>

ሀገሬን ሳሚልኝ! (ጋዜጠኛ/ደራሲ ወሰንሰገድ ገ/ኪዳን)

“እንዴት ነህ – እንዴት ነህ – እንዴት ነህ በአያሌው
ኑሮ እንዴት ይዞሃል? – አማን ነው ወይ ቀዬው?”

ብለሽ የጠየቅሺኝ – የእናቴ ልጅ ውዴ

እንደው በደፈናው – “አለሁ!” እልሻለሁ – የአፍ ሆኖ ልማዴ፡፡

እንጂ መኖር አይደል – ሁሉም ነገር ከፍቷል
ወገኔ ምትይው – ኩሩ ሀበሻ ሁሉ – ወገን አልባ ሆኗል፡፡
እንዴት? እንዳትይኝ – እንዴት እንደሆነ – እኔንም ጨንቆኛል
ሰው ስዋስው ሆኗል – ሰውነቱን ትቷል፤
እምነቱን ረስቷል!
ግን ለወጉ ያህል – ቤተስኪያን ይሄዳል
የአዛን ሠዓት ቆጥሮ – መስገዱን ይሰግዳል
ሆኖም እንደእምነቱ – መቆም አቅቶታል
ማጎብደድን ባህል – ዘዬው አድርጎታል
ታዲያ ይሄ መኖር – መኖር ነው ይባላል!?

ይኸው አሁን እንኳ – እንዴት ነህ? ስትይኝ፣
እንዲህ ነኝ እንዳልል – ማንነቴ ጠፍቶኝ
ነፍስያዬን ስቼ – በሥጋት ተውጬ
ማልቀስ ይቃጣኛል – በግፍ ተረግጬ፡፡

ይህ የምልሽ ሁሉ – የቀልድ እንዳይመስልሽ – አጉል እንቶ ፈንቶ
በአበሻ ምድር ላይ – እውነትና እምነት – ቃሉ ብቻ ቀርቶ
ተፈጥፍጦልሻል – የሚያነሳው አጥቶ፡፡

ያቺ የምታውቂያት – በኔም ባንቺም ልብ ውስጥ የረቀረፀችው
ኢትዮጵያችን ያልናት – ሥም ብቻ ሆናለች – በሥም ነው
ያለችው፡፡
ባይገርምሽ ውዴ ሆይ፣
አዋቂ ሚባለው – የተማረው ሁሉ – የተመራመረው
ለካስ ሆኖ ኖሮ – እውነት የመረረው – ሐቅ የጎፈነነው
አጎንባሽ አከንፋሽ – ብኩን ሆኖሻል
ህሊናውን ትቶ – ከራሱ ተጣልቷል
ግን ለወጉ ያህል – “አለሁ!” “አለን!” ይላል፡፡
ምን ምኑን ልንገርሽ፣
ሊቅ አይባል ደቂቅ – ትንሹም ትልቁ
“ወየው” ብቻ ሆኗል – ወየው ብቻ ስንቁ፡፡
.
“ዋ!….” ባይ ነው አዳሜ – “ዋ!” ባይ ነው ሹመኛው
“ዋ!” ሆኗል ገንዘቡ – “ዋ!” ሆኗል አዱኛው፡፡
ሁሉንም ዘርዝሬ – አልነግርሽም ይቅር
ሽምግልና ረክሷል – ሽበት አጥቷል ክብር፤
እርቅ የሚባል ነገር – ተረስቷል ተጥሏል
ተበዳይ ሲያለቅስ
ከበዳይ ጋር መዝፈን – ማጨብጨብ ወግ ሆኗል፡፡

አዬ የኔ ነገር – ምኑን ከምን ብዬ – ልንገርሽ ዘርዝሬ
ስሟ ብቻ ቀርቷል – ተሰዳለች መሰል – ምስኪን ይቺ አገሬ፡፡
.
እስቲ ፈልጊልኝ – ትገኝ እንደሆነ – ምናልባት አንቺ ዘንድ
ውለታ ዋይልኝ – ለመቼ ነው ዘመድ!
ድንገት ካገኘሻት – በእውነት አፋልገሽኝ፣
ባይደላውም እንኳ – ያፈቅርሻል ብለሽ – ሃገሬን ሳሚልኝ!!
.

Filed in: Amharic