>

ሀገሬ (ገብረክርስቶስ ደስታ)

(ገብረክርስቶስ ደስታ፡፡ መንገድ ስጡኝ ሰፊ፡፡ 1998)

ይኽ የገብረ ክርስቶስ ግጥም ተሳድደንም ይኹን ተቸግረን ከሀገር የምንወጣ ኢትዮጵያውያን ከሀገር ስንወጣ የሚጫነን ስሜት ይመስለኛል፡፡ ነጻነት እንደሌለ እያወቅን እንኳን ነጻነት ያለበት ሀገር እንሥላን፡፡ ሆዳችን ይባባል፡፡ ወላጆቻችን ኢትዮጵያን እንዴት አድርገው ቢከትቡን ነው?


አገሬ ውበት ነው፤
ለምለምና ነፋስ የሚጫወትበት፣
ፀሐይ የሞላበት፤ ቀለም የሞላበት፡፡
አገሬ ቆላ ነው፤ ደጋ ወይናደጋ
እዚያ ብርሃን አለ ሌሊቱ ሲነጋ፡፡
አገሬ ተራራ፣ ሸለቆ ረባዳ፣
አገሬ ጅረት ነው ገደልና ሜዳ፡፡
ውሸት ነው በበጋ ፀሐይ አትፋጅም፤
ክረምቱም አይበርድም፤
አይበርድም፤ አይበርድም፡፡
አገሬ ጫካ ነው፤
እንስሳት አራዊት የሚፈነጩበት፤
በወጥመድ ሳይገቡ ሳይነካቸው ጠላት፡፡
እዚያ አለ ነጻነት፡፡
በሀገር መመካት፣
በተወላጅነት፣
በባለቤትነት፣
እዚያ አለ ነጻነት፡፡
አገሬ ሀብት ነው፡፡
ጎመኑ ስብ ጮማ፣ ቆሎው ክትፎ ሥጋ
ድርቆሹ ፍትፍት ነው፤ ቃሪያው ሙክት ሠንጋ፡፡
ጠጁ ነው ወለላ
ከኮኛክ ይነጥቃል የመንደሩ ጠላ፡፡
እኽሉ ጣዕም አለው፤ እንጀራው ያጠግባል፤
በዓሉ ይደምቃል፤
ሙዚቃው ያረካል፤
ጭፈራው ዘፈኑ ችግርን ያስረሳል፡፡
እዚያ ዘመድ አለ፡፡
ሁሉም የናት ልጅ ነው፤
ሁሉም ያባት ልጅ ነው፤
ጠላትም አንዳንዴ ይመጣል መቃብር፤
ባላጋራም ቸር ነው “ያገር ልጅ” ሲቸገር፡፡
ገነት ነው አገ፡፡
ምነው ምን ሲደረግ!
ምነው! ለምን! እንዴት!
ዘራፊ ቀማኛ፣ ምቀኛ ወንበዴ
ጥርኝ አፈር በጁ ስንዝር ወሰን አልፎ
የተቀደሰውን ያፍሪቃ ላይ ደሴት
ባያገኝ ለማርከስ ጠላት ይመኝ እንዴት፡፡
እምቢኝ አሻፈረኝ!
አሻፈረኝ! እምቢ!
መቅደስ ነው አገሬ፤
አድባር ነው አገሬ፡፡
እናትና አባቴ ድኸው ያደጉበት
ካያት ከቅድመ አያት የተረካከቡት
አፈር የፈጩበት፣
ጥርስ የነቀሉበት፡፡
አገሬ አርማ ነው የነጻነት ዋንጫ፣
በቀይ የተጌጠ ባረንጓዴ ቢጫ፡፡
እሾሕ ነው አገሬ፤
በጀግናው ልጅ አጥንት የተከሰከሰ፤
ጠላት ያሳፈረ፣ አጥቂን የመለሰ፡፡
አገሬ ታቦት ነው፤ መቅደስ የሃይማኖት
ዘመን የፈተነው በጠበል በጸሎት፡፡
ለምለም ነው አገሬ፡፡
ውበት ነው አገሬ፤
ገነት ነው አገሬ፡፡
ብሞት እኼዳለሁ ከመሬት ብገባ፤
እዚያ ነው አፈሩ የማማ ያባባ፡፡
ስሳብ እኼዳለኹ ቢሰበርም እግሬ
አለብኝ ቀጠሮ ከትውልድ አገሬ፡፡
አለብኝ ቀጠሮ፣
ከትውልድ አገሬ ካሳደገኝ ጓሮ፡፡

Filed in: Amharic