>

በታላቅ ቅሬታ ተጀምሮ - በቅሬታ የተጠናቀቀው ኮንሰርት (እሳቱ ሰ)

ቴዲ – “ጃ ያስተሰርያልን ካልዘፈንሁ አትወዱኝም ማለት ነው?”
ወጣቱ – “አንወድህም!”

ቴዲ አፍሮ በባሕር ዳር ኮንሰርት ሊያካሂድ መሆኑንን ከሰማሁ ጀምሮ የምይዝ   የምጨብጠውን አጥቸ ነበር፡፡ መጀመሪያ አላመንሁም ነበር፡፡ በሆነ ምክንያት የሚቋረጥ ይመስለኝ ነበር፡፡ በማህበራዊ ሚዲያ እንዲሁም ምድር ላይ ሰለኮንሰርቱ የሚሰራጩ መረጃዎች ሁሉ ግራ የሚያጋቡ ነበሩ፡፡ ያም ሆኖ ቀኑን በልዩ ጉጉት እጠብቀው ነበር፡፡ . . .

በዚህ ላይ ከወልዲያ መርዶ መጣ፡፡ ወንድም እህቶቻችን በአረመኔው የአጋዚ ጦር መጨፍጨፋቸውን ሰማሁ፡፡ . . . ገዳዮቹ አዲስ አበባ ሄደው ግዳያቸውን ሊፈጽሙ ሞከሩ – አልተሳካም፡፡ የከተራ እና ጥምቀት ወጣቱን ሊያፍኑ ሞከሩ፡፡ የሚካኤል ግን ለበቀል ቋምጠው የሰነበቱ ወታደሮች ያለ ጠባቂ በሚኖረው ሕዝባችን ላይ ጭፍጨፋውን አካሄዱ፡፡ . . . ባሕር ዳር ላይ ሰለወልዲያው ጭፍጨፋ የሰማው ሰው ጥቂት ነው፡፡ አንዳንዶች በሁኔታው በማዘን በቴዲ ኮንሰርት ላለመታደም ወሰኑ፡፡ ሁኔታው ከባድ ነበር፡፡ . . . በፍፁም ሀዘን ውስጥ ብሆንም በጉጉት ስጠብቀው ወደ ነበረው የቴዲ ኮንሰርት ላለመግባት አልወሰንሁም፡፡
ጥር 13  ማለዳ
በጠዋቱ ተነስቸ ወደ ከተማ ሄድሁ፡፡ ባሕር ዳር ስቴዲየም አካባቢ ብዙም የተለየ ነገር አይታይም፡፡ የከተማዋን ዋና ዋና መንገዶች ዞርኋቸው፡፡ በርካታ ተሸከርካሪዎች በሞንታርቦ የከተማው ሕዝብ ትኬት ቆርጦ በኮንሰርቱ እንዲታደም ይቀሰቅሳሉ፡፡ የቴዲ አፍሮ ፎቶ የታተመባቸውን ቲሸርቶች ለብሰው የሚዟዟሩ ወጣቶች አልፎ አልፎ ይታያሉ፡፡ በሌላ ነገሯ ውቧ ባሕር ዳር ቀዝቀዝ ያለች ነበረች፡፡ . . . ረፋድ አካባቢ ነገሮች ሞቅ ሞቅ ማለት ጀመሩ፡፡ ቲሸርት የሚሸጡ ግለሰቦች ከፓፒረስ እስከ አዝዋ ያለውን ግራና ቀኝ መንገድ አጨናነቁት፡፡ የቴዲ አፍሮ ምስል የታተመባቸው ቲሸርቶች ለጉድ መቸብቸብ ጀመሩ፡፡ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ የእጅ የሚገቡ – በራስ የሚጠመጠሙ ሪቫኖችን ወጣቱ እየተሻማ ይገዛል፡፡ በሁሉም ሰው እጅ ቢያንስ አንድ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀለም የሚያሳይ ነገር ነበር፡፡ ሁኔታው የአንድ አርቲስት ኮንሰርት ሳይሆን የብሔራዊ ቡድን ኳስ ለመከታተል የሚደረግ መዋብ ይመስል ነበር፡፡ . . . 
ቀን
ኮንሰርቱ 12 ሰዓት እንደሚጀምር – የስቴዲየም መግቢያ በሮች 9 ሰዓት እንደሚከፈቱ ቢነገርም ሕዝቡ ወደ ስቴዲየም ማምራት የጀመረው እኩለ ቀን ላይ ነበር፡፡ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የክልሉ ፈጥኖ ደራሽ ወታደሮች በስቴዲየሙ አጥር ዙሪያ ጥበቃ ጀምረዋል፡፡ ወጣቶች መግባት ይቻላል እሰኪባል አዝዋ ሆቴል እና በአካባቢው ባሉ ምግብ ቤቶች ተቀምጠው ይጠባበቃሉ፡፡ . . . ስምንት ሰዓት ተኩል አካባቢ ወደ ስቴዲየሙ ለመግባት ሰልፍ ተጀመረ፡፡ ሰልፉ ሦስት አራት ቦታ እየተቆራረጠ ወደ ፍተሻ አመራ፡፡ ስቴዲየም ከመግባታችን በፊት ሁለት ጊዜ ተፈትሸን ወደ ሰፊው ስቴዲየም ገባን፡፡
በስቴዲየሙ የምስራቅ አቅጣጫ ግዙፍ መድረክ ተሰርቷል፡፡ ሰው ሜዳው ውስጥ ከመድረኩ ፊት ለፊት መቀመጥ ጀምሯል፡፡ ቦታችንን አመቻችተን ተቀመጥነ፡፡ ሙዚቃ በዲጀ ተከፈተ፡፡ One Love አለ ቦብ፡፡ ሲቀጥል ብዙ የሬጌ ዘፈኖች ተሰሙ፡፡ ከአማርኛም ጅጅ፣ ፋሲል፣ ማህሪ፣ ንዋይ፣ ኑረዲን ሰዒድ፣ ዳኘ፣ መስፍን፣ አሊ ቢራ ወዘተ ዘፈኑ፡፡ የሙዚቃ ኮንሰርቱ ይጀምራል የተባለበት 12 ሰዓት ደረሰ፡፡ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ ዓላማውን እያውለበለበ ለሚጠብቀው ሕዝብ ከመድረክ መሪው ጩኸት ውጭ ብቅ ያለለት ነገር አልነበረም፡፡ .
ማታ
አብዛኛው ታዳሚ ወጣት ነው፡፡ ከ9 ሰዓት ጀምሮ ሜዳ ላይ ቢሰጣም የተባለው ኮንሰርት አልጀምር አለ፡፡ አንድ ሰዓት ሆነ፡፡ ወጣቶች መድረክ መሪውን መሳደብ ጀመሩ፡፡ የተለመደው “ወያኔ ሌባ” የሚል ተቃውሞ በተለይ ከመድረኩ በስተቀኝ ሜዳ ውስጥ እና ከሜዳው በስተኋላ ካሉ ታዳሚወች መሰማት ጀመሩ፡፡ መልስ ጠፋ . . .፡፡ መድረክ መሪው “ቴዲ ሊመጣ ነው፡፡ አትገፋፉ – ወደ ኋላ ሁኑ” ከማለት ውጭ ምንም ማለት አልቻለም፡፡ ታዳሚው ለተቃውሞ የውኃ ላስቲኮችን ወደ መድረኩ መወርወር ጀመረ፡፡ ይባስ ብሎም ዝግጅቱን ከአየር ላይ ለመቅረጽ በሚበሩ “ድሮኖች” ላይ ውርወራውን ቀጠለ፡፡ ሁኔታው በዝግጅቱ አስተባባሪዎች ወይም በቴዲ አፍሮ ጥፋት ወደ አላስፈላጊ ብጥብጥ ሊያመራ ነው ሲባል 1፡35 ላይ አቦጊዳ ባንዶች ወደ መድረክ መጡ፡፡ ከአንድ ሰዓት ተኩል በላይ ለተጉላላው ታዳሚ ይቅርታ እንኳን ሳይጠይቁ የተወረወሩ ላስቲኮችን አንስተው ወደ ሥራቸው ገቡ፡፡ . . .
ከደቂቃዎች በኋላ ቴዲ መጣ፡፡ . . . ቴዲ መጣ! ያ ሁሉ መጉላላት፣ ያ ሁሉ መከፋት፣ ያ ሁሉ ቅሬታ ገደል ገባ፡፡ ቴዲ መጥቶ “በማርፈዳቸው ይቅርታ ይጠይቃል – ወልዲያ ሰለሞቱት የሆነ ነገር ይላል – አገሪቱ ሰላለችበት ሁኔታ አንድ ነገር ይናገራል – ሰለዝግጅቱ ያወራል – የሆነ ነገር ይሰብከናል ወዘተ” ብለን የገመትናቸው ሁሉ ሳይሳኩ ቀሩ፡፡ “ኦ አፍሪካዬ” በሚለው ሥራው ጀመረ፡፡ ሁሉም ከቴዲ እኩል ዘፈነ፡፡ ቀጥሎ ግርማዊነትዎን ተጫወተ፡፡ ግርማዊነትዎ ሊያልቅ አካባቢ የአቦጊዳ ባንድ ሙዚቃውን ወደ “ጃ ያስተሰርያል” የቀየረ መሰለ፡፡ ሜዳው ውስጥ ያለው ታዳሚ “ጃ ያስተሰርያል” ማለት ጀመረ፡፡ ቴዲ ግን አልዘፈነውም፡፡ . . .
ማር እስከ ጧፍ ሲዘፈን ምድር ቃውጢ ሆነች፡፡ ማን ዘፈኝ – ማን ታዳሚ እንደሆነ ግራ ያጋባል፡፡ ሜዳው መካከል ላይ የተተከሉ ምሰሶዎች ሳት መትፋት ጀመሩ፡፡ እስክስታ – ዝላይ – ጩኸት – ተቀወጠ፡፡ . . . ቴዲ መድረኩን እንደቦረቀበት የመጀመሪያውን ምዕራፍ ዝግጅቱን አጠናቆ ለእረፍት ከባንዱ ጋር ከመድረክ ወረደ፡፡ ተራው መጫዎቻ ሜዳው ላይ ወደ ሚገኙ ታዳሚዎች ዞረ፡፡
“ወያኔ ሌባ”
“ቢመችሽም ባይመችሽም – አንች ወያኔ አንለቅሽም”
“አማራ – ማንነም ማይፈራ”
የሚሉ ዝማሬዎች በቡድን በቡድን ከተሰበሰቡ ወጣቶች ጎልተው መሰማት ቀጠሉ፡፡ ሁኔታውን ለመቆጣጠር ይመስላል ለእረፍት የወረደው ባንድ በፍጥነት ወደ መድረክ መጣ፡፡ ሁለተኛው ዙር ተጀመረ፡፡ ቴዲ ከቆዩት እና ከአዲሱ ካሴቱ የተመረጡ ዘፈኖቹን እንዲሁም የሌሎችን ዘፋኞች ሥራ ቀነጫጭቦ ማቅረቡን ቀጠለ፡፡ በቃ ልዩ ነበር፡፡ . . . ቴዲ “ኧረ ደሴ ደሴ” እያለ እንዲህ አለ፡፡ . . .
“አዲስ ዘመን መጥቶ – አሮጌው ሲሸኝ
ምነው በቂም ቀርቶ – በፍቅር ቢዳኝ”
አራት ሰዓት አለፈ፡፡ ለሁለት ሰዓት ነው የተባለው ዝግጅት ሦስተኛ ሰዓቱን ያዘ፡፡ ግለቱ ሳይበርድ – ቴዲ አፄ ቴዎድሮስን ለመጫዎት ገና “ጎንደር – ጎንደር” ሲል ስቴዲየሙ ተንቀጠቀጠ፡፡ ሁሉም ስሜታዊ ሆነ፡፡ የፋሲል ከነማ የዳግማዊ ቴዎድሮስ ስዕል የተሳለበትን አርማ ለቴዲ ሰጠ፡፡ ቴዲ ከፍ አድርጎ ለታዳሚው አሳየ፡፡ አፄ ቴዎድሮስን ዝቅ ብሎ ሳመ፡፡ በዚህ ሁሉ መካከል ጩኸትና ፉጨቱ ለጉድ ነበር፡፡ ሲቀጥል አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ ዓለማ ተሰጠው፡፡ መድረኩ ላይ ይዞት ተወራጨ፡፡ . . . ቴዲን አልጠገብነውም ነበር፡፡ ሲዘፍን ቢያድር ልንሰማው የተዘጋጀን ነበር፡፡ ስሜታችን እንደጋለ “የተዘጋጁባቸውን ሥራዎች” አቅርበው መጨረሳቸውን ተናገረ፡፡ ታዳሚው “ጃ ያስተሰርያል” እያለ ጮኸ፡፡ መድረክ ላይ ውጥረት ነገሰ፡፡ ቴዲ ጊታር የሚጫዎተውን ልጅ እና ሌሎችንም ያናግራል፡፡ ሕዝቡ “ጃ – ጃ – ጃ” ይላል፡፡ እንደታዘብሁት ታዳሚው ከጅምር እስከ ፍጻሜው ከቴዲ ሥራዎች ሁሉ መስማት የፈለገው “ጃ ያስተሰርያልን” ነው፡፡ ዘፈኑ እንዲዘፈን “ቴዲ አይፈራም – ቴዲ አይፈራም” መባል ቀጠለ፡፡ ቴዲ ዘፋኝ ብቻ ሆኖ ለመታየት ፈልጓል፡፡ የተለመዱ ንግግሮቹ በትላንትናው ኮንሰርት አልነበሩም፡፡ ዘፈኖቹን ብቻ ማቅረብን መርጧል፡፡ “ቴዲ ይችላል – ቴዲ አይፈራም” ሲባል ቴዲ መልስ ሰጠ፡፡
“እኔ ፈርቸ አላውቅም፡፡”
ጩኸት፡፡
“የምትወዱኝ ከሆነ አንድ ነገር ግን ተረዱኝ፡፡ . . . ማንም ሰው በሥራዬ እንዲከፋ አልፈልግም፡፡” ጩኸት – ጃ – ጃ – ጃ – ወያኔ ሌባ – ወያኔ ሌባ –
“ጃ ያስተሰርያልን ካልዘፈንሁ አትወዱኝም ማለት ነው?”
“አንወድህም፡፡”
“እንግዲያስ አልዘፍነውም፡፡” ቴዲሻ አሳዘነኝ፡፡ የኛ ሀገር ሰው እንዲህ ነው፡፡ ለማስመሰል ብሎ “ቴዲን እንወድሃለን” ማለት አልቻለም፡፡ ፊት ለፊት ተናገረ – ንጉሡን አፍ አውጥቶ “አንወድህም” አለ፡፡ በቃ – የምንፈልገውን ካላደረግህ – አንወድህም አለው፡፡ ምን አልባት ቴዲ እንዲህ ሲባል የመጀመሪያው ይሆናል፡፡ ሕዝቡ የቴዲ ጭንቀት ገብቶታል – ግን ጃ ያስተሰርያል ማለት ይፈልጋል፡፡ ቴዲ ከባንዱ አባላት ጋር ተነጋግሮ ጃ ያስተሰርያልን ሊዘፍን ሊጀምር ሲል ማናጀሩ ወደ መድረክ መጣ፡፡ ምን እንደሚነጋገሩ አንሰማም፡፡ ወዲያው የኮንሰርቱ መዝጊያ “ጥቁር ሰው” ሆኖ ተዘፍኖ ዝግጅቱ ተጠናቀቀ፡፡ . . .
ቴዲ ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን ተናገረ፡፡ ታዳሚው የቀረው ነገር ሰለነበረ መሄድ አልፈለገም ነበር፡፡
“በሰላም ወደየቤታችሁ ግቡ” አለ ቴዲ፡፡ ታዳሚው በቅሬታ መውጣት ጀመረ፡፡ ያ ሁሉ ደስታ ፈዘዘ – ያ ሁሉ እርካታ ጠፋ – ያ ሁሉ ፈንጠዝያ ተረሳ – ያ ሁሉ ግለት ቀዘቀዘ – ወሬው ሁሉ ሰለቀረቡ ድንቅ ሥራዎች መሆኑ ቀርቶ ሰለ ጃ ያስተሰርያል አለመዘፈን ሆነ፡፡ ብዙዎች ያጉረመርማል፡፡ እንዴት አይዘፍንም ይላሉ፡፡ አንዳንዶች ግን ቴዲ “ጃ ያስተሰርያልን” ቢዘፍነው ሊነሳ የሚችለውን ተቃውሞ በመገመት እንኳንም አልዘፈነው ይላሉ፡፡ . . .
“በ17 መርፌ በጠቀመው ቁምጣ
ለለውጥ ያጎፈረው ስልጣን ላይ ሲወጣ
እንደ አምናው ባለቀን የአምናውን ከቀጣ
አዲስ ንጉሥ እንጅ ለውጥ መቸ መጣ”
ጃ ያስተሰርያል!
Filed in: Amharic