>
5:13 pm - Thursday April 18, 5912

ዶክተር መረራን እያስታወሱ ፈገግ ቢሉ (ደረጀ ሃብተወልድ)

እንቅልፍ በፓርላማ 

የኦሮሞ ብሄራዊ ኮንግረስ አመራር የሆኑትና ያለበደላቸው ለእስር ተዳርገው የቆዩት ዶክተር መረራ ጉዲና ዛሬ ረቡዕ ከእስር ተፈተዋል። የኢትዮጵያን ደረቅና የመነቼከ ፖለቲካ አልፎ አልፎ ጣል በሚያደርጓቸው ቀልዶች ትንሽ ሊያወዙት የሚሞክሩት ዶክተር መረራ የአውሮፓ ህብረት ባደረገላቸው ግብዣ መሰረት በብራሰልስ ስብሰባ ላይ ከፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ጎን መቀመጣቸው ነው እንደ ወንጀል ተቆጥሮ ለእስር ያበቃቸው።

ዶክተር መረራ ከሚጠቀሱባቸው ቀልዶች አንዱ:- በምርጫ 97 ወቅት ከቀድሞዋ የትምህርት ሚኒስትር ከገነት ዘውዴ ጋር ሲከራከሩ አሉት የተባለው ነው። ገነት፦ “መረራ እንዳለው” ብለው ንግግር ሲጀምሩ ዶክተር መረራ ፦”ሥነ ስርዓት! ቅል እንኳ ማንጠልጠያ አለው!! ዶክትሬቱን ያገኘሁትኮ እንደ አለቆችሽ ገዝቼው ሳይሆን ተምሬና ለፍቼ ነው!!! እንዴት አፍ እንዳመጣልሽ መረራ ትይኛለሽ!?”በማለት ይናገራሉ። ይህኔ ወይዘሮ ገነት “ይቅርታ ዶክተር መረራ ማለቴ ነው”በማለት ያስተካክላሉ።

ወዲያው የዶክተር መረራ መናገሪያ ተራ ሢደርስ በተራቸው፦”ገነት እንዳለችው”ብለው ይጀምራሉ። ይህኔ በነገሩ የተበሳጩት የቀድሞዋ የትምህርት ሚኒስትር፦” ሥነ ስርአት! አሁን መረራ አለችኝ ብለው ሢከሱኝ ነበር። ይሄው በተራቸው ግን እርሳቸውም ገነት ብለው ነው ያሉኝ። ቅል እንኳ ማንጠልጠያ አለው!” ብለው ሲቆጡ ፣ዶክተር መረራ ፈገግ እያሉ፦” እንዴ ተረጋጊ እንጂ ፣ የቀረውኮ ወይዘሮ ነው” ነበር ያሏቸው።

ይህ ብቻ አይደለም፦”የፓርላማ አባላት ትተኛላችሁ ይባላል” የሚል ጥያቄ ያቀረበላቸው ጋዜጠኛ ፦ኧረ በፍጹም ተኝቼ አላውቅም”የሚል ማስተባበያ ምላሽ ሲጠብቅ፣ ዶክተር መረራ ግን እንደሚከተለው ነው ያሉት፦” ምን እነዚህ የኢህ አዴግ አባላት በሆነ ባልሆነው እያጨበጨቡ እየቀሰቀሱን ምን መተኛ አለን?”

ይህን የፓርላማ መተኛት ነገር ዛሬ ያወሳሁት ትናንት በብሪታኒያ ፓርላማ የሞቀ ውይይት ላይ “ጧ” ብለው ተኝተው የነበሩት የሌበር ፓርቲ ተወካይ ዴዝሞንድ ዝዋይን ሳይወሉ ሳያድሩ ለህዝብ ይቅርታ መጠየቃቸውን በማንበቤ ነው።
እንግሊዝ ከአውሮፓ ኀብረት ስትወጣ ምን ያህል ክፍያ መክፈል አለባት? በሚለው አጀንዳ ዙሪያ የሞቀ ውይይት እየተደረገ ባለበት ሰዓት ጭልጥ ያለ እንቅልፍ የወሰዳቸው ዴዝሞንድ ዝዋዬን ሳይውሉ ሳያድሩ ይቅርታ የጠየቁ ሲሆን፣ “ከእንግዲህ ሥራ የምገባው፣ እንቅልፌን እቤቴ ጨርሼ ነው” በማለት ለመረጣቸው ሕዝብ ቃል ገብተዋል።

Filed in: Amharic