>

ሳልሳዊ ቴዎድሮስ ንጉሰ ነገሥት ዘኢትዮጵያ (ቬሮኒካ መላኩ)

ጥር ፲፫ በባህር ዳር ፈለገ ግዮን በአስራት ወልደየስ ስታዲየም(ስታዲየሙ በፕሮፌሰር አስራት ስም ብንጠራው መልካም ነው ) በዳግማዊ ቴዎድሮስ ሁለት መቶኛ አመት የልደት በአል ላይ ቴዲ አፍሮ ሳልሳዊ ቴዎድሮስ ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮጵያ ተብሎ በአንድ መቶ ሺህ ህዝብ ፊት ይነግሳል። የአማራ ህዝብ አዳኝ መሲህ ይመጣል ይወለዳል ኢትዮጵያን በፍቅር አንድ ያደርጋል እየተባለ ለዘመናት ትንቢት የተነገረለት ቴዎድሮስ የተባለው ንጉስ እነሆ መጥቷል። አንቺ የባህር ዳር ምድር ሆይ ምንኛ ታድለሻል። ቴዎድሮስን ልታነግሽ በኢትዮጵያው ካሉ ከተሞች ሁሉ አንቺ ተመርጠሻል። አይሁዶች ክርስቶስ የተባለ አዳኝ ከዳዊት ወገን እንደሚወለድ ተነግሯቸው በተስፋ ይጠባበቁ ነበር። እነሱ ይጠብቁ  የነበረው ጦር ሰራዊት አሰልፍ የሚመጣ ጦረኛ ነበር። የዛሬ ሁለት ሺህ አመት ገደማ ኢየሱስ በአህያ ውርንጭላ ሁኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ ጥቂት ህፃናት እና የከተማይቱ ነዋሪዎች ብቻ ነበሩ ሆሳእና በአርያም በዳዊት ስም የምትመጣ የአባታችን መንግስት የተባረከች ናት እያሉ አቀባበል ያደረጉለት። እነሆ ዛሬ ለሺህ ዘመናት ሲነገርለት እና ትንቢት ሲተነበይለት የነበረው የኢትዮጵያን ህዝብ በፍቅር አንድ አድርጎ የሚገዛው ቴዎድሮስ የተባለው ንጉስ መጥቷል። እኛም በአማራ እምብርት በፈለገ ግዮን ንጉስ ቴዎድሮስ ልንል ተዘጋጅተናል። በዳግማዊ ቴዎድሮስ ሁለት መቶኛ የልደት በአል ላይ ሳልሳዊ ቴዎድሮስ ንጉስ ሁኖ በኢትዮጵያውያን ልብ ላይ ይነግሳል። መይሳው ካሳ በቴዲ አፍሮ ካሳ ካሳ የቋራው አንበሳ ሙዚቃ መቃብሩን ፈነቃቅሎ ይነሳል። የአባ ታጠቅ ኢትዮጵያን አንድ የማድረግ ህልም በአባ ኮስትር ሀገር ባህር ዳር ላይ በሳልሳዊ ቴዎድሮስ ይዘመራል። ቴዎድሮስን ለማንገስ ኢትዮጵያውያን ከመላ ሀገሪቱ ወደ ጎንደር እና ባህር ዳር እየተመሙ ነው። ከውጭ ሀገራትም ብዛት ያለው ህዝብ ጥምቀትን ጎንደር ላይ አክብሮ ባህር ዳር ላይ ሳልሳዊ ቴዎድሮስን ለማንገስ ወደ ኢትዮጰያ እየገባ ነው። ደጆች ይከፈቱ! ንጉሱ ይግባ። እግሮች ሁሉ ወደ ባህር ዳር አስራት ወልደየስ ስታዲየም ያመራሉ።

Filed in: Amharic