>

አሁን ኢህአዴግ ተለውጦ ‹ገንዘብ› ይሆናል? (ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ)

በኢህአዴግ ተስፋ ስቆርጥ የእናቴ እናት (አያቴ) ትዝ ትለኛለች፡፡ በተለይ ባለፉት ሶስት አመታት በየእለቱ በኢህአዴግ ተስፋ ስለምቆርጥ፣ በየቀኑ ነው የማስታውሳት፡፡ አያቴ በልጅነታችን የማይሆን ነገር ስናደርግ ስትመለከት፣ ‹‹አሁን ይኼ ልጅ አድጎ ‹ገንዘብ› ይሆናል?›› ትል ነበር፤ አንጀቷ እያረረ፡፡ ‹‹ከህይወትም፣ ከትምህርት ቤትም ተምሮ ሰው አይሆንም፣ አይጠቅምም›› ለማለት ስትፈልግ እንደሆነ፣ ‹ገንዘብ› ስሆን ነው የገባኝ፡፡
.
ኢህአዴግ ተለውጦ ‹ገንዘብ› እንደማይሆን እያሳየ ነው፡፡ ከራሱ ያልታረቀ ድርጅት እንዴት አገር አስታርቆ መግባባትና ሰላም ይፈጥራል!? ክብሪትና ናፍጣ የያዘ ሰው እየዞረ እሳት ሲለኩስ፣ ውሀ በጀሪካን ተሸክመህ እየተከተልክ ብታጠፋ፣ ሰውየው ካልሞተ፣ አልያም ናፍታና ክብሪቱን ካልነጠቅከው፣ እድሜህን እሳት በማጥፋት ታሳልፋለህ፤ ወይ አንድ ቀን አንተኑ ያቃጥልሀል፡፡ ኢህአዴግ ባለጀሪካኑን ይመስላል፤ የህዝብ ቁጣ በገጠመው ቁጥር፣ መፍትሄ ያለውን ጣል እያደረገ፣ የህዝብን ቁጣ ሲከተል ይኸው 26 አመቱ፡፡ የህዝብን ጥያቄ ከስሩ ለመፍታት ፍጹም ፍላጎት የለውም፡፡ በእነለማ መገርሳ ጥያቄ ተሰንጎ በተያዘበት ወቅት እንኳን የገባውን ቃል ለመፈጸም ይቅርና የገዛ መግለጫውን እስካሁን አስተካክሎ አልጨረሰም፡፡ የጠ/ሚንስትሩን ‹‹የፖለቲካ እስረኞች ይፈታሉ›› በግማሽ ቀን ከአምስት ጊዜ በላይ ቃላትን እየቀያየረ ሲጫወት ማየት፣ ኢህአዴግ ከራሱ ጋር እርቀሰላም እንዳላወረደ ያሳያል፡፡ ‹‹የፓለቲካ እስረኛ የለም›› ያለው ኢህአዴግ ‹‹እንደፖለቲካ ተሳትፏቸው እየታዩ ይፈታሉ›› ሲል መስማት ግራ ያጋባል፡፡ ሰው እንደ ሰው ሊያብድ – ሊቀውስ ይችላል፤ ድርጅት እንደድርጅት፣ መንግስት እንደመንግስት አእምሮውን ሲስት የስፈራል፡፡ .
.
ኢህአዴግ ‹‹ለሁሉም ችግር መንስኤው እኔ ነኝ›› ብሎ ይቅርታ ጠይቆ፣ ‹‹እስረኛ እፈታለሁ፤ ማእከላዊን እዘጋለሁ›› ብሎ እያለ፤ የመከላከያ ሚንስትሩ በተነሳው ቀውስ ውስጥ ያሉ፣ ከዚህ ለማትረፍ የፈለጉ አካላት በቁጥጥር ስር ይውላሉ እያሉ፣ የእስር እቅድ ይነድፋሉ፡፡ ‹‹ምክንያቱ እኛ ነን›› ብሎ ባደባባይ ይቅርታ የጠየቀ እያለ የምን ማጣራት ነው!?
.
በየፍርድ ቤቱ ልብሳቸውን እያወለቁ የደረሰባቸውን ስቃይ እያሳዩ፣ ፍትህ በሚማጸኑበት ሀገር፣ ‹‹ደርግ ሲያሰቃይበት የነበረውን ማእከላዊ ዘጋሁ›› የሚል ድርጅት፣ ቶርቸርን ለማቆም እንዳልተዘጋጀ መጠየቅ አያሻም፡፡ ከልቡ ንሰሀ ያልገባ በሙሉ ልቡ ለጽድቅ አይሰራም፡፡ ለምን ቢሉ፣ ከንሰሀ ሸሽጎ ያስቀረው ሀጥያት ከልቡ አለና እንደማይጸድቃ ያውቃል፡፡ እውን ኢህአዴግ እስረኞች የሚፈታው፣ ማእከላዊን የሚዘጋው . . . . ወዘተ. እንደሚለው ለብሄራዊ መግባባትና ለሰላም ከሆነ እነማን የፖለቲካ እስረኞች እንደሆኑ፣ ከደርግ በኋላ ማእከላዊ ምን አይነት እስርቤት እንደነበረ ልቦናው ያውቃል፡፡ እና ልቦናው ውስጥ ምንም ሸሽጎ ሳያስቀር የሚያግባባና ለሰላም መሰረት የሚሆን እርምጃ መውሰድ አለበት፡፡ እሱ ራሱ 528 እስረኞች እፈታለሁ ባለበት ማግስት፣ ለዶ.ር መረራ ብቻ የወጣውን ‹‹የይፈታሉ – አይፈቱም›› መግለጫ ስመለከት፣ ንሰሀው ለጽድቅ ያበቃዋል የሚል ተስፋዬ ተሟጦ – ‹‹ኢህአዴግ መቼም ቢሆን ተለውጦ ‹ገንዘብ› አይሆንም›› ብዬ ደምድሜያለሁ – እንደአያቴ፡፡

Filed in: Amharic