አንዳንድ ጊዜ ይገርመኛል፡፡ ግን ደግሞ ይሻላል እላለሁኝ፡፡ ሃይማኖቱን ወይንም ሳይንሱን በደንብ ብንይዝ ኖሮ ጨቋኝ ነበር የምንሆነው፡፡ ዓለምን እንጨቁን ነበር፡፡ ግን ኩራታችን የውሃ ላይ ኩበት ነው፡፡ “የውጭ ወራሪ ቅኝ ገዝቶን አያውቅም” ከሚለው ባሻገር ሌላው ኩራታችን ምንጩ አይታወቅም፡፡
እንኳንም ሉሲን እኛ ቆፍረን ያላገኘናት፡፡ እኛ ብናገኛትና የኢቮሉሽን ፅንሰ ሀሳብን ብንፈለስፈው ኖሮ ዓለም ላይ ሌላውን የሰው ልጅ አናስቀምጥም ነበር፡፡ … ባልሰራናቸው ነገሮች በቀላሉ የመኩራት አቅም አለን፡፡ “አዳም ጎጃሜ ነው” ከማለት የሚመልሰን የለም፡፡ መረጃዎቹ አልገኝ አሉ እንጂ የሚመልሰን የለም ነበር፡፡ …
“Maximalizm” የሚባል የበሽታ አይነት ካለ … በእርግጠኝነት እኛ ኢትዮጵያውያን የዚህ በሽታ ተጠቂ ነን፡፡ “ማክሲማሊዝም” የአስተሳሰብ አይነት ነው፡፡ ትንጧን ማስረጃ ህዋን የሚያክል መጠን የለሽ ስፋት ለማልበስ የሚያስደፍር የአስተሳሰብ አይነት ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ይሄንን የአስተሳሰብ አይነት ሳይንሳዊ ፅንሰ ሀሳብን የሚመረኮዙ ምሁራን አሉ። ቀዶ ጥገና ከማድረጋቸው በፊት “OR” ውስጥ ተንበርክከው እንደሚፀልዩ ሰርጅኖች ማለት ነው፡፡ በሁለት እግር ሁለት ዛፍ መውጣት ማለት ነው፡፡ በተጨባጩና በማይጨበጠው መሀል መንጠልጠል ነው፡፡ መውደቅ አይኖርም፡፡ ምክኒያቱም አንደኛው ዛፍ መውደቅን “ማረግ” ብሎ ሊረዳው ይችላልና። መውደቅ እንደሌለው ሁሉ ወደ ላይ መውጣትም አይኖርም፡፡ ምክኒያቱም፤ መውደቅን “ማረግ” አድርጎ ያነበበው … መውጣት፣ መሻሻልን ከሰይጣን ጋር መዋዋል ብሎ ሊተረጉመው ይችላልና፡፡ ጉራ ብቻ ይቀራል – የማይነካ፣ የማይጨበጥ በመረጃ የማይረጋገጥ ርስታችን ነው፡፡
አንድ ሀገር ህዝቧ እንደተሰደደ … ሳይመቸው የሚኖር ከሆነ ተጨባጩ እውነት ይሄ ነው። ይሄ ለምን እንደተከሰተ መመርመር ይቻላል። በስደት ብትንትኑ የወጣ ህዝብን “ቅርብ ነው አይርቅም፤ የኢትዮጵያ ትንሳኤ” የሚል ሰባኪ … ባዶ ጉራን ከመመገብ ውጭ ምንም የረባ አስተዋፅኦ አያደርግም፡፡
“ማክሲማሊዝም” ይጎዳል፡፡ ጥንት ታላቅ የነበረ ህዝብ … ያንን የታላቅነቱን ዘመን እየተረከ፣ ውድቀቱን ግን በተጨባጭ የሚኖር ከሆነ ይጎዳል። .. መጎዳቱን ግን በየት በኩል ይሰማል? ከምንም ጊዜ በላይ ለዚህ ህዝብ ሳይንስ ያስፈልገዋል፡፡ ኩራት በሳይንስ ቋንቋ ትርጉም የሌለው ነገር ነው። … ጤነኛው ሳይንስ ሰውን እንደ “ምድር ጨው” አያየውም፡፡
ከአይሁድ ትውፊት የተወረሱ ሀይማኖቶች ግን ሰውን እንደ ፈጣሪ ተወካይ ነው የሚቆጥሩት፡፡ … ሰውን እንደ ምድር ጨው መስለው ማስተማራቸው ሰውን ጠቀመው ወይ? ካላችሁኝ፤ መልሴ አልጠቀመውም ነው፡፡ … ሁሌ “ሰው በምድር የፈጣሪ አምባሳደር ነው” ሲባል “የበለጠ ሰው ነኝ” የሚል ብቅ ይላል፡፡ … ሀይማኖቱን ያደረጅና ሌላውን የሰው አይነት ማሳደድ ይጀምራል፡፡ … ሁሉም ሰው መሆኑን ይዘነጋል፡፡ …
“አዳም ጎጃሜ ነበር” ከምትለኝ “ሉሲ ለሰው ልጆች ሁሉ ቅርብ አያታችን ናት ብትለኝ” ይሻለኛል። … ጥንታዊ ዝንጀሮ መሰል ሰዎች ተቆፍረው ይወጣሉ፡፡ ዘመናዊ ሰው ግን ተቀብሮም ሆነ በቅሎ አልተገኘም፡፡
በቀደም ከአንዱ ጋር ሳወራ “የክርስቶስ አጥንት ቢገኝ ሳይንቲስቶች ቅሪተ አካሉን በማጥናት መሲህ መሆኑን … እና በተጨባጭ የኖረ አምላክ መሆኑን ያረጋግጡ ነበር” አለኝ፡፡ ቀልዱን ይሁን እውነቱን አላወቅሁኝም፡፡ ቀልዱን ቢሆን ይሻላል፡፡ የኢየሱስ አካል ቢገኝ ለሳይንሱ አያገለግልም፡፡ የክርስትናን ሀይማኖት ግን ይጎዳዋል፡፡ አንደኛ “የእርገት” ታሪኩ ይበላሻል፡፡ ሞቶ የተነሳ አካል፣ መልሶ ካልሞተ አጥንቱ ሊገኝ አይችልም፡፡ …
ሀይማኖቱን ይጎዳዋል .. ነው ያልኩት? … እምነትማ አይጎዳም፡፡ እምነት ሺ ጊዜ ሺ ማስረጃ ቢመጣ … መሳሳቱን አይቀበልም፡፡ ከተቀበለማ … ሰይጣን ጎበኘው ማለት ነው፡፡ … እራሱ ክርስቶስ በድጋሚ መጥቶ “በእኔ ስም እያመናችሁ ያለው ሀይማኖት ስህተት ነው” ቢል … የሚሰማው የለም፡፡ “አንቲክራይስት” ነው የሚባለው፡፡ እንዲህ ማለቱም አስቀድሞ የሚጠበቅ ነው፡፡
ቀደምት የሚባሉት የክርስትና እምነት አባቶች … (ማለትም እንደ ጀስቲን ማርተር፣ ተርቱሊያን እና ኢሬኒየስ) አንዳንድ አረመኔ አቃቂር አውጭዎች … “የኢየሱስ ታሪኮች ቀደም ካሉ ትውፊቶች የተቀዳ ነው” ብለው ክርክር ሲገጥሟቸው .. የመለሱት መልስ አስደማሚ ነው፡፡ “…. ቀደም ያሉት ትውፊታዊ ታሪኮች ከክርስቶስ ታሪክ ጋር ተመሳሳይ የሆኑት በሰይጣን ስራ ምክኒያት ነው። ሰይጣን የክርስቶስን ታሪክ ስለሚያውቅ ወደፊት ቀድሞ ቀድቶ፣ ከዛ ወደ ኋላ ተመልሶ፣ የጥንቶቹ ትውፊቶች ላይ እንዲከናወኑ አደረገ” ብለው ነው መልስ የሰጡት፡፡
… አንዳንድ ጊዜ ሀይማኖት ራሱ እንደ ስልጣኔ የሚሰራ ነገር መስሎ ይታየኛል፡፡ የሚሰራባቸው ንጥረ ነገሮች ይታወቃሉ፡፡ … ንጥረ ነገሮቹ ብዙ ተጨባጭ መረጃ የሌላቸው መሆን አለባቸው፡፡ … ተጨባጭ መረጃዎች ሲጠፉ የእምነት ንጥረ ነገሩን ከፍ ማድረግ ይቻላል፡፡ የእምነት ንጥረ ነገር … ውስጡ ብዙ ስሜቶችን የያዘ ነው፡፡ ለምሳሌ ኩራት አንዱ የስሜት አይነት ነው፡፡ … የኩራቱ ምክኒያት እምነት እስከሆነ ድረስ የማስረጃ ጥያቄ አያስነሳም፡፡ … “ኩራቱ” ብቻ ይበቃል፡፡ እምነቱ ብቻ ይበቃል፡፡ ማስረጃ አያስፈልገውም፡፡
እስራኤል ፍራክለስታይን እና ኔል አሸር ሲልበርማን የሚባሉ ተመራማሪዎች “The bible unearthed” የሚል መፅሐፍ በመፃፋቸው ይታወቃሉ፡፡ … እነዚህ ተመራማሪዎች ባደረጉት ጥናት፤ የአይሁድ፣ የክርስትና. እና እስልምና ሀይማኖቶች እንዲሁም የብሉይ ወንጌል ታሪኮችና በታሪኮቹ ላይ የሚነሱ ቦታዎችና ሰዎች .. በማስረጃ ለማግኘት የተቻለው ኢ-ምንት ነው ብለው ይደመድማሉ፡፡
“ትንሹ መረጃ በትንሽነቱ ድንክ ሆኖ እንዲቀር ትፈልጋላችሁ” ተብለው በ“ማክሲማሊስቶቹ” ይወነጀላሉ፡፡ … ማክሲማሊስቶቹ … እነዚህን “ሚኒማሊስት” ብለው ይነቅፏቸዋል፡፡… እርግጥ የመፅሐፍ ቅዱሱ ታሪክ መቼም ከሜዳ አልመጣም። … ምንም ሆነ ምን ታሪኩ ዝም ብሎ ሊመጣ አይችልም … ብለን ልናስብ እንችላለን፡፡ ታሪኩ እርግጥ ከምንም አይመጣም፡፡ … ታሪኪ ተከሰተ በተባለበት ስፍራ በቂ ተጨባጭ ማስረጃ አልተገኘም እንጂ … እርግጥ ታሪኩ ዝም ብሎ አይመጣም፡፡
… ታሪኩ በሰው ልጅ ባህልና አስተሳሰብ ላይ ያለው ቦታ ብቻ በቂ ነው፡፡ ምንም እንኳን ተቆፍሮ የተገኘ ተጨባጭ ማስረጃ ባይኖርም የሰው አስተሳሰብ ላይ እምነቶቹ በጥልቁ ገብተው ተቀብረዋል፡፡ በቀላሉ ተቆፍረው ሊወጡም አይችሉም፡፡
… ለምሳሌ ዛሬ እንደው በጠዋት ተነስተን ወደ አንዱ ሟች መሪያችን … (ቆይ ምሳሌዋን ከዚህ ሀገር ላርቃት) … አንዱ የፈረንሳይ መሪ ለምሳሌ ናፖሊዮን ቦናፓርት መቃብር ብንሄድና … ድንገት አስከሬኑ ተሰውሮ ብናገኝ … “አረገ” አንልም፡፡ አፅሙን ሰው ሰረቀው ነው የምንለው፡፡… እንደ ናፖሊዮን አይነት ጀነራል “አረገ” ለማለት ይከብዳል፡፡ ግን አፅሙን እንደሰረቅነው … ሌሎች የሕይወቱን አሻራና ገድሎቹን ቀስ በቀስ ብንሰውር … በሰወርነው ፈንታም መንፈሳዊ የሚመስሉ ገድሎችን ብናስነግርለት… ማረጉ … ብዙ የማይታመን ነገር አይሆንም፡፡
በጎደለው ማስረጃ ልክ እምነት ይጠነክራል። ኩራትም ጎን ለጎን ይደረጃል፡፡ … የራስ ታፈራይ እምነት ተከታዮች ያኔ የንጉሱን ቅሪተ አካል ለመቅበር …ሲጠሩ “አምላክንማ እንዴት ለመቅበር እንመጣለን?” አሉ መባሉን በወሬ ደረጃ ሰምቻለሁኝ፡፡ ምክኒያቱ ግን ያን ያህል አልገባኝም ነበር፡፡ አሁን ግልፅ ሆኖልኛል፡፡
ለማንኛውም… እምነትና ሳይንስ ዝንተ አለም አይገጥሙም፡፡ ለኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ ሳይንስ ያስፈልጋታል፡፡ እምነትና ኩራት ተደራርበው የወሰዷት መንገድ … ጥሩ አይደለም፡፡ … አሁን አሁን … በእምነትና በግትርነት የማንወጣው አቅጣጫ ውስጥ እየገባን መሆኑ ግልፅ እየወጣ መጥቷል፡፡ እኔ ብንነቃ ይሻላል ነው የምለው፡፡ … ሁለት ዛፍ ላይ ተንጠልጥለን ማስመሰል የእውነት ጎድቶናል። በኩራትና በእምነት ብቻ የትም አይደረስም፡፡ ነገራትን እውነት እንደሆኑ ለማየት ከሳይንስ በላይ የሚያግዝ ብልሀት የለም፡፡
ኢትዮጵያዊ ኩራታችን በጨረፍታ... (ሌሊሳ ግርማ)
Filed in: Amharic