>

የኢትዮጵያ አብዮት ጥንስስ ፋና ወጊዎቹ (ሃረግ ዘ-ልደታ)

ወንድማማቾቹ መንግስቱና ገርማሜ ንዋይ

ታህሳስ ግርግር

የታኅሣሥ ግርግር በዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ዓመቱ በገባ በአራተኛው ወር ላይ የተከሰተው የታኅሣሥ ፲፱፻፶፫ቱ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ፤ የአገሪቷ መጭው ዕድሏ ፊቱን ገለጥ ያደረገብት ሁኔታ ነበር።

ለምን? ከ፲፱፻፷፮ቱ አብዮት በፊት ዙፋኑን ክፉኛ ያናጋ ተቃውሞ ቢኖር፤ እንዲያውም የአብዮቱ ምሥረታ፣ በኢትዮጵያ “ዘመናዊ” ታሪክ ውስጥ ወሳኝ የሆነ የፖለቲካ ተቃውሞ ምዕራፍ መክፈቻ ሊባል የሚገባው ይኼው የአምሳ ሦስቱ ሙከራ ስለሆነ ነው። ከዚያ በፊት ዙፋኑ “የማይደፈር፣ የማይሞከር”፤ ንጉሠ ነገሥቱ የማይፈተን መለኮታዊ ሥልጣን እና እንደ ሥርወ መንግሥታቸው አመጣጥ “ሰሎሞናዊ ጥበብ”ን የተቀዳጁ ናቸው የሚባለውን ዕምነት እውን እንዳልሆነ የተገነዘብንበት የታሪክ ምዕራፍ ስለሆነ ነው። ከዚህም አልፎ በአፍሪቃ አኅጉር ከንስር ወይም ግብጽ ስኬታማ መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ የተጸነሰው ሁለተኛው ሙከራ ነበር።

በሌላ አመለካከት ደግሞ ሙከራውን በጥምር ያቀነባበሩት ሁለቱ ወንድማማቾች ተምሳሌት የስድሳ ስድስቱን አብዮት በወታደርዊና የሲቪል ገጽታዎች መንታ ጥምርነቱ፣ የሚያንጸባርቅም ፈር ቀዳጅ ድርጊት ሆኖ እናገኘዋለን።

★ወንድማማቾቹ መንግሥቱና ገርማሜ ንዋይ

መንግሥቱ ንዋይ በ ፲፱፻፰ ዓ/ም አዲስ አበባ ላይ አራዳ ጊዮርጊስ ገዳም ሠፈር አካባቢ ተወለዱ። አባታቸው ዓለቃ ንዋይ የደብሩ ዓለቃ ነበሩ። መንግሥቱ በተወለዱ በስምንት ዓመታቸው በ፲፱፻፲፮ ዓ/ም ታናሽዬው ገርማሜ ንዋይ ተወለዱ። ሁለቱም ትምሕርታቸውን በ ተፈሪ መኮንን ትምሕርት ቤት ተከታትለው አዲሱ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሁለተኛ ደረጃ ትምሕርት ቤት ሲመሰረት ወደዚያ ተዛውሩ። የገነት ጦር ትምሕርት ቤት ሲከፈት ደግሞ፣ መንግሥቱ ንዋይ ተመልምለው ከገቡት ዕጩ መኮንኖች አንዱ ነበሩ። ሌሎች (በኋላ ጄነራሎች) እንደነ አቢይ አበበ፣ አሰፋ አያና፣ ኢሳያስ ገብረሥላሴና ከበደ ገብሬ በዚሁ ትምሕርት ቤት ከመንግሥቱ ጋር የነበሩ ዕጩ መኮንኖች ናቸው።

መንግሥቱ ከዚያው የጦር ትምሕርት ቤት በመቶ አለቃ ማዕረግ ተመርቀው ሲወጡ ወዲያው የጠላት ኢጣልያ ጦር አገሪቱን ይወርና እሳቸው ከሌሎች ጓዶቻቸው ጋር ወደማይጨው ዘምተው ግዴታቸውን ተውጥተዋል። ጠላትም ድሉን ሲቀዳጅ እና ንጉሠ ነገሥቱ ሲሰደዱ መቶ አለቃ መንግሥቱ በዚያን ጊዜ የኢትዮጵያ መንግሥት ወደሸሸበት ነቀምት ሄደው እዚያ “ጥቁር አንበሳ” የሚባለውን ማኅበር መሥራች አባል ናቸው። ከጥቂት ጊዜም በኋላ ከጓደኞቻቸው ጋር ወደጅቡቲ ተሰደዱ። በ፲፱፻፴፪ ዓ/ም ንጉሠ ነገሥቱ ተመልሰው ካርቱም ሲገቡ እነኚህን ስደተኛ መኮንኖች ከጅቡቲ ወደካርቱም እንዲመጡ ይደረግና መንግሥቱ ንዋይ ከነ ሙሉጌታ ቡሊ፣ ነገሠ ወልደሐና፣ ወልደማርያም ኃይሌ፣ ዘውዴ ገበሳ እና ታምራት ዘገየ ጋር ሆነው ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር ተቀላቀሉ። ወዲያውም ከእሳቸው ጋር በ፲፱፻፴፫ ዓ/ም አብረው ወደኢትዮጵያ በድል ሲገቡ በክብር ዘበኛ ውስጥ በጄኔራል ሙሉጌታ ሥር ሻምበል ሆነው ቆዩ። በመስከረም ወር ፲፱፻፵፱ ዓ/ም ኮሎኔል መንግሥቱ ብርጋዴር ጄኔራል ተብለው የክብር ዘበኛ ጠቅላይ አዛዥነትን ተሾሙ። ተራማጅ እና የክብር ዘበኛን ሠራዊት በሰገላዊ ውትድርና ንቃተ ሕሊናውን ለማዳበር ብዙ የጣሩ መኮንን እንደነበሩ ተመስክሮላቸዋል።

ገርማሜ የስምንት ዓመት ታናሽ ቢሆንም ከሁለቱ የበለጠ የተፈጥሮ ኮስታራ፣ ትጉሕ ተማሪ እና ስፖርተኛ (በተለይም በእግር ኳስ) እንደነበር ይነገርለታል።

ታላቅ ወንድሙንም ተከትሎ አንደኛ ደረጃ ትምሕርቱን በተፈሪ መኮንን ትምሕርት ቤት፣ ሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በኮተቤው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትምሕርት ቤት ካጠናቀቀ በኋላ በ፲፱፻፴፭ ዓ/ም ገደማ በልዑል አልጋ ወራሽ መርድ አዝማች አስፋ ወሰን ከሁለት ዘመዶቹ ገርማሜ እና አምዴ ወንዳፍራሽ፣ ሙሉጌታ ስነጊዮርጊስ፣ ሙላቱ ደበበ እና ምናሴ ኃይሌ (በኋላ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የነበሩት) ጋር ወደአሜሪካ ለትምሕርት ተላኩ። በዚህ ጊዜ ሌሎቹ ለጉዟቸው ሱፍ ልብስ ሲያሰፉ፣ ገርማሜ (ንዋይ) ግን በርኖስ ይገዛና ይሄንኑ ኮት እና ሱሪ አሰፍቶ ለብሶ ወደ ዊስኮንሲን ዩኒቨርሲቲ ይጓዛል። ከዊስኮንሲን የመጀመሪያ ጉላፑን (BA degree) ይቀበልና ሊቀኪን ጉላፑን (MA degree) ደግሞ ከ ኮለምቢያ ዩኒቨርሲቲ በ ደቦሰብ ሰገል (Social Science) ይቀበላል። አሜሪካ በነበረበት ጊዜም በ”ሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማኅበር” ፕሬዚደንት ነበረ። ለሊቀኪን ጉላፑ መመረቂያ ያቀረበው የጥናት ጽሑፍ “የነጮች የሠፈራ ፖሊሲ በኬንያ ላይ ያለው ተጽእኖ ” (“The impact of White Settlement Policy in Kenya” (Columbia University, 1954)) በሚል ርዕስ ሲሆን በጭቆና ቀንበር ሥር የሚኖሩ አፍሪቃውያንን ዕሮሮ የሚያስተጋባ ጽሑፍ ነው።

ትምሕርቱን እስከ ዲበሲን ጉላፕ (PhD) ደረጃ ለመከታተል ቢፈልግም ወደኢትዮጵያ እንዲመለስ በተደረገለት ጥሪ መሠረት በ፲፱፻፵፮ ዓ/ም አገሩ ተመልሶ ሲገባ መጀመሪያ በአገር ግዛት ሚኒስትር ውስጥ የደጃዝማች በኋላ ራስ መስፍን ስለሺ በኋላም የሚኒስቴሩ የራስ አበበ አረጋይ ዋና ጸሐፊ ሆኖ ሲያገለግል ቆየ። እዚሁ አገር ግዛት ሚኒስቴር ውስጥ በነበረበት ጊዜ በአፍሪቃ አኅጉር የመጀመሪያው መፈንቅለ መንግሥት በንስር የተሳካበት ጊዜ ነበር። ገርማሜም ለኮሎኔል ናስር መንግሥት በድብቅ “እባካችሁ ስለመንግሥታችሁ አቋም እና አመሠራረት ማብራሪያ ላኩልን” የሚል ደብዳቤ መላኩ ሲደረስበት በንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት እና በጊዜው ባለሥልጣኖች ላይ ምን ያህል ሽብር እና የእምነት ጉድለት እንደጣለ መገመት ይቻላል።

አለባበሱ ሁሌም በካኪ ልብስና ቀይ ክራባት ስለነበረም “ወልፈናኝ” (Communist) የሚል ቅጽል ስም ከማትረፉም በላይ ለአብዮታዊ መንግሥቶች ከጻፈው ደብዳቤ ጋር በትንሹ የንጉሠ ነገሥቱን መንግሥት ጥርጣሬ፣ በተጨባጭ ሁኔታ ግን ታላቅ ትኩረት እንዲሰጠውና በ”እንግልት ሥፍራ” መንፈሱ መሰበር እና ሎሌነቱ መፈተን እንዳለበት ወሰኑ። ስለዚህም በተከታታይ በስውር ግዞት የሩቅና ፈታኝ ግዛቶች አስተዳዳድሪ እየተደረገ ይሾማል። የገርማሜ ንዋይ የመጀመሪያው መፈተኛ የወላይታ አውራጃ ገዥነት ነበር። እሱ ግን ይሄንን የግዞት ቦታ የፍትሓዊ አስተዳደር ሙከራ ጣቢያ በማድረግ ብዙ “ፍሬያማ” ሥራዎችን ሠርቷል። ለምሳሌ፦ • በሺህ የሚቆጠሩ ተማሪዎች የሚማሩበትን ትምሕርት ቤቶች በመሥራት • የሥፍራ ዕቅድ በመጀመርና የጭሰኝነትም ውልም በጽሑፍ በመደንገግ የጭሰኛውን መከራ ከፈለለት

በንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት በኩል ግን፣ እንኳን መንፈሱ ሊሰበር ቀርቶ እንዲያውም በአውራጃው ሕዝብ የተወደደ ሲሆን እንግልቱ አንሷል እንደማለት ያህል ይመስላል፣ በዘመኑ የእንግሊዝ መንግሥት የኢጣልያ ሶማልያን እና በጊዜው በሞግዚትነት ያስተዳድር የነበረውን የኦጋዴንን ግዛት አጣምሮ “ታላቋ ሶማልያ” በሚል አንድ አድርጎ ከኢትዮጵያ እጅ ለመፈልቀቅ በሚዶልትበት ፈታኝ ጊዜ፣ ገርማሜን የጅጅጋ አውራጃ ገዥ ያደርጉታል። እሱ ግን የኢትዮጵያ ሱማሌዎችን ሕይወት ለማሻሻል በወሰዳቸው እርምጃዎች ተወዳጅነትን አገኘ እንጂ እንደተገመተው መንፈሱም አልተሰበረ፣ ሥራው አልከሸፈም። መንግሥት በዚህም በጠረፍ አስተዳደሩም ላይ ጣልቃ እየገባበት ሊያደንቅፈው መሞከሩን አልተወውም። ያንጊዜ ነው ማዕበሉን መለወጥ አማራጭ የሌለው ተግባር መሆኑን የተረዳው። ወንድሙንም ለዚሁ ዓላማ ማነሳሳት የጀመረው ያኔ ነው።

የሙከራው ጥንሰሳ

መንግሥቱ ንዋይ ለፖሊስም ሆነ በሕይወታቸው ላይ ለፈረደባቸው ችሎት እንደገለጹት፣ ከ ፲፱፻፵፯ ዓ/ም ጀምሮ ንጉሠ ነገሥቱን እየተከተሉ በየከተማው፣ በየአውራጃውና በየወረዳው ሲዘዋወሩ የአቤቱታ አቅራቢው ሕዝብ ብዛትና በአዋጅ የሚነገረው ሁሉ ተግባር ላይ አለመዋሉ ያሳስባቸው እንደነበር ተንትነዋል። የመፈንቅለ መንግሥቱም ሦስተኛ አባል የነበሩት የንጉሠ ነገሥቱ ልዩ ካቢኔ ጸጥታ ጉዳይ ኃላፊ የነበሩት ሌተና ኮሎኔል ወርቅነህ ገበየሁም እንዲሁ በፍትሕ ዕጥረት ምክንያት ብሶት እንደተሰማቸው ይነገራል። አራተኛው አባል ብርጋዴር ጄነራል ጽጌ ዲቡ የብርጋዴር መንግሥቱ የቅርብ ወዳጅ ከመሆናቸውም ሌላ የፖሊስ ሠራዊቱ ዋና አዛዥ ነበሩ። ጽጌና መንግሥቱ አብረው ይውላሉ አብረው ያመሻሉ። በፖሊስ ሠራዊት ፈጥኖ ደራሽ ግቢ መኮንኖች ክበብ ነው የሚውሉት የሚያመሹት።

ወንድማማቾቹ አባታቸው ዓለቃ ንዋይ በሞቱ በሁለተኛው ወር በአንድ ድግስ፤ መንግሥቱ ከወይዘሪት ከፋይ ታፈረ ጋር ገርማሜ ደግሞ ከወይዘሪት አያልነሽ ዘውዴ ጋር የካቲት ፱ ቀን ፲፱፻፶፩ ዓ/ም ተዳሩ። በሚቀጥለው ዓመትም ሚያዝያ ፳፪ ቀን ፲፱፻፶፪ ዓ/ም በሱሉልታ የተካሄደው የክብር ዘበኛ ሠራዊት የጦር ታክቲክ ትልቅ የማስጠንቀቂያ ደውል መሆኑን እና መፈንቅለ መንግሥቱ የዚያን ዕለት እንደተጀመረ እነ አቶ መኮንን ሀብተወልድ ገምተዋል ይባላል።

ለማንኛውም የሙከራው ጥንሰሳ ተደርሶበት ነበ፤። አልፎ ተርፎም ንጉሠ ነገሥቱን የጸጥታና ስለላ ክፍል ሃላዊዎቻቸው አስጠንቅቀዋቸው ነበር ቢባልም፣ “አያደርጉትም” በሚል ንቀትም ይሁን ወይም ደግሞ በዕርግጥ የሚከሰት ተግባር ከሆነ ደግሞ እራሳቸውን ከጥቃት አግጣጫ ለማስወገድ ያቀዱትም የ”ሰሎሞናዊ ጥበብ” ሊሆን ይችላል፤ ብቻ ንጉሠ ነገሥቱ ኅዳር ፳፩ ቀን ለጉብኝት መጀመሪያ ወደምዕራብ አፍሪቃ ቀጥሎም ወደብራዚል በረሩ። ለእድምተኞቹ ይሄ እንከን ወይም ተወዳዳሪ የሌለው አመቺ ሁኔታን ፈጠረላቸው።

ሙከራው ማክሰኞ ታኅሣሥ ፬ ቀን ተጀመረ። ለትላልቅ መሳፍንት፣ መኳንንቶችና ዋና ሚኒስቴሮች “እቴጌ ታመዋልና በአስቸኳይ ወደቤተ መንግሥት ይምጡ” የሚል የስልክ ጥሪ መልክት ተላለፈ። እነ ራስ ስዩም መንገሻ፣ ራስ አበበ አረጋይ፣ አባ ሐና ጅማ፣ መኮንን ሀብተወልድ እና ሌሎችም በተቀበሉት ጥሪ መሠረት ቤተ መንግሥቱ ሲደርሱ ከእቴጌይቱ እና ከአልጋ ወራሽ ጋር ቁጥጥር ስር ዋሉ። የጦር ሠራዊቱ ኤታ ማጆር ሹም ሜጀር ጄነራል መርድ መንገሻ እና የምድር ጦር አዛዡ ሜጀር ጄነራል ከበደ ገብሬ ግን በተደጋጋሚ ቢጠሩም አሻፈረኝ ብለው አፈንግጠው ቀሩ።

ዕሮብ ታኅሣሥ ፭ ቀን ወንድማማቾቹ መፈንቅለ መንግሥቱን ለሕዝብ ሲያስተዋውቁ፣ ለማስተላለፍ የፈለጉት ዐቢይ መልእክት ኢትዮጵያ በቅርብ ነጻ ከወጡት የአፍሪቃ አገሮች እንኳን ስትነጻጸር ምን ያህል ወደኋላ እንደቀረችና የመፈንቅለ መንግሥቱ ሙከራ የሀገሪቱን የቀድሞ ዝናና ክብር ለማደስ መሆኑን ነው። የሰፊው ሕዝብ ብሶት የቆረቆራቸው መሆኑን በመግለጽ፣ ፋብሪካዎች ለማቋቋምና ትምሕርት ቤቶች ለመክፈት ቃል ገቡ። የለውጥ ፈላጊ ናቸው የሚባሉትን ልዑል ራስ እምሩ ኃይለ ሥላሴን በጠቅላይ ሚኒስትርነት መሾማቸውንና አልጋ ወራሹን አስፋ ወሰንን (“አስገድደው”) በማስማማትም መንግሥት በቆረጠላቸው ደመወዝ እየተዳደሩ ለሕገ መንግሥት የሚገዙ ንጉሥ ሆነው እንደሚያገለግሉ እራሳቸው ለሕዝቡ በራዲዮ እንዲያስተላልፉ አደረጉ።

ይሄ የአልጋ ወራሹ መልዕክት በገርማሜ ንዋይ፣ በሌተና ኮሎኔል ወርቅነህ ገበየሁና ባልደረቦቻቸው የተዘጋጀ ንግግር ሲሆን በከፊል እንደዚህ ነበር፦

“…ድንቁርናን ከመካከላቸው አጥፍተው በአእምሯቸው መራቀቅና በኑሮ ደረጃው እየገፉ የሚሄዱ የዓለም ሕዝቦች ላይ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሊያደርሰው የሚችል የማይፈጸም የቃል ተስፋ መስማት ሳይሆን እውነተኛ ተግባር ላይ የዋለ የሕዝብ የአእምሮና የኑሮ እድገት የሀገር ኃብት ልማት ፕሮግራም እስከዛሬ ድረስ ተዘርግቶ ካለማየቱም በላይ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ነጻነታቸውን ያገኙ የአፍሪቃ አገሮች እንኳን ሳይቀሩ በሚፈጽሙት የስልጣኔ እርምጃዎች የኢትዮጵያን ሕዝብ እየቀደሙና ወደኋላ እየጣሉ ወደፊት የሚገሰግሱ መሆናቸው ለኢትዮጵያ ዕለት በዕለት ገሃድ እየሆነለት ሄደ። ይሄም ሁኔታ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ የኢትዮጵያን ሕዝብ የረጅም ተስፋ መጨረሻ ላይ አላደረሰውም። ይህም ከመሆኑ የተነሳ ከጥቂት ጊዜ ወዲህ የተጀመረው የሕዝብ እንቅስቃሴ እነሆ ዛሬ ሥልጣንን ጨብጦ ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለሀገሪቱም መድኅን ከመሆን ደረጃ ላይ መድረሱን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ልገልጽላችሁ ዕድል በማግኘቴ ደስታዬ ፍጹም ነው።…….”

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዋና ተቃራኒዎቹ፤ አንደኛው ከሻለቃነት ማዕረግ በአንድ ጊዜ ወደ ብርጋዴር ጄነራልነት የተተኮሱት ሜጀር ጄነራል መርዕድ መንገሻ ሲሆኑ ሌላው ደግሞ ሜጀር ጄነራል ከበደ ገብሬ ያለመያዛቸው ለተቃራኒው ኃይል ጊዜ የሰጠና በመጨረሻም የሙከራውን መክሸፍ ምክንያት ሆኑት ከሚባሉት ዐቢይ ጉዳዮች ዋናው ነው። ከመኳንንቱ መኃል ደግሞ የሕዝብ እንደራሴዎች ሸንጎ ምክትል ፕሬዚደንት የነበሩት ዳጃዝማች (በኋላ ልዑል ራስ) አሥራተ ካሳ ነበሩ፡ እነኚህ ሁለት ጄነራሎችን እና የመሳሰሉ ተቃራኒዎችን መንግሥቱ ንዋይ ሌሎቹን በቁጥጥር ሥር ባዋሉበት ስልት እንዲመጡ ቢጠይቋቸውም አሻፈረን ብለው መቅረታቸው እጅግ በጣም በጅቷቸዋል። ሌተና ኮሎነል ወርቅነህ ገበየሁ ለመፈንቅለ መንግሥቱ ስኬታማነት እነዚህን ሁለት ጄኔራሎች በአስቸኳይ ቁጥጥር ላይ ማዋል ወሳኝ መሆኑን ደጋግመው ቢያስታውሱም ጄነራል መንግሥቱ ግን “ደም መፋሰስን ያስከትላል” በሚል ዕምነት ውድቅ አደረጉባቸው።

“ክርስቲያን የሆናችሁ ልጆቼ እንዲሁም የመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ…..ትናንትና አንዳንድ የክብር ዘበኛ ሠራዊት አባላት….ሀገራቸውን ክደዋል።….እነኚህን ከሃዲዎች አትመኑ አትከተሏቸው። በተሰጠኝ ሥልጣን አውግዣችኋለሁ…” የሚለውን መልክታቸው በሠፊው ተሰራጨ/ተበተነ።

አቶ ጌታቸው በቀለ “The Emperor’s Clothes” በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ፣ ኮሎነል ወርቅነህ “ስለ መፈንቅለ መንግሥቱ መጠንሰስ የሰማሁት ከተጀመረ በኋላ ነው። አሁን ተቃዋሚ ብሆን ጠንሳሾቹ ይገሉኛል። ከነሱ ጋር ሆኜ ለለውጥ ስዋጋ ብሞት ይሻለኛል ብዬ ወስኛለሁ።” አሉኝ ብለዋል መንግሥቱ ንዋይና ሁለቱ ጓደኞቻቸው ስላልተያዙት ሁለት ጄነራሎች የነበራቸው ግምት በጣም አነስተኛ ሲሆን ጄነራል መርድ የተገመቱት በአዲሱ መንግሥት ውስጥ ስለሚኖራቸው የሥልጣን ክፍያ ዋስትና ለማግኘት ፍላጎት እንዳላቸው ሲሆን፤ በጥሩ ኢትዮጵያውነት የተወሱት ከበደ ገብሬ ደግሞ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ደህንነት ባላጋራ እንደማይሆኑና ከመርዕድ መንገሻ ጋር እንዳልተስማሙ በተጨባጭ መግለጫ የተደገፈ ነበር። ሆኖም የነኚህን አፈንጋጭ ጄነራሎች ከሥልጣን መሻር በራዲዮ አስነገሩ።

ሐሙስ ታኅሣሥ ፮ ቀን የነጄነራል መርድ ተቃራኒ ኃይል ዝግጅቱን ጨርሶ በዚያው ዕለት ከቀትር በኋላ በዓየር እና በታንክ ጭምር የተፋፋመ ውጊያ ሲጀምር መንግሥቱ ንዋይ መምሪያ ክፍላቸውን ወደ ገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ያዛውራሉ። ዓርብ ታኅሣሥ ፯ ቀን የሙከራው ኃይል እየተዳከመ በአንጻሩ ደግሞ ተቃዋሚዎቻቸው እያደር እየጎለመሱ መሄዳቸውን የተገነዘቡት ሽብርተኞች በቁጥጥራቸው ላይ የነበሩትን ሃያ መሳፍንት፣ መኳንንት፣ ሚኒስትሮችንና መኮንኖችን ወደ አረንጓዴ ሳሎን ያዛውሩና አልጋወራሹንና አዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ለብቻቸው እንዲጠበቁ ያደርጋሉ። ጄነራል ጽጌ ዲቡ ወዲያው ከተቃራኒ ወገን በተተኮሰ ጥይት ሲገደሉ፣ እነ ጄነራል መንግሥቱ የያዟቸውን እስረኞት ረሽነው ለማምለጥ ወሰኑ።

ከነዚህ እስረኞች መሃል የነበሩት ብርጋዴር ጄነራል መኮንን ደነቀ

“እኔ አውቆ ይሆን ሳያውቅ እንደሆነ አላውቅም፣ ነገር ግን መጀመሪያ ጥይት የተተኮሰው በሙሉጌታ ላይ ነው።” “መንግሥቱ ንዋይ ውጡ ሲል ሲወጡ ከጀርባቸው ተኩስባቸው ብሎ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር መንግሥቱ። በኋላ ተነሱና ውጡ አሉ፡ አባ ሐና እኔ ቤቱን አውቀዋለሁ ከዚህ የተሻለ ቦታ የለም ሲሉ መንግሥቱ “ታዲያ አትሏቸውም?” ሲል ተኩሱ ተከፈተ።”

ይላሉ። መንግሥቱ ንዋይ ግን በ የካቲት ወር ፲፱፻፶፫ ዓ/ም ለፍርድ ቤት በሰጡት ቃል “እኔ ግደሉም አላልኩም እራሴም አልተኮስኩም” ብለዋል።

ያም ሆነ ይህ፣ ከሀያዎቹ መኻል እነ ሙሉጌታ ቡሊ፤ ራስ ሥዩም መንገሻ፤ ራስ አበበ አረጋይ፤ አቶ መኮንን ሀብተወልድ፤ አባ ሐና ጅማ፤ አቶ አምደሚካኤል ደሳለኝ፤ ብላታ ዳዊት ዕቁበ እግዚ፤ አቶ ገብረ ወልድ እንግዳ ወርቅ፣ ብላታ አየለ ገብሬ፤አቶ ታደሰ ነጋሽ፤ በጠቅላላው አሥራ አምስቱ ሲገደሉ፣ ሦስቱ ቆስለው ራስ አንዳርጋቸው መሳይ እና አንድ ሌላ ሰው ደግሞ ምንም ሳይነካቸው ተርፈዋል። ተቆሰሉትም አንዱ በአሥራ ሁለት ጥይት ተመተው የተረፉት ብርጋዴር ጄነራል መኮንን ደነቀ ናቸው። ጽጌ ዲቡ ከጦር ሠራዊት ኃይሎች ጋር ሲታኮሱ ቀደም ብለው ሲሞቱ፣ ኮሎኔል ወርቅነህ ደግሞ በተከበቡ ጊዜ “እጄን አልሰጥም ብለው” ራሳቸውን አጠፉ። መንግሥቱና ገርማሜ ግን በቤተ መንግሥቱ ጋራዥ በኩል ሾልከው ወደቀጨኔ መድሃኔ ዓለም በኩል ጫካ ለጫካ ኮበለሉ።

ከሙከራው በኋላ ንጉሠ ነገሥቱ በማግስቱ ቅዳሜ ታኅሣሥ ፰ ቀን በአስመራ በኩል አድርገው ብዙም ወደአልተረጋጋችው አዲስ አበባ ከተማ ሲገቡ ወዲያው የወንድማማቾቹን ፎቶግራፍ የያዘ ማስታወቂያ በሠፊው ተሰራጨ።

ታኅሣሥ ፲፭ ቀን ወንድማማቾቹና ባልደረባቸው ሻምበል ባየ ጥላሁን ከአዲስ አበባ ድሬ ጨለባ በሚባል ሥፍራ ወደሚገኝ የዘመዳቸው እርስት በማምራት ላይ ሳሉ ነው የተከበቡት። እዚሁ ሥፍራ በተደረገው የተኩስ ልውውጥ ሻምበል ባየ እና ገርማሜ ሲገደሉ መንግሥቱ ነዋይ ግን ክፉኛ ቆስለው ይያዛሉ። የሁለቱ ሟቾች አስከሬን አዲስ አበባ ቤተ መንግሥቱ ደጃፍ ላይ ካደረ በኋላ በማግሥቱ ከኮሎኔል ወርቅነህ ገበየሁ አስከሬን ጋራ ምኒልክ አደባባይ ላይ ተሰቅሎ ዋለ።

መንግሥቱ ንዋይ ቆስለው ከተያዙ በኋላ ከወር በላይ በህክምና ቆይተዋል። ከህክምናውም በኋላ የካቲት ፫ ቀን ለፍርድ ሲቀረቡ አንድ ዓይናቸው ድሬ ጨለባ ላይ የጠፋ ከመሆኑም በላይ ሁለተኛውም አስተማማኝ አልነበረም፡፡
ፍርድ ቤቱ መጋቢት ፲፱ ቀን ውሳኔውን ሰጠ። ጄነራሉ ይግባኝ ይሉ እንደሁ ሲጠየቁ ከዚህ የሚከተለውን እንደትንቢት የሚቆጠር ምላሽ ሰጡ።

”እናንተ ዳኞች! የበየናችሁብኝን የሞት ፍርድ ያለይግባኝ ተቀብያለሁ። ይግባኝ ብዬ የሚመለከትልኝ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቢሆን ኖሮ ይግባኝ ማለት በፈልኩ ነበር። ነገር ግን ይህ እንደማይሆን አውቃለሁና የዓፄ ኃይለ ሥላሴን ፊት ለማየት አልፈቅድም። በእግዚአብሔር ስም በተቀመጣችሁበት የፍርድ ወንበር ላይ ከመቀመጣችሁ በፊት በእኔ ላይ የምትሰጡትን ፍርድ ታውቁት እንደነበር ሳስበውና ፍርድ እስከዚህ መድረሱን ስታዘብ ኀዘኔ ይብሳል። ለኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት፣ ነጻነትና እርምጃ የተነሳሁ ወንጀለኛ ነኝ እንጂ ላፋጀው የተነሳሁ ወንበዴ አይደለሁም። ይህን ማድረግ ፈልጌ ቢሆን ኖሮ ማንም የማይወዳደረው ሠራዊትና መሣሪያ ሳላጣ ዛሬ ከእናንተ ፊት ለመቆም ባልበቃሁ ነበር። እኔ ከዓፄ ኃይለ ሥላሴ ድንክ ውሾች ያነሰ ደመወዝ የሚያገኙ ሁለት የተራ ወታደሮችን አጣልቼ ለማደባደብና ሀገር ለማፍረስ አለመነሳሳቴን የሚያረጋግጥልኝ ከእናንተ በትዕዛዝ ያገኘሁትን ፍርድ ለመቀበል እዚህ መቆሜ ነው። ከእኔ በፊት በግፍ የፈሰሰው ንፁህ የኢትዮጵያዊያን ደም ብዙ ነው፡፡ በዓፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ግፍ ሽልማት በመሆኑ እኔ ለመሞት የመጀመሪያው ሰው አልሆንም፡፡ ሥልጣን አላፊ ነው፡፡ እናንተ ዛሬ ከጨበጣችሁት የበለጠ ሥልጣን ነበረኝ፡፡ ሀብትም አላጣሁም፡፡ ነገር ግን ሕዝብ የሚበደልበት ሥልጣንና ድሃ የማይካፈለው ሀብት ስላልፈለግሁ ሁሉንም ንቄ ተነሳሁ። አሁንም እሞታለሁ፡፡ ሰው ሞትን ይሸሻል ፡፡ እኔ ግን በደስታ ወደሞት እሄዳለሁ፡፡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ታላቅነት ቀድመውኝ መስዋዕት የሆኑትን አብረውኝ ተነስተው የነበሩትን ጀግኖች ወንድሞቼን ለመገናኝት ናፍቄአለሁ፡፡ የጀመርኩት ሥራ ቀላል አይደለም። ነገር ግን አልተሸነፍኩም። ወገኔ የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ የጀመርኩትን ሥራ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ፈጽሞ እራሱን እንደሚጠቅምበት አልጠራጠርም። ከሁሉ በበለጠ የሚያስደስተኝ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ልሠራለት ካሰብኳቸው ሥራዎች አንዱ የኢትዮጵያን ወታደር ዋጋና ክብር ከፍ ማድረግ ሲሆን ይህ ኀሳቤ ሕይወቴ ከማለፉ በፊት ሲፈፀም ማየቴ ነው፡፡ ዛሬ መኖራችሁን በማየቴ ነገ መሞታችሁን ረስታችሁ አሜን ብላችሁ ቀናችሁን በማስተላለፍ በመገደዳችሁ በእኔ ላይ ሳትፈርዱ በራሳችሁ ላይ የፈረዳችሁ መሆናችሁን አላስተዋላችሁም፡፡ እኔ የተነሳሁት ከትክክለኛ ህግና ከህሊናችሁ ውጭ ለመፍረድ እንዳትገደዱ ለማድረግ ነበር፡፡ ባጭሩ በእኔ ላይ ለመፍረድ የቸኮላችሁትን ያህል አሥር እና አሥራ አምስት ዓመት የምታጉላሉት የድሀውን ሕዝብ ጉዳይ እንደዚህ አፋጥናችሁ ብትሠሩትና ብትሸኙት ኖሮ የእኔ መነሳት ባላስፈለገ ነበር። ከእናንተ ከዳኞችና የሞት ፍርድ እንድትበይኑብኝ ካዘዛችሁ ሰው ይልቅ ፍርድ ተቀባይ የዛሬው ወንጀለኛ የነገው ባለታሪክ ነኝ። የኔ ከጓደኞቼ መካከል ለጊዜው በሕይወት መቆየትና ለእናንተ ፍርድ መብቃት የመመዘኑን ፍርድ ለመጭው ትውልድ የሚያሳይ ይሆናል፡፡ ዋ ! ዋ ! ዋ ! ለእናንተና ለገዢአችሁ፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ሃሳቤ በዝርዝር ገብቶት በአንድነት በሚነሳበት ጊዜ የሚወርድባችሁ መዓት አሰቃቂ ይሆናል፡፡ በተለይ የአፄ ኃ/ስላሴ የግፍ መንግስት ባላደራዎች ሆነው ድሀውን የኢትዮጵያ ህዝብ ሲገሸልጡት ከነበሩት መኮንን ሀ/ወልድና ገ/ወልድ እንግዳወርቅን ከመሳሰሉት በመንፈስ የታሰሩ በስጋ የኮሰሱ መዠገሮች መካከል ጥቂቶቹን ገለል ማድረጌን ሳስታውስና የተረፉትም ፍፃሜያቸውን በሚበድሉት በኢትዮጵያ ህዝብ እጅ ላይ መውደቅ ሲሰማኝ ደስ ይለኛል፡ ”

በዚሁም መሠረት ጄነራሉ መጋቢት ፳፩ ቀን ፲፱፻፶፫ ዓ/ም በስቅላት ተቀጡ።

መንግሥቱ ንዋይ በተከተሉት ጥቂት ዓመታት የንጉሠ ነገሥቱን ስርዓት በመቃወም ለቀጠለው ትግል እና ከአሥራ ሁለት ዓመት በኋላም ስርዓቱን ላወደመው አብዮት ዋና ፈር ቀዳጅና አርአያ ሲሆኑ በወንድማቸው እና በአባታቸው ስም የሰየሟቸው የሁለት ወንድ ልጆች አባትም ነበሩ።

ዋቢ ምንጮች 
መስፍን አረጋ(ዲባቶ) “ሰገላዊ አማርኛ” ፳፻ ዓ/ም
Bekele, Gaitachew “The Emperor’s Clothes” (1993)
ጦቢያ መጽሔት፣ አራተኛ ዓመት ቁጥር 2፣ ጥቅምት 1988 ዓ/ም
ጥቁር ደም ጋዜጣ፣ ሁለተኛ ዓመት ቁጥር 64፣ መስከረም 23 ቀን 1992 ዓ/ም
Filed in: Amharic