>

ጡረታ፣ በጠላት ሀገርና ህዝብ ላይ (ጌታቸው ሽፈራው)

ትህነግ አላማዋን አትረሳም፣ አላማዋ በኢትዮጵያ ላይ ነው እንጅ ለኢትዮጵያ አይደለም። የማትፈልገውንም ቢሆን የምታራግፈው በዚህ ህዝብና ሀገር ላይ ነው። ቆሻሻዋን ጥላ አትጥልም። እዳው የዚህ ሀገርና ህዝብ ነው። አላማዋ ዘረፋ ነው። የሚዘርፈው በአንድ ወቅት አብሯት የታገለ ሰው ነው። የሚዘረፈው ደግሞ በየጊዜው ” ብትንትናውን አወጣዋለሁ” እያለች የምትዝትበት ጠላት ህዝብና ሀገር ነው። በጠላትነት ፈርጃ ትግል የገባችበት! ታዲያ ይህ ሀገር ላይዘረፍ ነው?

አባይ ወልዱን ብትጠላው ብትጠላው የኢትዮጵያን ያህል አትጠላውም። የፈለገ ብትጥለው የኢትዮጵያን ያህል አትጥለውም፣ የምትጥለውም ከዚሁ መከረኛ ሀገር ላይ ነው።

የትህነግ/ህወሓት ኮሎኔል ናቸው። አዋሳ ጉምሩክ ተቆጣጣሪ በነበሩበት ወቅት በሙስና ተከሰው ቂሊንጦ አገኘኋቸው። ኮሎኔሉ እንደገለፁልኝ ከመከላከያ የወጡት የህወሓት ኮለኔሎች እንደ ጡረታ ተቆጥሮላቸው ገንዘብ የሚበላበት አካባቢ ይመደባሉ። በርካቶቹ እንደ እሳቸው ጉምሩክ ውስጥ ተመደቡ። ይህ አይነት ምደባ በትግርኛ “አገልግላችሁናል፣ እንሆ ብሉ! ሀገሩንም ዝረፉት!” ማለት እንደሆነ ግልፅ ነው። አብሯቸው የተከሰሰው ወጣት ደግሞ እነ ኮሎኔል እንዴት እንደሚዘርፉ በዝርዝር፣ የሸቀጥ ዋጋና ትርፉን አስልቶ አጫውቶኛል።

ልክ እንደ ጉምሩክ ሁሉ እስር ቤት የትህነግ/ህወሓት ታጋዮች ጡረታ መውጫ ነው። ከምስኪን እስረኛ ከ50 ብር ጀምሮ ሲቃርሙ ይውላሉ። መልሰው ይከሱታል። በፖሊስ ምልመላ መስፈርት አይን ወሳኝ ነው። ቃሊቲ በትግሉ አይናቸውን የተጎዱ ታጋዮች አመራር ሆነው ይሰራሉ። ጡረታ መውጫ ነዋ!

ሌላኛው ጡረታ መውጫ ኤምባሲ ነው። የኤምባሲ ደህንነቶች የግድ የትህነግ ደህንነቶች ናቸው። በትግርኛ ብቻ የሚሰለል ይመስል፣ ሌላ ሰው አይመደብም። አማካሪ፣ የፖለቲካ አታሼ……… የትህነግ ታጋይ ነው። ተራ ደህንነት ተብሎ የተላከው አምባሳደሩን ያሾረዋል፣ አታሸውም እንደዛው! አሁን አሁን ደግሞ አምባሳደር እያደረጉ ይልኳቸዋል። ተገምግሞ “አትረባም” የተባለው ሁሉ አምባሳደር ሆኖ እንዲበላ ይላካል። ህገወጥ ንግዱን ያጧጡፋል። ሌላም ሌላም!

በትህነግ ዘመን ኢትዮጵያ እንዲህ ለዘራፊ ቦታ የሚመቻችባት ድንቅዬ ሀገር ነች! የብሔር ብሔረሰቦችን እኩልነት ለማረጋገጥ፣ መልካም ለሚያስቡትም ቦታ አላቸው፣ እስር ቤት!

Filed in: Amharic