>

"ኃላፊነቱን እንወስዳለን!" እያሉ እንደገና ጭፍጨፋ ውስጥ መግባት ብልጠት ወይስ ድንቁርና?

 

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

“ኃላፊነቱን እንወስዳለን!” ወያኔ ወንጀሎቹን የመካጃ፣ የማስተባበያ፣ የመዋሻ፣ የማምለጫ፣ የማወናበጃ፣ የጊዜ መግዣ ምክንያቶቹን ሁሉ ሲጨርስ እንዲሁም የሚፈጽማቸው ግፎች በበቂ ማስረጃ የተያዙና ማስተባበል፣ መዋሸት፣ መካድ የማይችለው ነገር እንደሆነ ሲረዳ አሁን በመጨረሻ ላይ ያመጣት የማታለያ፣ የማጃጃያ፣ የጊዜ መግዣ ቃል መሆኗ ነው፡፡

ወያኔ/ኢሕአዴግ “ኃላፊነቱን እንወስዳለን!” በማለት ሙሉ ለሙሉ እራሱን ተጠያቂ ሲያደርግ ይሄ የመጀመሪያ ጊዜው ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ግን ጥፋት የፈጸሙ አንዳንድ ኪራይ ሰብሳቢዎች ከመሀሉ እንዳሉ ይገልጽና፣ በስብሰናል ገምተናል ምንትስ ይልና ሕዝብን ለማታለል፣ ለመደለል፣ ጊዜ ለመግዛት ተሐድሶ፣ ጥልቅ ተሐድሶ፣ በጣም ጥልቅ ተሐድሶ በማለት ነበረ ለማሞኘት ሲሞክር የነበረው፡፡

አስገራሚው ነገር ግን ወያኔ እንደ ዘውዳዊ አገዛዝ ሥልጣኑን የያዝኩት በዐፅመ ርስትነት ነው ብሎ ያምናል መሰለኝ መግማቱን፣ መበስበሱን፣ በጥፋት ማጥ ውስጥ መስጠሙን አምኖ እየተናገረም “ብበሰብስም፣ ብገማም፣ ብከረፋም፣ ጥፋት በጥፋት ብሆንም እኔው ብቻ እገዛለሁ እንጅ!” ብሎ በሕገ መንግሥቱ የሥልጣን ባለቤት ነው ያለውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ሌላ መንግሥት እንዳይመሠርት ፈጽሞ አለመፍቀዱ ነው፡፡ እንዲህ እያደረገም ደግሞ ሳያፍር ዲሞክራሲያዊ (መስፍነ ሕዝባዊ) ነኝ ይላል፡፡

“ኃላፊነቱን እንወስዳለን!” የሚለው ቃል መጀመሪያ ላይ የተሰማው ወያኔ/ኢሕአዴግ የ17 ቀናት ግምገማ ካደረገ በኋላ ባወጣው መግለጫ ላይ “በሀገሪቱ ለደረሰው ጥፋት ሁሉ ተጠያቂዎቹ እኛ ነን ይቅርታ እንጠይቃለን!” በማለት ሲናገሩና ኃላፊነቱንም እንደሚወስዱ ሲገልጹ ነበር የተሰማው፡፡

ከዚያ በኋላ ደግሞ ሰሞኑን ከወልዲያው፣ ከቆቦው የግፍ ግድያዎች በኋላ ሕዝቡ እራስን የመከላከል እርምጃ መውሰድ በጀመረ ማግሥት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ችግሩን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ “ለተፈጸመው ጥፋት ኃላፊነቱን እንወስዳለን!” ሲል ቃሉን ደግሞ አንሥቶታል፡፡ ይሁን እንጅ እያሉት እንዳሉት ሁሉ እንኳንና ኃላፊነት ወስደው ቀጥለው መውሰድ ያለባቸውን እርምጃ ሊወስዱ ቀርቶ ከወትሮው በባሰ ኃላፊነትና ተጠያቂነት የሚባል ነገር ጨርሶ በሌለበት መልኩ በሕዝብ ላይ ግፍ በመፈጸም የሕዝብ ደም እያፈሰሱ ይገኛሉ፡፡

ለመሆኑ ኃላፊነትን መውሰድ ማለት ምን ማለት ነው? ኃላፊነትን መውሰድ ማለት ጥፋትን ማመንና ለተፈጸመው ጥፋትም ተጠያቂ በመሆን በተፈጸመው ጥፋት ልክ ፍትሐዊ ቅጣትን በመውሰድ የሕዝብን ጥያቄ ተቀብሎ መቃናት፣ መታረም፣ መስተካከል ማለት ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ሌላ ትርጉም የለውም፡፡ የቃሉን አጠቃቀም በአሸባሪዎች ዐውድ ያየነው ከሆነ ትርጉሙ “አደጋውን ያደረስነው እኛ ነን!” ማለት ነው፡፡

ወያኔ በቃል “ኃላፊነትን እወስዳለሁ ለተፈጸመው ጥፋት ሁሉ ይቅርታ እጠይቃለሁ!” አለ እንጅ እስከአሁን ድረስ ለደረሰው ጥፋት ተጠያቂ የሆኑና ፍትሐዊ ቅጣት እንዲያገኙ የተደረጉ አንድም የጥፋት እርምጃዎቹ እንዲወሰዱ ትዕዛዝ ያስተላለፈ ባለሥልጣንና ነፍሰ ገዳይ ወታደር የለም፡፡ ወደፊትም ይኖራል ተብሎ አይታሰብም፡፡

ወያኔ ሌሎች የማጭበርበሪያ የማወናበጃ ዘዴዎችን ስለጨረሰ ለማጭበርበር ያህል ይሄንን ቃል ተናገረ እንጅ ኃላፊነትን ከመውሰድ ጋር ተያይዘው ያሉ እርምጃዎችን ለመውሰድ ፈልጎ ፈቅዶና ተዘጋጅቶ የተናገረው ቃል አይደለም፡፡ ወያኔ እንዲህ ላድርግ ቢል ሕዝባዊ ዐመፁ ለመቀስቀሱና ዐመፁን ተከትሎ ለተወሰደው ግፍ የተሞላበት አረመኔያዊ እርምጃ ተጠያቂ የማይሆን አንድም የወያኔ ባለሥልጣን አይኖርምና ነው፡፡ ከዚህ የተነሣ የዋሃን ተላሎች ካልሆኑ በስተቀር ይሄንን “ኃላፊነቱን እንወስዳለን!” የሚለውን የወያኔን ቃል ከልብ የተባለና የሚፈጸም አድርጎ ያሰበ ኢትዮጵያዊ ይኖራል ብየ አላስብም፡፡

እናም ወያኔ ቃሉን የተጠቀመው እንደለመደው ሕዝብን ለማታለያነት፣ ለማወናበጃነት፣ ለጊዜ መግዣነት ብቻ ነው ማለት ነው፡፡ ይሄ ለመሆኑ አንዱ ማረጋገጫው ደግሞ ሰሞኑን አስቀድሞ ያሰበበትንና የተዘጋጀበትን የግፍ ግድያ ወልዲያ ላይ ሃይማኖታዊ ሥርዓት በመፈጸም ላይ ባሉ ምእመናን ላይ ከፈጸመ በኋላ በላኮመልዛ (ወሎ) ከሰባት በላይ ከተሞች ሕዝብ ላይ እየወሰደው ያለው ግፍ የተሞላበት፣ ፈጽሞ ኃላፊነትና ተጠያቂነት የሚባል ነገር የሌለበት አረመኔያዊ እርምጃ እየወሰደ ያለ መሆኑ ነው፡፡

ይሁን እንጅ ይህ የወያኔ/ኢሕአዴግ ባለሥልጣናት በገዛ አንደበታቸው ጥፋቱ የራሳቸው መሆኑን አምነው የተናገሩት ቃል ወንጀለኝነታቸውን፣ ተጠያቂነታቸውን ኦፊሴላዊ (ይፋዊ) በሆነ መንገድ በራሳቸው ላይ በመመስከር ያረጋገጡበት ቃል በመሆኑ ይህ መግለጫ ወደፊት አንዳችም ምስክርና ማስረጃ ሳያስፈልግ ወንጀለኝነታቸውን አረጋግጦ ተገቢውን ፍርድ የሚያሰጣቸው የራስ የምስክርነት ቃል በመሆኑ ለወደፊቱ ጠቀሜታው እጅግ የጎላ ነው፡፡ እነኝህ የወያኔ/ኢሕአዴግና የአቶ ገዱ መግለጫዎች ተጠብቀው መያዝ ይኖርባቸዋል፡፡ በመሆኑም “ኃላፊነቱን እንወስዳለን!” እያሉ እንደገና ጭፍጨፋ ውስጥ መግባት ብልጠት ሳይሆን እጅግ የከፋና ከባድ ዋጋ የሚያስከፍል ድንቁርና ነው!!!

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
amsalugkidan@gmail.com

Filed in: Amharic