>

ወገን ሆይ! ምንድን ነው የምንጠብቀው??? (ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)

እንዴ! ዝም ብለን እየተመለከትን ወገኖቻችንን አስጨረስናቸው እኮ!!! እንዴ! ሁላችንም እንነሣ እንጅ ምንድን ነው የምንጠብቀው??? ኧረ ከእንቅልፋችን እንንቃ!!!

ሕዝባዊው ዐመፅ ከተቀሰቀሰ ሁለት ዓመታት አለፈው፡፡ እስከአሁን ሕዝቡ በተለያየ ጊዜ በተለያዩ አካባቢዎች የወያኔ አገዛዝ እንደበቃው፣ እንደማይፈልገው በዐመፅ ሲገልጽ ቆየ እንጅ በተመሳሳይ ሰዓት ሁሉም ቦታ ላይ ማድረግ አልተቻለም፡፡ ይሄም መሆኑ ለወያኔ ተመችቶታል፡፡

በተለይም እስከአሁን ባለው ጊዜ አዲስ አበባ ሕዝባዊውን ዐመፅ አለመቀላቀሏ ችግሩ የተወሰኑ አካባቢዎች መስሎ እንዲታይ አድርጎታል፡፡ አዲስ አበባን ሕዝባዊውን ዐመፅ እንዳትቀላል ያደረጋት የአዲስ አበባ ነዋሪ ሕዝብ ከሁሉም አካባቢ የመጣ በመሆኑና የተለያየ እርስበርሱ የማይስማማ ጩኸት ለሚንጸባረቅበት የጎሳ ፖለቲካ አዲስ አበባ የተለያየ ወይም ወጥ ያልሆነ ምላሽ ለመስጠት ስለሚቸግራትና ስለማትፈልግም ነው፡፡

ይሁንና አዲስ አበባ በዚህ መልኩ እስከመጨረሻው መቀጠል እንደማትችልና እንደማትፈልግም ዓይነ ውኃዋን ዓይታቹህ መረዳት ትችላላቹህ፡፡ በጎሳ ፖለቲካ ከፋፋይነት የተነሣ ዐመፅ ለማድረግ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ባይሟላላትም እንኳ ዐመፅ ለማድረግ የሆነ የራሷን ጊዜና ሁኔታ እየጠበቀች እንዳለች እንዲሁ መረዳት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ እንዲህ እንደሰሞኑ ወያኔ በማንአለብኝነትና በእብሪት በየቦታው በሕዝብ ላይ የሚፈጸሙ የግፍ ግድያ ትዕግሥቷን ከሚያሟጥጡት ጉዳዮች ዋነኛው ነው፡፡ አዲስ አበባን ዝም ብላቹህ ስታዩዋት “እንዴ አሁንስ በዛ!” እያለች ለራሷ እያጉረመረመች እንዳለች ዓይታቹሃት ትረዷታላቹህ፡፡

እኔም በዚህ አጋጣሚ አዱገነትን “አዎ አሁንስ በዝቷል በቃ!” በይና ቤተመንግሥቱን ተቆጣጠሪ፣ ከቤተ መንግሥት ውጭ በተቀናጡ መኖሪያ ቤቶቻቸው ተዝመንምነው የሚኖሩትን የወያኔ ባለሥልጣናትን እያነቅሽ በቁጥጥር ሥር አውይና የግፍ አገዛዙን ዕድሜ አሳጥሪው ልላት እወዳለሁ፡፡ አዎ አዱ ገነት ሆይ! ትችያለሽ አቅሙም በሚገባ አለሽ! አድርጊው??? ታደርጊዋለሽም!!!

ሰሞኑን ወያኔ ወልዲያ የቃና ዘገሊላ ለት ታቦተሕጉን በመሸኘት ላይ በነበረ ሕዝብ ላይ አስቀድሞ የሰበበትን የግፍ ግድያ መፈጸሙን ተከትሎ የወልዲያ ሕዝብ ማድረግ የሚጠበቅበትን የአጸፋ እርምጃ የቻለውን ያህል ወስዷል፡፡ በወልዲያ ሕዝብ ላይ የተፈጸመውን ኢሰብአዊ ግፍ በመቃወም የራያቆቦ ሕዝብ ላሰማው የተቃውሞ ድምፅ ወያኔ የወሰደው እርምጃ የከፋና በሔሊኮፕተር (በደውደዊት) የተደገፈ ጭፍጨፋ ነበረ፡፡ በእነኝህን ሁለት ከተማ ሕዝብ የተወሰደውን አረመኔያዊ ግፍ የተሞላበት እርምጃ በመቃወም የመርሳ ከተማ ሕዝብ ዛሬ ቅዳሜ 19,5,2010ዓ.ም. ላሰማው የተቃውሞ ድምፅ ወያኔ እንደለመደው አረመኔያዊ ጭፍጨፋ በመፈጸም፣ ከጭፍጨፋ የተረፉትን ወጣቶችንም እንደ እባብ ቀጥቅጠው በመሠባበር አፍሰው እየጫኑ ወደ ትግራይ እስር ቤቶች በማጋዝ የሕዝብን ጥያቄና ድምፅ ለማዳፈን እየጣረ ይገኛል፡፡

ይህ ሁሉ ግፍ ሲፈጸም በተቀረው የሀገራችን ክፍል የምንኖር ኢትዮጵያውያን ጭጭ ብለን የግፍ ጭፍጨፋውን ዜና እያዳመጥን ከንፈር ከመምጠጥ ያለፈ ማድረግ የቻልነው ነገር ሊኖር አልቻለም! ይሄ በጣም ስሕተትና ፈጽሞ መቀጠል የሌለበትም ነገር ነው፡፡ አንድላይ ወጥተን ወያኔንና አጋሮቹን አሽቀንጥረን ካልጣልናቸው በስተቀር ሕዝባችንን ከማስፈጀት ባለፈ ዛሬ የአንዱ ከተማ ሕዝብ ሌላ ጊዜ የሌላው በሚያደርገው ዐመፅ ፈጽሞ ሊመጣ የሚችል ለውጥ አይኖርም፡፡ ስለሆነም ጭጭ ብለን ወያኔ የሚፈጽመውን የግፍ ግድያ እያደመጥን ከንፈር ከመምጠጥ ወጥተን ፈጥነን እነሱን በመቀላቀል የወያኔን ግብአተ መሬት መፈጸም ይኖርብናልና ፈጥነን እንነሣ!!!

ከሀገር ውጭ የምትኖሩ ወገኖቻችንም ከማዘንና ከንፈር ከመምጠጥ ባለፈ በየምትኖሩበት ሀገር ማቄን ጨርቄን ሳትሉ ፈንቅላቹህ በመውጣት የአደባባይ ተቃውሞ ሰልፍ ብታኪያሒዱ ወያኔን እየረዱ እየደገፉ ያሉ ምዕራባውያን መንግሥታትን ለየሕዝቦቻቸው ብታሳጧቸው እንዲሸማቀቁና ጫና ተፈጥሮባቸው ከሚያደርጉት ድጋፍ እንዲታቀቡ ስለሚያደርጋቸው የግል ጉዳየ ምንትሴ ሳትሉ በየቦታው የተሟሟቀ የተቃውሞ ሰልፎችን በማድረግ እያለቀ ያለውን ወገናቹህን፣ ውድ ሀገራቹህን እንድትደግፉ እንድትረዱና የዜግነት ግዴታቹህን እንድትወጡ አጥብቄ ማሳሰብ እወዳለሁ!!!

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
amsalugkidan@gmail.com

Filed in: Amharic