>
5:18 pm - Wednesday June 14, 6017

የበረከት ተመልሶ መምጣት ማረጋገጫ (ኤርሚያስ ለገሰ )

የዛሬው አዲስ ዘመን ርዕሰ አንቀፅ የበረከት ስምኦን ተመልሶ መምጣት የሚያረጋግጥ ነው። የአዲስ ዘመን ርዕሰ አንቀፅ የመንግስት አቋም የሚገለፅበት በመሆኑ የሚፃፈው በህውሃት/ ኢህአዴግ የፓለቲካ መሪዎች ብቻ ነው። በተለይ በእንደዚህ አይነት የቀውጢ ወቅት አዲስ ዘመን ከስኳር መጠቅለያነት ወጥቶ የፓለቲካውን አቅጣጫ ማሳየት ስላለበት በፕሮፐጋንዳ ክፍሉ ልዩ ትኩረት ይሰጠዋል። የሚፅፈው አሊያም በስልክ ዲክቴት የሚያደርገው ደግሞ በረከት ስምኦን ነው።

እናም ወደ ዛሬው ርዕሰ አንቀፅ ስንመጣ የሟቹ መለስ ዜናዊ ገድል የተገለፀበት ” የሁለት ምርጫዎች ወግ” ግልባጭ ሆኖ እናገኘዋለን። በምርጫ 97 የታሰሩት የፓለቲካ እስረኞች በኢትዬጲያ አዲሱ ሚሌኒየም ሲፈቱ በረከት በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ተፈቺዎችን ጥንብ እርኩስ የሚያወጣ ፅሁፍ ፃፈ። በአንደበቱም በኢትዬጲያ ቋንቋ በሚተላለፋ አለም አቀፍ ሚዲያዎች በመውጣት ” እግራችን ስር ወድቀው ይቅርታ ስለጠየቁ ይቅር አልናቸው” በማለት አይኑን በጨው አጥቦ ተናገረ። በወቅቱ በፓርቲው ውስጥ የነበረውን ነብስ ውጪ፣ ነብስ ግቢ ለተካፈልን ሰዎች የሰውየውን የኩሸት ደረጃ ከማድነቅ አልቦዘንም ነበር። የሰው ልጅ በዚህ ደረጃ መዋሸት ይቻለዋል ወይ? የሚለው ጥያቄ ግን በየአጋጣሚው የሚነሳ ነበር።

የሌባ አይነደረቅ እንዲሉ አቶ በረከት በ2002አ•ም• ባሳተመው ” የሁለት ምርጫዎች ወግ” መፅሀፍ በአዲስ ዘመን ርዕሰ አንቀፅ የፃፈውን ሳይቀንስ ሳይጨምር ደገመው። በገፅ 233 ” ፓለቲካና ፍትህ፣ ሰኔና ሰኞ ሲገጣጠም” በሚል ንዑስ ርዕስ የሚከተለውን ፃፈ፣

” የቅንጅት ታሳሪዎች የፍርድ ሂደት ነፃ መሆን በግልፅ የታየበትና መንግስት የቅንጅት መሪዎች የተከሰሱባቸውን ወንጀሎች ከበቂ በላይ ማስረጃ አቅርቦ በማረጋገጡ ሕዝቡ የሰዎቹን ጥፋተኝነት በጥያቄ ውስጥ የጣለበት ሁኔታ አልነበረም። … የዳኝነት ነፃነት የተረጋገጠበት የአገራችን የፍትህ ስርአትና ለዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ቁልፍ ተፈላጊነት እንዳለው የህግ የበላይነት ከሆነ ፣ የታሰሩት የቅንጅት መሪዎች የይቅርታ ጥያቄ ፣ የፍርድ ሂደቱ እንዲጓተት ለማድረግ የሚያስችል የጊዜም ሆነ የአሰራር ክፍተት እንዲፈጥር እድል የሚሰጥ አልነበረም። በይፋ የተጀመረን የፍርድ ሂደት በአቋራጭ መግታት የፍርድ ቤቶችን ነፃነት ይጋፋልና ነፃው ፍርድቤት የቅንጅት መሪዎች ጥያቄ ማቅረባቸውንም ሳይሰማ ብይኑን አሳለፈ።…ሂደቱም ሰዎቹ ( የቅንጅት መሪዎች) ህግ አክባሪነትን በደህናው ቀን ለመማር ብቻ ሳይሆን በፍጥነትም ለመማር የሚቸገሩ መሆናቸውን ያረጋገጠ ነበር” በማለት ያትታል።

ይህን የበረከት አገላለጥ ወደኃላ መለስ ብለን ብንመለከተው የምንገነዘበው ነገር ቢኖር ሰውየው ለጊዜው እስከጠቀመው ድረስ ምንም ከማለት የማይመለስ መሆኑን ነው። ለማንኛውም ለበረከት ቢያንስ አንድ ጥያቄ አንሰቼለት ወደ ተነሳሁት ልመለስ። ጓድ በረከት! የተጀመረን የፍርድ ሂደት በአቋራጭ መግታት የፍርድ ቤቶችን ነፃነት የሚጋፋ ከሆነ አሁን ለምን ለማቋረጥ ተገደዳችሁ? የአሁኑ እርምጃችሁ የፍርድ ቤቶችን ነፃነት አይጋፋም ማለት ነው?

እነሆ! ከአስር አመት በኃላ (ጥር 2010 አ•ም•) አቶ በረከት በአዲስ ዘመን ርእሰ አንቀፅ ተመልሶ መጥቷል። በህዝብ እምቢተኝነት ተገዶ የፓለቲካ እስረኞች እየፈታ እንደሆነ ልቦናው ቢያውቀውም በመንግስት እና የፓርቲ ፕሮፐጋንዳ ጉያ ውስጥ ተደብቆ ማስፈራራቱን ቀጥሎበታል። አሁን የሚፈቱት የፓለቲካ እስረኞች የኢትዬጲያን ህዝብ አስቀይመዋል፣ በድለዋል ይለናል። ተፈቺዎች ጥፋታችንን አንደግምም ማለት እንዳለባቸው ያስጠነቅቃል። ይህን ካላደረጉ በትውልዱ እንደሚጠየቁ፣ በታሪክ እንደሚወቀሱ ፣ የምህረት እና የይቅርታን ዋጋም ዝቅ እንዳደረጉ ይቆጠርባቸዋል ይለናል። በረከት ስምኦን!!

አቶ በረከት የዶክተር መረራን የደመቀ አቀባበል አስቀድሞ ቢገምትም ኖሮ እንዲህ አይነት ርእሰ አንቀፅ ከመፃፍ ወደ ኃላ አይልም ነበር። ለማንኛውም ” ምህረትና ይቅርታውን እንጠቀምበት” የሚለው የአዲስ ዘመን ( የህውሓት) የዛሬ ርእሰ አንቀፅ በከፊል ይሄን ይላል፣

“… በምህረት እና ይቅርታ የሚወጡ ዜጐች ያስቀየሙትንና የበደሉትን ህዝብ በልማት መካስ ይጠበቅባቸዋል። ምህረት እና ይቅርታውን ስራ ላይ ማዋል ይኖርባቸዋል። ሁሉም እንደ ሙያቸው ፣ እንደ ትምህርት ዝግጅታቸውና ልምዳቸው ለልማት መሰለፍ እንጂ መስነፍ አይኖርባቸውም። የፓለቲካ ምሁራኑ በእልህና በግትርነት ላይ ከተመሰረተ ጉንጭ አልፋ ክርክሮች በመራቅ ልማትና ዕድገትን ወደፊት የሚያስቀጥሉ የለውጥ ሀሳቦችን ማፍለቅ አለባቸው።…

” ምርጫ 97ትን ተከትሎ በተፈጠረ ግጭትና ሁከት ለእስር የተዳረጉ አንዳንድ የፓለቲካ አመራሮችና አባላት ለይቅርታ የሰጡት አይነት ምላሽ ዛሬ ላይ ሊታይ አይገባም። በወቅቱ ህዝቡና የአገር ሽማግሌዎች ፓለቲከኞቹ እንዲፈቱ ባደረጉት ጥረት በይቅርታ መፈታታቸው ይታወሳል። ከተፈቱት የተወሰኑት የወሰዱት እርምጃ ራሳቸውን ለትዝብት፣ ህዝቡን ለንዴት መዳረጉ አልቀረም። ያንን ሲያስታውሱ የሚቆጩና የሚበሳጩ ዜጐች በርካታ ናቸው። ለዚያውም አገሪቱ አዲሱን ምዕተ አመት በፍቅር ለመቀበል በተዘጋጀበት ዋዜማ ላይ መሆኑ ደግሞ የቁጭቱን ደረጃ ከፍ አድርጐት ነበር። ግለሰቦቹ ከማረሚያ ቤት መልስ ህዝባቸውንና አገራቸውን ያገለግላሉ ተብሎ ሲጠበቅ ምላሻቸው አገር ጥሎ መሰደድ ሆነ። እንዲፈቱ ሲታገልላቸው የነበረውን ህዝብ የኃሊት እያዩ የሩጫውን ዙር አከረሩት።…

” ዛሬ ላይ ይህ አይደገምም፣ እንደማይሆንም ይገመታል። ከስህተትና ጥፋት ታርሞ አምራችና ብቁ ዜጋ ሆኖ አገርን ማገልገል እንጂ ጥፋትን መድገም አይታሰብም። ሊታሰብም አይገባም። ሕዝብን አክብሮና አፍቅሮ አለማገልገል በትውልድ ያስጠይቃል። በታሪክ ያስወቅሳል። የምህረትና ይቅርታን ዋጋም ዝቅ ያደርገዋል” ይላል። የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ርእሰ አንቀፅ። የጓድ በረከት ርእሰ አንቀፅ። የትግራይ ነፃ አውጪ ድርጅታዊ አቋምና የቀጣይ አቅጣጫ!!

Filed in: Amharic