>
5:08 pm - Wednesday February 22, 7584

«ኢህአዴግ ጠላት አይንቅም…» (ዮናስ ሃጎስ)

ኢህአዴግ አይታደስም ስንል ውስጡ ጨዋ የሆኑ በመርህ ብቻ ኢህአዴግን የሚደግፉ ምናምን ጥሩ ሰዎች ጠፍተው አይደለም። በእርግጥ ወንጀል ባይፈፅሙም ቅሉ የተፈፀመ ወንጀልን አይተው በዝምታ ማለፍ በራሱ ወንጀል ቢሆንም ቅሉ እሱን እንተወውና ኢህአዴግ መልካም የሆኑ ሰዎች አሉት ብንል እንኳ እድሳቱን ከየት ጀምረው ወዴት እንደሚዘልቁ መገመት አይቻልም። ከመሰረቱ የበሰበሰን ቤት ላይ ላዩን ቀለም ብትቀባውና አጥሩን ብታጠባብቅ የቀለምና የአጥር ወጪ ትከስራለህ እንጂ ኢህአዴግ ታደሰ ማለት አይደለም።
•°•

ዝነኛው አርቲስት ቴዲ አፍሮ በባሕር ዳር ለጥር 13 ኮንሰርት ለማቅረብ እንደተፈቀደለት የሚያሳይ ዜናን ተከትሎ የሰዉ ደስታ የሚገርም ሆኗል። በእውነቱ አንድን አርቲስት የሙዚቃ ስራውን እንዳያቀርብ ማገድ «ኢህአዴግ ጠላት አይንቅም…» የሚለውን ብሒል ከማረጋገጡ ው ለኢህአዴግ የሚፈጥረው አንዳችም እርባና የለውም። ኢህአዴግ ቴዲ አፍሮ በመላዋ ኢትዮጵያ እየተዘዋወረ ኮንሰርት ቢያቀርብ አንዳችም ጉዳት አያገኘውም። ግን ያው ከስረ መሰረት የተበላሸው የአምባገነን ባሕርይው አልለቀው እያለ ነው ከክልል ክልል እየተከታተለ የአርቲስቱን ስራ ለማጨናገፍ ሲደክም የሚታየው። በአዲስ አበባ የተሳካለት ቢሆንም የባህር ዳሩ ይሳካለታል የሚል እምነት የለኝም። ቢሳካለትም ለቴዲ የሚቀርበት ነገር የለም። ቴዲ ቢዘፍንም ለብዓዴን «ወንዳታ!» የሚል ተጨማሪ ድጋፍ ከማሰባሰብ ውጭ ለኢህአዴግ አንዳችም የሚጎልበት ነገር የለም። ምናልባት ጥቂት የሕወሐት አመራሮች በ«ተደፈርን!» ስሜት ሊንገበገቡ ይችሉ ይሆናል። ሌላ ምንም ነገር የለም።
•°•
ኢህአዴግን ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ማስወገድ ወይንም በተሻለ መተካት ላቃተው ያገራችን የተቃውሞ ፖለቲካ ግን ወሬው ሁሉ ስለዚህ ኮንሰርት ብቻ ቢሆን የሚገርም ይመስላል። የሐገራችን የተቃዋሚዎች ፖለቲካ በራሱ በከፍተኛ ሁኔታ ተስፋ እንደቆረጠ የታወቀው ከኢህአዴግ ውስጥ የለውጥ አቀንቃኝ ሆነው ብቅ ያሉትን የለማን አስተዳደር በሙሉ ድምፅ መደገፍ በጀመረበት ወቅት ነው። ፈስ ያለበት ዝላይ አይችልም ሆነና የተጠበቀው ለውጥ እንደ ሻማ ጭላንጭል ብቅ ብሎ ድርግም ሲል አሁን የተሸናፊነት ስሜትን በቴዲ አፍሮ ኮንሰርት ለማጣጣም የሚሹ ተቃዋሚዎችን ስናይ ይህቺ ሐገር ፕራዮሪቲ የምትሰጣቸው ነገሮች ምን ያህል ምስቅልቅላቸው እንደወጣ የሚያሳይ ክስተት ሆኗል።
•°•
በነገራችን ላይ የቴዲ አፍሮ አድናቂ ነኝ። በቃ ጥበብ ስሙን እስከነ አያቱ ጠርታ ነው ወደርሱ የዘለቀችው። የሚሰራቸው አልበሞች በሙሉ አነጋጋሪ ብቻ ሳይሆኑ ጥበባዊም ጭምር ናቸው። አውቃለሁ «ለምን ስለ እንትና ዘፍኖ ስለ እንትና አልዘፈነም?»፣ «የሚዘፍነው የድሮዋን ጨቋኝ የነበረችውን ኢትዮጵያን ጉዳይ ነው!»፣ «የድሮ ጨቋኝ አፄዎችን ይወዳል…» ምናምን ባይ ተቃዋሚዎች እንዳሉት። ለኔ ግን አንዳቸውም ስሜት አይሰጡኝም። ቴዲ አፍሮ ካሳሁን በእውነትም የሚችል አርቲስት መሆኑን በአስር ጣቴ እፈርማለሁኝ።
•°•
የርሱን ኮንሰርት ሁለት ጊዜ ለመታደም በቅቻለሁኝ። አንዴ አዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ሁለተኛ ናይሮቢ ኢስሊ መጥቶ የዘፈነ ጊዜ ታድሜያለሁኝ። በቃ ስቱድዮ የዘፈነውን ዘፈን እስክታንቋሽሽ ድረስ የመድረክ ተሰጥዖው ምርጥ ሆኖ ታገኘዋለህ። አሁን ሞባይሌን ተቀብለኸኝ ብትጎረጉር ከስቱድዮ ዘፈኖቹ ይልቅ «አትላንታ!» እያለ የሚጣራባቸው የመድረክ ዘፈኖቹ በዝተው ታገኛለህ። ሐገር ውስጥ ብሆን የማልቀርበት ቀጠሮዬ የቴዲ አፍሮ ኮንሰርት ነው።
•°•
ነገር ግን ተቃዋሚዎች…
እባካችሁ በትላልቅ ጉዳዮች እየተሸነፍን በሽርፍራፊ ድሎች ደስታችን ጣራ አይንካ? ሳምንት አልሆነውም እኮ ይፈታሉ በተባሉ የፖለቲካ እስረኞች ላይ «ፍርድ ቤት በመዳፈር» ተጨማሪ ስድስት ወራት እስር ቅጣት ከተጣለባቸው… ይዘጋል የተባለው ማዕከላዊ አድራሻ መቀየሩን እንጂ ስራው ባለበት እንደሚቀጥል ባንዱ ኮማንደር ከተነገረን አስራ አምስት ቀን አልሞላውም። የኦሮሚያ ፋኖዎች በፌደራል ፖሊስ ምርመራ ስር መግባታቸውን በአደባባይ ከተነገረን ቆየን እንዴ? ታድያ ምላሻችን ምንድነው?
•°•
«ቴዲ ባህር ዳር ልክ ልካቸውን ሊነግራቸው ነው!»
•°•
ይኸው ነው በቃ? 
•°•
በነገራችን ላይ ዛሬም የኳስ ድብድብ ነበረ አሉ። ይኼ መከረኛ ኳስ ከሁለቱም ክልሎች ርቆ አዲስ አበባ ላይ እንዲካሄድ ተወስኖም የሁለቱ ክልል ደጋፊዎች ለጠብ አይርቀንም ብለው መኪና ሞልተው መጥተው በድንጋይ ሲራኮቱ ዋሉ አሉ። (ለዚያውም ያለ ግብ ላለቀ ጨዋታ)
•°•
ለማንኛውም ኢህአዴግ ይህን የባህር ዳር ኮንሰርት እሰርዛለሁ ብሎ የጅል ነገር እንዳያደርግ ምክሬን አስተላልፋለሁኝ። የሚሰርዘው ነገር የግድ የሚያስፈልገው ከሆነ ፕሪሚየር ሊጉን እስከነ አካቴው ይሰርዘው! ፖሊሶቹም እረፍት ያገኛሉ። «ደጋፊዎቹም» ድንጋይ ይዘው ከክልል ወደ ክልል ከመንከራተት ይድናሉ። እኛም ኳስ ጨዋታ አለ በተባለ ቁጥር «ስንት ጎል ገባ?» ብለን መጠየቅ እየተገባን «ስንት ሰው ተፈነከተ?» ከሚል የጅል ጥያቄ እንገላገላለን። እንዲያውም ቢችል ለባህር ዳር ኮንሰርት ፖሊሶቹን በሙሉ የዛን ቀን እረፍት ቢሰጣቸውና ከማግስቱ ጀምሮ ለሚቀጥለው የአምባገነናዊው ስርዓት ትንፋሽ ማስቀጠል ስራቸው በቂ ትንፋሽ ያገኙ ዘንድ ቢያደርግ ምክሬ ነው።
Filed in: Amharic