
በጃዝ ሙዚቃ እና በግጥም የታጀበው ይህ የስነጽሁፍ እና የሽልማት ዝግጅት እጅግ ደማቅ ነበር ።

የኮክስፋም ኖቪፕ ፕሬዝዳንት ሚስ ፋራ ካሪሚም እስክንድር ነጋ በከፍተኛ ተጽእኖ ውስጥ ሆኖ ሃሳቡን በመግለጹ መታሰሩን ገልሰው – ለእስክንድር እና እንደ እስክንድር ላሉ የፕሬስ ነጻነት ተፋላሚዎች ትልቅ ክብር እንደሚሰጡዋቸው ተናግረዋል።
በሽብር ተወንጅሎ 18 አመታት የተፈረደበት ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የዓለም አቀፍ ሽልማት ሲያገኝ ይህ የመጀመርያው አይደለም። በከፍተኛ ተጽእኖ ውስጥ ሆኖ ሃሳቡን በመግለጹ እና በዚህም ለፍትህ አልባ እስር በመዳረጉ፤ እ.ኤ.አ. በ2011 የፔን አሜሪካ አዋርድ በኒውዮርክ ፤ በ2012 ፔን ባርባራ ጎልድስማን ፤ በ 2014 ፔን ዋኒፍራ ጎልደን አዋርድ፤ በ2015 ፔን ካናዳ አዋርድ እንዲሁም ሂዩመን ራይት ዋች ባዘጋጀው የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ተሸላሚ መሆኑ የሚታወስ ነው።
የእስክንድር ባለቤት ሰርካለም ፋሲል ሽልማቱን በባለቤትዋ ስም እንድትቀበል ብትጠራም በአንዳንድ የጉዞ እክሎች ሄግ ላይ መገኝት አልቻለችም። ሰርካለም ከቨርጂንያ የላከችው ልብ የሚነካ መልእክት ግን በአዳራሹ ለታደመው ሕዝብ እንዲነበብ ተደርጋል። ከጫፍ እስከጫፍ ጢም ያለው በዚህ አዳራሽ ውስጥ በርካታ ሎሬቶች፤ አለም አቀፍ ደራሲያን እና ገጣሚዎች እንዲሁም ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ተገኝተዋል።