>

ከዚህ በታች የተጻፈውን ፕሬዚደንት ትራምፕ አለ ተብሎ ፌስቡክ ላይ ያገኘሁት ነው፤(ፕ/ር መስፍን ወልደማሪያም)

  1. 1. “ነፃነታችሁን ካገኛችሁ ከ50 ዓመታችሁ በኋላ ለሕዝቦቻችሁ አስፈላጊውን የመገናኛ ዘዴ ካልሠራችሁላቸው እናንተ ሰው ናችሁ?
  2. እናንተ በወርቅ ላይ፣ በዕንቁ ላይ፣ በዘይት ላይ፣ በማንጋኒዝ ላይ፣ በዩራኒየም ላይ ተቀምጣችሁ ሕዝቦቻችሁ የሚበሉት ሳይኖራቸው ሲቀር እናንተ ሰው ናችሁ?
  3. እናንተ በሥልጣን ላይ ሆናችሁ የጦር መሣሪያ ከባዕዳን ለመግዛትና ዜጎቻችሁን ለመግደል የማታመነቱ ከሆነ እናንተ ሰው ናችሁ?
  4. የናንተ ማኅበረሰባዊ ዓላማ ሕይወታችሁን በሙሉ በሥልጣን መንበር ላይ መቆየት ከሆነ እናንተ ሰው ናችሁ?
  5. እንደሚታደን አውሬ ዜጎቻችሁን የምትገድሏቸው ከሆነ ማን ያከብራቸዋል? ”                                   (ባለቤት ያቀለለውን አሞሌ ባለዕዳ አይቀበለውም!)
እነዚህ ሁሉ እውነቶች የሚያጠራጥሩ አይመስለኝም። ነገር ግን የሚያጠራጥሩ ነገሮች አሉ። የትራምፕ ዓላማ ምንድን ነው?
 የአፍሪካ መሪዎችን ለማረምና ለማሻሻል ነው?
  • የአፍሪካ መሪዎችን አዋርዶና አሸማቅቆ ታዛዥ ባሪያዎች ለማድረግ ነው?
  • የአፍሪካን ሕዝቦች የነፃነትና የመብት ትግሎች ለማበረታታትና ለማጠናከር ነው?
ትራምፕ ስለአፍሪካ መሪዎች የተናገረው እውነት የመሆኑን ያህል የትራምፕ ዓላማ የአፍሪካ ሕዝቦች ኑሮ እንዲሻሻል  አስተዋጽኦ ለማድረግ አይደለም። እንዲያውም አንድ መሠረታዊ እውነት ያለጥርጥር ሆን ተብሎ አለመነሳቱ የትራምፕን ዓላማ ከተደበቀበት ያወጣልናል።
የአፍሪካ አገሮች በራሳቸው ገንዘብ መሣሪያ መግዛታቸው የማይካድ ቢሆንም አብዛኛውን መሣሪያ የሚያገኙት በርዳታ ነው። ዋናው የርዳታ ምንጭም አሜሪካ ነው። ከኮሪያ እስከ አፍጋኒስታን በሺዎች የሚቆጠሩ የብዙ አገሮች ሕዝቦች የሞቱበትና አካለ ጎዶሎ የሆኑበት የአሜሪካ መሣሪያ ነው። ዛሬም በኢራቅና በሶሪያ፣ በየመንና በአፍሪካ ቀንድ፣የሚካሄዱት ጦርነቶች ላይ የአሜሪካ መሣሪያዎች አሉ።
የትራምፕ ንግግር የአፍሪካ መሪዎችንn ለማሸማቀቅና ተከታዮቹ ለማድረግ የታቀደ ይመስላል። የአፍሪካ መሪዎች ነገሩን በትክክል ከተገነዘቡት ግዜ ሳይፈጁ ራሳቸውን ለማቃናትና አገሮቻቸውን ለማፅዳት ግዜው መድረሱን ማየት ይቻላል።
Filed in: Amharic