>

«ስቶክሆልም ሲንድሮም» የሚባለው የህሊና በሽታ ተጠቂ የሆኑት የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች! (አቻምየለህ ታምሩ)

 

አንዳንዴ ሳስበው የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች በተለይም በተቃዋሚ ጎራ የተሰለፉት የስነ ልቦና ሊቃውንት «ስቶክሆልም ሲንድሮም» ብለው በሚጠሩት የህሊና በሽታ ተጠቂ የሆኑ ይመስለኛል።

«ስቶክሆልም ሲንድሮም» ታጋቾች ከአጋቾቻቸው ጋር ከመላመዳቸው የተነሳ አጋቾቻቸውን አዳኝና ተከላካይ [savior and defender] አድርገው በመውሰድ ስለነሱ ያላቸው ኃዘኔታና ርህራሔ እንዲሁም አወንታዊ ስሜት በጣም ከፍ ወዳለ ፍቅር ያድግና ከአጋቾቻቸው መለየት እጅግ በጣም ከባድ የሚሆንባቸው ደረጃ ላይ የደረሱ ታጋቾችን የሚገልጽ የስነልቦና ክስተት ነው።

የታገተው የኢትዮጵያ ሕዝብም በመንግሥትነት ከተሰየሙት አጋቾቹ የትግራይ ወያኔዎች ጋር እጅግ በጣም ከመላመዱ የተነሳ አጋቾቹ በግፍ ያጎሯቸውን የህሊና ሰዎች በጭካኔ ከሚመትሩበት ከጠባቡ የሰው መታረጃ ቄራ ወደሰፊው የማሰቃያ እስር ቤት ወደ ሆነችው ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲዘዋወሩ ስለፈቀዱላቸው በታጋቾቹ ወገን ያሉ ተቃዋሚ ነን የሚሉ ፖለቲከኞች አጋቾችን ፋሽስት ወያኔዎችን አዳኝና ተከላካይ አድርገው በመውሰድ መቼም ሊለቃቸው በማይችለው የአጋች ፍቅር ተለክፈው የአበሻ ሲንድሮም ውስጥ የወደቁ ይመስለኛል። ይህንን ለማየት ያስፈደረኝ ሰሞኑን ፋሽስት ወያኔ በግፍ ያጎራቸውን የህሊና ሰዎች በጭካኔ ከሚመትርበት ከጠባቡ የሰው መታረጃ ቄራ ወደሰፊው የማሰቃያ እስር ቤት ወደ ሆነችው ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲዘዋወሩ እፈቅዳለሁ ስላለ ብቻ ወያኔ በጎ እርምጃ እንደወሰደ አድርገው የሚያመሰግኑና ውጭ አገር ያሉትም ወዳገራቸው ለመግባት ሻንጣቸውን እየሸከፉ እንዳሉ የሚያስመስል ንግግር የሚሰጡና ጽሁፍ የሚበትኑ ፖለቲከኞቻችን በማየቴ ነው።

ይህም በመሆኑ ፋሽስት ወያኔ መናኛ ስራ ስለሰራ ሳይሆን ከአፍንጫቸው አርቀው ማሰብ በማይችሉ «ስቶክሆልም ሲንድሮም» በሚባለው የህሊና በሽታ በተጠቁ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ወለፈንዲነት ምክንያት ኢትዮጵያውያን ስንት መስዕዋትነት እየከፈሉበት ያለው ሕዝባዊ ትግል ፋሽስት ወያኔ ነጥብ እያስቆጠረበት እየተንገዳገደ ይገኛል።

የትግላችን አላማ ምንድን ነው? እየታገልን ያለነው በግፍ የታጎሩ እስረኞች እንዲለቀቁ ብቻ ነው ወይንስ የታሰሩለትም አላማ እንዲፈታ ነው? በግፍ የታሰሩ ሰዎች በግፍ የእግር ብረት ውስጥ ሆነው በጠባቡ ማሰቃያ ቤት ታጉረው ከሚመተሩት death chamber ወጥተው በረጅሙ ታስረው ወደ ሰፊው እስር ቤት መለቀቃቸው የወያኔን በጎ እርምጃ ያሳያል? በግፍ የታጎሩት ሰዎች የታሰሩለት አላማ እንደተፈታ ያሳያል? ካልሆነ የትኛው ነው በጎ ጅምር ነው? ትግላችን መስዕዋትነት እየከፈልን እስረኛ ለማስፈታት ብቻ ነው ማለት ነው? እስረኛ መፈታቱ የወያኔን ወንጀለኛነት ይለውጠዋልን?

አንዳንድ ፖለቲከኛ ነን ባዮችማ በየቀየው እንዳሸን በሙሉ የበይነ መረብ መስኮቶችና ባለም አቀፍ ሜዲያዎች ሁሉ ሳይቀር እየወጡ ወያኔ የህሊና ሰዎችን አጉሮ በጭካኔ ከሚመትርበት ከጠባቡ የሰው መታረጃ ቄራ አስወጥቶ ተሃድሶ የሚሉትን የአርፋችሁ ተቀመጡ የቅጣት ትምህርት ሰጥቶ «አይደገመንም» በማስባል ወደሰፊው የማሰቃያ እስር ቤት እንዲዘዋወሩ ስላደረጋቸው በጎ ጅምር እንደሆነ፣ ፍትህ እንደተገኘ፣ ሰላም እንደመጣ፣ ነጻነት እንደተጎናጸፍን አድርገው ወያኔን ስለ «መልካም እርምጃው» ያመሰግኑታል። በነዚህ ወለፈንዲ ሰዎች አማካኝነት ስንት መስዕዋትነት እየተከፈለበት ያለው ሕዝባዊ ትግል ወንጀለኛው ወያኔ በኛ ላይ ግፍ መፈጸሙ ሳያንሰን በግፍ ከታጎርንበት ጠባብ ማሰቃያ የታሰርንበትን አለማ አስሮ ወደ ሰፊው እስር ቤት በረጅሙ አስሬ እለቃለሁ ስላለ እያመሰገኑት በፖለቲካው ሜዳም ሽዎት በተሰውበት ትግል ገዳያችን ሌላ ነጥብ እንዲያስቆጥር እያደረጉት የገጽታ ግንባታ እያካሄዱለት ይገኛሉ። ያሳዝናል!

Filed in: Amharic