ህወሃት ራሱን ከትግራይ ህዝብ ለይቶ ማየት ሳይችል፣ ሌሎች ለይተው እንዲያዩለት መጠበቁ ራሱ እጅግ ይገርማል። ሳሞራ የኑስ “ ህወሃት እና የትግራይ ህዝብ አንድ ነው” ማለቱ ተሰንዷል። ሰሞኑን ህወሃት ጉባኤዋን ስታጠናቅቅ ባወጣችው መግለጫ ላይ ደግሞ፦ በትግራይ ህዝብ እና በህወሓት መካከል “ በደም የተሳሰረና የፀና ግንኙነት” እንዳለ ጽፋለች። “በደም የተሳሰረ” ግንኙነት የሚለው አነጋገር አንድነትን ወይም ጥብቅ ቁርኝትን የሚያመለክት ነው፤ ሰውን ከደም በላይ የሚያስተሳስረው ነገር የለም – በእናትና ልጅ መካከል እንዳለው ግንኙነት ማለት ነው። በህወሃት ውስጥ ያለው አመለካከት ይኸው ነው። ህወሃት አደጋ ሲገጥመው ካልሆነ በስተቀር፣ ህወሃትና የትግራይ ህዝብ ተነጣጥለው እንዲታዩ አይፈልግም። ሚስጢሩ ይህ ሆኖ ሳለ ታዲያ፣ ማእበል በተነሳ ቁጥር፣ የህወሃት ሰዎችም ሆኑ ሚዛናዊያኖች “ የትግራይን ህዝብና ህወሃትን ለዩ” ብለው የሞራል አስተማሪ ሆነው ሲቀርቡ አይዋጥልኝም።
ህወሃቶች ራሳቸው “ አንድ ነን” ማለታቸውን ሳያቆሙ፣ ሌሎች “ ሁለት ናቸው” ብለው እንዲናገሩላቸው እንዴት ይጠብቃሉ? አስተማሪህ “አንድ ሲደመር አንድ መልሱ ‘አንድ’ ነው” ብሎ ነግሮህ፣ አንተም “ልክ አይደለም” ብለህ ተከራክረኸው፣ “በቃ እመን፣ ባታምን ግን ትወድቃለህ” ካለህ በሁዋላ፣ ፈተና ላይ “ ሁለት” ብለህ መልሰህ “ኤክስ” ብታገኝ ስህተቱ የአንተ እንጅ የእሱ አይደለም ። ስህተት መሆኑን እያወቅህ እንኳ የነገረህን ትደግምለታለህ እንጅ፣ ያልነገረህን አትደግምለትም። አስተማሪው ሌላ ጊዜ “ለምን ሁለት ብለህ አልመለስክም?” ብሎ ቢናገርህ፣ ” አንተ ራስክን ሳታርም እኔ እንዴት ላርምህ እችላለሁ” ብለህ ብትለው የሞራል የበላይነት ታገኛለህ። አስተማሪህን አንተ ብታስተካክለው እሱ ራሱን ካላስተካከለ ምንም ፋይዳ የለውም። ህወሃቶችና ሚዛናውያን ጥፋተኛ የሚያደርጉት ተማሪውን እንጅ አስተማሪውን አለመሆኑ ሁሌ ይገርመኛል።
የህወሃት አባላት፣ ከደፈሩ፣ መጀመሪያ ድርጅታቸው የትግራይን ህዝብ አንድና ሁለት እያደረገ የሚጫወተውን ጨዋታ እንዲያቆም መጠየቅ ነው። እምቢ ካለ በግልጽ ማወጅና መለዬት ነው። ድርጅታቸው “የአንድ እና ሁለት ጨዋታውን ሳይቆም” ሌሎች እንዲያቆሙ መጠየቅ ግን ግብዝነት ነው። “እሽ እናቆማለን” ቢባል እንኳ፣ ማእበሉ ጸጥ ሲል፣ “ በደም የተሳሰሩትን ህወሃትንና የትግራይን ህዝብ ለመነጠል ሞክረሃል” ተብለህ ትወገዛለህ። ለእኔ “የትግራይ ህዝብ እና ህወሃት አንድ ናቸው ወይስ አይደሉም?” የሚለው መሰረታዊ ጥያቄ አይመስለኝም። መሰረታዊው ጥያቄ “ ህወሃት የትግራይን ህዝብ አንድ እና ሁለት አድርጎ ማየቱን ያቆማል ወይስ አያቆምም?” የሚለው ነው። የህወሃት ደጋፊዎችም ሆኑ ሌሎች ሚዛናውያን ይህንን ጥያቄ በተገቢው መንገድ ሳይመልሱ፣ የሞራል አስተማሪ ሆነው ቢመጡ አይታኘከኝም። ባለፉት 26 አመታት “የትግራይ ህዝብና ህወሃት አንድ አይደሉም” እያሉ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ሲናገሩ የነበሩ ሰዎች፣ የሚሰማቸው ያጡት በአብዛኛው ህወሃት የአንድና ሁለት ጨዋታውን ማቆም ባለመቻሉ ነው ። የህወሃት አባላትም ሆኑ ሌሎች ተቺዎች፣ ጣታቸውን በሌሎች ላይ ከመቀሰራቸው በፊት በቅድሚያ ድርጅታቸው ላይ መቀሰር አለባቸው። ህወሃት ሲያደርገው ትክክል ፣ ሌሎች ሲያደርጉት ግን ስህተት ተደርጎ መራገቡ፣ ሚዛናችንን ከማንጋደዱም በላይ ችግሩ እንዳይቀረፍ ያደርገዋል። በአጭሩ እዳው ያለው ህወሃት ላይ ነው። እዳውን እንዲከፍል መጠየቅ የሚገባውም ህወሃት ነው።
ማንም ጤነኛ አዕምሮ ያለው ሰው መላው የትግራይ ህዝብ መቶ በመቶ የህወሃት ደጋፊ ወይም አባል ነው ብሎ አያምንም። እንዲህ ብሎ ማመን ከሎጂክም ከታሪክም ጋር መጣላት ነው። ህወሃትን በመቃወም ህይወታቸውን ያጡ አሁንም በመቃወም ላይ ያሉ የትግራይ ሰዎች አሉ። ከአዛውንቶች ገብረ መድህን አርያን ፣ ከወጣቶች የማነ ምትኩን በምሳሌነት መውሰድ ይቻላል። እስካሁን እንዳየሁዋቸው እነዚህ ሁለት ሰዎች የመርህ ሰዎች ናቸው። ሌሎች የማላውቃቸው ሰዎችም ይኖራሉ። እነዚህም ሆኑ ሌሎች ትግሬዎች “ የትግራይን ህዝብና ህወሃትን ለዩ” እያሉ መናገራቸው ተገቢ ነው ብዬ ባስብም፣ ህወሃት “የአንድና ሁለት” ጨዋታውን እሳካላቆመ ድረስ ምንም ለውጥ ሊመጣ እንደማይቻል ግን በእርግጠኝነት ልነግራቸው እችላለሁ። በተለይ የህወሃት አባላት፣ የትግራይ ህዝብ እጣ ፋንታ ያሳስበናል የሚሉ ከሆነ፣ ህወሃት ሲመቸው የትግራይን ህዝብና ህወሃትን አንድ አድርጎ መመልከቱን፣ ሳይመቸው ሲቀር ደግሞ “የትግራይን ህዝብና ህወሃትን ለይታችሁ እዩ” እያለ የሚጫወተውን ጨዋታ እንዲያቆም መጠየቅ አለባቸው። ካላቆመ ደግሞ ራሳቸውን ከድርጅቱ መነጠል አለባቸው። ማንም የፖለቲካ ድርጅት፣ የአንድን አካባቢ ህዝብ የራሱ የግል ንብረት አድርጎ ሊቆጥር አይገባም፤ ለድርጅቱም ለህዝቡም አይበጀውምና። ያ ካልሆነ “አህያውን ፈርቶ …” እንዲሉ ከመሆን አያልፍም።