>

በተቀደደለት ቦይ የሚፈስ ሁሉ ግሳንግስና  አሰስ-ገሰስ የተሸከመ ጎርፍ ነው

ድሸት ኢትዮጵ

” ማንም ሰው እግዚአብሄር የሰጠውን አእምሮ ብቻ በመጠቀም እውነትን ከተከተለ አፄ ምንሊክ በጦርም ሆነ በሰላም ያሳዩትን አመራርና ለሕዝብ ያላቸው ፍቅርና አክብሮት በቀላሉ መቀበል አያስቸግረውም ፤ ሕዝቡ እንደእናቱ ” እምዬ ” ሲላቸው ትእዛዛቸውን ለማክበር በሙሉ ልብ ተዘጋጅቶ ነው ፤ የገዛ ስንቁን ቋጥሮ ከወላይታና ከሲዳሞ ፣ ከከፋ፣ ከኢሉባቡርና ከወለጋ ፣ ከሐረርና ከአርሲ ፣ ከሸዋ ያንን ሁሉ ሰራዊት ከ5-6 ወራት በፈጀ የእግር ጉዞ አደዋ ድረስ ሄዶ ማዋጋት በጣም ከባድ ነው ። የአገሩ ሕዝብ ከዳር አስከዳር የተነቃነቀው በአንድ አዋጅ በቻ ነው ። ”
(ፕሮ/መስፍን ወ/ማሪያም-በአዲሱ መፅሐፋቸው)
.እንግዲህ ቀና አመለካከት ላለውና የመሰሪዎችን የፈጠራ ታሪክ ሰምቶ እንደጋሪ ፈረስ ላልሰገረ ዜጋ ሁሉ ፤ በእኚህ ሰው አመራራዊ ብቃት ፣ አስተዳደራዊ ጥበብና የማሰተባበር ብልሃት  መደመምና እንደ ኢትዮጵያዊነቱም በእሳቸው መኩራት አለመቻል አስገራሚ ሊሆን አይችልም ?

አንድ ዜጋ የሚነፍስለትንስ ፀረ-ምንሊክ የፈጠራ ታሪክን ከሚከተሉት ጥያቄዎች ጋር መዛመድ አይኖርበትም ?
.*በእውነት ይህን የመሰለ የሕዝብ ታዛዥነት ፣ ይህን የመሰለ ” እሺ ” ባይነት ለማይወዱት” ክፉ ገዢ ” እንዴት ሆነ ?
.*ዘመናዊ መገናኛና የትራንስፖርት አገልግሎት በሌለበት በዚያ ጨለማ ዘመን የንጉሳቸውን ጥሪ ተቀብለው ፤ ያውም ከአንደኛው የአገር ጥግ ወደ ሌላኛው የአገር ጥግ መስዋእት ለመሆን በእግር መትመምስ “ለክፉ መሪ ” (እምዬ ምንሊክ ክፉ ከሆኑ) እንዴት ተቻለ ?
.*ደግሞስ በሌላ መልኩ ከምንሊከ በፊትም ሆነ በኀላ ከነበሩት የኢትዮጵያ መሪዎች የበለጠ ጨቋኙና ጨካኙ እሳቸው ስለነበሩ ነው ?…. በዚህ የሕወሓት ዘመን ከሌሎቹ በተለየ /እንዲያውም ከደርግም በባሰ / በመንግስት ሳይቀር የውግዘት በትር በሳቸወ ላይ ብቻ ያረፈው ?..ወይስ ይህ ስርአት እሳቸውን በተመለከተ ሌላ አጀንዳ ስላለው ?
*ለመሆኑ ” እምዬ ” የሚለው መጠሪያ ቃልስ ምንሊክ ለሕዝባቸው በግድ ያሸከሙት ነው ?..
በግዛት ዘመናቸው ” በግድ አሸክመዋል ” ቢባል እንኳ ይህ ልብን በሐሴት የሚያሞቅ ስም እንዴት ትውልድና ዘመን ተሻጋሪ ሊሆን ቻለ?
.*ንጉስ ሲሞት ወይም ሲወድቅ ፤…. ከሞቱ ማግስት ጀምሮ ….. ክፋቱ ፣ ጉድፉ ፣ እንከኑ ፣ ጥፋቱ ፣ መጠላቱ ፣ ወዘተ..በአስለቃሾች ፣ በቆሎ ተማሪዎች ፣ በእረኞች ሳይቀር ለአደባባይ ይሰጣል ፤ ስለ ምንሊክ እምዬነትና ስለ ምንሊክ የአገር እናትነት ግን በነዚህ የህብረተሰቡ እውነት ነጋሪዎች ዘንድ በአሉታዊ ገፅታ ስለመነሳቱ ብዙ መረጃ ለምን አልኖረም ?
.ለማነኛውም በተቀደደለት ቦይ የሚንደረደርና የሚፈስ ሁሉ ግሳንግስና አሰስ-ገሰስ የተሸከመ ጎርፍ ነው ፤ ያልተጨበጠ ፣ ያውም በመሰሪዎች ሴራ የፈበረከ ፀረ-ምንሊክ ትርክትን ተቀብሎ እንደበቀቀን ማስተጋባትም ከግዑዙ ጎርፍ ተሽሎ አለመገኘት ነው ።
.
ክብር ለምዬ ምንሊክና ለሀገር ለሰሩት ውለታ !!!
Filed in: Amharic