>

“በእስር ቤት ቆይታዬ ብዙ ነገሬን አጥቻለሁ” [ቀለብ (አስቴር) ስዩም]

– ባለቤቴም፣ በኔ ምክንያት ከመደበኛ ስራው ተፈናቅሎ በችግር ላይ ነው ያለው፡፡ በአጠቃላይ በኔ መታሰር ቤተሰቤ ተጎሳቁሏል፣ ቤተሰቤ ተበትኗል፡፡ የነበረው እንዳልነበር ሆኖ ነው የጠበቀኝ፡፡–”
ቀለብ ስዩም ወይም አስቴር ስዩም በመባል ትታወቃለች፡፡ የ28 ዓመት ወጣት ነች፡፡ አርማጭሆ ተወልዳ ያደገችው ወጣቷ፤ ገና የ12ኛ ክፍል ተማሪ እያለች ነው ወደ ፖለቲካው ዓለም የገባችው፡፡ ሁለተኛ ድግሪዋን በያዘች ማግስት ግን በአሸባሪነት ተጠርጥራ ለእስር መዳረጓን ትናገራለች፡፡ እንዴት ታሰረች? በእስር ቤት ቆይታዋ ምን አጋጠማት? የፖለቲካ ጅማሮዋንና የእስር ታሪኳን ለአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ እንዲህ አውግታዋለች፡፡ እነሆ፡-
እስቲ ስለ አስተዳደግሽና ትምህርትሽ ሁኔታ ንገሪኝ?
የተወለድኩት በሰሜን ጎንደር አርማጭሆ ነው። እድገቴም እዚያው ነው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቴን እዚያው አርማጭሆ ከተማርኩ በኋላ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን በጎንደር ፋሲለደስ አጠናቅቄያለሁ፡፡ የመጀመሪያ ድግሪዬን ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በኬምስትሪ አግኝቻለሁ፡፡ ቀጥሎም ሁለተኛ ዲግሪዬን (ማስተርስ) ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ በኢን-ኦርጋኒክ ኬምስትሪ ወስጃለሁ፡፡ አስተዳደጌን በተመለከተ ደግሞ አባቴም እናቴ በትምህርቴ እንድጎብዝ፣ ለእውነትና ለሃቅ መቆም እንዳለብኝም እየመከሩ ነው ያሳደጉኝ፡፡ ወላጆቼ ገበሬዎች ናቸው። እነሱ ሳይማሩ ነው እኔን ለማስተማር ብዙ የደከሙት፡፡
ትምህርትሽን እንዳጠናቀቅሽ በምን ሥራ ላይ ነበር  የተሰማራሽው?
በመጀመሪያ  በመንግስት ት/ቤት ተቀጥሬ፣ ደባርቅ ከተማ አስተማሪ ሆኜ ሰርቻለሁ፡፡ ደባርቅ ሁኔታው ስላልተመቸኝ ወደ ምዕራብ አርማጭሆ ሄጄ፣ በድጋሚ በማስተማሩ ቀጥያለሁ። ግን አሁንም በመንግስት ት/ቤት መስራቱ ከኔ አመለካከት ጋር የማይሄድ በመሆኑ ተቸግሬ ነበር፡፡ ሁሉም ነገር ከፖለቲካ ጋር የተያያዘ በመሆኑ ጨርሶ አልተመቸኝም፡፡ በዚህም የተነሳ ይህን ነገር እንዴት ነው መታገል የምችለው ብዬ ማሰብ ጀመርኩ። የበለጠ ሁኔታውን መታገል እንዳለብኝም ለራሴ ቃል ገብቼ መንቀሳቀስ ያዝኩ፡፡
የፖለቲካ ትግል ውስጥ ገባሽ  ማለት ነው?
የፖለቲካ ፓርቲ አባል የሆንኩት ገና የ12ኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ ነው፡፡ በወቅቱ የአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ አባል ሆኜ ነበር፡፡ የአንድነት አባል የሆንኩት ደግሞ በአካባቢዬ ከማየው የፖለቲካ አተያይ ተነስቼ ነው፡፡ በተለይ ተማሪ ሆኜ፣ በህብረተሰቡ ላይ በፖለቲካ አመለካከት ልዩነት የተነሳ የሚፈጠሩ ተፅዕኖዎችን አስተውል ነበር፡፡ ለዚያም  ነው፣ ገና በወጣትነቴ የፓርቲ ፖለቲካ ውስጥ የገባሁት፡፡ በኋላም በ2005 ዓ.ም ወደ ፓርቲው የአመራርነት ደረጃ ከፍ በማለት፣ የሰሜን ጎንደር ዞን፣ የፓርቲው አደረጃጀት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሆኜ ሰርቻለሁ፤ እስከምታሰር ድረስ። የፓርቲው የብሄራዊ ም/ቤት አባልም ነበርኩ፡፡ እንግዲህ አስቀድሞ የፓርቲው አባል በመሆኔ ብቻ በጥቃቅንና አነስተኛ ፕሮጀክት ተሳታፊ እንዳልሆን ተደርጌያለሁ፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል በመሆኔ ብቻ በአግባቡ የወሊድ ፍቃድ እንኳ አልተሰጠኝም ነበር፡፡ በዙሪያዬ የነበሩ ጓደኞቼም በተለየ ሁኔታ ነበር የሚታዩት፡፡ በአጠቃላይ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል መሆን በራሱ እንደ ወንጀል ይቆጠር ነበር፡፡
መቼና እንዴት ነበር  የታሰርሽው?
የግንቦት 7 አባል ሆነሽ፣ ኤርትራ ሄደሽ ልትቀላቀይ ነው በሚል ነው፣ የታሰርኩትና የተፈረደብኝ፡፡
እስቲ የታሰርሽበትን ሁኔታና አጋጣሚ ንገሪን?
እንግዲህ ሰኔ 29 ቀን 2007 ዓ.ም በማስተርስ ዲግሪ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከተመረቅሁ በኋላ በማግስቱ ስራ ለማፈላለግ፣ ከዚያ ቀደም አይቻት ወደ ማላውቃት አዲስ አበባ ነው የመጣሁት፡፡ አዲስ አበባ ሰኔ 30 ቀን 2007 ዓ.ም መጣሁ፡፡ በሁለተኛው ቀን አዲስ አበባን እንኳ በወጉ ሳላያት ነው ወደ ማዕከላዊ የገባሁት፡፡ የተያዝኩት ደግሞ 4 ኪሎ አካባቢ ከታክሲ ወርጄ ትንሽ ራመድ እንዳልኩ፣ ስሜ ከኋላዬ ሲጠራ በተደጋጋሚ ሰማሁ፡፡ እኔ ዝም ብሎ ጉንተላ መስሎኝ ወደ ኋላ ሳልዞር፣ መንገዴን ብቀጥልም ከኋላዬ ደርሰው ያዙኝ፡፡ አራት  ናቸው። ወዲያው ስልኬንና የያዝኩትን ሁሉ ነጠቁኝ፡፡ ከጠዋቱ 4 ሰዓት አካባቢ የያዙኝ፣ አይኔን በጨርቅ አስረውኝ፣ መኪና ውስጥ ካዋሉኝ በኋላ ምሽት ላይ ወደ ማዕከላዊ ወስደው አስገቡኝ፡፡
በቁጥጥር ስር ስትውይ፣ ምክንያቱ ተነግሮሽ ነበር?
በጭራሽ አልተነገረኝም፡፡ ምክንያቱን ስጠይቃቸው፣ “ስራሽን ስለምታውቂ ለምን እኛን ትጠይቂናለሽ” የሚል ምላሽ ነበር የሰጡኝ፡፡ እሺ ማንነታችሁን ንገሩኝ ስላቸው፣ ከብዙ ሰአታት በኋላ የብሄራዊ ደህንነት ባልደረቦች እንደሆኑ ነገሩኝ፡፡ ቀኑን ሙሉ አይኔን በጨርቅ ታስሬ መኪና ውስጥ ነው የዋልኩት፡፡ በዚህ ወቅት ግን ረጅም ርቀት በመኪና መጓዜ  ይታወቀኝ ነበር፡፡ ከዚያም ማታ ማዕከላዊ፣ ሴቶች ካሉበት ክፍል ገባሁ፡፡ የዚያኑ ዕለት ሌሊት 6 ሰዓት አካባቢ፣ ለምርመራ ወደ ቢሮ ተወሰድኩ፡፡
በምርመራው ወቅት የተያዥሽበት ምክንያት ተነገረሽ?
አዎ፤ ሰሜን ጎንደር ውስጥ የግንቦት ሰባት አመራር ሆነሽ ስትሰሪ ነበር፣ አሁን ወደ አዲስ አበባ የመጣሽው ወደ ኤርትራ ለመሄድ ነው፡፡ እኛ መረጃው አለን፡፡ ጉዳዩን በደንብ እንድታስረጅን እንፈልጋለን አሉኝ፡፡ የሚገርመው እኔ ስራ ፍለጋ ወደ አዲስ አበባ ስመጣ፣ የ6 ወር አራስ ልጄን ለእናቴ ጥዬ ነበር፡፡ እኔ ሃሳቤ ስራ ፈልጌ ወደ ቤተሰቦቼ ለመመለስ ነበር፡፡ ከልጄም ተነጥዬ አላውቅም። ማዕከላዊ ሆኜ ጡቴ ወተት እያዘለ ይፈስ ነበር፡፡ በወቅቱ እኔ ስለሚሉት ጉዳይ ጨርሶ እንደማላውቅ ተናግሬ ነበር፤ ግን ያ ምንም ለውጥ አላመጣም። የፈለጉትን ነገር ለማግኘት ባለመቻላቸውም፣ ከሰዎች ተገልዬ ብቻዬን ለሁለት ወር ታስሬ ነበር፡፡ በኋላም አንዲት ሴት አምጥተው ከኔ ጋር ቀላቀሏት። ይህቺ ልጅ ብዙ ቀናት አብራኝ ከቆየች በኋላ ምንም ነገር እንደላገኘችብኝ፣ ነገር ግን ልትሰልለኝ እንደመጣች ነግራኛለች፡፡ ይሄን የነገረችኝ ደግሞ በወቅቱ  እናቴና ልጄ ይናፍቁኝ ስለነበር፣ ሁሌ ሳለቅስ ስለምታየኝ አዝናልኝ ነው፡፡
ፍ/ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ  የቀረብሽው መቼ ነበር?
ማዕከላዊ እንደገባሁ በ7ኛው ቀን ቀርቤ፣ የ4 ወር ቀጠሮ ተጠየቀብኝ፡፡ በተደጋጋሚም ቀጠሮ ሲጠየቅብኝ ነበር፡፡
ከጎንደር ወደ አዲስ አበባ ስትመጪ ልጅሽን ለማን ትተሽ ነበር?
ቤቴ ጎንደር አዘዞ ነበር፡፡ እናቴ ደግሞ አርማጭሆ ነበር የምትኖረው፡፡ እሷ መጥታ ነው ልጄን ይዛልኝ ወደ አዲስ አበባ የመጣሁት፡፡ በኋላ እኔ ስታሰር እናቴ ልጄን ወደ አርማጭሆ ይዛው ሄደች፡፡ በጣም የሚገርመው አርማጭሆ ከአዲስ አበባ በ1200 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ነው የሚገኘው፡፡ ግን እናቴ ማዕከላዊ እያለሁ፣ ሁለት ጊዜ ልጄን ይዛ መጥታ ጠይቃኛለች፡፡ ከዚያም ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ወረድኩ፡፡ እዚያም እናቴ ለሦስት ጊዜያት ልጄን ይዛ መጥታ ጠይቃኛለች፡፡ ለመጨረሻ ጊዜ እናቴ የመጣችው መጋቢት 4 ቀን 2008 ዓ.ም ነበር። ወንድሜንና ልጄን ይዛ ነበር የመጣችው፡፡ እኛ በሽብር የተከሰስን እስረኞች የምንጠየቀው ከ6፡00 እስከ 6፡30 ነበር፡፡ እናቴ ይህ 30 ደቂቃ ስላልበቃት፣ ሰዓት ቢጨምሩልኝ ብላ በቢሮ በኩል ለማነጋገር ስትሞክር፣ አይቻልም በማለታቸው ሳታገኘኝ፣ በጣም አዝና  ወደ ጎንደር ተመለሰች፡፡ እናቴን ከዚያ በኋላ አላየኋትም፡፡ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየች። ልጄንም እኔንም ትታ አለፈች፡፡ ይሄ ዛሬ ህመም ሆኖብኛል፡፡
ወላጅ እናትሽ ማለፋቸውን እንዴት ነበር የሰማሽው?
የሚገርመው ማረሚያ ቤት ሆኜ ትፈለጊያለሽ ተብዬ ወደ ቢሮ ተጠራሁ፡፡ ለምንድነው ነው የተጠራሁት ብዬ ስሄድ፤ “አንቺ እዚህ እታገላለሁ ትያለሽ እናትሽ ግን ሞታለች” አሉኝ፡፡ በወቅቱ አፄ ቴዎድሮስ ያሉበትን ቲ-ሸርት ለብሼ ነበር፡፡ ምስሉን እያሳየሁ፤ ”አፄ ቴዎድሮስ እኮ አልሞተም፤ ዛሬም አለ፤ እናቴም አልሞተችም አለች” የሚል ምላሽ ሰጥቼ ነው ከቢሮ የወጣሁት፡፡ በወቅቱ ይህን በማለቴም ብዙ ተንገላትቻለሁ፡፡ በኋላ ስረዳ ግን እነሱ የእናቴን ሞት የነገሩኝ፣ እናቴ ከሞተች ከ8 ወር በኋላ ነበር፡፡ ይመስለኛል ሃሳባቸው አዕምሮዬን ለማቀወስ ነበር፡፡ ግን ውስጤን አጠንክሬ ለመቆየት ችያለሁ፡፡
እናትሽ በሞት ከተለዩ በኋላ ልጅሽን የሚይዝልሽ ማን ነበር?
እናቴ ከሞተች በኋላ በወቅቱ የ10ኛ ክፍል ተማሪ የነበረችው እህቴ ላይ ነበር ሃላፊነቱ የወደቀው፡፡ ትምህርቷን አቋርጣ ልጄን እስከ ዛሬ እያሳደገች ያለችው እሷ ነች፡፡ ወንድሞቼ ገበሬዎች ናቸው፤ ገጠር ነው የሚኖሩት፡፡ እናቴ ከሞተች በኋላ ቃሊቲ መጥተው ጠይቀውኝ ነበር፡፡ እናቴ በጣም ጎበዝ ነበረች፡፡ አባቴ ከሞተ በኋላ ቀጥ አድርጋ ያሣደገችን እሷ ነበረች፡፡ እናቴ በሃገር ደረጃ ምሣሌ የምትሆን ሴት ነች፡፡ እሷ ከሞተች በኋላ ወንድሞቼ በሚሰጧት ትንሽ ገንዘብ፣ እህቴ ናት ትምህርቷን አቋርጣ፣ ልጄን ስታሳድገው የቆየችው፡፡
ከእስር ከተፈታሽ  በኋላ ከልጅሽ ጋር ተገናኘሽ ?
እስካሁን አላገኘሁትም፡፡ ምክንያቱም መታወቂያዬ በምያዝበት ወቅት በመወሰዱና እስካሁን ስላልተመለሰልኝ ትኬት ቆርጬ፣ ወደ ጎንደር ለመሄድ አልቻልኩም፡፡ አሁንም ልጄ እንደናፈቀኝ ነው ያለሁት፡፡ መታወቂያዬን ስጠይቅም እስካሁን ምላሽ የሚሰጠኝ አላገኘሁም። በዚህ ምክንያት ልጄንም ሆነ ቤተሰቦቼን ሄጄ ለማየት  አልቻልኩም፡፡ ያለ መታወቂያ ደግሞ መንቀሳቀስ አልችልም፡፡
የክሱ እና የፍርዱ ሂደቱ እንዴት ነበር?
ከማውቃቸው 5 ሰዎች ጋር ነው በአሸባሪነት የተከሰስኩት፡፡ በአሸባሪነት የተፈረጀው የግንቦት 7 አባል ሆናችሁ፣ ወደ ኤርትራ ልትሄዱ ነው የሚል ነበር ክሱ፡፡ አብረውኝ የተከሰሱት ተመስክሮባቸውና ማስረጃ ቀርቦባቸው ነበር፡፡ እኔ ላይ  በወቅቱ የቀረበ የሰው ምስክር አልነበረም። ፍ/ቤቱ ተከላከሉ ባለበት ወቅትም “ማስረጃ ባልቀረበበት ሁኔታ እንዴት ነው የምከላከለው” ብዬ ነበር፡፡ ነገር ግን የስልክ ልውውጥ አድርጋለች ስለተባለ የመከላከያ ማስረጃዬ የሆነው የቴሌ ማስረጃ ነበር፡፡ ቴሌ 6 ስልኮችን መነሻ አድርጎ በላከልኝ ማስረጃ ላይ በቀለብ ስዩም ስም የወጣ ሲም ካርድ የለም፡፡ ዳታ ቤዙ ላይም የስልክ ልውውጥ አላደረገችም ተብሏል። የስልኮቹ ባለቤቶቹንም ከእነ ፎቶግራፋቸው ነበር የላከው፡፡ ፍ/ቤቱ ግን ማስረጃዎቹን አልተቀበለም። እናም የ4 ዓመት እስር ተፈረደብኝ፡፡ ከዚያ በኋላ ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ጠይቄ፣ 9 ወር ተቀነሰልኝ፡፡ ሶስት አመት ከ3 ወር ታስሬ ከሁለት ሳምንት በፊት ተፈትቻለሁ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ዳኛ ያዕቆብ መኩሪያን አመሰግናለሁ። የጥፋተኝነቱ ብይን በተላለፈበት ወቅት በልዩነት “ለእኔ ቀለብ ስዩም ነፃ ነች” ብሎ ነበር፡፡
የማረሚያ ቤት ቆይታሽ ምን ይመስል ነበር?
ቃሊቲ በነበርኩበት ወቅት “አንቺ መታረም የማትችይ ሰው ነሽ” እየተባልኩ ዘለፋ ይደርስብኝ ነበር፡፡ የተለያዩ ስልጠናዎችንም ተከልክያለሁ። የታሰርኩት በስርቆት ወንጀል ከተፈረደባቸው ሰዎች ጋር ነበር፡፡ ልክ አንድ አሸባሪ እየታየሁ ክትትል ሲደረግብኝ ነበር፡፡ እዚህ ላይ አንድ የማስታውሰው ነገር፣ ባለቤቴ መጥቶ ሲጠይቀኝ፣ በእንግሊዝኛ አውርተሻል በሚል፣ ለ1 ወር ቤተሰብ እንዳይጠይቀኝ ተደርጌ ነበር፡፡ በዚህ አጋጣሚ ባለቤቴም፣ በኔ ምክንያት ከመደበኛ ስራው ተፈናቅሎ በችግር ላይ ነው ያለው፡፡ በአጠቃላይ በኔ መታሰር ቤተሰቤ ተጎሳቁሏል፣ ቤተሰቤ ተበትኗል። የነበረው እንዳልነበር ሆኖ ነው የጠበቀኝ፡፡ እዚህ ጋ ሳልጠቅሰው ማለፍ የማልፈልገው ነገር ቢኖር፣ በማረሚያ ቤት እያለሁ፣ እስረኞችን የሚሰልሉና የሚከታተሉ ታሳሪዎች መኖራቸውን  ነው፡፡
ለወደፊት ምንድን ነው የምታስቢው? በፖለቲካ ተሳትፎሽ ትቀጥያለሽ ወይስ?
ከመቶ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን አንዷ እኔ ነኝ፡፡ በወጣትነቴ ለመብት በመታገል ማድረግ ያለብኝን እያደረግሁ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ አሁንም ይህቺ ሀገር የጋራችን ነች፡፡ ሀገራችንን ከዳር ቆመን መመልከት የለብንም፤ ሁላችንም ለእድገቷ፣ ለዲሞክራሲ፣ ለህግ የበላይነት  መታገል አለብን፡፡ ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ ሆና የቆየችው፣ አባቶቻችን በየጊዜው መስዋዕትነት በመክፈላቸው ነው፡፡ ዛሬም ኢትዮጵያ ልትኖር የምትችለው በኛ መስዋዕትነት ነው፡፡ እኔ ለመብት፣ ለዲሞክራሲ ስታገል ብዙ ነገሬን አጥቻለሁ፡፡ ኑሮዬ ተዛብቷል፡፡ እናቴን በሞት አጥቼ ሳልቀብራት ተሰናብታኛለች፣ ልጄ የእናት ጣዕም ሳያውቅ እንዲያድግ ተገድዷል፡፡ ይህ ሁሉ ግን ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግል የተከፈለ መስዋዕትነት ነው፡፡ የወደፊት የፖለቲካ ተሳትፎዬ የሚወሰነው በሂደት ነው፡፡ ያልተገባ መስዋዕትነት ከፍያለሁ የሚል እምነት ግን የለኝም፡፡ በዚህ አጋጣሚ በእስር ቤት ሳለሁ ተመላልሳችሁ ለጠየቃችሁኝ፣ በተለያየ አጋጣሚ የኔን ጉዳይ፣ ጉዳዬ ብላችሁ ለተጨነቃችሁ ሁሉ ማመስገን  እፈልጋለሁ፡፡
እንደ’ኔ አሁንም ሁላችንም እንደ ዜጋ፣ ለሀገራችን አንድነትና ዕድገት፣በፍቅር መቆም አለብን፡፡ በአገሪቱ ላይ የሚታየው ወቅታዊ ችግርም በሁሉም ኢትዮጵያዊ ተሳትፎ መፈታት አለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡
ቀለብ በአሁኑ ሰዓት የወገን ድጋፍ ትሻለች፥ የምትፈልጉ በተዘጋጀው Gofundme መርዳት ትችላላችሁ፥
ምንጭ:- አዲስ አድማስ
Filed in: Amharic