>

የህወሓቱ የቂሊንጦ እስር ቤት ኃላፊ የፖለቲካ እስረኞችን ለመግደል መዛቱ ተገለጸ

BBN_ቂሊንጦ ጥር/18/2010
በቂሊንጦ እስር ቤት በኃላፊነት ቦታ ላይ የሚሰራ የህወሓት ሰው፣ በፖለቲካ እስረኞች ላይ ግድያ ሊፈጸም እንደሚችል በዛቻ መልክ ተናገረ፡፡ በቂሊንጦ እስር ቤት ተነስቶ በነበረው የእሳት ቃጠሎ እጃችሁ አለበት ተብለው የፖለቲካ ክስ የተመሰረተባቸው ተከሳሾች ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበው ነበር፡፡ በእነ ማስረሻ ሰጤ መዝገብ ክስ የተመሰረተባቸው 38ቱ የፖለቲካ እስረኞች፣ የዓቃቤ ህግን ቀሪ ሁለት ምስክሮች ለማዳመጥ ዛሬ አርብ ጥር 18 ቀን 2010 ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ቢቀርቡም፤ የዓቃቤ ህግ ምስክሮች ግን በችሎቱ ሊገኙ አልቻሉም፡፡

ከዚህ ቀደም ‹‹ምስክር›› ያላቸውን 28 ሰዎች ፍርድ ቤት አቅርቦ ማስደመጥ ባለመቻሉ፣ ምስክር የመስማት ሂደቱ የታለፈበት ከሳሽ ዓቃቤ ህግ፤ ለመጨረሻ ጊዜ እንዲቀርቡ የተባሉትን ሁለት ምስክሮችም በዛሬው ዕለት ሊያቀርብ አልቻለም ተብሏል፡፡ ቀሪ ምስክሮችን ለማቅረብ ለመጨረሻ ጊዜ ዕድል እንዲሰጠው የጠየቀው ዓቃቤ ህግ፤ ከተከሳሾች እና ከጠበቆቻቸው ተቃውሞ የገጠመው ሲሆን፤ የተከሳሾች ጠበቆች ፍርድ ቤቱ ምስክር የመስማት ሂደቱን አልፎ በመዝገቡ ላይ ብይን እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡ ዓቃቤ ህግ በተደጋጋሚ የተሰጠውን ምስክር የማሰማት ቀጠሮ ባለመጠቀሙ፣ ምስክር የማሰማት ሂደቱ እንደተዘለለበት ችሎቱን የተከታተሉ እማኞች ጽፈዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ በመዝገቡ ላይ ብይን ለመስጠትም ለመጋቢት 3 ቀን 2010 ቀጠሮ መያዙ ታውቋል፡፡

የዓቃቤ ህግን ‹‹ምስክሮችን›› ለመስማት ዛሬ አርብ ጥር 18 ቀን 2010 ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት የተገኙት ተከሳሾች፣ እየደረሰባቸው የሚገኘውን ግፍ እና መከራ ለፍርድ ቤቱ ያብራሩ ሲሆን፤ በመዝገቡ 32ኛ ተከሳሽ የሆነው ቶፊቅ ሽኩር በበኩሉ፣ ገ/ እግዚያብሔር ገ/ሐዋርያት የተባለው የቂሊንጦ እስር ቤት ኃላፊ ‹‹እንገድላችኋለን›› ብሎ እንደዛተበት ገልጿል፡፡ ከእስር ቤት ውጭ ካለው ወቅታዊ የሀገሪቱ ሁኔታ ጋር በተገናኘ፣ ‹‹ከፈለግን እንገድላችኋለን!›› የሚል የማስፈራሪያ ቃል የህወሓቱ ሰው እንደተናገረው የገለጸው ተከሳሽ ቶፊቅ፤ ‹‹ትናንት ጠርቶ ውጭ ያለውን ሁኔታ ታውቃላችሁ፤ ከፈለግን በጥይት እንመታችኋለን፤ እንገድላችኋለን ብሎናል፡፡›› ሲልም የህወሓቱ የእስር ቤት አለቃ ያደረሰውን የግድያ ዛቻ እና ማስፈራሪያ ዘርዝሯል፡፡

ከህወሓቱ ሰው በደረሰው ዛቻ እና ማስፈራሪያ የተነሳ ‹‹ለህይወታችን ዋስትና የለንም!›› ሲል ለችሎቱ የተናገረው ተከሳሹ፤ በቀጣይ ህይወታቸው አስጊ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ እና ለደህንነታቸውም እንደሚሰጉ አክሏል፡፡ በዚሁ የክስ መዝገብ የተከሰሰ ሌላ ሰው፣ በቂሊንጦ እስር ቤት የግድያ ዛቻ እና ማስፈራሪያ እየደረሰው እንደሆነ በመግለጽ፤ ለህይወቱ እንደሚሰጋ ከዚህ ቀደም በነበረ የፍርድ ቤት ችሎት ተናግሮ ነበር፡፡ በፖለቲካ እስረኞች ላይ እየደረሰ ያለው ዛቻ እና ማስፈራሪያ አሁንም እንደቀጠለ መሆኑን የዛሬው ችሎት አረጋግጧል፡፡
ከዚህ ቀደም በነበረ ችሎት ምስክርነት ለመስጠት ፍርድ ቤት ቀርቦ የነበረው እና ገብረማርያም ወልዳይ የተባለው የቂሊንጦ እስር ቤት የደህንነት እና ጥበቃ ክፍል ኃላፊ፣ ምስክርነት በሚሰጥበት ወቅት ተከሳሾች ‹‹አፋጥጠውታል›› በሚል ምክንያት ወከባ እና ዛቻ ሲደርስባቸው ነበር፡፡ በደረሰባቸው ዛቻ እና ማስፈራሪያ ‹‹ለህይወታችን እንሰጋለን!›› ሲሉ የፖለቲካ እስረኞቹ ተናግረው ነበር፡፡ ተከሳሾቹ የቂሊንጦ እስር ቤት ኃላፈዎች ከሆኑት የህወሓት ሰዎች ዛቻ እና ማስፈራሪያ እየገጠማቸው እንደሚገኝ ከዚህ ቀደም ለፍርድ ቤት አመልክተው ነበር፡፡ ተከሳሾች ባቀረቡት አቤቱታ መሰረት፣ የእስር ቤቱ ኃላፊ ችሎት ተገኝተው ምላሽ እንዲሰጡ ትዕዛዝ ተሰጥቶ የነበረ ቢሆንም፤ ትዕዛዙ ተፈጻሚ መሆን ባለመቻሉ፣ የእስር ቤቱ ኃላፊዎች ምላሽ ሳይሰጡ እንደቀረም ተነግሯል፡፡

በተለያዩ እስር ቤቶች የኃላፊነት ቦታዎችን ይዘው የሚገኙት የህወሓት ሰዎች፤ ዛሬም ንጹኃንን ለመግደል ዝግጁ መሆናቸውን በተከሳሽ ቶፊቅ ሽኩር በኩል ለተከሳሾቹ ያደረሱት ዛቻ እና ማስፈራሪያ ማረጋገጫ እንደሚሆን ታዛቢዎች ይናገራሉ፡፡ ከቂሊንጦ ኃላፊዎች አንዱ የሆነው ገ/ እግዚያብሔር ገ/ሐዋርያት የዛተው የግድያ ዛቻ፣ ከእስር ቤት ውጭ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እየተካሄደ ያለው ህዝባዊ ተቃውሞ፣ የህወሓት ባለስልጣናትን ስጋት ላይ እንደጣላቸው ያመላክታል ሲሉም ታዛቢዎቹ ገልጸዋል፡፡ አክለውም፡- ህዝባዊ ትግሉ እየገፋ ሲመጣ፣ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ የተቀመጡ የህወሓት ባለስልጣናት፣ የበቀል እርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ ሲሉም አገዛዙ ምን ያህል በተስፋ መቁረጥ ውስጥ እንደሚገኝ አመላክተዋል፡፡

Filed in: Amharic