>

ሕይወት ብለን ሞት - ለልጆቻችን አወረስን! (ሎሬንት ጸጋዬ ገብረመድህን)

 
ባለቅኔ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድን 1967 ዓም በ“እናት ዓለም ጠኑ” ቲያትራቸው ውስጥ “ዳንበል” በተባለ ገፀ-ባሕርይ አማካኝነት የተናገሩት መራር ዕውነት የዛሬ ኢትዮጵያዊ ማንነታችንን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ይመስላል፡፡ ስለዚህም የ“ዳንበል”ን ቃለ- ተውኔት ላካፍላችሁ ወደድኩ፡፡ እነሆ፡-
አፋዊ ሆንን!

ሕያዊ ሳንሆን አፋዊ!
ቃለ ሕይወት ሳንሆን፣ ብኩን ቃለ-አፍ ብቻ!
እንጂ! ቤታችን አንድ ነው፡፡
“ቤት” ብለን ለልጆቻችን ያወረስናቸው
ፍቅር የሞተበት ቤታችን! አንድ ነው፡፡
አባቶቻችን ልባም
እኛ አፋም፡፡
እሳት ዐመድ ወለደ ሆንን እንጂ- ቤታችንስ አንድ ነው፡፡
ነፃነት ብለን ባርነት
ሕይወት ብለን ሞት – ለልጆቻችን አወረስን፡፡
ብኩን ቃለ-አፍ!
ህይወት ብለን ንፍገት
ጀግንነት ብለን ፍርሃት – ከተብናቸው!
በወረረን ባዕድ ሞት ማግስት፣
አዲስ ተስፋ ለተራበ ህልውና፤ አዲስ የሃገር ውስጥ ሞት!
ለአዲስ ትንሳዔ በቃተተ ዓይን
አዲስ መቃብር ከፈትን!
አፋዊ! ጋዜጣዊ!- ብኩን የሃሰት ነፃነት ዘረጋን!
ልጆቻችን በተስፋ ልክፍት ቃ‘ተው መከኑ!!
አንዲት የዱር አውሬ – በምትወልድበት ሰሞን
ልጇን ትበላለች ይላሉ – ምጥ የበዛባት እንደሆን
ልጆቻችንን በላን!
ትናንት የነፃነትን ምጥ ከአፋፍ መንግለን
የጥላቻ ውርስ አቆይተን
አፋዊ ነፃነት አውርሰን
“ምነው?” ባሉ! ልጆቻችንን ገፍተን
አፋዊ እኩልነት- አፋዊ ክትባት ከትበን
ፍርሃት ወርሰን – ፍርሃት አውርሰን
ጥላቻ ወርሰን – ጥላቻ አውርሰን
ሕያው ሳንሆን አፋዊ
ቃለህይወት ሳንሆን ብኩን ቃለ አፍ
እንጂ ቤታችንስ አንድ ነው፡፡
ትናንት የነፃነትን ምጥ ከአፋፍ መንግለን
የጥላቻ ውርስ አቆይተን
አፋዊ ነፃነት አውርሰን
“ምነው?” ባሉ! ፈረድንባቸው!
በልጆቻችን ፈረድንባቸው!!
የህይወት ጣሙን ሳይሆን – ወጉን
የፍቅር ወዙን ሳይሆን – ስሙን
የነፃነት ግብሩን ሳይሆን – ተረቱን
እንዳወረስናቸው ባወቁብን
በነቁብን
ፈረድንባቸው፡፡
ፍቅራችን የሻል ወርቅ፣ የነጭ ጓንቲ፡ የተከፈለ ፎቶግራፍና የድግስ ጃዝ እንጂ የልብ እውነት፣ የእሳትና አበባ ጉዳይ አለመሆኑን ባወቁብን፣ በነቁብን፤ ፈረድንባቸው፡፡
የዕውቀት ሙቀታቸውን
በበድን ቅዝቃዜያችን
ቸስቸስ አድርገን – አቀዘቅዝናቸው!
መንፈሳቸውን አኮላሸናቸው፡፡
አበው ያወረሱንን ሰብዓዊ የፍቅር ግለት በውስጣችን አክስለን
እንደመንጋ በዘፈቀደ መፈቃቀዳችንን
በልተን ጠጥተን – ጓሮ እንደመዞር መገናኘታችንን
ሆድሞልተን – ሜዳ እንደመውጣት መፈቃቀዳችንን
ፍቅርን እንደዐቃቢት ቃል ኑዛዜ፣ ምላሳችን ላይአሻግተን ማነብነባችንን
ልጆቻችን ነቅተው ባዩብን – ፈረድንባቸው!
አዎ! – እንጂ ቤታችንስ አንድ ነው፡፡
ላሳበድናቸውም ላወናበድናቸውም
ለሳቁብንም ለተሳለቁብንም
ለገፉንም ለተቀበሉንም
ላጭበረበርናቸውም ለፈነገልናቸውም
ያወረስናቸው ቤታችን
ፍቅር የሞተበት ቤታችን – ያው አንድ ነው፡፡
የታሪክ እጢያችንን – ጥለን ከርመን ፣
የሌለብንን ሐቀኝነት – ሰብዓዊነት- በወሬ ግተን አደድረን
ልጆቻችን አድገው
ምስጢሩን ገልጠው
ያቆየናቸው ብኩን አፋዊ ቅዠት እንጂ – ሕያው አለመሆኑን ነቅተው ያዩበት
ፍቅር የሞተበት
ቤታችን
ያው አንድ ነው!!
እኛ ፈላስሞቹ ….
ደምሰው መርሻ
Filed in: Amharic