>
5:13 pm - Tuesday April 19, 3205

በወልድያ ቆቦ ጭፍጨፋ የፈሰሰው ደም የሁሉም ኢትዮጵያውያን ደም ነው!!

የኢትዮጵያ ህዝብ ባለፉት ሀያ ሰባት አመታት ያሳለፋቸው የሰቆቃ ጊዜያትና የቻለው የግፍ በትር ፤ ከልኩ ሞልቶ በመፍሰሱ ካለፉት አራት አመታት ወዲህ በቁጣ የገነፈለው ተቃውሞ ወሳኝ የሽግግር ምእራፍ ላይ ደርሷል። ወያኔ መራሹ ገዢ ቡድን ሆን ብሎና አቅዶ ፤ ተዘጋጅቶ ፤ ከጥምቀት እለት ጀምሮ በወልደያ እስኪ ቆቦ ለቀናት የዘለቀ ፤ በጦር ሄሊኮፕተሮች ቅኝት የተደገፈ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ጥቃት ከፍቷል። ለበርካታ ንጹሃን ዜጎች ህይወት መጥፋትና ለበርካቶች መቁሰል ምክንያት ሆኗል።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ብሄራዊ ንቅንቄ በአንባ ገነኑ ፋሺሽት የትግሬ ነጻ አውጭ ቡድን ጦር ሀይል ለተጨፈጨፉ ወገኖቻችን የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን በዚህ አጋጣሚ መግለጽ ይወዳል። ድርጊቱንም በጽኑ ያወግዛል። የወንጀሉ አስፈጻሚዎች ፈጻሚዎችና ተባባሪዎች ለፍርድ እንዲቀርቡም ይጠይቃል።

እርግጥ ይህ በወገኖቻችን ላይ የደረሰው ጭፍጨፋ የመጀመሪያውም የመጨረሻውም አይደለም። በሶማሌ ልዩ ጦርና በአጋዚ የተቀናጀ ወረራ በኦሮሞ ወገኖቻችን ላይ የተካሄደው መጠነ ሰፊ ጭፍጨፋ ከህሊናችን ሳይርቅ ፤ በከንቱ የፈሰሰው የወገኖቻችን ደም ጠገግ ሳይል ነው ይህ ድርጊት የተደገመው። ወደኋላ ሄደን የሀያሰባቱን አመታት እልቂት ለመተረክ በዚህ አጭር መግለጫ አንችልም። ድርጊቱን አውግዘን ወይም አዝነን ማለፍ ሳይሆን ዛሬ ነገ ሳንል ለነጻነት የሚደረገውን ትግል ማፋፋምና የፋሺሽቱን ትግሬ መራሽ መንግስት ግብአተ መሬት ማፋጠን እንዳለብን የኢትዮጵያ ወጣቶች ብሄራዊ ንቅንቄ በፅኑ ያምናል።

በመላው አለም የሚገኙ በሃገር ቤትም ሆነ በስደት በማይረባ ጥቃቅን ልዩነት የተነሳ ቆመንለታል ስለሚሉት ህዝብ የተለያየ አመለካከትና አስተሳሰብ የሚያራምዱ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ ልዩነቶቻቸውን ሁሉ ወደጎን ትተው ፤ አንድ ሐገር፤ አንድ ህዝብ፤ ዲሞክራሲ፤ እኩልነት፤ እናም የህግ የበላይነት ብለው ፤ በመሰባሰብ ህዝቡ ያፋፋመውን ትግል መልካም ፈርና አንድ አቅጣጫ ለማስያዝ ወደፊት መምጣት ያለባቸው ጊዜ አሁን ነው። ወሳኝ የትግል ምእራፍ ላይ ደርሰናል ብሎ የኢትዮጵያ ወጣቶች ብሄራዊ ንቅናቄ ያምናል። ይህም ይፈጸም ዘንድ ባገር ውስጥም በውጭም ላሉና ለተበታተኑ የፖለቲካ ድርጅቶች እንዲሰባሰቡ ጥሪ ያስተላልፋል።

የተበታተነ ትግል ምንጊዜም የማይጣጣሙ ትልሞችና ግቦች ውጤት እንደሆነ እናምናለን። የተበታተነ ትግል ለጎንዮሽ ፍትጊያና የግል ወይም የቡድን ጥቅም ፍላጎት ግብ መምቻ እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብ አሁን ላንቀሳቀሰው ስር ነቀል ለውጥ ግስጋሴ አንዳችም ፋይዳ አይኖረውም ብለን እንናገራለን። የኢትዮጵያ ወጣቶች ብሄራዊ ንቅንቄ ተበታትናችሁ የተበታተነ ትግል ለምታራምዱ የፖለቲካ ድርጅቶች በአንድ የጋራ ግብ ዙሪያ የተሰባሰበ ትግል ኢንዲካሄድ የየበኩላችሁን ጥረት እንድታደርጉ ጥሪ ያስተላልፋል።

በአሁኑ ሰአት በወሎ እየተካሄደ ያለውን ጭፍጨፋ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን በተለያየ ጊዜ በተናጠል አስተናግደውታል። ብዙ ህዝብም ሰለባ ሆኗል። ከጋንቤላው ጭፍጨፋ ብንጀምር እንኳን፤ በደቡብ፤ በኦጋዴን፤ በመላው ኦሮሚያ እስካሁን ያልተቋረጠ ፤ በአፋር ፤በአማራው፤ ባህርዳርና ፤ጎንደር ወዘተ…. እያልን ሁሉንም ማዳረስ ይቻላል።ወያኔ እያረፈና እየተዘጋጀ ገደብ የለሽ ጥቃት ለመፈጸም እድል የሰጠው ፤ አንዱ ሲመታ ሌላው ተራው እስኪደርሰው ተቀምጦ መጠበቁ ነው። ሃረርጌ ሲመታ በአራቱም ማእዘን ሁሉም አብሮ መነሳት ነበረበት። አማራ ሲመታ ደቡብም አፋሩም ሶማሌና ኦሮሞውም አብሮ መነሳት አለበት። የመላው አገሪቱ ህዝብ መናበብ እና አንዱ ሲነካ ሁሉም አብሮ በመነሳት ወያኔን በየአካባቢው በመወጠር ሃይሉን መበታተንና ማዳከም ግድ ይላል። እንደልቡ የተወሰነ የህብረተሰብ ክፍል ማጥቃት እንዳይችል ማድረግ ከህዝቡ ይጠበቃል።የኢትዮጵያ ወጣቶች ብሄራዊ ንቅናቄ ዛሬውኑ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድነት በአንድ ጊዜ ትግሉን እንዲያፋፍም ጥሪ ያስተላልፋል።

በመጨረሻም ንቅናቄያችን አበክሮ የሚያስተላልፈው ጥሪ “የተነቃነቀ ጥርስ መውለቁ አይቀርም ” እንደሚባለው፤ መሰረቱ ክፉኛ በህዝባዊ ማእበል እየተናጋ ያለው፤ የትግራይ ዘረኞች መንግስት መውደቁ ስለማይቀር መጪው የሽግግር ወቅት ትርምስና ውዝግብ እንዳይኖረው ለማድረግ ከወዲሁ የተዘጋጀ ፤ የሽግግር መንግስት መሆን የሚችል፤ በውጭም በሃገር ውስጥ ያሉ የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ሁሉ፤ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ የሀገር ሽማግሌዎች፤ መላውን ያገሪቱ ዜጎች በሚወክል ስብጥር የተሰባሰቡ የሚሳተፉበት ሁነኛ ተቋም እንዲቋቋም ጥሪ እናስተላልፋለን። ይህ ተቋም በድህረ ወያኔ ኢትዮጵያ ሊቋቋም የሚገባውን በህዝብ የተገነባ መንግስት፤ ሰብአዊ መብት የሚያስከብር፤ በዜጎች እኩልነት የሚያምን፤ ዲሞክራሲ የሚያሰፍን፤ የህግን የበላይነት እውን የሚያደርግ ገጽታ እንደሚኖረው ማረጋገጫ ይሆናል። ትግሉንም ለማፋጠን አለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ዘመቻ የሚያደርግና የመንግስታትን ድጋፍ የሚያሰባስብ ይሆናል።

ድል የህዝብ ነው! ኢትዮጵያ ለዘላለም በክብር ትኑር! የኢትዮጵያ ወጣቶች ብሄራዊ ንቅናቄ

Filed in: Amharic