>

መያዧ መጨበጫ ጠፍቶባቸዋል! (ጌታቸው ሽፈራው)

~ ለብሔራዊ መግባባት ሲባል የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ ስምምነት ላይ ተደርሷል ተባል!

~ ትንሽ ቆይተው ስምንት ጊዜ ደልዘው አንድንድ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትንና ሌሎች ግለሰቦችን እንፈታለን አሉ!

~ ይህም ቆጫቸው፣ ሽንፈት መሰላቸውና የፖለቲካ እስረኛ የለም አሉ!

~ቆይተውም ተጠቃሚ የነበረ፣ ተገፋፍቶ ወንጀል የፈፀመ፣ ሕገ መንግስቱን ያልናደ ብለው ቀባጠሩ፣

~ ካጎሩት ሁሉ እስረኛ 115 እንፈታለን አሉ። ከእነዚህ መካከል ወደ እስር ቤት የሚመልሱት እንዳለ ታወቀ!

~ የህዝብን ቀልብ ይስብላቸው ዘንድ የእነ ዶክተር መረራን ስም ጠቅሰው በሁለት ቀን ውስጥ እንደሚፈቷቸው በዜና ለፈለፉ!

~ ዜናውን ሰምተን ሳንጨርስ እነ ዶክተር መረራን ለመፍታትም ሁለት ወር ጠብቁ እያሉ ነው። ለብሔራዊ መግባባት እንፈታቸዋለን ያሉትን አሁን ደግሞ የይቅርታ ኮሚቴ ይመረምረዋል ማለታቸው እየተነገረ ነው!

~ቢጨንቃቸው እስር ቤት ውስጥ ተኩሰው የገደሏቸውን እነ አብዲሳ ቦካን ከተፈች ዝርዝር ውስጥ አጠቃለሉ! ሟቾችን በምህረት ፈታን ሊሉን!

~ ትንሽ ቆይተው “እስረኛ የለም” ሊሉም ይችላሉ። አይ ኤስ ያረዳቸውን ወንድሞቻችን “ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን አላረጋገጥንም” እንዳሉት “እስረኛ መኖሩን አላረጋገጥንም፣ እናጣራ” ሊሉንም ይችላሉ።

~ የሚይዙትን የሚጨብጡትን በማጣታቸው፣ ባለመስማማታቸው ነው። አንድ እስረኛ ሲፈታ ስልጣናቸው ላይ የሚያመጣውን በማሰብ ነው። በዚህ ሁሉ መቀባጠር ኃይል እንደከዳቸው አላወቁም፣ አሊያም ማወቅ አልፈለጉም።

~ ይህ ሁሉ ያዙኝ ልቀቁኝ እስረኞች ያለውድ በግድ የሚፈቱበት ቀን ሩቅ አለመሆኑን በግልፅ የሚያሳይ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ለአሳሪዎቹ ይቅርታ ያደርጋል ወይ በሚለው ላይ ግን እርግጠኛ መሆን አይቻልም።

Filed in: Amharic