>

ኤች አይ ቪ ኤድስ እንድያዝ የተፈፀመብኝ ተንኮል (ሻምበል አስረስ ብዙነህ ጎጃሜው) - በጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው

~ የትህነግ/ህወሓት መከላከያ ውስጥ የተሰራ ዘግናኝ ወንጀል፣ የሻምበሉ አሳዛኝ ታሪክ

ከአፋር ወደ ሽራሮና ወደ ሌሎች ግምባሮች  በመጓዝ  ብዙ  ውጤታማ ስራዎችን ሰርቻለሁ። በ1992 ዓም  ከሻዕቢያ በተተኮሰ  የከባድ መሳርያ ፍንጣሪ ቆሰልኩ። አብረውኝ የሚሰሩት አብዛኛዎቹ ሲቪሎች ስለነበሩ  ደንግጠው ይመስለኛል፣ በወቅቱ እርዳታ አላደረጉልኝም። ደሜ ፈሶ አልቆ መናገር አልችልም ነበር። ራሴን ስቼ ነበር በፊልድ ሐኪሞች የተነሳሁት። ሐኪሞች አንስተው  ወስደው ፊልድ ሆስፒታል ድንኳን  ውስጥ አስተኙኝ።

አሁን አንባቢን የሚፈታተን የሕይወት እጣዬን ላካፍላችሁ። ……ለስልጣን ሲባል ምን ያህል  ለህሊና የሚቀፍ ነገር  እንደሚፈፀም አንባቢ ቢያውቀው  ክፋት የለውም በሚል ነው የፃፍኩት።

በተፈጥሮዬ  ማጎብደድ መጎናበስ አላውቅም።  ……ስራየን ይህ ምስኪን ሕዝብ ከኪሱ አውጥቶ ለሚከፍለኝ ደመወዝ  የተመጣጠነ ስራ ለመስራት  እተጋለሁ።።… ይህን የማደርገው በዚህ ዝብርቅርቅ አስተዳደር ነው።  የምሰራው  ከሚከፈለኝ ዋጋና አቅሜ በታች ከሆነም በራሴ ራሴን እከሳለሁ።

በዚህ ምክንያት የአንድ ሀገር ህዝቦች ሆነን፣በሀገር መከላከያ ውስጥ በቆየሁበት ጊዜ ከችሎታ ችሎታ፣ ከትምህርት ትምህርት፣ከአገልግሎት አገልግሎት የሌላቸው ሰዎች “ምርጥ ዘር” በመሆናቸው ብቻ ፣ ያለ አቅማቸው ከአቅማቸው  በላይ ዋጋ ሲከፈላቸው፣ በአንፃሩ ደግሞ በቂ  የስራ ችሎታ ፣ በቂ የትምህርት ዝግጅት እና በርካታ አመት የስራ ልምድ  ያላቸው ዜጎች  ከእውቀታቸውና  ከስራቸው  ጋር የማይጣጣምና የማይመጣጠን  ዋጋ ሲከፈላቸው ሳይ፣ቦታው  ህይወት የሚያስከፍል ቢሆንም  በድፍረት ተቃውሞዬን  በመግለፅ እዳፈር ነበር።

በጠቅላላው የኢህአዴግ የመከላከያ ሠራዊት  ቤት  ጥቅምና የተሟላ ኑሮ ወደ አንድ ወገን  እያደላ ሲሄድ በጣም አዝን ነበር።  እኔ  መፍትሄ አመጣ ይመስል አላስችል እያለኝ ፊት ለፊት  ከማይነቃነቅ  ድንጋይ ጋር በተደጋጋሚ ተጋጭቻለሁ። ለእውነት መቆሜ ብዙ አስከፍሎኛል።

ይሄው ባህሪዬ  በመንግስቱ ኃይለማርያም  መዳፍ ውስጥ ሊያስጨፈልቀኝ ነበር። ደግነቱ ቀድሜ ሸሽቻለሁ። ምን ያደርጋል፣  እድሜ ልኩን በቁም መግደል  ከሚችልበት የህወሓት/ኢህአዴግ መዳፍ ውስጥ ወድቄያለሁ። ጨካኝ ካድሬዎች በ1992  በሻዕቢያ ጥይት ቆስዬ ሆስፒታል ተኝቼ ሳለ፣ በተፈጠረ አጋጣሚ በየጊዜው  እየተሟገተች የተዳፈረቻቸውን ምላሴን ፀጥ ለማድረግ፣ በበሽታ እንድመረዝ አደረጉ።

ዘመኑ እጅግ በተራቀቀበት ወቅት አንድ በኤች አይ ቪ ታሞ አጠገቤ ከተኛ የአስር አለቃ  (የአድዋ ልጅ ነው) የደህንነት ሰራተኛ የተወጋበትን መርፌ እንስት ሀኪም ተብየዋ ረዳት ተጋደልቲ ወጋችኝ። በወቅቱ  መንቀሳቀስ አልችልምና  እዚያው በተኛሁበት  “እሪ”  ብዬ ጮህኩ። ወዲያውኑ  የዋርዱ ኃላፊ  ዶክተር ሳምሶን የሚባል  ሲቪል ወጣት  መጥቶ “ምን ሆንክ?” ብሎ ሲጠይቀኝ፣ “እንዴት በሌላ ሰው መርፌ ትወጋኛለች? መርፌ ደግሞ እየቀቀሉ መጠቀም እንኳ ድሮ ቀርቷል……” እያልኩ ጮህኩ።

ይች ተጋደልቲ ሐኪም በድንገት የተሳሳተች ለመምሰል  ከወዲያ ወዲህ ትሯሯጣለች  አንባቢያን ሊረዳልኝ የምፈልገው በመጀመሪያ እኔ መኮንን ነኝ። አጠገቤ የተኛው ደግሞ አስር አለቃ ነው። በወታደራዊ ህግ በኩል አስር አለቃው መኮንኖች ዋርድ የመተኛት መብት የለውም። ሆን ተብሎ በእቅድ የተሰራ ነበር።

“ዶክተር እንዴት እንዲህ ይደረጋል?” ብየ አለቀስኩበት። ዶክተሩ የታዘዘውን መስራት እንጅ ምንም ሥልጣን እንደሌለው  እናውቃለን። በተራ ተጋዳልቲ  እየታዘዘ ነው የሚሰራው። እናም የተወጋሁትን ታፋዬን በአልኮል እያጠበ “አይዞህ ምንም አይደል!” እያለ ሊያፅናናኝ ሞከረ። በጣም ማዘኑ ከፊቱ ያስታውቃል። ከዶክተሩ ጋር የምትሰራዋ ሌላኛዋ ሲቪል ነርስም በጣም እያዘነች ነበር። እራሷን እያረጋጋች “ለማንኛውም  ከወር በኋላ ቸክ አድርግ!”አለችኝ። ይህች ነርስ ዛሬም በህይወት አለች። ዶክተሩን ግን ከዚያች ጊዜ በኋላ አላየሁትም። የት እንዳለም አላውቅም።

አጠገቤ ተኝቶ የነበረው አስር አለቃ  ደህንነት አይኔ እያየ አጠገቤ ሞተ።  ከዚህ በኋላማ ለደቂቃም አእምሮዬ  ሊያርፍ አልቻለም። ውስጤ በፍርሃት እየራደ አለቀ። ነርሷ እንደመከረችኝ  በወሩ ስመረመር “ያጠራጥራል” ተባለ። ቁስሌ  ሲያገግም  ከትግራይ ወደ አዲስ አበባ ጦር ኃይሎች ሆስፒታል ተላኩ። በሁለተኛው ወር አዲስ አበባ ስመረመር “ፖዘቲቭ” መሆኔ ተነገረኝ። ይህ  ውጤት ሲነገረኝ አራት ቀን ምግብ አልበላሁም። እንቅልፍ የሚባል በአይኔ አልዞር አለ። ኒሞኒያው፣ቲቪው፣ አልማዝ ባለጭራው፣ ጉንፋኑ  …ምኑን ልንገራችሁ?  በሽታ ሁሉ  እንደ ንብ መንጋ የሰፈረብኝ መሰለኝ። ከሆስፒታል ወጥቼ ቤቴን ትቼ ጃንሜዳ ሜዳው ላይ 3 ቀን ዋልኩ። አደርኩ። በ3ኛው ቀን ቤተሰብ ፈልጎ አገኘኝና በስንት ልመና ወደ ቤቴ ገባሁ።

ከመስርያ ቤት የስራ ስንብት ጠየኩ።  ማመልከቻዬ ታይቶ ሳይፈቀድልኝ ቀረ።  ያልተፈቀደልኝ ደግሞ  ለኔ ታስቦ ወይም ስለምጠቅማቸው አይደለም። ከእነሱ ስላልመጣ ነው። እናም በህክምና ምክንያት  ብዙ ጉዳት  ደረሶብኝ  ይኸው ከሞትኩ ቆየሁ።

(ታሪኩ ሻምበሉ ከፃፉት የካድሬው ማስታወሻ መፅሐፍ ላይ የተወሰደ ነው)

Filed in: Amharic