>
6:14 am - Wednesday July 6, 2022

የአዲስ አበባ ሕዝብ ኀወሓት-ኢህአዴግን ወገቡ እስኪጎብጥ ድረስ ለምን ተሸከመው? (ዳንኤል ሺበሺ)

የአዲስ አበባ ሕዝብ ከትግሉ ለምን ይሸሻል ?

ከላይ የተነሳውን ጥያቄ የአ/አ ሕዝብ ለምን ዝም አለ? ወይም ኀወሓት-ኢህአዴግን ወገቡ እስኪጎብጥ ድረስ ለምን ተሸከመው? ብለን መጠየቅም ይቻላል፡፡

የፖለቲካ ትግል ምክንያቶቹ ብዙ ቢሆንም፤ መገለጫው መግፋትና መገፋት መኖር ነው፡፡ ጨቋኝና ተጨቋኝ መኖር ነው፡፡ የትግል ሥልቶቹም በግልጽና በሥውር፤ በቀጥታና በተዘዋዋሪ፤ ወይም በግልና በጋራ ሊሆን ይችላል፡፡ አሁን በአአ ሕዝብ ላይ እየተነሣ ያለው ጥያቄ በግልጽ በሚካሄደው ትግል ውስጥ ጎልተው አለመውጣታቸው ነው፡፡ በኦሮሚያና በአማራ (ወይም በክልሎች) እየተካሄደ ያለው አይነት ትግል፤ ወይም ራሱ የአአ ሕዝብ ም/97 ውጤትን ተከትሎ የተቀማውን ድምፁን ለማስመለስ ያካሄደው አይነት የአደባባይ ተቃውሞና ድጋፍ ዛሬ ላይ ማጣቱ ለምንነው የሚለው ለጥያቄው መንሥዔ ነው የሆነው፡፡
ታዲያ ለሕዝቡን የዝምታ ምክንያቶችን በርጋታ ብንፈትሽ በርግጠኝነት ሥርዓቱ ስለተመቸው አለመሆኑ የታመነ ነው፡፡ እንዲያው በ1997ቱ ምርጫ ወቅት የአአ ሕዝብ ኢህአዴግን ባለመምረጡ ምክንያት ቅም ይዞበት እስከዛሬ ድረስ በሁሉን አቀፍ (Holistic) መንገድ ሥልት ነድፈው እየተበቀሉ ይገኛሉ፡፡ የችጋርንና የሥቃይን ግድብ ሰብረውት የመከራ ጎርፍ በመልቀቅ እያበጠሩት እንደሆነ ለማስረዳት መሞከር እንዲያው ጊዜ ማጥፋት ነው የሚሆነው፡፡

ታዲያ ለምን ዝም አለ? ሕዝቢ አዲስ፡፡
እኔ ወደ 12-መላምቶቼን ጠቆም አድርግያለሁና እናንተም ይህ ቀረ የሚትሉትን አክሉበት ፡፡

1ኛ/ ለአአ ሕዝብ ብሄርም በሉት ብሄረሰብና ጎሣ ቦታ ማጣት፦
አዲስ አበባ ልዩ ልዩ ማኀበረሰብ፣ ኀብረተሰብ እና የብሔረሰብ ስብጥር ያለባት ከተማ ናት፡፡ የኢህአዴግን የመረጃና የስታትስቲክስ ታአማኝነት ቁልፍ ችግር መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ከአጠቃላይ ከተማዋ ነዋሪዎች ውስጥ ሲጠጋጋ አማራውን 56፤ ኦሮሞውን 19፤ ጉራጌውን 16፤ ትግሬውን 5፤ ጋሞ 2፤ ስልጤውን ወደ 3 እጅ አድርገው አስቀምጠውታል፡፡ ይህ ሁኔታ ሲታይ፤ ሁሉም በሕግና በፍቅር ተሳስበውና ተቻችለው ከመኖር ውጭ በአአ ላይ ማንም የባለቤትነት ጥያቄ ማንሳት አይችልም፡፡
ከዚህ የተነሣ አሁን በየክልሎቹ የሚደረገው አይነት ብሄረሰብ-ተኮር መሠረት ያለው ትግል ለሸገሩ ሕዝብ አይመቸውም፡፡ ከዚህ የተነሣ ይህ በአአ ከተማ ውስጥ እንደፈንድሻ የተበተነው ኀብረተሰብ ክፍል አንዱ ሌላው የመጠባበቅና እንቅስቃሴዎቹን ሁሉ በአዎንታዊነትና በአሉታዊነት የማዳመጥ አዝማሚያም አለው፡፡ ከዚህ በዘለለ ከሶማሌ ክልል ኦሮሞዎች ይውጡ! ከኦሮሚያ ክልል አማራው ወይም ወላይታው፤ ከሲዳማ ወላይታው ወዘተ አንዱ ሌላውን ይውጣ/ይግባ እንዲባል በሥርዓቱ ሰዎች እንደሚሸረበው አይነት አዝማሚያ ለአዲሳባዎቹ ከባድም መራራም ነው፡፡ የዚህ አይነት ዝቅ ያለ ሀሳብ በአአ ከተማ ማራመድ ማንም ሊፈታው የማይችለውን መዘዝ ያመጣል፡፡ በአአ የኔ ብሄር ተጠቃ፣ የእከለ ልዩ ጥቅም፤ የእነርሱ ዋና ዋና ጥቅም ወዘተ ተሸራረፈ ብለህ ለድል መብቃት ይቅርና ስለ ድል ማሰብ እንኳን ቦታ አይኖረውም፡፡ የአንዱ ጥያቄ ሁሉንም ስለሚነካ በከተማዋ ውስጥ አጠቃላይ ቀውስ Crisis ወዲያው ከች ማለቱ ፈጦ የሚታይ ሃቅ ነው፡፡ ለዚህ ነው፤ እዚህ በአፍንጫው ሥር ወገን እየረገፈ የአአ ሕዝብ ዝምታን የመረጠው፡፡ ለዚህ ነው እነ መድረክ የመሳሰሉ ፓርቲዎች ስብስብ በቆሙበት የቀሩት፡፡

2ኛ/ የመሪ እጦት ፦ ከአፄ ምኒሊክ ወዲህ ኢት/ያ ሁነኛ መሪ ያገኝችበትን ዘመን ለማወቅ ሁለቴ ማሰብን ይጠይቃል፡፡ ኢትዮጵያ በርሃብ ብቻም ሳይሆን በመሪ ርሃብም የተመታች ሀገር ናት፡፡ የምገርመው ሁለቱም ርሃብ መንሥዔው ሰው ሰራሽ መሆናቸው ነው፡፡ … ለአአ ሕዝብ ብሄሩም ዜግነቱም ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነቱ ነው፡፡ ታዲያ ለትግሉ ጭቆና መኖሩ አንድ የሚያደርገን ከሆነ ጭቆናን ለማጥፋት በኢትዮጵያዊነት አጀንዳ ተደራጅተው ለምን አይታገልም? ከተባለ ደሞ ለአአ ሕዝብ ከልኩ ላቅ፤ ከዘመኑ እልፍ ያለ፤ አሊያም የሚመጥን መሪ (እንደ ግለሰብም፣ እንደ ተቋምም) ይፈልጋል፡፡ በተበታተነ ትግል የአአ ሕዝብ አንድ አይሆንም፡፡ በተለይ ከምርጫ-97 ወዲህ ለአዲስ አባባም ሆነ ለመላው ኢትዮጵያ የተሻለ የመሪነት ሚና ለመጫወት አንድነትና ሰማያዊ ፓርቲዎች በአአ ከተማ የተሻለ ሕዝባዊ መሠረት መጣላቸው አይካድም፡፡ በተለይ የአንድነትን ሕጋዊነት የቅንጅት ዕጣ የመግጠሙ መንሥዔው ደግሞ ወደ መሪነት ክበብ ውስጥ መግባቱ ነበር፡፡ ቅንጅትም ቢሆን በጠመንጃ ኃይልና በተቀሩ ብዙ ምክንያቶች ይክሸፍ እንጂ ሲጨመቅ የተሻለ ስብጥር ይዞ መምጣቱ ወዲያው ተቀባይነት አግኝቶ ለድል እንዲበቃ ረድቶታል፡፡ አውራ ዶሮ ከጫጩቶቹ ውስጥ ወንድ ጫጩቶችን እየለየ አነጣጥሮ አናት አናቱን እየቀጠቀጠ እንደሚገል ሁሉ፤ የሀገራችን የፖለቲካ አውራዎችም ጫጩቶቻቸው አድገው መሪ እንዳይሆኑ አውራው ወዲያ አናት አናቱን በኮኩ እያፈረሰ አምክኗል፡፡ ያም ሆነ ይህ ሕዝቡ ዛሬም ከብሄር ወሰነ-ልክ ያለፈ አሰላለፍና አስተሳሰብ ይዞ የሚመጣ መሪ እየጠበቀ ያለ ይመስለኛል፡፡

3ኛ/ የ97ቱ ሀንጎበር፦ የ1997ቱን ምርጫ ተከትሎ የአአ ሕዝብ ዘግናኝ ዋጋ መክፈሉ አይዘነጋም፡፡ ጦላይ፣ ብርሸለቆ፣ ሸዋሮቢት፣ ብላቴ፣ ዝዋይ፣ ቃሊቲ፣ በየክልሉ ወዳሉ እሥር ቤቶች ወዘተ መጋዙን መመስከር ከተፈለገ ይህ ትውልድ ሕያው ምስክር ነው፡፡ በአገዛዙ ኢኮኖሚ ጠበብት ሆን ተብሎ በተፈበረከ ኑሮ ውድነት፣ መኖሪያ ቤት ፈረሳ፣ በሥራ አጥነት፣ በግብር ጫና፣ በመብራትና ውሃ እጥረት፣ በኢኮኖሚ ድቀት ወዘተ ዘግናኝ ዋጋ ከፍሏል፡፡
ከዚህ የተነሣ ለቅንጅት ይህን ያህል ተከፍሎ ምን አመጣልን? የሚሉ ብዙ የአአ ነዋሪዎች አሉ፡፡ የሚገርመው የተከፈለውም ሆነ እየተከፈለ ያለው ዋጋ ለሀገር መሆኑን አንዳንዶቹ ዘንግተውታል፡፡ ባጠቃላይ አገዛዙ ምርጫ-97 ተከትሎ የአአ ሕዝብ የተቀማውን ድምፅ ለማስመለስ ባደረገው ጥረቱ ምክንያት ዳግም እንዳያንስራራ አድርጎ መመታቱ ይታወቃል፡፡ ከዚህ ሀንጎበር ዛሬም ያልተላቀቀው ብዙ ነው፡፡ በተለያየ አጋጣሚዎች ሲጠየቁ እኛ በ1997 ይህንና ያንን ዋጋ ከፍለን ምን ለውጥ መጣ? መከራችን እጥፍ ድርብ ሆነብን እንጂ የምል ምላሽ የሚሰጡ ዛሬም በቁጥር በርከት ያሉ ናቸው፡፡ የወጣቱ የትግልና የለውጥ ስሜቱ ተሽመድምዷል፡፡ ሰው ሁሉ በሕይወት መኖርን እንደ ትልቅ ድል ቆጠረና የፍትህ/የነፃነት ጥያቄ ከአብዘኛው ነዋሪ ውስጥ ተቀብሮ ቀረ፡፡
4ኛ/ የነዋሪው የተመጣጠነ ሀብት፦ የአአ ነዋሪ የኑሮ ይዞታ አይተን እንደሆን ቅጥ ያጣ ቅንጦትና በከባድ ጉስቁልና ማዕቀፍ ውስጥ የሚጫወት ነው፡፡ በሀብታምና በድሃ መካከል ሊታረቁ የማይችሉ የሀብት ልዩነቶች ተፈጥሯል፡፡ ሃብታሙ የመዝነኛና የቅንጦት ኑሮው እንዳይጎልበት ሲጨነቅ፤ ድሃው በተቀራኒው በዕለት ጉሩሱ ላይ ተጠምዷል፤ ከእጅ ወደ አፍ የሆነውን ሕይወቱን ይገፋል፡፡ ቢያንስ በቀን አንድ ጊዜ ለመብላት፣ በቤት ኪራይ፣ በትራንስፖርት ችግር፣ የራስና የልጆቹ ትም/ት ቤት ወጪ ወዘተ እየተጨነቀ ነው፡፡ እንግዲህ (ከላይ በተ.ቁ 2 ላይ እንደተጠቀሰው) ከዚህ አይነት ጉድ ውስጥ የሚያወጣ መሪና አመራር ማግኘት ግድ ይለናል፡፡ እንደ ሙሴ ከነዓንን የሚያሳይ ብቻም ሳይሆን የሚያስወርስ መሪ፡፡

5ኛ/ የሥርዓቱ ጥብቅ ቁጥጥር ፦ እንደ እኔ ግምት ከ1997 ወዲህ ኀወሓቶች በተለይ በትግራይ እና በአዲስአበባ ከተማ ምንም አይነት ኮሽታ እንዳይኖር ልዩ ክትትልና ቁጥጥር እያደረጉ ነው፡፡ በደንነትና በሲሌላ መረብ ተብትበው ይዟዋታል፡፡ አአ ለፌዴራሉ መናገሻና ለአፍርካና በተለይ ለቀንዱ አከባቢ፣ የዓለም አቀፉ ኀያላን ማኀበረሰብ (በተለይም ለአውሮጳ እና ለአሜሪካ) ትኩረት ውስጥ ያለች ከተማ ሲትሆን፤ መቛሌ ደሞ የትውልድ መንደራቸው ናት፡፡ ማንም መሪ በትውልድ መንደሩ መጠላት፣ መሸነፍና ደጋፍ ማጣት አይፈለግም፡፡ በተለይ አከባቢያዊነት/ ብሄረተኝነት ስሜት ለሚሰባሰብና በጎሴኝነት ለተጠናወተው ኃይል ከአከባቢው ተቃውሞ እንዳይገጥመው ብርቱና ፈርጀ ብዙ ሥራ ይሰራል፡፡ እንደሚታወቀው ኀወሓት ከመንደርተኝነትም አልፎ የጎጠኞች ስብስብ መሆኑ አያከራከርም፡፡ ጎጠኛ እንደ ጉንዳን የጎሳው ጠረን እየተከተለና ጎጡን እየፈለገ እንደ መደበቂያ ዋሻ በመቁጠር ብዙ አደገኛና ክፉ ፖለቲካዊ እርምጃዎችን ይወስዳል፡፡ መሠረቱን በአጠቃላይ በሀገሪቱ ሕዝብ ላይ ሳይሆን የትውልድ መንደሩን ስለሚያደርግ ሥርዓቱን አላይም/ አልሰማም የሚል ጠንካራ ተቀዋሚ በተለይ ከትውልድ አከባቢው እንዳይፈጠር ለየት ያለ ክትትልና ቁጥጥር ያደርጋል፤ ፈርጀ-ብዙ ተጽዕኖውን ያሳርፋል፡፡

6ኛ/ አዲሳባ የሁሉም ናት፦ የሁሉም ለሆነ ጉዳይ ለአብዘኛው የሚሆነ ነገር ያስፈልጋል፡፡ አአ ልዩ ልዩ ሃይማኖት፣ ቋንቋ፣ ግዙፋዊ የሃገሪቱ ምጣነ-ሀብትና ብዙ፤ብዙ እሴቶቻችን ባለቤት ናት፤ ባለ ኀብረ-ቀለም፡፡ በተጨማሪም የዲፕሎማቲክ እና የትላልቅ ቱጃሮች፣ ማኀበረሰብምና የኀብረተሰብም ከተማ፡፡ አአ የዓለም ትላልቅና ታላላቅ ተቋማትን የተሸከመች የሀገራችን ካፒታል ከተማ፡፡ ከዚህ የተነሣ አአ’ን በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በባህል፣ በጎሣም በሉት በዘር መሸንሸን አይቻልም፤ ወይም በዚህ መንፈስ ውስጥ ተሁኖ ወደ አንድ ትግል ቋት ማምጣት ከቀልድ የዘለለ ውጤት አይኖርም፡፡ በዚህ ከተማመነን ደሞ ሌላ ጥሪት ያለ አጀንዳ ያስፈልጋታል ማለት ነው፡፡ መሪ ሀሳብ እና ሀሳቡን የተሸከመ ተቋምንና ግለሰቦችን አምጠው መውለድ ግድ ይለናል ማለት ነው፡፡
መፍትሄ፦ በአሰላለፉ እንደ 1997ቱ ቅንጅት-CUD ግን የታደሰ (updated program) ፤ አዲሳባ፤አዲሳባን የሚሸት ፖለቲካ ፕሮግራም፤ ማነፌስቶና ስብጥርን ታሳቢ ባደረገ መልኩ የፖለቲካ ካፒታል ያላቸው መሪዎችን በመያዝ ደመቅ ብሎ መቅረብ፤

7ኛ/ በሰላማዊ ፖለቲካ ትግል ተስፋ መቁረጥ ፦ በውል አልተረዳነውም እንጂ ሕዝቡ በአሁኑ ወቅት እያካሄደ ያለው የትግል ዘዴ በአመዛኙ ነጭ ሰላማዊ ትግል ነው፡፡ ይሁን እንጂ እስከ አፍንጫው ከታጠቀ ኃይል ጋር በባዶ እጁ መታገል፤ በሕይወት ላይ መቀለድ ነው፡፡ በእሣት መጫወት ነው ሲባል ይሰማል፡፡ በእነርሱ ጫማ ሥር ሆኜ ሳስበው ምክንያታዊ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት በመላው ሀገራችን ክልሎች ባለው አብዘኛው ሕዝብ እንደምናስተውለው ሕዝቡ በሠላማዊ ትግል ላይ ተስፋ የመቁረጥ አዝማሚያ ቢታይም እያካሄደ ያለው ትግል በሰላማዊ ማዕቀፍ ላይ የሚወድቅ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ያልተረዳነው ነገር (ከላይም እንደተጠቀሰው)፤ በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ያለው የሕዝብ ትግል በአመዛኙ በሰላማዊ ትግል ማዕቀፍ ውስጥ የሚወድቅ መሆኑን ነው፡፡
መፍትሄ ፦ የአአ ሕዝብ ለትግሉ መንታ መንገድ ላይ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ምቹ ጊዜና ሁኔታ እየጠበቀ ካልሆነ በስተቀር፡፡ ባጠቃላይ በሀገራችን ሰላማዊ ትግል እንዲያው ለወጉ ነካ ነካ (on and off) ካልሆነ በስተቀር በደንብ ተሞክሯል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ከዓለም ታሪክ ትምህርት እንውሰድ ከተባለ እንኳ አምባገነንን ላንደም ለመጨረሻም ድራሹን የሚያጠፋው ሰላማዊ ትግል የሚያህል ያለ አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ በደንብ ታስቦበት በተቀናጀ መልኩ መታገልና ማታገል ነው መፍትሄው፡፡

8ኛ/ የአገዛዙ ማምከኛ ዘዴዎች፦ በሀገር ላይ የተጠመደ ፈንጂ አለ፡፡ ሆን ተብሎ በወጣቱ ላይ የተሰራውና ትግልን ብቻ ሳይሆን ትውልድን እያመከነ ያለው ሴራ ቢኖር፦ ሱስ አስያዥ ዕፆችን ማስፋፋት፤ አሊያም የይምሰል ቁጥጥር ማካሄድ ነው፡፡ እንደ ሰደድ እሳት እየተዛመተና አሳቢ አእምሮ እያወደመ ያለ የተጠና ሥልት ነው፡፡ በተለይ በታዳጊዩና የነገ ሀገር ተረካቢ ወጣቶቹ ዙሪያ የጫት፣ የሐሽሽና ሌሎች የአደንዛዥ ዕፆች፣ ሰዶማዊነት፣ የአልኮል መጠጥ፣ የምሽት ክሌቦች፣ የሃይማኖት ተፅዕኖ፣ የሥዴት ዕቅድ፤ የባህር ማዶ እግር ኳስና ፍልሞች ወዘተ ቀላል በማይባል ደረጃ የአአ ወጣቶችን ከሀገር ፍቅር ልቦናቸውን እንዲሸፍት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅት ስለእነዚህ ጉዳት ቢትሰብክ ቀድሞ የሚያጠፉህና ወጥመድ ጠማጁ ኢህአዴግ ሳይሆን ራሱ ተጠቃሚ ወጣቱ (ግለሰቦች) ነው፡፡ ባጠቃላይ ሀገርን ከገንዘብ፣ ከቁስና ከጊዜያዊ ፈሽታ ጋር አደባልቀው ማሰብ ወዘተ ተጽዕኖም በቀላሉ የሚታለፍ አይደለም፡፡ በርግጥ የተጠቅነት መጠኑ በመላው ሀገሪቱ ያለ ቢሆንም የአአ የሚብስ ይመስለኛል፡፡
መፍትሄው፦ በቅርብ ያለ መፍትሄ አይታየኝም፡፡ አሁን ሀገራችን ከገባችበት ሁለንተናዊ አጣብቂኝ አንፃር የአጭር ጊዜ መፍትሄ ባስብ ባስብ ቸገረኝ፡፡ በት/ቤቶች፣ በእምነት ተቋማት፣ በወላጆች ወዘተ የሚሰራ ነገር መኖሩ አይካድም፡፡ ለዚህ ይህ ሀገር አልታደለም፡፡ ትልቁ ጉልበት ያለው በመንግሥት እጅ ነው፤ ይሁን እንጂ መንግሥትን ከተነደፈው ስትራቴጂካል ማዕቀፍ ያወጣዋልና አይሞክራትም፡፡ ለዚህ ነው “ልጆችን ለማረም አስቸጋሪ የሚያደረገው ችግሩ ወላጆቹጋ ሲኖር” የሚባለው፡፡

9ኛ/ የሥርዓቱ ምህረት የለሹ እርምጃ፦  የሥርዓቱ ምህረት የለሹ እርምጃ (ዱላ) ሲባል ማንም በገዛ ዜጋው ይቅርና በቅኝ ግዛት ዘመን እንኳን ለመፈፀም የማይደፍረው ነው፡፡ ተቀዋሚውን ጎራ ጭር ለማድረግና የደገፈውን ደሞ ከኳዋክብት ተረታ ለማሰለፍ የተጓዘበት ሥልት ነው፡፡ የኢኮኖሚና የማኀበራዊ ትስስሮችንም ጭምር የሚያሽመድምድበት አደገኛ ሁኔታ ነው፡፡ በሥውሩ ሴራ በዜጎች መካከል እንደ ሸቀጥ ደረጃ የማውጣቱ ነገርም ነዋሪዩን ይበልጡን ለትግል ከማነሣሣት ይልቅ ተስፋ የሚያስቆርጥም ይመስላል፡፡ በደል፣ ግፍና ጭቆና ከትግል ለማፈግፈግ እንደት ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ለማብራራት ራሱን የቻለ ርዕስ ይጠይቃል፡፡ እንደ አጠቃላይ ግን ደካማ ሕዝብ፤ የሚቀምሰውን እስኪያጣ ድረስ ጭቆና ብዙም … እስከ አጥንቱ ዘልቆ ላይሰማው ይችላል፡፡
ባጠቃላይ ከአገዛዙ በኩል እነዚህ ምህረት የለሹ መርዛማ ዓይኖች በተለይ ጠያቂ ትውልድ እንዳይኖር፣ እንዳይወለድና እንዳይለመልምም ጭምር የሚያስውጡት ማምከኛ ታብሌቶች ናቸው ፡፡ ለዚህም ከምጠቀሙበት ዜዴዎች አንዱ የትምህርት ፖሊሲ፣ ጥቃቅንና አነስተኛ ፕሮጀክቶች፣ 1ለ5 አደረጃጀቶች፣ የጋራ መኖሪያ ቤቶች፤ የፍረጃ ቃላቶች (አማራውን ነፍጠኛ/ትምክህተኛ፣ ፍትህ ናፋቅውን ፀረ-ሕዝብ፣ ሥራአጡን አደገኛ ቦዘኔ፣ የአስተሳሰብ ልዩነት ያላቸው ተቀዋሚዎችን አሸባሪ/ ኦኔግ/ ግንቦት7፣ ነውጤኛ፣ ፀረ-ልማት፣ ወዘተ) በግንባር ቀደምነት የሚጠቀሱ ሲሆን፤ በሌላ በኩል በአብዘኛው ነዋሪዩ ዘንድ ተፈጥሮአዊ የሰው ልጅ የነፃነትን ዋጋ ጠንቅቀው ያለማወቅም የራሱ የሆነ ድርሻ መኖሩንም መካድ የሚቻል አይመስለኝም፡፡

10ኛ/ የቱጃሮቹ ሥነ-ልቦና፦ ቱጃሮቹ ስንል በዚህ ሥርዓት ከተፈጠረው ቦይ እየቀዱ ሀብት ያከማቹ ዜጎቻችን ናቸው፡፡ እነዚህ ዜጎች የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር የኢኮኖነሚያቸውን ጡንቻ ወደ ፖለቲካ ጡንቻ መቀየራቸው አይቀርም፡፡ አንዴም ለራሳቸው ሲሉ፤ በሌላ በኩል ለሀገራቸው በማሰብ፤ በተለይ በላቡ የከበረ ሲሆን እንደ ዜጋ የሚሰማቸው ነገር ሊፈጠር ይችላል፡፡ ከሥርዓቱ ጋር ተጣብቀው የከበረ ከሆነ ደግሞ ያለው ምርጫ ከሁለት አንዱ ነው፡፡ የመጀመሪያው፦ ሥርዓቱ የሚቀጥል መስሎ ከታየው ለሥርዓቱ መስገድ ሲሆን፤ ሁለተኛው፦ ሥርዓቱ ደከም ካለ ወደ ተቀዋሚዩ ማዘንበላቸውም እማይቀር ነው፡፡ ምክንያቱም በጭንቅላታቸው የተጠቀጠቀው ፍትህ፣ ዴሞክራሲ ሳይሆን ቁስና ገንዘብ ስለሆነ፡፡ ዞሮ ዞሮ በሁለቱም በኩል ገንዘብ በእጃቸው ሲላሌ ተጽዕኗቸው ቀላል አይሆንም፡፡ ይህንንም ከግምት ውስጥ መክተት ፋይዳው ከፍ ያለ ነው፡፡
ከአዲሳባ ተጽዕኖ ፈጣሪ ነዋሪዎች ውስጥ በርካቶቹ የግልና የጋራ መኖሪያ ቤት ያለው ሲሆን፤ እንደየ ሁኔታ በቂ ባይሆንም የየራሱ ገቢም ያለው ስሆን፤ ደግሞ የከተሜነቱ ተፈጥሯዊ ባህሪ ታክሎበት፤ አመዛኙ ሕዝብ ብልጣብልጥ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ አስሊ ነው፡፡ ስለማስላት ስናስብ ለሀገርም ሆነ ለሰብዓዊ ፍቅር አለብኝ ካልን መገለጫው ፍቅርና ፍቅር ብቻ ከመሆን ውጭ ሌላ ትርጉም የለውም፡፡ ፍቅር ደሞ በስሌት ሲሆን ፍቅር የለም ማለት ነው፡፡ በፍቅር ውስጥ የስሌት መርኀ የለምና፡፡ ሀገሬን አፈቅራለሁ ካልን ሳይንቲፊክ ካልኩሌለሽን ማሽኑን ወዲያ መጣልን ይጠይቃል፡፡ የተወሰነው በበብዥታ፣ ገምሱ ከጥቅምና ጉዳት አንፃር ያሰላና ወጣ ገባ ይላል፡፡ የተቀረው ደሞ ግለኝነት ይንፀባረቅበታል፡፡ ልጆቹንና ራሱን ወደ ቤቱ በመክተት በሮቹን በላዩ ላይ ይከረችምና ሌላው በየአደባባዩ እንዲጮህለት ይፈልጋል፤ በሌላው ደም መንደላቀቅ ይፈልጋል፡፡ ሌላው እንዲደቅለትና የተፈለገው ለውጥ እንዲመጣለት ይፈልጋል፡፡ የሥርዓት ለውጥ እንዲመጣለት ይፈልጋል፡፡ ባለ ኪላሹ፤ ጥይት እንደማይተኩስ ሲያረጋግጥና ከራሱ ጋር ወደ አደባባይ ወጥቶ መብቱን የሚጠይቅ ተሰላፊ ብዙ መሆኑን ሲረዳ፥ አብሮነትን ለማሳየት ወደኀላ የማይልበት ወቅትም አለው፡፡ ይህ ማለት የአአ ሕዝብ በአመዛኙ አቧራ የሚያስነካ/የሚያቆሽሽ ትግል ለመታገል ምቾት አይሰማውም ማለት ነው፡፡ ሁሉንም እያልኩ እንዳልሆነ ይሰመረልኝ፡፡ በንጉሡ ዘመን፣ በኢህአፓ ዘመን፣ በኀወሓት ዘመን ወዘተ ለነፃነት፡ ለፍትህ፣ ለዴሞክራሲና ለሀገር ሉዓላዊነት በሺዎቹ የሚቆጠሩ የአአ ልጆች የጥይት ሲሳይ እንደሆኑ፣ እንደተሰደዱ፣ አካላቸውን እንዳጡ፣ መተኪያ የሌለውን ህይወታቸውንም ጭምር ሳይሰሰቱ ለሀገራቸው እንደገበሩ እንካድ ብንል እንኳ መካድ የሚቻል አይደለም፡፡ ይህ ዋጋ የተከፈለው ለአአ ከተማ ብቻ አይደለም፤ በዘመናቸው አይተውት ለማያውቋት ለገጠሪቱ ኢትዮጵያና ለሕዝቧም ጭምር ነው፡፡ አንድ ካሬሜትር መሬት ሳይኖራቸው እስከ ዳር ድንበር ድረስ ዋጋ ከፍሏል፡፡ ለሚሊዮኖቹ ኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃነት ግዙፉን ዋጋ ከፍለዋል፡፡
እዚህ ላይ የቅርብ ዘመን ትንታግ የአአ ልጆችን ብንወስድ እንኳ እነ ዘሪሁን ገ/እግዚአብሔር፣ ዮናታን ተስፋዬ፣ ኢየሩሳሌም ተስፋው (ጄሪ)፣ እነ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ ጌታነህ ባልቻ፣ እስክንድር ነጋ፣ ብርሃኑ ተ/ያረድ፣ ይድነቃቸው ከበደ (ይድኔ)፣ ሀብታሙ አያለው (መብረቅ)፣ ሀና ዋለልኝ፣ ናትናኤል ያለምዘውድ፣ ፕ/ር አሥራት ወ/የስ፣ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ (ተሜ)፣ ዞን9 ጦማሪያን፣ የሙዝቃ ሰው ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሩ)፣ ኤርሚያስ ለገሰ፣ አንዱዓለም አራጌ፣ ወዘተ ወዘተ ቤቱ ይቁጠረው፡፡ ከአአ ነዋሪ አንፃር ብልጣብልጥ ብዙኃኑ እንዳሉ ሁሉ በሀገር ፍቅር የተለከፉ ሴቶችና ወንዶች በርካቶችም እንዳሉ ከብዙ በጥቂቱ ለመጥቀስ ያህል ነው፡፡

11ኛ / የአኗኗሪነት ስሜት፦ የኢህአዴግን ቋንቋ ልዋስና “እኛ አናሳ (Minority) ኀብረተሰብ/ ብሄረሰብ ክፍሎች እንደመሆናችን መጠን የአናሳዎችን መብት ለማስከበር የአናሳዎቹ ትግል ወንዝ አያሻግርም የሚል ስሜትም ይደመጣል፡፡ በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ደሞ በታሪኳ ጉልበተኞች የሚኖርባት ሀገር ናትና ለምንና ለማን ብዬ ነው ይህን ያህል ዋጋ የሚከፍለው? የምሉ መኖራቸውም አይካድም፡፡ ነገር ግን እነዚህ ኅብረተሰብ ክፍሎች እንደ ትላልቆቹ ሁሉ በአአ ከተማ ዕኩል ድርሻ ያላቸው በተወሰነ መልኩ ላቅ ያለ ተጠቃሚ መሆናቸው የሚካድ አይመስለኝም፤ ለምሳሌ ዶርዜ፣ ትግሬ፣ ወላይታ፣ ሶማሌ፣ ጉራጌ ወዘተ መጥቀስ ይቻላል፡፡
በዓለም ታሪክ ቢሆንም አሸናፊ ሆነው የወጡት በቁጥር አናሳዎች ናቸው፡፡ እሥራኤል፣ ጁባ፣ ኤርትሪያ፣ ጅቡቲ፣ በሀገር ቤት ትግራይን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ስለዚህ የአአ ውስጥ ያሉ አናሳ ቁጥር ያላቸው ብኀረሰብ ክፍሎች ለራሳቸው የሰጡት ቦታ ትክክል ያለመሆኑን ነው፡፡ የእነርሱ ትግል ፋይዳው ብዙ ነው፡፡
መፍትሄው፦ አአ የእኛ ናት ብለው አለመነሳት በራሱ አደገኛ አስተሳሰብ ነው፡፡ ዴሞክራሲ ሲሰፍን የአናሳና የብዙኃን ብሎ ነገር የለም፡፡ ስለዚህ አናሳ ነኝ ለሚለውም፤ ብዙኃን ነኝ ባዩም የሚሸከም ሥርዓት ለማስፈን የሚያስችል ፕሮግራም በማዘጋጀት መንቀሳቀስ፡፡

12ኛ/ የምቾት ቀጠና፦ የአአ ነዋሪ በየኔትወርኩ መገናኘት ይችልበታል፤ በአከባቢያዊነት (የሀገር ቤቱ ትስስርን በመከተል)፤ በእድር፣ በሃይማኖታዊ፣ በማህበር፣ በዕቁብ መገናኘት፤ የየራሱን የምቾት ቀጠና (Comfort Zone) መፍጠርም አንዱ ስልታቸው ነው፡፡ እንዲሁም (በአንፃራዊነት) ከቡድንነት (Group) ይልቅ ግለኝነት (Individual) ይቀነዋል፡፡ በግሉ ኑሮ መጠመድ፤ ለራሱና ለቤተሰቡ መኖር፣ በቅድሚያ የራስ ህይወት መምራት ምርጫው ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ ታዛ ውሰጥ ቶሎ ለመውጣትና ትግሉን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለመቀላቀል/ለማገዝ ፈቃደኛ አይደለም፡፡
መፍትሄው ፦ ሁሉንም እንደ ማስትሽ ሊያጣብቅ የሚችል የጋራ አጀንዳ መቅረጽ አንድ ጉዳይ ሆኖ ሳለ የሀሳቡ ተደራሽነትም ያስፈልጋቸዋል፡፡

አጠቃላይ መፍትሄ ፦
ልብ በሉ! እስካሁን እያወራን የመጣነው ስለ አአ ነው፡፡ ኢህአዴግ መውደቁ አይቀርም!! በዚህ ከተስማማን ሂደቱን ለማፍጠን የአዲሳባ ሚና ብዙ ነው፡፡ ሚናቸውን እንዲጫወቱ ደግሞ፥ አአ-ተኮር በኢትዮጵያዊነትና በዜግነት ላይ መሠረቱን የጣለና ሌሎች እሴቶቻችንን ታሳቢ ያደረገ ግልጽ የፓለቲካ ፕሮግራምና የመታገያ አጀንዳ ያስፈልጋታል፡፡ ከዚህ ውጭ ምናልባትም ለሠራተኛው ክፍል Labour department ወይም ለበር ፓርቲ ያስፈልግ ይሆናል??

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በከበርተውና በምሁሩ በኩል ለውጥ መጥቶ አያውቅም፡፡ እነዛ የድል አጥቢያ ጀግኖች ናቸው፡፡ ከለውጡ በኀላ የማዕዱ ተቋዳሽ ለመሆን እጃቸውን ታጥበው፤ ጥርሳቸው ፍቀውና አደፍጠው የሚጠባበቁ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ የበፊትና የአሁን ታሪካቸውን በግልና በጋራ እንዲያድሱ ማገዝ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ከነድክመቶቻቸው ጋር ቢሆንም ዜጎቻችን ናቸውና፡፡ ሰው በሀብት/በቁስ ብቻ እንደማይኖር ይታወቃል፡፡ ከዚህ በኀላ በሚካሄደው ትግል በተለያየ መንገድ ማሳተፍ ብቻም ሳይሆን ተፅዕኖ ፈጣሪ፣ ውሳኔ ሰጪ እንዲሆኑ በተለያየ መንገድ ማገዝ፤ ወጣቱን፣ ጭቁኑንና የተገፋውን ከመሪዎች ኀላ የሚያሰለፍ አደረጃጀትቶችን መፍጠር የትግሉ ጥያቄ ነው፡፡ እንዲህ ከሆነ ትግሉን በድል ለመቋጨት፤ እንደ መዠገር የተጣበቁ አምገነኖችን አሽቀንጥረን ለመጣል፤ ምናልባትም እንደ ግብፆች 17ቀናትን ሳይሆን 17-ሰዓታትን ይጠይቀን ይሆናል፡፡ እንደ እኔ እይታ ከሆነ በአአ የሚጀመርም ሆነ በአአ የሚጠናቀቅ ትግል ውጤታማ ነው ፡፡

ማጠቃለያ ፦
እንግዲህ እያወራን ያለነው ስለ አአ ነው፡፡ በአአ ያለውን ሀቅ በክልሎችም፤ በክልሎች ያለውን እውነታን አዲስ አበባዎችም የሚጋሩት መኖሩ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ባጠቃላይ አዲሳባ ብዙ ዕውቄትና ብዙ ድንቁርና ያለባት ከተማ ናት፡፡ አአ በኢኮኖሚውም፣ በማኀበራና በፖለቲካው መሠረቶችም ከአንድ በላይ የሆነች ከተማ ናት፡፡ የአዲሳባ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ብሄረኝነትም ሆነ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነትን አይቀበልም፡፡ አዲስ አበባን ፊንፍኒዎችም፣ ቱንጋዎችም፣ ሸገረዎችም፣ አዲሳባዎችም፣ ፖለቲከኞችም ወዘተ ከምር ካንጀት መረዳትን ይጠይቃል፡፡ ወሳኝ የሆኑ ጉዳዮችን፣ ነገሮችንና ሁኔታዎችን በጥልቀት ካልተረዳን ውጤቱ በአረም መመላለስ ነው የሚሆነው፡፡

በሚገርም ሁኔታ በዓለም በተለይም በአፍሪካ ከ3000 ዓመታት ላላነሰ ዓመታት የአገር ታሪክ ይዛ፤ በዘመኗ አምባገነኖችን በጉያዋ አቅፋ የያዘች፤ ተሸክማ የምትቀልብ የሀገርና የአህጉራት መዲና የሆነች ከተማ ቢኖር አዲሰ አባባ ናት፡፡ ይህ ትውልድ ለምን? ተብሎ መጠየቅ ካለበት ጊዜው አሁን ነው፡፡
በዚህ ከተስማማን ደሞ ከዚህ ለመገላገል ፊቱን መዲሃኒቱ “በሰው’ነቱ እና በኢትዮጵያዊነቱ” መሰባሰብ ነው፡፡

ባጠቃላይ በምኒልክ ቤተመንግሥት የመሸገውን ኃይል ለማስወገድ ከአአ ብዙ ብዙ ይጠበቃል፡፡ አአ ሳትነቃነቅ ቤተመንግሥቱ አይነቃነቅም፡፡ አዲስን ለማነቃነቅ ደሞ እኛ ከጥንት ከጧቱ ስንታገልና ስንጮኸ የመጣነውና አሁን ደሞ ዘግይተው ቢሆንም የኦሮሚያው ጎልማሳው እነ ለማ መገርሳም ጭምር የተቀላቀሉንን ሀገራዊ ስሜት በአአ ከተማ በድጋሚ መውለብለብ አለበት፡፡ የዛኔ ነው የአአን ነዋሪ መንቀፍም ሆነ ማሞገስ የሚቻለው፡፡ አአን ከፍርሃትና ከጥርጣሬ ቆፈን የሚያላቅቅ ስትራቴጂ ይህ ኢትዮጵያዊነትና ሰው’ነት ስሜትን ከምር ካንጀት አንግቦ መነሣት ነው፡፡

እንግዲህ ችግሩንም መፍትሄውን እንደ አቅሜ ጠቆም አድርግያለሁ፡፡ ሰፋ ባለመልኩ ማሰስ ቀሪ የቤት ሥራችሁ ነው፡፡ መፍትሄው ከችግሩ ውስጥ ፈልቅቀን ማውጣት ወይም ከችግሩ ጎን ማሰስ የኛ ድርሻ ነው የሚሆነው ፡፡ እንደ አዲሳባም ሆነ እንደ ሀገር፤ ከችግሮቻችን ጋር ዘመናትን ተሻግረናል፤ የ3000 ዓመት የመከራ ፣ የጭቆናና የእልቂት … ዘመን ተሻግሬን ዛሬም እዛው ነን፡፡ እምቦጭ!!

የመፍትሄው አካል መሆን ያልተቻለበትን ምክንያት ላይ በድፍረት ማነጣጠር ያስፈልገናል፡፡ በ1997 ዓም የ10 ዓመት የነበረ ልጅ ዘሬ ላይ የ23 ዓመት ወጣት ነው፡፡ በዚሁ ልክ አስተሳሰቦች፤ አመለካከቶች፤ የኢኮኖሚው ሁኔታና ብቁ የሕዝብ ቁጥርም ጨምሯል፡፡ እስራኤላዊያን ስለ ታሪክ አንድ አባባል አሏቸው፤ “አባቶች ይሞታሉ ልጆች ይረሳሉ” ይላሉ፡፡ አዎን! ያንን ለዴሞክራሲ የተከፈለውን ዋጋ ያልገባው፤ ከቁራ ጩኼት የማይቆጥር ና በብልጭልጭ ነገር ላይ የሚደፋደፍ ትውልድ እየተፈጠረ ይገኛል፡፡ እንዲህ አይነት ሁኔታ ደሞ ሥር ከሰደደ የኀላኀላ ያፈርሰናል፤ የኪሣራው መጠን ያነ ከገባን ትልቁ ኪሣራ ነው፡፡ በአንፃሩ ደሞ በቁጥር የመብዛትና የማነሱ ጉዳይ ልተውውና በአስደናቂ ሁኔታ፤ የሚገርም አስተሳሰብ የሚያፈልቁና በራሳቸው ጥረት ለሀገራዊ ኃላፊነት ራሳቸውን ያበቁም ብዙ ናቸው፡፡ ይህ ኃይል ጥቅም ላይ መዋል አለበት፡፡

የታላላቆቹን ዋጋ በወጉ የተረዱ እየበረከቱ መምጣት ለትግሉ ትልቅ ግብዓት ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ አዲሳባ ለለውጥ ቋፍ ላይ ያለች ከተማ መሆኗን እኛም ሆነ ገዥዎቻችም እየተረዳን የመጣን ይመስለኛል፡፡ ነዋሪዩም በአንዴ ወጥቶ ነገሮቹን ግልብጥብጥ ለማድረግ ቀን እየጠበቀ ነው ብል ከሀቁ የራቅኩ አይመስለኝም፡፡
በየትኛውም ዓለም ለለውጥ ሁሉም እኩል ዋጋ እንደማይከፍል ይታወቃል፡፡ አሁን የሀገራችን ትግል ወስደን እንደሆን በተለይ በኦሮሚያና በአማራ እየተካሄደ ያለውን ትግል ቢሆንም ሁሉም ዜጋ እኩል ዋጋ እየከፈለ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ስለዚህ … በተቻለ መጠን የወደቀብንና ትግሉ የሚጠይቀው ጫና በጥቂቶቹ ትከሻ ብቻ የሚከባለል አይደለም፡፡ በእኩል ባይሆንም የተቀራረበ መዋጮ ማዋጣት የወቅቱ ጥያቄ ነው፡፡
ሰላም!

Filed in: Amharic