>
5:18 pm - Monday June 15, 5040

አሁን የበደል ፅዋ ሞልቶም እየፈሰሰ ነው!! (መስከረም አበራ)

ወልድያ ላይ የሆነውን በተመለከተ እንደሰማሁ የናጠኝ ክፉ የመጠቃት ስሜት ብዕር የሚያስነሳ ሆኖ አልተሰማኝም፨ በዛ ስሜት ውስጥ ሆኘ ብፅፍ ጥሩ እንዳልሆነ ከራሴ ጋር መክሬ ዋል አደር ማለቱን መረጥኩ፨

ለአማራ ህዝብ ኢትዮጵያዊነቱን ማጉላቱም አማራነቱን ማውሳቱም በበጎ አይታይለትም፨ ሁለቱም ውስጥ አንዳች ክፉ ነገር የጠነሰሰ እንደሆነ ይታሰባል፨ የዘመኑ መንፈስ ነውና በአማራነቱ ተደራጅቶ ጥቃቱን ለመመከት ቢሞክር ያለአባት በሆነ ሁኔታ በመጥበብ ፣ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነትን ፈተና ውስጥ በመክተት ይብጠለጠላል፨ ኢትዮጵያዊነቱን ሲያጠብቅ በትምክህተኛነት፣ የድሮውን ስርአት በመናፈቅ ፣ በኢትዮጵያዊነት ሽፋን የበላይነቱን ለማስፈን ነው ተብሎ የጎሪጥ ይታያል፨ መከራው ሲብስ ደግሞ ብአዴንን የመሰለ ይዞ አስገራፊ የጉያ ረመጥ ተሸክሞ ይዞራል፨ በረከት ስምኦንን የመሰለ አቃፊ መሳይ ገፍታሪ፤ “አማራ ካልሆንኩ ሞቸ እገኛለሁ” ባይ ተኩላ ይመላለስበታል፨ እዚህ ሃገር እንደ አማራ ህዝብ ግራ የገባው አለ ይሆን???

በነኩት ቁጥር የማይበረግገው ፣ የገለባ ካድሬን ዘለፋ ለመናቅ በራስ መተማመን የማይቸግረው፣ ሙያን በልብ ማድረግ የሚያውቀው የአማራ ህዝብ እስከዛሬ የሆነበትን ሁሉ ቸል ያለው እንደሚባለው አህያ ስለሆነ አይደለም ! ይልቅስ የተነሳ ዕለት በቀልድ እንደማይመለስ ስለሚያውቅ፤ የበደል ፅዋ በማያስመልስ ሁኔታ እስኪሞላ ለመታገስ ነበር፨ አሁን የበደል ፅዋ ሞልቶም እየፈሰሰ ነው! በታቦት ፊት በጥይት ከመረፍረፍ አልፎ የማተቡ ማህተም የሆነውን ታቦት የተሸከመ ካህን በአምባገነኖች ጭስ መሬት ሲንከባለል አይቷል፨

የሚገርመው ይህን ሁሉ የሚያደርጉ አውሬዎችን ቤት ለእንግዳ የሚሉ ባለጊዜዎች በላይ ሆነው እንደተበደሉ ፣ ዘራቸው ብቻ ተቆጥሮ እንደተጠቁ ለማስመሰል የተለመደ የቆርቆሮ ጩኸታቸውን ማንኳኳታቸው ነው፨ ከትናንት በስቲያ በቪኦኤ ቀርበው ጩኸት ያበረከቱት አቶ ሃይላይ የተባሉ ሰው ሰላሳ አመት ከኖሩበት ወልዲያ ከተማ ቤተሰቦቻቸውን ይዘው ወደመቀሌ መሸሻቸውን እያዳነቁ ያወራሉ፤ እዛው ሃገር የህንፃ ባለቤት መሆናቸውን ያክላሉ (ምን ሰርተው፣ ከመቼ ወዲህ ባለፎቅ እንደሆኑ መገመት አያዳግትም)፨

ሰውየው የደረሰባቸውን በደል ሲያወሩ እሳቸው እና መሰሎቻቸው ቀን ሰጥቷቸው በገተሩት ፎቅ ጫፍ ላይ ሰፍረው የድሃ ልጅ በመትረይስ ከሚፈጁ እርኩሶች ጋር ያላቸውን ግንኙነት አያወሩም፨ የቀጣፊ እምባ እምቧይ ያካክላል እንደሚባለው የአዞ እምባቸውን ሲያነቡ ምሬት አሳብዶት ቤታቸው የተገኘውን ህዝብ በተራ ዘራፊነት ይከሳሉ፣ (ዘራፊ ከዘረፋ ውጭ ሌላ ሊታየው አይችልም )፣ የተጠቃውም የትግሬ ቤት ብቻ እንደሆነ ለማስመሰል የራሳቸውን የዘረኝነት ጭቃ ዘር መቁጠር በማይሆንለት ህዝብ ላይ ለመቀባት ይቀባጥራሉ (ጋዜጠኛ ሰለሞን ምስጋና ይግባውና የዛው አካባቢ ተወላጆች ቤት አልተነካም ሲል አጥብቆ ጠየቀ በስተመጨረሻ እያቃራቸውም ቢሆን የተጠቃው የትግሬ ቤት ብቻ እንዳልሆነ በገደምዳሜ አመኑ ፤ ጠያቂዋ አዳነች ፍስሃየ አለመሆኗ ደግ ነገር !)፨

ይሉኝታቢስነት እንዲህ ነው! ‘እንዴት እንደተሰራ በሚያነጋግራችሁ ፎቅ አናት ላይ የሰው አውሬ እንደ ዶሮ አስፍሬ አናታችሁን በመትረይስ ሳስበረቅስ ዝም በሉኝ፤ ያኔ ደግነታችሁን አውቃለሁ ነው ነገሩ’፨ ከገዳይ ጋር የወገነ ትግሬ ሆነ አደሬ፣ ተጉለቴ ሆነ ሞረቴ ደም በመጠጠበት ሃገር ፎቁን እያመለከ ተዝናንቶ ትናንት ተኖሯል ማለት ነገም ይኖራል ማለት አይደለም! ልጅ ውላጅን አንኳትቶ መቀሌ መግባት በደል ሆኖ ከተወራ ለጥምቀት ነጭ ለብሶ ወጥቶ በመትረይስ መቆላት ምን ሊባል ነው ?!

በህዝብ ላይ እያላገጡ መምነሽነሽ ድሮ ቀረ!!! ዛሬ ቀኑ ሌላ ነው ፤ ፅድቅ ሃጢያት ሳይመርጡ ያጋፈፉትን እንደ አዛባ የከበደ ሃብት ሳይበሉት ከነ ልጅ ልጅ እግሬ አውጭኝ ብሎ መፈርጠጥም አለ፤ ያግበሰበሱትን ሁሉ እግርን ዘርግቶ መብላት መቻል አለመቻሉን የሚወስነው ሁሉንበቅርብ ሆኖ የሚያውቀው የአካባቢው ህዝብ እንጅ አዲስ አበባ ስልጣን ላይ ቂጥጥ ያለው የወንዝ ልጅ አይደለም !!ጌታን አምኖ ውጭ ማደር አምና ቀረ!!! ደግሞስ አራቱም ማዕዘን ከተዘጋበት ከወልድያ ከተማ መቀሌ የተገባው በምን ምስጢር ነው ?! – “ለፃድቃን” ጥበቃ በተመደቡ መላዕክት ክንፍ ???¡¡¡

Filed in: Amharic