት የቆየውንና ብርቱ ጉዳትም ያደረሰበትን አንድነትን፣ ፍቅርን፣ መተሳሰብን፣ ትስስርን ሽንጣቸውን ገትረው እንዲሰብኩ እያደረገ ይገኛል፡፡ ይሁንና በምን አንደበት ምን ቢነገር አያምርም አድማጭም አያገኝምና እነሱ የሚሉት፣ የሚሰብኩት፣ የሚወሸክቱት ነገር ሁሉ በሕዝብ ልብ ላይ ጠብ ሊል አልቻለም፡፡ ሕዝብ ማንን መስማት እንዳለበት፣ ከማን አንደበት ምን ቢወጣ ማመን መቀበል እንዳለበት ጠንቅቆ ያውቃልና፡፡

ቴዎድሮስ ካሳሁን ሀገር ውስጥ የዘፈን ትዕይንት ለማሳየት ፈልጎ በተንቀሳቀሰ ቁጥር ምን ያህል ፈተናና ችግር ሲገጥመውና ሲሰናከልበት እንደቆየ የምታውቁት ነገር ነው፡፡ አሁን ግን ነገሩ ተቀይሯል ወያኔ ቴዲን ሊጠቀምበት ፈልጓል፡፡ ቴዲ በተለያዩ የሀገራችን ከተሞች ሊያደርገው የፈለገውን የዘፈን ትዕይንትም እንዲያቀርብ ከሙሉ ድጋፍና ትብብር ጋር እንዲያቀርብ ፈቅዶለታል፡፡ በዚህም መሠረት የመጀመሪያውን የዘፈን ትዕይንት በባሕርዳር ከተማ በከተማዋ ግዙፍ ስታዲየም (ዐውደ ቅሪላ) እንዲያቀርብ ከሙሉ ድጋፍና ትብብር ጋር ተፈቅዶለታል፡፡ ቴዲ የወያኔ መጠቀሚያ መሆን ከጀመረ እኔም የምሠጋው ነገር አለኝና “ኢትዮጵያ ወደ ፍቅር ጉዞ!” በሚል መሪ ቃል የሚደረገውን የቴዎድሮስ ካሳሁን የዘፈን ትዕይንት ጉዞ ለሀገርና ለሕዝቧ የማይጠቅም ይልቁንም የሚጎዳ መሆኑን መግለጽ ይኖርብኛል፡፡

ይሄውልህ ቴዲሻ ምን መሰለህ የቱንም ያህል ብንጥር፣ ብንመኝ፣ ብንታትር ሰላምና ፍቅር በአንድ ወገን ስለተፈለገ ብቻ ፈጽሞ ሊመጣም ሊገኝም አይችልም፡፡ በዚህ ሰዓት በዚህ ዘመን ወያኔ ከኦሕዴድ ብአዴን እስከ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ድረስ አሰማርቶ ሰላም ሰላም ፍቅር ፍቅር እያለ እያላዘነ ያለው ከልቡ ሰላምና ፍቅርን ፈልጎ፣ ለሰላምና ፍቅር ታማኝ ሆኖ፣ ሰላምና ፍቅር ሊያሰፍኑ የሚችሉ እርምጃዎችንም ለመውሰድ ቁርጠኛና ዝግጁ ሆኖ ከመሰለህ እጅግ የዋህና ያልበሰልክም እንደሆንክ ልነግርህ እወዳለሁ፡፡ በፍጹም ለዚህ አይደለም፡፡ ይሄንን እያደረገ ያለበት ብቸኛው ምክንያት ሕዝብ እያመፀ ካለበት ታቅቦ ወደ ቤቱ እንዲከተትለት ለማድረግ እንጅ የሕዝብ ጥያቄዎችን በመመለስ፣ ፍላጎቶችን በመፈጸም ሰላምና ፍቅርን ለማስፈን ዝግጁና ፈቃደኛ ስለሆነ አይደለም፡፡

ይሄ በሆነበት ሁኔታ አንተ “ኢትዮጵያ ወደ ፍቅር ጉዞ!” እያልክ መላ ኢትዮጵያን እየዞርክ ሰላም ሰላም ፍቅር ፍቅር ብትልና ሕዝቡ አንተን ሰምቶ ወደ ቤቱ ክትት ቢል ተጠቃሚ የሚሆነው ማን ይመስልሀል? አንተስ ማንን እያገለገልክ ነው የሚመስልህ? የኢትዮጵያ ሕዝብ ኦኮ እርስ በእርሱ ምንም ዓይነት ችግር ኖሮበት አያውቅም፡፡ ከፋሽስት ጣሊያን ወረራ ዘመን ጀምሮ እስከ ዘመነ ወያኔ ድረስ ተከስተው ያየሃቸውና የሰማሃቸው የዘር ግጭቶች በሙሉ በፋሽስት ጣሊያን፣ በኦነግ፣ በሸአቢያ፣ በወያኔና በግብረአበሮቻቸው አቀናባሪነት፣ ቀስቃሽነትና ፈጻሚነት የተከሰቱ እንጅ አንዱም እንኳ በሕዝቡ በራሱ ተነሣሽነት የተከሰተ ግጭት ኖሮ አያውቅም፡፡ ስለሆነም ሰላም ሰላም ፍቅር ፍቅር ብለህ ማዜም ካለብህ እነወያኔ እነኦነግ እነ ሸአቢያና ግብረአበሮቻቸው ይሰብሰቡልህና ለእነሱ አዚምላቸው፡፡

በስንት መከራ የተነሣሣውን፣ የተቀሰቀሰውን፣ የተቀጣጠለውን የሕዝባችንን የነጻነት ትግል ስሜትና ተነሣሽነት “ኢትዮጵያ ወደ ፍቅር ጉዞ!” እያልክ እየዞርክ ሰላም ሰላም ፍቅር ፍቅር ብለህ ውኃ እንድትቸልስበትና ሕዝቡ እራሱን ለእርድ እንዲያቀርብ እንድታደርግብን ፈጽሞ አንፈቅድም፡፡ እንዳልኩህ ችግሩ ያለው በጥፋት ኃይሎች ላይ እንጅ ሕዝቡ መሀል አይደለምና እነሱን ሰብስበህ ለነሱ አዚምላቸው፡፡

ወይ ደግሞ ማለት የፈለከው ወያኔን ጨምሮ እነኝህ የጥፋት ኃይሎች ከሕዝቡ ጋር ሰላምና ፍቅር እንዲፈጥሩ ከሆነ ፍላጎትህና ሰላም ሰላም ፍቅር ፍቅር እያልከን ያለህበት ምክንያት እንኳን በእውን በሕልም እንኳ ሊታይ የማይችልን ቅዠት እያስመኘህ እያስቃዠህ ጊዜያችንን በከንቱ እንድናቃጥል ከማድረግህም ባለፈ እንድንዘናጋ አድርገህ ልታስፈጀን ነውና እረፍ!!!

እናም ቴዲሻ አርፈህ ተስፋ ቆርጠህ ብትቀመጥ ይሻልሀል! በምንም ተአምር መቸም ቢሆን ወያኔ ለሀገር ሰላም ሊፈጥር የሚችልን፣ ሕዝብን የሥልጣን ባለቤት ሊያደርግ የሚችልን ሁሉን አሳታፊ የሆነ ዲሞክራሲያዊ (መስፍነ ሕዝባዊ) ምኅዳር ሊፈቅድ፣ ሊፈጥር አይፈልግም፡፡ ወያኔ ሁለቴና ሦስቴ አይደለም ሽህ ጊዜ እንኳን በምርጫ ቢሸነፍ ተሸንፌያለሁ ብሎ ወይም በሌላ ሰላማዊ አማራጭ ፈጽሞ ሥልጣን ሊያስረክብ የማይፈልግበት ዋነኛው ምክንያት ሥልጣን በለቀቀ ማግሥት በሕዝብ ላይ በፈጸመው አረመኔያዊ ግፍ ወይም ወንጀል፣ ሀገር ያራቆተ ሙስናና የሀገር ክህደቶች ሁሉ እየታነቀ ለፍርድ እንደሚቀርም አሳምሮ ስለሚያውቅ ነው፡፡

ቴዲሻ አንተና ብዙዎች እንደምትመኙት ከወያኔ ጋር ተደራድረን በሰላም መለያየታችን ወይም በሌላ አማራጭ ሰላማዊ ሽግግሽ እንዲደረግ ማድረጉ ወይም ወያኔን ያካተተ ብሔራዊ እርቅ እንዲፈጸም መደረጉ ለሕዝባችንና ለሀገራችን ጎጅ እንጅ ጠቃሚ አይደለም እሽ? ጠቃሚ የማይሆንበት ምክንያትም የኢትዮጵያ ሕዝብ ከወያኔ ጋር በሰላም ከተገላገለ እስከወዲያኛው ድረስ እንዳጣቸው የሚቀሩ በርካታ ብሔራዊ ጥቅሞች ስላሉ ነው፡፡

ከወያኔ ጋር በሰላም ብንለያይ ወያኔ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል!” እያለ የራሱን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲል የሀገር ክህደት ፈጽሞብን ብሔራዊ ጥቅማችንን አሳልፎ በመስጠት በተለይ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ለተፈራረማቸው ስምምነቶች ሁሉ ተገዥ የመሆን ዕዳንም ጨምሮ ነው ሀገሪቱና የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚሸከሙት፡፡ በኃይል ቢወገድ ግን ቀድሞውንም ሥልጣን የያዘው በሕዝብ ይሁንታና ፈቃድ ሳይሆን በኃይል ስለሆነ የራሱን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲል የሀገር ክህደት በመፈጸም ብሔራዊ ጥቅማችንን አሳልፎ በመስጠት ከባዕዳን ጋር የተፈራረማቸውን ውሎች የኢትዮጵያ ሕዝብ “አናውቅም! ውክልና አልሰጠነውም፣ በእኛ ይሁንታና ፈቃድ አይደለም ሥልጣን ላይ የወጣው ለአንድም ቀን አልተቀበልነውምና የሱ ስምምነቶች ሊገዙን አይችሉም! በእኛ ስም ስምምነት የማድረግ መብት አልነበረውም!” የማለትና ብሔራዊ ጥቅሞቻችንን ያሳጡንን ስምምነቶች ውድቅ የማድረግ ዕድል ይኖረዋል፡፡

ይሄንን ዕድል አግኝተን ለሱዳን ለጅቡቲ የተሰጠውን መሬት ለሸአቢያ የተሰጠውን የአሰብ ወደብ ወዘተረፈ. መልሰን ለማግኘት እንድንችል የተከፈለው መሥዋዕትነት ተከፍሎ ወያኔን በኃይል ማስወገድ ይኖርብናል እንጅ ፍቅር ያሸንፋል ፍቅር ይበልጣል ብለን ወያኔን “ውሾን ያነሣ ውሻ ይሁን!” ብለን ጫፉ ሳይነካ በሰላም ስንሸኘው አይደለም፡፡ ወንድሜ የሀገራችን ፖለቲካ አንተና አንተን የመሰሉት እንደምታስቡት ቀላል አይደለም እጅግ የተወሳሰቡ ነገሮች አሉበት፡፡ ያልገቡህ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡

ጉዳዩን በዝርዝር መረዳት ከፈለክ ከአራት ዓመታት በፊት “ሕወሀት ኢሕአዴግ” በቅርብ ጊዜ የብሔራዊ እርቅ ተማጻኝ!”

https://www.google.com/url…

በሚል ርእስ ባጻፍኩት ጽሑፍ ላይ በሚገባ ተንትኘ አብራርቸልሀለሁና ሊንኩን (ይዙን) ተጭነህ በማንበብ እውነታውን ለመረዳት ሞክር፡፡ ቴዲ በሞያህ ሀገርና ሕዝብ ተጠቃሚ ሊሆኑ በሚችሉበት መልኩ ሚና መጫወት ከፈለክ ሕዝቡ ለትንሣኤው እንቅፋትና መሰናክል የሆኑትን ጠላቶቹን እንዲያነሣ እንዲያስወግድ አዚምለት ተጫወትለት፡፡ የፍቅር ጉዞ ምንትስ የሚለው ነገር አይሠራም አያዋጣምም፡፡ በተረፈ ወጥመዳቸው ውስጥ ሰተት ብለህ ገብተህላቸዋልና ቀስ ብለህ ውጣ፡፡ ይህ ስሕተት ባንተ ይፈጠር ወይስ በዙሪያህ ባሉ ሰዎች እስካውቀው ቸኩያለሁ፡፡ በተረፈ የራስህን ዘፈን ኡኡታዬን ጋብዠሀለሁ፡፡ በመጨረሻ አንድ ነገር እንዳትረሳ ላሳስብህ እወዳለሁ አንተ ማለት ያለሕዝቡ ምንም ነህና ተጠንቀቅ!!!

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን
amsalugkidan@gmail.com

Filed in: Amharic