>

በግንቦት 7፣ በዴምሒት፣በኦነግ ሻእቢያ ትክሻ ዓረቦች ሀገራችን ሊገቡ ነው! (ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)

ወገን ሆይ አልቆልናል! ወያኔ በዓረብ ጅብ ሊያስበላን ነው፡፡ አቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ ግብጽና ዓረብ ሀገራት ሲሯሯጥ፣ ሲሻጠር፣ ሲዶልት፣ ሲተልም፣ ሲያቅድ ከሰነበተ በኋላ ትናንትና ለራሱ የብዙኃን መገናኛ በሰጠው ቃለ ምልልስ “Game Over ! ወያኔ ሞቷል ! ምንም አይነት መላላጥ አያድነውም!” እያለ ሲያውጅ አምሽቷል፡፡ አቶ ኢሳይያስ ማለት በእብሪትና ግትርነት ላይ እብደትና ደደብነት ተቀላቅሎ ያለበት ሰው ማለት ነው፡፡ ኃላፊነት የሚባል ነገር ፈጽሞ አይሰማውም፡፡

ወያኔ ሊያበቃለት መሆኑ ባልከፋ እኛም አብሮ የሚያበቃልን መሆኑ ነው እንጅ ችግሩ፡፡ ይህ የዚህ እብድና ደደብ ሰውየ ቃለ ምልልስን ከእስከዛሬው የተለየ የሚያደርገው “ነጻ ሉዓላዊ ሀገር ነው ያለን!” የሚለውን አቶ ኢሳይያስን የሉዓላዊ ሀገርን ሉዓላዊነት በመዳፈር በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለታላቅ ትዝብት በሚዳርግ መልኩ “…. ከዚህ በኋላ ወያኔ በኢትዮጵያ ምድር ላይ መንግሥት አይደለም! ፣ አዝለን እንዳመጣነው አንቀልባውን ቆርጠን እንወረውረዋለን!….” በማለት የሰሞኑ ሩጫቸው ዓላማና ግብ ወረራ አድርጎ ወያኔን እስከማስወገድ ድረስ የሚዘልቅ እንደሆነ ይፋ ማድረጉ ነው፡፡

እርግጥ ነው ሸአብያም ሆነ አብረውት የተሰለፉት ዓረቦች የሀገራችንን ድንበር ሰብረው በመግባት ሀገራችንን የመውረር መብት የላቸውም፡፡ የመንግሥታቱ ድርጅትም ይሄ ሲሆን ዝም ሊል እንደማይችል መርሑ እና ሕጉ በግልጽ ያስቀምጣል፡፡ ይሁን እንጅ ችግሩ ይሄኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (united nations) እና አስቀድሞ የነበረው የመንግሥታቱ ማኅበር (league of nations) ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ኢትዮጵያን በተመለከቱ አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ የአድልኦ፣ የዳተኝነት፣ የኢፍትሐዊነት ዝጋብ (record) ያላቸው ከመሆናቸውም ባሻገር ሸአቢያም ሆነ ዓረቦች ሲወሩን ሸአቢያ በሸአቢያነቱና ዓረቦችም በዓረብነታቸው የሚወሩን አለመሆናቸው ነው፡፡ ሸአቢያና ዓረቦቹ ሲወሩን የሚወሩን በዴምሒት (ትሕዴን) ፣ በግንቦት 7፣ በኦነግ እና በሌሎች መቀመጫቸውን ኤርትራ (ባሕረ ምድር) ባደረጉ ተቃዋሚ ኃይሎች ስም ሽፋን የሚወሩን መሆኑ ነው ችግሩ፡፡ ስለሆነው ወረራው የሸአቢያና የዓረቦች ሳይሆን የዴምሒት (ትሕዴን) ፣ የግንቦት 7፣ የኦነግ እና የሌሎች ተቃዋሚ ኃይሎች ፀረ ወያኔ ትግል የድል ግስጋሴ እንደሆነ ተቆጥሮ ነው ሸአቢያና ዓረቦች ሰተት ብለው የሚገቡትና ሀገራችንን የሚቆጣጠሯት ሊያደርጉ የሚፈልጉትን ሁሉ ጥፋትና እልቂትም ያለከልካይ የሚፈጽሙት፡፡

ደንቆሮው አህያው ወያኔ የኢሳይያስ መሯሯጥ፣ የዓረቦቹ መመሳጠር ስላላማረው መሰንበቻውን ሸአቢያን ለማባበል ያላደረገው ጥረት አልነበረም፡፡ ባድመን ጨምሮ ሌላ ሸአቢያ የሚፈልገው ነገር ካለም እሱን ጨምሮ ለመስጠት ዝግጁ እንደሆነ በመግለጽ ሸአቢያን ለማባበል በጣም ጥሮ ነበረ፡፡ ሸአቢያ ግን ከወያኔ እጅ ከሚያገኘው ጥቅም ይልቅ “ወያኔን አጥፍቸ አገኘዋለሁ!” ብሎ የሚያስበው አስጎምጅ ጥቅም ስለበለጠበት ለወያኔ ማባበያ ጨርሶ ጆሮ ሳይሰጠው አልፎ ሥራውን ሲሠራ ሰንብቶ ግብጽን ጨምሮ ዓረቦችን ከጎኑ በማሰለፍ ዝግጅቱን ሊያጠናቅቅ ችሏል፡፡

ወያኔ ደንቆሮና አህያ በመሆኑ አያስብም እንጅ እንደዚህ ወቅት ማድረግ ያለበትን ሁሉ በማድረግ የኢትዮጵያን ሕዝብ በአንድነት እንዲቆም ማድረግ የሚያስፈልግበት ወቅት አልነበረም፡፡ እሱ ግን ደንቆሮና አህያ በመሆኑ እንዲህ ዓይነት ግዙፍ አደጋ ከፊታችን ተጋርጦ እያለ የኢትዮጵያ ሕዝብ የተጋረጠበትን አደጋ መከላከል እንዲችል በአንድነት እንዲቆም ማዘጋጀት ሲኖርበት ከዚህ ይልቅ በዘር እየከፋፈለ ሶማሌን ከኦሮሞ፣ አፋርን ከአማራ፣ ጉምዝን ከአማራ፤ ሶማሌን ከአፋር፣ ትግሬን ከአማራ፣ ኦሮሞን ከደቡብ፣ ኦሮሞን ከአማራ ወዘተረፈ. በማባላት፣ በማጋጨት፣ በማፋጀት ሸፍጥና ሴራ ምን ያህል ተጠምዶ እንደባጀ፣ እንደከረመና እንደሰነበተ የምታውቁት ነገር ነው፡፡

በዚህ ላይ ሕዝቡ በወያኔ አረመኔያዊ ግፍ ቁምስቅሉን ሲያይ የከረመ፣ ፍዳውን ሲበላ የኖረ በመሆኑ በዴምሒት (ትሕዴን) ፣ በግንቦት 7፣ በኦነግ እና በሌሎች ተቃዋሚ ኃይሎች የፀረ ወያኔ የነጻነት ፍልሚያ ስም የሚመጣውን የሸአቢያንና የዓረቦችን ወረራ “ጎሽ!” ብሎ በደስታ ይቀበለዋል እንጅ “የሸአቢያና የዓረቦች ወረራ ነው!” ብሎ ሀገሩን ለመከላከል ከወያኔ ጎን ተሰልፎ ወረራውን ለመከላከል ይነሣል የሚል ግምት አለመኖሩ ነው፡፡

እርግጥ ነው ወያኔ ይህ ወረራ በሚቃጣበት ወቅት የባጡን የቆጡን እየቀበጣጠረ እየማለና እየተገዘተ ሕዝቡን ከጎኑ ለማሰለፍ መጣሩ አይቀርም፡፡ ይሁን እንጅ የዛሬ ሃያ ዓመታት የሸአቢያ ወረራ በተቃጣብን ወቅት ወያኔ እየማለና እየተገዘተ “የደርግ ሠራዊት ነው!” ብሎ የበተነውን የቀድሞ ሠራዊት አባላትንና ሕዝቡን ከጎኑ አሰልፎ ድል ከተቀዳጀ በኋላ ድሉ የራሱ ብቻ እንደሆነ ምን እያለ እንደደነፋ፣ ለድል ባበቁት በቀድሞ ጦር አባላት ላይ ምን ዓይነት ግፍ እንደፈጸመ ሕዝቡ ጠንቅቆ የሚያውቅ በመሆኑ ወያኔ አሁንም ችግር ሲገጥመው ዓይኑን በጨው አጥቦ የባጡን የቆጡን እየቀበጣጠረ እየማለና እየተገዘተ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከጎኑ ለማሰለፍ ቢጥር ሕዝቡ “ሞኝህን ፈልግ! ስንቴ እንጃጃልልሀለን?” ይላል እንጅ የሚሰማው ይኖራል ወይ? የሚለው ነገር እጅግ አጠራጣሪ ይመስለኛል፡፡ በመሆኑም ውጤቱ መልካም የሚሆን አይመስለኝም፡፡
ሕዝቡ በሸአቢያ እየተወረረ እንደሆነ ቢያውቅም እንኳ “አሁንም በወያኔ እጅ ሰቆቃና ግፍ እየተፈጸመብኝ እየሞትኩ ነው ሸአቢያም ቢመጣ መሞት ነው ለኛ ለውጥ የለውም፡፡ መሞታችን ካልቀረ ወያኔን ባለመተባበር በወያኔ እጅ አይቀርልኝ የነበረውን ሞት ከወያኔ ጋር በሸአቢያ እሞታለሁ እንጅ ወያኔን ለማትረፍ፣ ለመታደግ፣ ገዳየን ወያኔን ለማዳን ስል አልሞትም!” የሚል ይመስለኛል፡፡ ደንቆሮው ወያኔ ግን በሕዝቡ ላይ ባደረሰው ግፍና ሰቆቃ ምክንያት ሕዝቡ የዚህን ያህል ሆድ እንደባሰውና ብቻውን ቆሞ እንዳለ እንኳ አይገነዘብም አይገባውምም፡፡

ወያኔ ይሄ ያልኩት ሁሉ በሀገር በሕዝብና በራሱም እንዳይደርስ ከፈለገና ኃላፊነትም የሚሰማው ከሆነ ፈጥኖ ሊያደርግ የሚገባውን አራት ነጥቦች መጠቆም እወዳለሁ፦

1. ወያኔ በሀገርና በሕዝብ ላይ የፈጸማቸውን ኢሰብአዊ ግፎች፣ የሀገር ክህደቶች፣ ሀገር ያራቆተ ሙስናው ጉዳይ በኋላ የምንተሳሰባቸው ጉዳዮች ሆነው ለጊዜው ግን ይሄንን ጊዜ የማይሰጥ አደጋ ለመከላከል ሲባል የግድ በአንድነት መቆም ስላለብን ሀገሪቱን ከሕዝቡ ነጥቆ የብቻው ካደረገበት ባለቤትነቷን መልሶ ለሕዝቡ በመስጠት ገዳቢ፣ አግላይ፣ አሳሪ ሕጎቹን በሙሉ መሻር፣ የትግራይን ግዛት ለማስፋት ዓይን ባወጣ ውንብድና ወደትግራይ የከለላቸውን የጎንደርና የወሎ ስፍራዎች መመለስ፣ በኢፍትሐዊነት ጠቅልሎ የያዘውን ሥልጣን በፍትሐዊነት ለሚገባቸው ማስተላለፍና ተመሳሳይ እርምጃዎችን መውሰድ፡፡

2. ወያኔ በመላ ሀገሪቱ ለቁጥር በሚያታክቱ እስር ቤቶቹ ለነጻነታቸው በመታገላቸው፣ ሰብአዊ መብታቸውን በመጠየቃቸው፣ የዜግነት ግዴታቸውን ለመወጣት በመጣራቸው ወንጀለኛ እያደረገ ወኅኒ የወረወራቸው ዜጎች በሙሉ ሀገሪቱ ያሏት ጀግና ጀግና፣ ቆራጥ፣ ወንድ፣ ቆፍጣና ዜጎች እነዚሁ በመሆናቸው እነኝህን ወኔ ያላቸው፣ ኃላፊነትና የዜግነት ግዴታ የሚሰማው ዜጎች መታሰራቸው አግባብ ካለመሆኑ ባሻገር ከፊታችን የተደቀነውን ወረራ ለመከላከልና ለመመከት የእነኝህ ጀግኖች ቆራጦች ቀጥተኛም ይሁን ተዘዋዋሪ ተሳትፎ እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ አንድ እንኳ ሳያስቀር መፍታት፡፡

3. ከአማራ ሕዝብ ትጥቅ ያስፈታቸውን ትጥቃቸውን መልሶ መስጠት፣ ትጥቅ ለሌላቸው በነፍስ ወከፍ ማስታጠቅ፡፡

4. የፖለቲካ ምኅዳሩን ታማኝነትንና ተጨባጭነትን በሚያሳይ መልኩ ክፍት ነጻና ፍትሐዊ በማድረግ ኤርትራ (ባሕረ ምድር) በትጥቅ ትግል ያሉ ወገኖችን ጨምሮ ለሁሉም የተቃውሞ ኃይሎች ይፋዊ የሰላም ጥሪ ማቅረብ የሚሉት ናቸው፡፡ ወያኔ እነኝህን እርምጃዎች በመውሰድ የኢትዮጵያን ሕዝብ አሳምኖ ከጎኑ ማሰለፍ ይጠበቅበታል፡፡ ወያኔ መለወጥና መንቃት ተስኖት እነኝህን ለውጦችና እርምጃዎች መውሰድ ካልቻለ ግን ያው በሸአቢያና በዓረብ ሰይፍ እየተቀላን ተያይዘን ገደል መግባታችን ነው፡፡

ሕዝባዊው ዐመፅ እስከአሁን ለፍሬ በቅቶ ማለት ወያኔን ማስወገድ ችሎ ቢሆን ኖሮ ሸአቢያና ዓረብ የመውረሪያ ምክንያት ባላገኙ ነበረ፡፡ ለመውረር ቢፈልጉም እንኳ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከወታደሩ እስከ ሕዝቡ እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆኖ ጥቃቱን በሚገባ መመከት በቻለ ነበረ፡፡ አሁን ግን እንደምታዩት ወያኔን የሚወስድ አንዳች መዓት እንዲወርድ እየጸለየ ባለበት ሁኔታ ይሄ ወረራ ቢቃጣ የጸሎቱ ምላሽ እንደሆነ ያስባል እንጅ ጥቃቱ ለሱም እንደማይበጅ አያስብም፡፡ ቢያስብም ወያኔን እስካጠፋልኝ ድረስ ይሁን ነው የሚለው፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ ሕዝብ ምኞትና እውነታው ተላልፈዋል፡፡ ምን ጥረት ብናደርግ በቀረው ጊዜ ወያኔን አስወግደን አንድነታችንንና ትስስራችንን አድሰን በሙሉ የሀገር ፍቅር ስሜት፣ የኃላፊነት ስሜትና የዜግነት ግዴታን የመወጣት ወኔ ሀገራችንንና ራሳችንን ለመጠበቅ የምንደርስ አይመስለኝም፡፡

በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን አንድ ከጥንት ጀምሮ ሲነገር የኖረ ትንቢት አለ፡፡ ዓረብ ሀገራችንን ለ3 ዓመታት ወሮ የሚይዛትና ሕዝቡንም የሚፈጅ መሆኑን የሚናገር ትንቢት ነው፡፡ በነገራችን ላይ ይሄ ትንቢት በእስልምና ተከታይ ወገኖቻችን በኩልም ያለ ትንቢት ነው፡፡ ዓረቦቹ እነሱንም የማይምሩ መሆናቸውን የእነሱም ትንቢት ይናገራል፡፡ ትንቢቱ ሊፈጸም የሚችል መሆኑን ባምንም ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን በማሰብ በዚህ ዘመን ተፈጻሚ ሊሆን የሚችልበት መንገድ አልታይህ ብሎኝ ቆይቶ ነበር፡፡

የሸአቢያና የዓረቦች ጦር እስከማስፈር ድረስ የደረሰ የተጠናከረና የጠበቀ ግንኙነት ወይም ወዳጅነት መፈጠሩን ሳይ ግን ይሄ ትንቢት ተፈጻሚ ለመሆን መንገዱን እየጠረገ መሆኑና መምጫውም ይሄው መሆኑ ገባኝ፡፡ ይሄንን ስላቹህ ትንቢቱ ትንቢት ነውና ወደድንም ጠላንም መፈጸሙ አይቀርም እያልኳቹህ አይደለም፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ትንቢት ከተነገረባቸው በኋላ ትንቢቱ የተነገረባቸው አካላት እግዚአብሔር በይቅርታው በምሕረቱ እንዲጎበኛቸው በጾም፣ በጸሎት፣ በሥግደት፣ በምሕላ በመማጸናቸው በትንቢት የተነገረባቸው መዓት፣ ቁጣና መቅሰፍት ሊቀርላቸው መቻሉን ይነግረናል፡፡ ንጉሥ ሕዝቅያስ ኢሳ. 38፤1-8, የነነዌ ሰዎች ዮናስ ም.1-4, አይሁዶች አስ. ም. 1-11

እርግጥ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይሄ ትንቢት ተፈጻሚ እንዳይሆንብን በማለት እግዚአብሔርን በጾም፣ በጸሎት፣ በስግደት፣ በምሕላ አልተማፀነም፡፡ ሕዝቡ በጾም፣ ጸሎት፣ ስግደት ባይማፀንም ይሄ ትንቢት ከተሰማ ጊዜ ጀምሮ ገዳማውያኑ መናንያኑ በብርቱ ጾም፣ ጸሎት፣ ስግደትና ምሕላ ሲማፀኑ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡ እንግዲህ የገዳማውያኑ የመናንያኑ በቂ ሆኖ ካልተገኘ ወረራውና ተያይዞ ያለው ፍዳ የማይቀርልን ይሆናል፡፡

እንግዲህ ለሁሉም ወያኔ ካነሣኋቸው ነጥቦች አኳያ ለጉዳዩ በሚሰጠው ምላሽ ወይም ለዚህ ነገር በሚኖረው አያያዝ የምትረዱት ይመስለኛል፡፡ ወያኔ ከላይ የጠቀስኳቸውን አራት እርምጃዎች የሚወስድና በአንድነት የሚያስተባብረን ከሆነ እግዚአብሔር ምሕረት አውርዶ ነገሩን እንደነነዌ ሰዎች የትንቢቱን ምልክት ብቻ አሳይቶ ሊመልስልን እንደፈለገ እንደ ምልክት ልትወስዱት ትችላላቹህ፡፡ ወያኔ የዘረዘርኳቸውን እርምጃዎች መውሰድ የማይፈልግና በአንድነት መቆም መሰለፍ የማንችል ከሆነ ግን ትንቢቱ ሊፈጸምብን መሆኑን በምልክትነት ልትወስዱት ትችላላቹህ! እስኪ መድኃኔዓለም ክርስቶስ የቸርነቱን ሥራ ይሥራልን! አሜን!!!

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
amsalugkidan@gmail.com

Filed in: Amharic