>

ቴዎድሮስ ካሳሁን ከባሕርዳር ትዕይንቱ ምንም የሚማረው ነገር አይኖር ይሆን?

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

ይሄ ጉዳይ የእግር እሳት ሆኖብኛል ወገኖቸ፡፡ ከትዕይንቱ ማግስት በጻፍኩት ጽሑፍ ላይ የተሰጡ አስተያየቶችና የማይመስሉ ማስተባበያዎች ጉዳዩን እንደገና እንድመለስበት ግድ ብሎኛል፡፡ ከብስጭቴም በረድ ብያለሁና በሰከነ ሁኔታና በጽሞና መነጋገሩ በተለይ ቴዲን ሊጠቅም ይችላል ብየ ስላሰብኩ እንደገና መመለሱ የግድ አስፈላጊ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡

የሕዝቡ ቁጣና ከጃ ያስተሠርያል ዘፈን ጋር ተያይዞ የተፈጠረው ችግር እንዴት ሊከሰት እንደቻለ እንይና ከዛ ትዕይንቱን እንሔሳለን፡፡ በዚያ የዘፈን ትዕይንት (ኮንሰርት) ላይ ሕዝቡ ላይ እንደዚያ ዓይነት ቁጣና ተቃውሞ እንዲቀሰቀስ ያደረጉት እራሳቸው እነ ቴዎድሮስ ካሳሁን ነበሩ፡፡ እውነቱ ይሄ ሆኖ እያለ “ሕዝቡን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ላለምራት ሲባል ነው ጃ ያስተሠርያልን ያልተጫወተው!” የሚለው ብልጣብልጥ ምክንያት በጣም አሳዝኖኛል፡፡ እንዴት እንደሆነ እንይ፦

ምንም ዓይነት ነገር ያልታየበትና የተረጋጋ የነበረው ሕዝብ ቁጣና በኋላም ወደብጥብጥ ሊቀየር ጥቂት ቀርቶት የነበረው ችግር ሊፈጠር የቻለው “ከአመሻሹ 12 ሰዓት ላይ ይጀምራል!” ተብሎ የተነገረው ዝግጅት ሁለት ሰዓታት ያህል መዘግየቱ በሕዝቡ ላይ ከሰዓት ወደ ሰዓት እየተጋጋለ የመጣ ቁጣ ፈጥሮ ነበረ፡፡ መጨረሻ ላይ መድረኩ ከሕዝቡ “ወያኔ ሌባ! ወያኔ ሌባ!” ከሚል የውግዘት ቃል ጋር በቁጣ በተወረወሩ የላስቲክ (የተለጥ) ኮዳዎች ተሞልቶ ነበረ፡፡

ይህ የሕዝቡ ቁጣ ወደብጥብጥ ሊቀየር ጥቂት ሲቀረው ነው የአቡጊዳ የሙዚቃ (የዘፈን) ቡድኑ ወደ መድረክ የወጣው፡፡ የላስቲክ ኮዳው እንዲፀዳ ከተደረገ በኋላ መዝፈን ተጀመረ፡፡ ከቀትር ጀምሮ ከስታዲየሙ (በዐውደ ቅሪላው) ዙሪያ፣ ከ9 ሰዓት ጀምሮ ደግሞ ውስጥ ገብቶ ፀሐይ እየተቀቀለ ከግማሽ ቀን በላይ በታላቅ ትዕግሥት ምንም ዓይነት ኮሽታ ሳያሰማ የቆየውን ሕዝብ ወደ ታላቅ ቁጣ እንዲገባ ያደረገው አንዱ ጉዳይ ይሄ ነበረ፡፡

የዘፈን ቡድኑ እንዲህ ዓይነት አሳፋሪ መጉላላት በሕዝብ ላይ ከፈጸመ በኋላም ለሕዝብ አክብሮት ሰጥቶ ይቅርታ ይጠይቃል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረውን የሕዝብ ቁጣና ቅሬታ ከምንም ሳይቆጥሩና አንዳችም ነገር ሳይሰማቸው ምንም ዓይነት ይቅርታ ሳይጠይቁ ወደ ትዕይንታቸው ገቡ፡፡

እንዲህ ዓይነት ጥፋቶች መፈጸምና ይቅርታ ለመጠየቅ ያለመቻል ችግር ቴዲ ሊቀርፈው ያልቻለው አንዱ ችግሩ ሆኖ እስከዛሬ ከዚህ ችግሩ ጋር መኖሩ ይገርመኛል፡፡ ለሕዝብ ክብር አለኝ የሚል ሰው ፈጽሞ በምንም ዓይነት ተአምር ቢሆን ለጥፋቱ ሕዝብን ይቅርታ ለመጠየቅ አይቸገርም፣ አይተናነቀውም፣ ይቅርታ መጠየቅንም አይዘነጋም፡፡

የሩቁን ትቸ የቅርቡን አንዱን ብቻ ላስታውሳቹህ፡፡ እንደምታስታውሱት ባለፈው ጊዜ ቴዲ አዲሱን አልበሙን (የዘፈን ጥራዙን) ለገበያ ባቀረበ ሰሞን አሜሪካ ያለው ማኅበረ ግዩራን ዘረ ኢትዮጵያ (SEED) የተባለው ሸላሚ ድርጅት ከዘንድሮ ተሸላሚዎች አንዱ ቴዲን አድርጎት ነበረ፡፡ በሽልማቱ ቀን ቴዲ ሁለት ሰዓታት ዘግይቶ ነበር የደረሰው፡፡ ይታያቹህ! ሁለት ሰዓታት አይደለም ሁለት ደቂቃ መዘግየት ብዙ ነገሮችን በሚለዋውጥበት፣ ብዙ ዋጋ በሚያስከፍልበት ሀገር በርካታ ታላላቅ ሰዎችን፣ የተከበሩ እንግዶችን፣ ሳይንቲስቶችን (መጣቅያንን) እና በተለያየ ሞያ ታላላቅ ደረጃ የደረሱ ብርቅና ድንቅ ኢትዮጵያንን ቴዲ ለሁለት ሰዓታት ያህል ጎልቶ ማዋሉ አይደለም የሚገርመው፡፡ ሊፈነዳ እንደተቃረበ ፊኛ በትዕቢት ተወጣጥሮ በቦታው ከተገኘ በኋላ ይቅርታ ለመጠየቅ የሚያስችል አቅል፣ ማስተዋልና አክብሮት አጥቶ ይቅርታ ሳይጠይቅ በሦስት አራት ቃላት ምስጋናውን ገልጾ ሽልማቱን ይዞ መውጣቱ ነበር እጅግ ያስደነቀው ነገር፡፡

በአሜሪካ ድምፅ እንግዳ ሆኖ ቀርቦ ለምን እንደዘገየ ሲጠየቅ የመንገድ መጨናነቅ እንዳዘገየው ተናገረ፡፡ “ለምን ታዲያ ይሄንን የገጠመህን ችግር ገልጸህ በትዕግሥት ለጠበቀህ ሕዝብ ይቅርታ አልጠየክም ነበረ?” ተብሎ ሲጠየቅ ለትዝብት በሚዳርግ አገላለጽ ይቅርታ መጠየቁን ረስቶት ሳይጠይቅ እንደቀረ ተናገረ፡፡ ያሁኑ ይባስ አትሉም? ይሄ የቴዲ ሕዝብን ከመናቅና ራስን አለቅጥ ከማንጠራራት ከማስታበይ ስሜት የተነሣ ለጥፋቱ ይቅርታ ለመጠየቅ ያለመቻል የመከበድ ችግሩ የዋለ ያደረና በርካታ ታላላቅ ሰዎችም ያዘኑበት የዋለ ያደረ ችግሩ ነው አዲስ አይደለም ለማለት ፈልጌ ነው፡፡

ሁለተኛው ሕዝቡን ወደቁጣ እንዲያመራ ያደረገው ችግር ደግሞ፦ ቴዲ ዘፈኖቹን መዝፈን ከጀመረ በኋላ ሕዝቡ አብሮት እየዘፈነ ሁለት ሦስት ዘፈኖችን ከዘፈነ በኋላ የዘፈን ቡድኑ እንደ ማጓጓት አድርጎ ጃ ያስተሠርያል የሚለውን ዘፈን ጀመር ሲያደርገው ሕዝቡ ተቀብሎ መጫወት ጀመረ፡፡ ወዲያውም እሱን ተወት አደረጉትና ማር እስከ ጧፍን መጫወት ቀጠሉ ሕዝቡም ይሄንንም አብሮ ዘፈነ፡፡ ዘፈኑ እንዳበቃም ሕዝቡ ጀመር ተደርጋ የተቋረጠችውን ዘፈን ጃ ያሥተሠርያልን መዝፈን ቀጠለ ቡድኑ ግን ሌላ ዘፈንን ቀጠለ፡፡ ከዚያ በኋላ ቴዲ ሌላ ዘፈን ተጫውቶ ባበቃ ቁጥር እስከመጨረሻው ድረስ ሕዝቡ ጃ ያስተሠርያል እንዲዘፈንለት ሌላ ችግር እንዳይፈጥር በሚያሠጋበት አኳኋን አጥብቆ መጠየቅ ቀጠለ፡፡

ቴዲም ጃ ያስተሠርያል የፍቅር ዘፈን መሆኑን ደጋግሞ ገለጠ፡፡ ይሁንና ሊጫፈተው ግን አልፈለገም፡፡ ምክንያቱም ብሎ “ማንንም ማስቀየም ስለማልፈልግ!” በማለት ተናገረ፡፡ ዘፈኑ የፍቅር ዘፈን ከሆነ ቢጫወተው ማን በምን ምክንያት ሊቀየመው እንደሚችል ግን ግልጽ አላደረገም፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ ፈቃዱን የሰጠው “በሕወሓት ላይ ፊቱን አዙሯል!” የተባለው ብአዴን አይደለም እንዴ? እንዲያ ከሆነ ታዲያ ጃ ያስተሠርያልን እዚያ ቦታ መዝፈን እንዴት የሚያሳስብ ሊሆን ቻለ???

እነኝህና ሌሎች አባባሎቹ ሕዝቡን ምን እንዲያስብ አደረገው? ቴዲ ጃ ያስተሠርያልን እንዳይዘፍን እንደተከለከለ እንዲያስብ አደረገው፡፡ በዚህም ምክንያት “ወያኔ ሌባ! ወያኔ ሌባ! ቴዲ አይፈራም! አማራ አይፈራም!” የመሳሰሉ ነገሮች በሕዝቡ እንዲጮሁ አደረገ፡፡ ሕዝቡ ሙጥኝ ማለቱን ቴዲ ሲያውቅ “ጃ ያስተሠርያልን ካልዘፈንኩ አትወዱኝም ማለት ነው?” ሲል ሕዝቡን ጠየቀ፡፡ ሕዝቡም በአንድ ድምፅ ያለአንዳች ማንገራገር “አዎ አንወድህም!” ሲል መለሰለት፡፡ ቴዲም “እንግዲያውስ እኔም አልዘፍነውም!” ብሎ ሌላ ዘፈን ዘፍኖ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ለሕዝቡ ተናገረና ሕዝቡ ተሸኘ፡፡

የቴዲ አምላኪዎች ግን “ቴዲ ጃ ያስተሠርያልን ያልተጫወተው ፈርቶ ወይም ተከልክሎ ሳይሆን ሕዝቡ በስሜት ተነሣሥቶ ግርግር እንዳይፈጥርና ችግር ላይ እንዳይወድቅ አስቦ ነው፡፡ ይሄም ሊያስመሰግነው ይገባል!” በማለት አጥብቀው ይሟገታሉ፡፡ ሐሰተኛ ምክንያት እንደሆነ በምክንያት ላረጋግጥላቹህ እወዳለሁ፡፡

ሲጀመር ዘፈኑን ጀመር በማድረግ ሕዝቡ ዘፈኑን መዝፈን እንዲጀምርና እንዲጓጓ እስከመጨረሻውም ሙጥኝ እንዲል ያደረገው ማን ሆነና??? ሲቀጥል ሕዝቡ በዚህ ዘፈን የተነሣ ግርግር ግጭት የሚፈጥር ቢሆን ኖሮ ለዚህ ዘፈን አለመዘፈን ምክንያት የሆነው ወያኔ እንደሆነ እንዲያስብ ስለተደረገ ያምፅ የነበረው ዘፈኑ ባለመዘፈኑ ነው እንጅ በመዘፈኑ አይደለም፡፡ ያለመዘፈኑ ምክንያት ወያኔ መሆኑን የተቀበለው ሕዝቡ ግን ያደረገው ነገር ምንድን ነበር? “ወያኔ ሌባ! ወያኔ ሌባ!” ብሎ ብቻ ነው ቅሬታውን ገልጾ በአደብ ወደየቤቱ የገባው እንጅ ሌላ ነገር ልፍጠር አላለም፡፡ ሦስተኛ ሕዝቡ የፈለገውን ያህል ስሜቱ ቢቀሰቀስ፣ ቁጭት ቢፈነቅለው ሰዓቱ ምሽት ወይም ጨለማ በመሆኑ ዐመፅ ግርግር ለመፍጠር የማይመች በመሆኑ ዐመፅ ወይም ግርግር መፍጠሩ የማይታሰብ ነበረ፡፡ ለዚህም ማረጋገጫው ይሄው ሦስተኛ ዓመቱን የያዘው ሕዝባዊው ዐመፅ ከተቀሰቀሰ ጊዜ ጀምሮ ሕዝቡ ዐመፁን በቀን ሲያደርግ ነው የቆየው እንጅ በጨለማ ያደረገበት ጊዜ አለመኖሩ ነው፡፡ በመሆኑም የከተበው ምክንያት አሳማኝና አመክንዮአዊ ሊሆን ቀርቶ ትንሽ እንኳ ሊመስል የሚችል አይደለም፡፡ ትክክለኛውን ምክንያት ራሱ ቴዎድሮስ “ዘፈኑን ዘፍኘ ማንንም ማስቀየም አልፈልግም!” ብሎ ተናግሯል፡፡ በመሆኑም ዘፈኑ ያልተዘፈነው ወያኔ እንዳይቀየም ተብሎ ነው አለቀ፡፡

ሲጀመር ሕዝቡን እንደ ውሻ ጃስ ሲሉት ሮጦ የሚይዝ እረፍ ሲሉት አደብ ገዝቶ የሚቀመጥ የራሱ የሚያስብበት፣ የሚያሰላስልበት፣ የሚወስንበት ጭንቅላት የሌለው ግልብ ተደርጎ መቆጠሩ እጅግ የሚያሳዝንና ለሕዝብ ያላቸውንም ንቀት የሚያሳይ ነው፡፡ ሕዝቡ ይሄንን ዘፈን ሙጥኝ ያለበት ምክንያት ዐመፅ የማስጀመሪያው ፊሽካ በቴዲ አፍ ውስጥ ስላለ በዚህ ዘፈን ፊሽካውን ነፍቶ ዐመፁን እንዲያስጀምርለት ፈልጎ ሳይሆን ዘፈኑ ያለንበትን ወቅታዊ የፖለቲካ (የእምነተ አሥተዳደር) ችግር የሚያወሳና የሚገልጥ ስለሆነ ብሶቱን በዘፈኑ ለመተንፈስ ነው፡፡ አለቀ! ምክንያቱ ተለቃልቆ ይሄው ነው ሌላ የለውም፡፡

ዘፈኑ ባይዘፈንም ሕዝቡ

“ወያኔ ሌባ! ወያኔ ሌባ!

ቢመችሽም ባይመችሽም – አንች ወያኔ አንለቅሽም!

አማራ – ማንንም የማይፈራ!”

በማለት ከቴዲው፦

“በ17 መርፌ በጠቀመው ቁምጣ፤

ለለውጥ ያጎፈረው ሥልጣን ላይ ሲወጣ፤

እንደ አምናው ባለቀን የአምናውን ከቀጣ፤

አዲስ ንጉሥ እንጅ ለውጥ መቸ መጣ፡፡”

ከሚለው የጃ ያስተሠርያል ስንኝ በላይ የወያኔን ማንነት በመግለጽ በማስተጋባት ብሶቱን በአንድነት ጮሆ ተንፍሷል፣ ቁጭቱን ገልጿል፡፡

ይሄ መተላለፍ ሊፈጠር የቻለው ቴዲ “ሕዝቡ ድግሴ ላይ የሚታደመው ሊጨፍር ሊዝናና ሊደሰት ነው!” ብሎ በማሰቡና ሕዝቡ ደግሞ እነ ጃ ያስተሠርያልን፣ እነ ኡኡታየን፣ እነ ባልደራሱን ወዘተ. አስቦ ብሶቴን እተነፍሳለሁ፣ ሐዘኔን በሙዚቃዊ ሙሾ በመቆዘም የሐዘን ስሜቴን አስታግሳለሁ ብሎ አስቦ መግባቱ ነው፡፡ ቴዲ ግን እንኳንና የወልዲያው ፍጅት በዋዜማውና በዕለቱ ለት ተፈጽሞ ቀርቶ ባሕርዳር አምና ፍጅት ተፈጽሞባት ሕዝቡ “ሐዘን ላይ ነን!” እያለ “የዘፈን ትዕይንት አያሳየን አንፈልግም!” እያለ ስንት የዘፈን ድግስ እንዳሰረዘ እያወቀ ሕዝቡ ሊዝናና፣ ሊደሰት፣ ሊጨፍር ነው የሚመጣው!” ብሎ አስቦ ያለ እነኝህ ዘፈኖች የዘፈን ትዕይንት ለማዘጋጀት ማሰቡ ነው እጅግ አስገራሚው ነገር፡፡

ሌላው አስገራሚው ነገር ደግሞ ይሄንን ያህል ለወያኔ በስፋት ከቸረው የፍቅር ያሸንፋል በረከት ወልዲያ ላይ ላለቁ ወገኖችንም ተርፎ እነሱንም ለማሰብ አለመብቃቱ “ወልዲያ ወልዲያ!” እያለ የሚጮኸውን ሕዝብ ሐዘን ለመጋራት አለመፍቀዱ ነው፡፡ ታዲያ ምኑ ላይ ነው ፍቅር ያሸንፋሉ? ለሕዝብ ያለውስ ክብር የቱ ነው? ነው ወይስ የቴዲ “ፍቅር ያሸንፋል!” መርሕ ትርጉም ያለ ዋጋ፣ ያለ ጠያቂ፣ ያለ አሳቢ፣ ያለ ማጉረምረም እንደ መሥዋዕት በግ እየታረዱ ማለቅ ማለት ነው???

ፍላጎታችን ቴዲ መሣሪያ አንሥቶ በፊታውራሪነት እንዲዘምትና እንዲያዘምት አይደለም፡፡ በሞያው ሳይፈራና ሳያፍር ሲያበረክት የነበረውን አስተዋጽኦ ማበርከቱን እንዲቀጥል ነው፡፡ “ዋጋ አያስከፍለውም ወይ?” ከሆነ ጥያቄው “አዎ ያስከፍለዋል!” ነው መልሱ፡፡ ሲያስከፍለውም ቆይቷል፡፡ ትግል ማለትም ይሄው ነው፡፡ ዋጋ ሳይከፈል የሚገኝ ነገር የለም፡፡ ድልም ተፈልጎ፣ ዋጋ መክፈልም ተጠልቶ ሊሆን የሚችል ነገር የለም፡፡ ሁሉም ሰው በሚችለው ሁሉ ለሕዝባዊው የነጻነት ትግል አስተዋጽኦ ማበርከት አለበት፡፡ የግድ ሁሉም በረሀ ይውረድ አይደለም ጥያቄው፡፡ ማበርከት በሚችለው ነገር ሁሉ አስተዋጽኦውን ያበርክት ነው፡፡ አለቀ!

እኔም ይሄው በምችለው እራሴን ለአደጋ አጋልጨ፣ መራራ ዋጋ እየከፈልኩ ሕዝብን በመቀስቀስ፣ በማንቃት፣ በማስተማር እያገለገልኩ ነው፡፡ ከዚህም አልፌ ከዚህ ቀደምም እንደገለጽኩላቹህ እንደ አጥፍቶ ጠፊዎች በወገቤ ፈንጅ ታጥቄ የወያኔ ባለሥልጣናት ባሉበት መሀል መገኘት ብችልና ይዣቸው መጥፋት ብችል ደስታውን እንደማልችለውና እንደሚያስጎመጀኝም ምኞቴን መግለጤ ይታወሳል፡፡ እየኳሸሁ አይደለም! የምሬን ነው፡፡ ምኞቱ ወደ ተግባር መለወጡ ቸገረ እንጅ፡፡

“ወያኔ የጠላውን ነገር መንካት አንፈልግም! ፣ አታድርጉ ያለውን ነገር ማድረግ አንፈልግም! ፣ ቴዲም እኛም ዋጋ መክፈል አንፈልግም!” ከሆነ እየተባለ ያለው እንግዲያውስ እያንዳንድሽ ማማረርሽን፣ ማለቃቀስሽን ትተሽ በገዛ ሀገርሽና ቀየሽ የጥራጊው፣ የወራዳው፣ የአህያው፣ የአረመኔው የወያኔ ባሪያ መሆንሽን አምነሽ ተቀብለሽ ፀጥ ለጥ ብለሽ ተገጠቢ፣ ግፍሽን ተጋች፣ ውርደትሽን ተከናነቢ፣ መጫወቻ መቀለጃ ሁኝ!!!

እናም ቴዲሾ ከሕዝብ ጋር አሁን የገጠምከው ችግር ይባሱኑ ተወሳስቦብህ አይወድቁ አወዳደቅ ከመውደቅህ በፊት ለእነኝህ ሁሉ ስሕተቶችህ በግንባርህ ተደፍተህ ሕዝባችንን ይቅርታ ጠይቅና ተመለስ፡፡ አድናቂዎችህን አግኝተህ ፍላጎታቸውን ማሟላትና ማርካት ካልቻልክ፣ በዚህም ምክንያት “አንወድህም!” እስከመባል ከደረስክ ለወያኔ ፈቃድ ተገዥ ሆነህ አድናቂዎችህን ማግኘትህ ኪሳራ እንጅ ትርፍ የለውም፡፡ ትጎዳበታለህ እንጅ አትጠቀምበትም፡፡

ስለዚህም ግድ የለህም ቴዲየ እኔን ስማኝ ይቅርብህና ተወው፡፡ ተመለስልንና በቀደመው ወኔህ፣ መሰጠትህ፣ ቁርጠኝነትህ፣ ጽናትህ ሀገርህንና ሕዝቧን አገልግል፡፡ ካንተ ብዙ ጃ ያስተሠርያሎችን፣ ብዙ ኡኡታየን፣ ብዙ ባልደራሱን እንጠብቃለን፡፡ እነኝህ ጃ ያስተተሠርያሎች፣ ኡኡታየዎች፣ ባልደራሱዎች ለሕዝባዊው የነጻነት ትግል ያለጥርጥር አስተዋጽኦ ያበረክታሉ፡፡

“አይ! ከዚህ በኋላ የምዘፍነው አዲስ ጃ ያስተሠርያል፣ አዲስ ኡኡታየ፣ አዲስ ባልደራሱ አይኖረኝም የበፊቶችም ወያኔን ስለሚያስቀይምብኝ ላላነሣቸው ጥያቸዋለሁ፡፡ ከዚህ በኋላ እነ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያን የመሳሰሉ ዜማዎችን ብቻ ነው መጫዎት የምፈልገው!” ካልክ ሕዝቡን ጠይቀኸው ከአንደበቱ በገዛ ጆሮህ በግልጽ እንደሰማኸው ምንም ስለማትጠቅመን አንፈልግህም! ፣ አንወድህም! ብቻ ሳይሆን ከዳተኛ ስለሆንክ እንጠላሃለን! እንወጋሃለንም፡፡ የምንጠላህ በሞያህ ስላልረዳኸን ስላላገለገልከን ብቻ አይደለም፡፡ ፍቅር ብሎ ነገር ፈጽሞ ሊገባው ለማይችለው ለአጋንንት ቡድን ለወያኔ ሕዝባችንን “ፍቅር ያሸንፋል!” እያልክ አዘናግተህ አሳንፈህ፣ አጃጅለህ፣ ትጥቃችንን አስፈትተህና አስጥለህ ለእርድ የምታቀርብና ወያኔን የምታገልገል፣ ተጠቃሚ የምታደርግ ሸፍጠኛ ጠላታችን በመሆንህም ነው፡፡

አሁን ራሱ ወያኔ ምን እንዳሰበ፣ ምን እንደደገሰ ሳታውቅ ላንተ ያሰበልህ መስሎህ ራሱ መጥቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ ኮንሰርቱን እንድታቀርብ አግባብቶ ካሳወጀህ በኋላ ወገኖቻችንን በጨፈጨፈበት ማግስትና ዕለት ሐዘን ያቆሰለውንና ያቃጠለውን ሕዝብ ሰብስበህ በመራር ሐዘኑ ላይ እንዲጨፍር ማድረግህ እርሙን አስበልተህ ቅስሙ እንዲሠበር፣ የሥነልቡና ሑከትና መቃወስ እንዲደርስበት፣ መንፈሱ በወያኔ የሸፍጥ መንፈስ እንዲቆስል፣ ክብሩ እንዲደፈር፣ ሰብእናው እንዲዋረድ፣ ማንነቱ እንዲጎድፍ አድርገህ ወያኔ በአማራ ሕዝብ ላይ ላደረሰው ሁለንተናዊ ጉዳት ዋነኛ ተባባሪ ሆነሀል፡፡ የወያኔ ሸፍጠኛ ቁማርም ይሄ ነበር፡፡

አንተ ግን በዚህ ደረጃ መጠቀሚያ መሆንህ ጥቂትም እንኳ አላስደነገጠህም፣ ያሳሰበህም አትመስልም፡፡ በስንት ጉትጎታና ጩኸት ትናንትና የመጽሐፈ ገጽ መዝገብህ (የፌስ ቡክ አካውንትህ) ላይ ጥቁር ምሥል በመለጠፍ አዝኛለሁ ለማለት ሞክረሀል፡፡ ይሁን እንጅ ከውስጥህ በፈለቀ ፍላጎትና ስሜት ሳይሆን ተገደህ ተጎትጉተህ ከረፈደ ያደረከው ስለሆነ ስሜት አልሰጠም፡፡ በዚህም እጅግ እንዳሳዘንከን እንድታውቅ እንፈልጋለን፡፡ ለዚህ ሁሉ ድርጊትህ ቶሎ ተመልሰህ ንስሐ ካልገባህበት፣ ሕዝብን ይቅርታ ካልጠየክበት ፈጽሞ ልትገምተው የማትችለውን ከባድ ዋጋ እንደሚያስከፍልህ እንድታውቅ!!!

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
amsalugkidan@gmail.com

Filed in: Amharic