>

 ኦሮሞና አማራ እንደዚህም ነበሩ!! (አፈንዲ ሙተቂ)

ዘንድሮ “አማራና ኦሮሞ ተቀራርበዋል” የሚል አነጋገር ሲደጋገም እሰማለሁ። ይገርማል! በፊት ተራርቀው ነበር እንዴ? ምን ያህል ነው የተራራቁት?

“የፖለቲካ ኤሊት ነን” የሚል ሹመት ለራሳቸው ሰጥተው ራሳቸውን የኮፈሱ ወገኖች እንደዚህ ብለው ሊያስወሩ ይችላሉ። ነገር ግን የነሱን ትርክት መሬት ላይ ያለ ሐቅ አድርጎ መደምደም ለስህተት ይዳርጋል። መንግስታት ቢለዋወጡም፣ የፖለቲካው የጡዘት ደረጃ ቢቀያየርም፣ የፕሮፓጋንዳው ጩኸት እየወጣ ቢወርድም ህዝቦቹ አልተቀያየሙም።

እርግጥ ለሁለቱ ህዝቦች መብት እንታገላለን የሚሉ የዘመናችን ፖለቲከኞች ተቀራርቦ በመስራቱ ላይ ችግሮች ነበሩባቸው። ዘንድሮ ግን ሁኔታው ተለውጦ ከመገፋፋት ወደ መተባበር እየተሸጋገሩ ነው። በቀድሞ ዘመናት ግን ከዚህ ላቅ ያለ ክስተትም ተፈጥሮአል። ለምሳሌ አማራ ሆነው ለኦሮሞ መብት የታገሉ አንበሶችን በዐይናችን አይተናል። በዚያድ በሬ ወረራ ዘመን ደግሞ አማሮች በሶማሊያ ወታደሮች ሲጋዙ የቆሬ ከተማ ነዋሪ የነበሩ ኦሮሞዎች “እኛን ነጥላችሁ እነርሱን ማጋዝ አትችሉም፣ እህል ውሃችን አንድ ላይ ነው። ስለዚህ እኛንም ጨምራችሁ እሰሩን” በማለት ተቃውሞ በማሰማታቸው ወደ ሶማሊያው መንዴራ እስር ቤት ተወስደው ከአማራዎቹ ጋር ለአስራ አንድ ዓመታት ታስረዋል።

ስለዚህ ጉዳይ ስጽፍ በቅድሚያ ትዝ የሚለኝ አብሬው ያደግኩት የሀረርጌው አማራ ነው። እስቲ ለዛሬም እዚያ የተፈጠረውን አንድ ታሪክ እናውጋችሁ።
——-
በታህሳስ ወር 1984 ነው። የደርግ መንግስት ከወደቀ ስድስት ወር ያህል ሆኖታል። የምስራቁ የኦሮሞ ህዝብ ከመቶ አመት በኋላ የመጀመሪያ የሆነውንና ኦዳ ቡልቱም በሚባለው ጥንታዊ ማዕከል የሚከናወነውን የገዳ ጉባኤ ለመመልከት ከየአቅጣጫው ወደ ስፍራው ይጎርፋል። ለበዓሉ የመጣው ህዝብ እጅግ ብዙ በመሆኑ የትራንስፖርት እጥረት ነበር። በመሆኑም ሁሉም እንደየአካባቢው እየተቧደነ በእግሩ ወደ ስፍራው ይሄድ ነበር። በተጨማሪም ህዝቡ በወቅቱ የነበሩትን ቀስቃሽ ዜማዎች ያዜም ነበር።

እኔ በነበርኩበት ቡድን ውስጥ ሀምሳ ያህል ሰዎች የነበሩ ሲሆን ሁሉም የገለምሶ ተወላጆች ናቸው። አንድ ጠና ያለ ጎልማሳ ግን የአካባቢያችን ሰው አልነበረም። ታዲያ የቡድናችንን መዝሙር የሚመራው ይኸው አዲስ ሰውዬ ነው። ሰውዬው ባማረ ድምፅ እንዲህ እያለ ይዘምርልን ነበር።

Waan cunqursaa oofaa gaa
Bilisummaa rooba gaa
Bilisummaa

ትርጉሙ

ጭቆናን የሚያባርረው
ነፃነት እኮ ነው የዘነበው።
—–
በበኩሌ መዝሙሩን ከዚያ ቀን በፊት ሰምቼው አላውቅም። በእድሜ ጠና ያሉ ሰዎች ሲሰሙት ግን በስሜት እንደ ማበድ ያደርጋቸው ነበር። በሌላ ቡድን ውስጥ የነበሩ ሰዎችም እየሮጡ የኛን ቡድን መቀላቀል ጀመሩ። ነገሩ ግራ ገባኝ። ከሰውዬው ነው ወይስ ከመዝሙሩ? ከሰውዬው ከሆነ እርሱ ማን ነው? “ጠይቄ መረዳት አለብኝ” አልኩ ለራሴ።

ኢብራሂም ሳኒ የሚባለውን ዘመዴን “ይህ ሰው ማን ነው?” ብዬ ጠየቅኩት።

“ሚሊዮን አበበ ቁንኑ ነዋ! አታውቀውም እንዴ? የድሮ አብሮ አደጋችን ነው። አሁን የሚኖረው ቦኬ ከተማ ነው”
“አበበ ቁንኑ የገለምሶው? እሳቸው አማራ አይደሉም እንዴ?”
“ቢሆኑስ! ሚሊዮን ከኛ ጋር ስለኦሮሞ ነፃነት መዘመር አይችልም እንዴ!”
“ማለት ነገሩ ገርሞኝ ነው”
“ወዳጄ እንዲያውም ልንገርህ!! ሚሊዮን ይህንን ዜማ ያዜመው በ1970 በተከበረው የሀብሮ አውራጃ ባዛር ላይ ነው። በዚያ ሳቢያም በደርግ መንግስት ታስሮበታል፣ ተገርፎበታል። ከዚያ ወዲህም በሚስጢር በሚደረጉት የኦሮሞ ህዝብ የመብትና የነፃነት እንቅስቃሴዎች ተሳታፊ ነበር”

በአድናቆት ፍዝዝ ብዬ ቀረሁ። ብዙ ጎልማሶች ከነበሩበት ቡድን እየኮበለሉ የኛን ቡድን የተቀላቀሉት ሚሊዮን ለኦሮሞ ህዝብ ባለው ፍቅርና በትግሉ ውስጥ በነበረው አስተዋፅኦ መነሻነት እንደሆነም ተረዳሁ።

Filed in: Amharic