>

ይድረስ ለፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፤ ዘምቢል ሙሉ… (ሃራ አብዲ)

ዘምቢል ሙሉ…

ዘምቢል ሙሉ ጥበብ፤ ዘምቢል ሙሉ እውቀት፣
ዘምቢል ሙሉ ብልሃት፤ ዘምቢል ሙሉ ጥናት፣
ያምቦዉ የምጥ ብስራት፤ የጦቢያ አንጡራ ሃብት፣
እንዴት አማረብህ ፤ ስትወጣ ከእስር ቤት!!
የታደለች ዘምቢል፤ በፕሮፌሰር እጅ፤
ጨበጥ ተደርጋ፤ በቀለማት ደምቃ፣
በውበት ታጅባ፣ የመንፈስ ምስክር፣
ልትሆን አብራ ወጣች፣
የብረቱን መዝጊያ ፤ ሰብራ ተራመደች፣
የወያኔን ፣ ሀኬት ፤ እየተጠየፈች።
የመረራ ዘምቢል ፤ ትታይ ከፍ ብላ፣
በሺህ ፣ በመቶ ሺህ ፤ ጨረታ ይጠራ፣
ከእስር ስትፈታ ፤ ሀገሬ ኢትዮጵያ፣
ለግፍ ለሰቆቃዉ ፤ ትሁን መታሰቢያ።
ለማስፈን ታግለሃል ፤ የዲሞክራሲ መብት፣
የዘመንህ ገሚስ፤ ተውጦአል በንግልት።
መኖር እስካልቀረ፤ መማር እስካልቀረ፣
መረራ ባንተ ልክ፤ ሰው ሁሉ በኖረ።
እውቀት በአእምርህ፤ ጥበብ በልቦናህ፣
ጽናት በመንፈስህ፤ እውነት ባንደበትህ፣
አዋህደህ ይዘህ፤ ታግለሃል በሰፊው፣
አልባከነም ጊዜህ፤ ለህዝብህ ያዋልከው።
የአውሮፓን ህብረት፤ ያሜሪካን መንግስት፣
የንግሊዝን መንግስት፤ ሌላና ሌላውን፣
ከእንግዲህ ወዲያ፤ ማንንም አትመን።

ማንንም አናምንም፣
ያህያ ባል ናቸው፤ ከጅብ አያስጥሉም፣
ከህዝብህ ጋራ ነው፤ ሞትህም ፤ ትንሳኤህም።
እነሆ ይድረስህ፤ ዘምቢል ሙሉ ፍቅር፣
ዘምቢል ሙሉ ሞገስ፤ ዘምቢል ሙሉ ክብር፣
ዘምቢል ሙሉ መውደድ፤ ዘምቢል ሙሉ ሃሴት፤
እድሜ ከጤና ጋር፤ ዘምቢል ሙሉ ስኬት፣
አንሶላ፣ ብርድ ልብስ፤ የተውከው ፣ እስር ቤት፣
ቅኝ ገዢዎቻችን፤ እንዲገነዙበት!!
በእስር ቆይታህ፤ የረገጥከው ምድር፣
ችሎቱ፣ መኪናው፤ ማናቸዉም ነገር፣
ይፍጃቸው እንደ እሳት፤ ጸጸት ይግረፋቸው፣
እንዳይጠፋፋ ፤ ትውልድ በሴራቸው፣
የጆችህ ካቴና፤ ይጥለቅ ባንገታቸው፣
ያለጣር አይሁን ፤ መርገፍ፣ መፍረሳቸው።
እጅግ ከሚወድህ፤ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር፣
ላንተ ግን ይድረስህ፤ ዘምቢል ሙሉ ፍቅር፤
ዘምቢል ሙሉ ሞገስ፤ ዘምቢል ሙሉ….ክብር

Filed in: Amharic